ኢትዮጵያ በብዝኃ ማንነት፣ ባሕልና እሴቶች የደመቀች፣ በኅብረ ብሔራዊነት የተጋመደች፣ ወንድማማችነትን ከፍ አድርጋ ያፀናች ታላቅ ሀገር ናት። በክረምት ወራት ተራርቆ ሳይገናኝ የቆየ ዘመድ አዝማድ መስከረም ላይ ይገናኛል። በዚህ ወቅት በደጋ እና ወይና ደጋ አካባቢ የሚኖረው የኦሮሞ ሕዝብ ከዘመን ወደ ዘመን በሠላም ላሸጋገረው አምላክ ምስጋና ያቀርባል።
ኢሬቻ ይህን ምስጋና የሚያቀርብበት በዓል ነው። በዚህ ወቅት ኦሮሞዎች ከብቶቻቸውን ወደ ሆራ ወይም ጨዋማ ውሃ በማሰማራት፤ ክረምቱን በፈጣሪ ፍቃድ የሞላው ውሃ ጎድሎ ከዘመድ አዝማድ አገናኘን ብሎ ምስጋና ያቀርባሉ። ከጨለማ ወደ ብርሃን ላሸጋገራቸው አምላክ ምስጋና ያቀርባሉ።
ኢሬቻ ማኅበራዊ ደረጃ እና የእድሜ ልዩነት ሳይፈጠር የኦሮሞ ሕዝብ ለዘመናት በጋራ ሲያከብረው የቆየው በዓል ነው። በውስጡ ባሕልንና ፍልስፍናን፤ ትውልድና የመኖር ምስጢርን፤ በተፈጥሮ እና በሰው፤ በተፈጥሮና በፈጣሪ፤ በሰው እና በፈጣሪ መካከል ያለውን መስተጋብርን ያቀፈ ነው።
በኢሬቻ በዓል ላይ የኦሮሞ ሕዝብ ለመላው የሰው ልጅ ሠላምና ደኅንነት ፈጣሪውን ይለምናል፤ ያመሰግናል። የተጣላ ታርቆ፣ ቂሙን ትቶ በነፃ ልቦና ፈጣሪ ንጹሕ ወዳደረገው የውሃ አካል ይሄዳል። ኢሬቻ ቀልብ የሚነጻበት ቦታ ነው። ይህ ለብዙ ሺህ ዘመናት ሲከናወን የቆየ ማኅበረሰባዊ ትውፊት ነው፡፡
ኢሬቻ ሠላም ነው፣ ሠላም ለኦሮሞ ሕዝብ ትልቅ ትርጉም ያለው ነው፣ ሰው ከሰው ጋር፣ ሰው ከራሱ ጋር፣ ሰው ከተፈጥሮ ጋርና ሰው ከፈጣሪው ጋር ሠላም ሊኖረው ይገባል የሚለው ጽንሰ ሐሳብ የክብረ በዓሉ ጭብጥ ነው።በበዓሉ ወቅት ከሚከናወነው ሥነሥርዓት መረዳት እንደሚቻለው ኢሬቻ የምስጋና በዓልም ነው።
ኢሬቻ ምስጋና ብቻ ሳይሆን የአንድነት፣ የወንድ ማማችነት፣ የእርቅና የሠላም በዓልም ነው።የኢሬቻ ቀን ከመድረሱ በፊት የተቀያየመ፣ የተጣላ ሁሉ ታርቆ፣ ይቅር ተባብሎ ቂም በቀልን አስወግዶ፤ በኢሬቻ ቀን ፈጣሪውን እያመሰገነ ከወዳጅ ዘመዶቹ ጋር በዓሉን ያከብራል። ይህ የኢሬቻ ባሕላዊ እሴትና አከባበር ሥነ ሥርዓት በሀገራችን ወንድማማችነት እንዲጠናከር፣ አብሮነት እንዲጎለብትና ዘላቂ ሠላም እንዲረጋገጥ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡
ከማመስገን አልፎ አንድነት የሚፀናበት ሀገራዊ ሀብት ነው።በኢሬቻ ዕለት ከተለያዩ የኦሮሚያ ዞኖች እና ከተለያዩ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሚወከሉ ዜጎች የሚሳተፉበት ነው። የአንድ ሀገር ልጆች በአንድነት የሚሰባሰቡበት፤ በፍቅር የሚደምቁበትና የሚጠያየቁበት ነው። በአንድ ቦታ፤ የአንድ ሀገር ልጆች ተሰባስበው ሀገራዊ እሴታቸውን የሚያዳብሩበት የኅብረት መገለጫም ነው።
ኢሬቻ ለሠላምና ወንድማማችነት ከሚያበረክተው አስተዋፅዖ የተነሳም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል በዩኔስኮ የተመዘገበው የገዳ ሥርዓት አካል ነው። ከኦሮሞ ሕዝብ በተጨማሪ በርካታ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች አብረው የሚያከብሩት፣ የሁላችንም ኢትዮጵያውያን ሀብት ሆኗል ።
