ኢትዮጵያ ለጋራ ተጠቃሚነትና ለቀጣናዊ ትብብር የሰጠችውን ዋጋ ማሳወቅ ይገባል!

የሀገራት ፖለቲካዊ ብስለት መለኪያ ብሄራዊ ጥቅምን ከሰላማዊ ሂደት ጋር አጣምሮ መሄድ ነው። ሰላምን ማዕከል ያደረገ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በዓለማችን ለሚገኙ ሀገራት የእርስበርስ ተጠቃሚነት መሠረታዊ ሚዛንም ተደርጎ ይወሰዳል። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያም በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ከሚገኙ ጎረቤት ሀገራት አንስቶ በዓለም ዙሪያ ካሉ ሀገራት ጋር የረጅም ዘመናት ትስስሮች ፈጥራ እስካሁን የዘለቀችበት ጠንካራ አቋሟ ነው።

ዛሬም እንደትናንቱ ኢትዮጵያ ሰላምን መሠረት አድርጋ ዘላቂ እድገቷን ስታስብ መሠረቷ ማንንም ሀገር ሳትጎዳ ተገቢ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቷን ማረጋገጥ ላይ አተኩራ ትሠራለች። የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ዋና መሠረቱ ከጎረቤቶቿ ጋር ያላት ግንኙነት ነው። ከጎረቤቶቿ ጋር ለዘመናት የቆየ ትስስሮች አሏት።

የውጭ ግንኙነቷ እነዚህን ትስስሮች በማዳበር፣ የተሰበሩ ካሉ በመጠገን እንዲሁም ዋና የሚባሉ የኢኮኖሚ፣ የባህል ትስስሮችን ማስፋትና ማጠናከር ላይ ያተኩራል። ችግሮችም በሚፈጠሩ ጊዜ በሰላም እንዲፈቱ ማድረግን ቅድሚያ የሚሰጥ ዲፕሎማሲ ትከተላለች።

በእርግጥ የኢትዮጵያ የሰላም ዲፕሎማሲ ጎዞ በርካታ ዘመናትን የተሻገረ እንደሆነ ይታወቃል። ሰላምን መሠረታዊ መርህ አድርጋ የያዘችው ለአንድ ሀገር ብቻ ሳይሆን ለምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ሀገራት በሙሉ እኩል የሰላም ተቆርቋሪነቷን ያሳየችበት ነው። ኢትዮጵያ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ከጥንስሱ ጀምሮ ቻርተሩን በማርቀቅ፣ በማፅደቅ ከዛም በኋላ ሰላም ማስከበር ላይ በሱዳን፣ በደቡብ ሱዳን፣ በሱማሊያ በመሳተፍ ለራሷም ለቀጣናውም ደህንነት ብዙ አስርት ዓመታት ከፍተኛ ሚና ተጫውታለች።

ኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅሟን ከማስከበር ባሻገር በአፍሪካ ቀንድ ከሚገኙ ሀገራት መካከል በሶማሊያ ለአስራ ሰባት ዓመታት የዘለቀ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዋ ይጠቀሳል። ሶማሊያ ሠላሟን አጥታ እርስ በእርሷ ስትታመስ ኢትዮጵያ የጉርብትናዋ መገለጫ የሆነውን ሠላም ለማረጋገጥ የአለሁልሽ ድምጿን አሠምታለች። እንደአልሸባብ አይነት ዓለምአቀፍ አሸባሪ ሃይል መፈልፈያ ለሆነችው ጎረቤት ሀገር ሶማሊያ ኢትዮጵያ ያበረከተችው የሠላም አስተዋፅኦ በእንዲሁ በዋዛ የሚታይ አይደለም።

ኢትዮጵያ ሏዓላዊነቷን ካስከበረች በኋላም ለሶማሊያ ሕዝብ ሠላም መረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክታለች። የሰላም አስከባሪ ሃይል ከመሠማራቱ በፊትም ሠራዊቷን ወደ ቀጣናው በመላክ የሕዝቡን የሠላም ፍላጎት ማረጋገጥ የቻለች ጎረቤት ሀገር ናት።

ባለፉት ዓመታት በሶማሊያ ምድር የሶማሊያ ሕዝብ በአሸባሪ ቡድኑ አልሸባብ አማካኝነት ሠላም ርቆቶ ሕዝቡ ለረሃብ ለስደትና ለከፍተኛ እንግልት ተጋላጭ ሲሆን የአለንላችሁ ድምፃቸውን ካሠሙ ጥቂት ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷና የመጀመሪያዋ ናት። የጎረቤት ሀገር ሠላም የእኔም ሠላም ነው በሚለው ፅኑ አቋሟ ሠራዊቷን ወደ ሶማሊያ የላከችው ኢትዮጵያ አንድም በሰላም ማስከበር ተልዕኮ በሌላ በኩል ከሰላም ማስከበር ውጪ ሶማሊያ እንደ ሀገር እንድትቆምና የሶማሊያ ሕዝብ ሠላም እንዲረጋገጥ ትልቅ ታሪካዊ ዐሻራዋን አሳርፋለች።

ይህ የኢትዮጵያ ተልዕኮ ሶማሊያ እንደሙሉ ሉዓላዊ መንግስት ከነሙሉ ስልጣንና ሃላፊነት ማብቃት ነበር። በዚህም ጉዞው ተጀምሮ ጥሩ ርምጃ ተሄዷል። አልሸባብ በተወሰኑ አካባቢዎች እንዲወሰን ተደርጓል። ስድስት የሚደርሱ ፌዴራላዊና አካባቢያዊ መንግስታት እንዲቋቋሙ ተደርጓል።

ይህ ለሶማሊያ ትልቅ እድገትና ለውጥ ነው። ለኢትዮጵያም ለቀጣናዊ ትብብር የምትሰጠው ሥፍራ ትልቅ መሆኑን ማሳያ ነው። በአካባቢው የሚገኙ ሀገራትና ሕዝቦች በጋራ የሚጠቀሙበት የኢኮኖሚ መንቀሳቀሻና የጋራ የዕድገት ምንጭ ለማድረግ ዛሬም ጥረቱ ቀጥሏል። ለዚህም ነው ወደብን ለማግኘት የተደረገው ስምምነት ሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ መሠረት ያደረገው። ጅማሬው ዛሬ ላይ ያልሆነና ቀድሞም የነበረው ይህ መግባቢያ በወዳጅነት የተገመደ ሰላምን ባስጠበቀ መልኩ ወደ ፊት የሚራመድ ነው።

ኢትዮጵያ በውጭ ግንኙነቷ ወዳጅነትን የጠበቀ መርህ ስትከተል ቆይታለች፣አሁንም ቀጥላበታለች። ሶማሌላንድ ጋር የተደረገው ስምምነትም ይህንኑ ያሳያል። የኢትዮጵያ ሰጥቶ የመቀበል መርህን ሶማሌላንድ በመቀበሏ በኢኮኖሚና በሰላም ዙሪያ በጋራ ይተባበራሉ። መርሁ ሀገራቱ ከትብብር ባለፈም አንዱ ለሌላው ማደግ እንዲቆረቆሩ ያደርጋል፤ ግጭትን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታና ለጋራ ደህንነት ትኩረት እንዲሰጥ አበርክቶው ትልቅ ነው።

ለዚህም ነው ኢትዮጵያ ሰላምና ፅጥታን ለማስጠበቅ የጎረቤት ሀገራት ሰላም መደፍረስ የእኔም ጉዳይ ነው በማለት ጦሯን አዝምታ ሰላም አደፍራሾች አደብ ይገዙ ዘንድ ሚና ስትወጣ የቆየችው። ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳንና ሌሎች ጎረቤት ሀገራት ሰላማቸው ሲደፈርስ ቀድማ የተገኘችው ኢትዮጵያ ነች። አብሮ ለመሻሻል፣ ለመልማት እና ለማደግ ቀጣናዊ ትብብርንም አስተዋውቃለች።

ኢትዮጵያ ምስራቅ አፍሪካን በኢኮኖሚ ለማስተሳሰር የሚጠቀሱና የሚታወቁ ተግባራትን ከውናለች፤ ሲሻገርም ሲል የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የተሻለ ደረጃ ይደርስ ዘንድ መንገድ ለመጥረግ የባህር በር ባለቤት ለመሆን ጥረቷን ቀጥላለች። ሙሉ ጥረቷ ሲሰምር ጥቅሙ ከፍተኛ ነው። ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባ ምርት መብዛትና ወደ ውጭ ተልኮ ምንዛሬ ያመጣ ዘንድ የሚታሰበው የግብርናም ሆነ ሌሎች ምርቶች በቁጥር ረገድ ከፍተኛ አለመሆናቸው ክፍተትን ይደፍናል። ለዚህም ከሶማሌላንድ ጋር የተደረገው ስምምነት መፍትሄ ሆኖ መጥቷል።

ኢትዮጵያና ሶማሌላንድ ያደረጉት ስምምነት የኢትዮጵያን ምርት በቀላሉ ወደዓለም ገበያ ማድረስ የሚያስችል አንዱ አማራጭ ነው። በሚላከውና በሚገባው የነበረው ከፍተኛ ልዩነት እንዲመጣጠን ያደርጋል። ይህም ሰጥቶ የመቀበል መርህ ያስገኘው ውጤት ነው።

ሰጥቶ መቀበል መርህ ለሀገራት ይህ ነው የማይባል ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያስገኛል። የኢትዮጵያ የግብርና ምርቶች የሰው ወደብን በመጠቀም የሚያደርጉትን ጉዞ አቁመው በራሳቸው መጠቀም ሲጀምሩ በዓለም ገበያ ላይ በትኩስነታቸው ምርቶችን ማድረስ ይቻላል። ይህ እድል የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ሀብቶቻቸውን በጋራ እንዲጠቀሙ ያግዛቸዋል።

ኢትዮጵያ ጎረቤት ሀገራትን በኢኮኖሚ ለማስተሳሰር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ጭምር በማቋቋም እየሠራች ትገኛለች። በቀጣናው ሰላም በማስከበር ያላት ድርሻ ላቅ ያለ ከመሆኑ ባሻገር በአካባቢው ያሉ ሀብቶችን የአካባቢው ሀገራት ፍትሀዊ በሆነ መንገድ በጋራ እንዲጠቀሙ ፅኑ አቋም ይዛ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እያደረገች ነው።

የኢትዮጵያ ስኬት የሚያማቸው፣ የዕድገት መንገድን ለመከተል ስትነሳ አይናቸው የሚቀላ ሀገራት ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም። ስለሆነም የጋራ ተጠቃሚነት እና ሰጥቶ መቀበል መርህን ያደረገ ግንኙነት ከመፍጠር ባሻገር የሚመጣውን ተፅዕኖ ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት ሁሉም ሃላፊነት አለበት።

ኢትዮጵያ የባህር በር አግኝታለች ብሎ ሁሉም ሀገራት ደስ ይላቸዋል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው። ይህ እንዳይሳካ የሚሠሩ ሀገራት እንዳሉ በጥንቃቄ ማሰብ ያስፈልጋል። በራሳችን የተፈጥሮ ሀብት፣ በራሳችን ገንዘብና ጉልበት የሠራነውን የህዳሴ ግድብ ጥሩ ምሳሌ ሆኖናል። በማይመለከታቸው ጉዳይ ሀገራት ሲቃወሙ አይተናል። አሁንም በባህር በር ጉዳይ ተመሳሳይ አካሄድ የሚከተሉ ሀገራት ሊኖሩ ስለሚችሉ ራስን ማዘጋጀት ይገባል።

በተግባር እንደሚታየው የምስራቅ አፍሪካ ቀንድ ቀጣና ከቀይ ባህር አንስቶ በርካታ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥቅም ፍላጎት ባላቸው አንዳንድ ሀገራት ጣልቃ ገብነት ይስተዋልበታል። በኢትዮጵያ በኩልም የሰላም ዲፕሎማሲ ውለታዋን የዘነጋችው ሶማሊያ /በተለያዩ ግፊቶች ሊሆን ይችላል/ ድርጊትን ሳይቀንሱ ሳይጨምሩ እውነታውን መግለጥ ተገቢ ነው። ከወዲሁ ለሚመለከታቸው የዓለም ሀገራት እውነታውን የማሳወቅ ሥራ የየዕለት ተግባር ሊሆን ይገባል።

በእርግጥ የሶማሊያና ኢትዮጵያ ሰላማዊ የፖለቲካ ግንኙነት ላይ የተቃርኖ እንቅፋት የማስቀመጥ ተግባርን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እየፈፀመች ያለችው ግብፅ ጣልቃ ገብነቷ በግልፅ እየታየ ነው። ኢትዮጵያ ከግብፅ ጋር በቀጥታ የድንበር ግንኙነት ሳይኖራት ይህን ዘላ፣ ሶማሌን በአንቀልባ አዝላ ብቅ ብላለች። ምክንያቷ ደግሞ ኢትዮጵያ በአካባቢው በኢኮኖሚ ጠንካራና ሃያል እንደምትሆን ምልክቶች እያሳየች በመሆኑ ነው።

ግብፅ የዓባይ ግድብ ወደ ማጠናቀቂያው ምዕራፍ መድረሱ ይፋ በመደረጉም ኢትዮጵያ የቀጣናውን ሀገራት በሃይል አቅርቦት በማስተሳሰር የጋራ ተጠቃሚነት መርህ እውን መሆኑ አይቀሬነትን ስታስብ እንቅልፍ ነስቷታል። ይህንን ለማምከን የማትሄድበት መንገድ፣ የማትፈነቅለው ድንጋይ እንደማይኖር በግልፅ መረዳት ያስፈልጋል። በተግባርም እያደረገችው ነው።

አሁን ግብፅ እየሄደችበት ያለው መንገድ ወይም ትግል ግልፅ ሆኗል። እዚህ ላይ የመላው ኢትዮጵያውያን ተሳትፎ ያስፈልጋል። የአፍሪካ ወንድምና እህቶችን በማሳመን ከእኛ ጋር እንዲቆሙ ብዙ ሥራ ይጠበቅብናል። ብሄራዊ ጥቅማችንን እንደሚጎዳ እና እንደሚፃረር ለሌሎች ማስረዳት ማሳመን ይገባናል።

በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ጉዳያችንን ማቅረብ አለብን። ነገ ይሄ ጉዳይ ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ ቢፈነዳ ዓለምአቀፍ ጉዳይ ስለሚሆን ካሁኑ የሚያመጣውን ችግር ማሳወቅ ይገባል። አሁን መክሰስና ጉዳያችንን ለዓለምአቀፉ ማህበረሰብ የማሳወቅ መብት አለን።

ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ባሻገር ለምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ሰላምና ደህንነት በከፈለችው ዋጋ ልክ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ትኩረት እንዲሰጣት በኢትዮጵያ ውስጥ ከመንግሥታዊ ተቋማት አንስቶ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ መላው ዜጋ፣ ሲቪክ ማህበራት እንዲሁም የመገናኛ ብዙሃን በሃላፊነት መሥራት ይጠበቅባቸዋል። ይህ የብሄራዊ ደህንነት ስጋት መሆኑ በግልፅ ሊታወቅ ይገባል። በቀጣናው የሚከሰቱ ነገሮች በቀጣናው ብቻ ተወስነው የሚቀሩ ሳይሆኑ ቀጣናውን ባለፈ አውሮፓንም እንደሚነካ ማሳወቅ ያስፈልጋል።

ግብፅ በሶማሊያ ብሎም በተለያዩ መልኮች ጣልቃ በመግባት የኢትዮጵያን የምስራቅ አፍሪካ አስተዋፅኦ በሚያንኳስስ መልኩ ያልተገባ ፖለቲካዊ አካሄድን ለማረም ጠንካራ የዲፕሎማሲ ትግሎች በቀጣይነት ተጠናክረው መቀጠልም አለባቸው። በዲፕሎማሲው ረገድ መንግሥት ወይም አምባሳደር ብቻ ሳይሆን ሁሉም ዜጋ ሊሠራ ይገባል። እውነታውን መግለፅ ይኖርብናል። ኢትዮጵያ ሁልጊዜም ከጎረቤት ሀገራት ጋር በጋራ በመጠቀምና በአንድነት የማደግ ፍላጎት አላት። ይህንንም የጋራ ተጠቃሚነት ፍላጎት በግልፅ ማሳወቅ እና በዲፕሎማሲያዊ ጥረት ለዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ማስረዳት ይገባል።

ታሪኩ ዘለቀ

አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You