ክብረ በዓሉ ሕዝቦችን በማስተሳሰር ረገድም ከፍተኛ ሚና እንዳለው ይታመናል።አንድነት በማምጣት ረገድ፣ ሰው ወደ ማንነቱ እንዲሄድ በማድረግ ከፍተኛ አስተዋፅዖ አለው። የሌሎችን የማንነት መገለጫ የራስ በማድረግ አየተሳሰርን እንድንሄድም የማድረግ አቅም አለው። ከጥቂት ዓመታት ወዲህ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓሉን ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር አብረው በማክበር በዓሉ የአንድነት፣ የሠላም እና የወንድማማችነት ምልክት በመሆን በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት እያገኘ መጥቷል።
ኢሬቻ በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ተሳታፊዎች የሚታደሙት ከመሆኑም በላይ ሴቶች፤ ወንዶች፤ ሕጻናት፤ ወጣቶች፤ ሽማግሌዎች፤ አባገዳዎች እና ሃደ ሲንቄዎች በውብ አለባበስ ደምቀው የሚያከብሩት የውበት በዓል ነው። ይህም በቱሪዝም መስሕብነት ሊኖረው የሚችለው ፋይዳ ከፍ ያለ ነው፤ እንደ አንድ ሀገራዊ የቱሪስት ሀብት ተደርጎም የሚወሰድ ነው፡፡
አደይ አበባ እና እርጥብ ሣር ተይዞ በአባ ገዳዎች እና ሃደ ሲንቄዎች ‘መሬሆ’ እየተባለ ውብ ዝማሬ የሚሰማበት የኢሬቻ በዓል፤ የተለያዩ አካባቢ ወጣቶች ባሕላዊ ጭፈራ እና ዘፈን የሚያሳዩበት ባሕላዊ የጥበብ መድረክም በመሆን ከሀገር ውስጥና ከውጭ በርካታ ቱሪስቶችን በመሳብ ለሀገር ኢኮኖሚ መነቃቃት ከፍተኛ ድርሻ ይኖረዋል፡፡
ይህ ባሕላዊ እና የውበት መገለጫ የሆነው የኢሬቻ በዓል ከሀገር አልፎ የዓለም ሀብት በመሆኑ፤ የቱሪዝም ምንጭ ሆኖ እንዲያገለግል ሥርዓቱን በጠበቀ መንገድ ማክበር ያስፈልጋል። የበዓሉ እሴት ሳይበረዝ እንዲቀጥል የበዓሉ ባለቤት የሆነው መላው ሕዝብ የበዓሉን እሴት ሳይለቅ እንደሌላው ጊዜ ሁሉ በፍቅር፤ በሠላምና በአንድነት ሊያከብረው ይገባል፡፡
አከባበሩን ከአባቶች በመማር ቱባ ባሕሉን ሳይለቅ ሊቀጥል ይገባል። በዓሉ አሁን አሁን የሌሎችንም ብሔሮችና የውጭ ዜጎችን ቀልብ እየሳበ በመሆኑ ሀገር በማስተዋወቅ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሙ እየጎላ በመምጣቱን በአግባቡ ተይዞ ወደ ሃብትነት መቀየር አለበት። ከባሕላዊ ትውፊቱ ባሻገር ለቱሪዝም ስበት ከፍተኛ ሚና አለውና ልንጠብቀው ይገባል።
የኢሬቻ በዓል ወንድማማችነታችንን እና አንድነ ታችንን ባከበረ፣ ባሕላዊ እሴቱን በጠበቀና ፍፁም ሠላማዊ በሆነ አግባብ እንዲከበር ሁላችንም እንደወትሮው ሁሉ የሚጠበቅብንን ኃላፊነት መወጣት ይገባናል። ኢሬቻ ለኅብረብሔራዊ አንድነት ግንባታና አብሮነት ዓይነተኛ ሚና ያለው ቅርሳችን በመሆኑ ባሕላዊ እሴቶቹ ተጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፍ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ መወጣት አለበት! መልካም የኢሬቻ በዓል!
ገለታ ከሸገር
አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም