አጠቃላይ ሀገራዊ የመንገድ ሽፋንን ከ182 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ ለማድረስ ታቅዷል

አዲስ አበባ፡በ2017 በጀት ዓመት አጠቃላይ የመንገድ ሽፋንን ከ182 ሺህ ኪ.ሜ በላይ ለማድረስ ማቀዱን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታወቀ።

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የኮሙኒኬሽን የኅትመት ቡድን መሪ አቶ ተወዳጅ መልካሙ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በተያዘው የ2017 በጀት ዓመት አጠቃላይ የመንገድ ሽፋንን ወደ 182 ሺህ 936 ኪ.ሜ ለማድረስ ታቅዷል።

በአሁኑ ወቅት ከባድ፣ መደበኛ እና ወቅታዊ ጥገናን ጨምሮ በመላው አገሪቱ ከ300 ኘሮጀክቶች በላይ እየተከናወኑ የሚገኙ ሲሆን በሚሠራው አጠቃላይ የመንገድ ግንባታ ሥራም በበጀት ዓመቱ መጨረሻ አጠቃላይ የመንገድ ሽፋንን ከ165 ሺህ 863 ኪሎ ሜትር ወደ 182 ሺህ 936 ኪ.ሜ ለማድረስ ታቅዷል ብለዋል።

አቶ ተወዳጅ እንደገለጹት፤ በተያዘው በጀት ዓመት በአጠቃላይ ከ17 ሺህ 938 ኪ.ሜ በላይ የመንገድ ጥገና እና ግንባታ ሥራ ለማከናወን ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል። ከዚህም የአንድ ሺህ 91 ኪ.ሜ የመንገድ ግንባታዎችን ለማከናወን የታቀደ ሲሆን 762 ኪ.ሜ የአዳዲስ መንገዶች ግንባታ፣ 314 ኪ.ሜ የነባር መንገዶች ደረጃ ማሻሻል፣ 15 ኪ.ሜ የነባር መንገዶችን ማጠናከር ሥራ መሆኑን አስታውቀዋል።

እንዲሁም 126 ኪ.ሜ የመንገዶች ከባድ ጥገና፣ 810 ኪ.ሜ የመንገዶች ወቅታዊ ጥገና እና 13 ሺህ 600 ኪ.ሜ የመንገዶች መደበኛ ጥገና ለማከናወን እቅድ መያዙን ገልጸዋል።

በአጠቃላይ ለካፒታል በጀት ከ85 ቢሊዮን ብር የተመደበ እንዲሁም ለመደበኛ በጀት ከመንግሥት 951 ሚሊዮን ብር እና ለጥገና ከመንገድ ፈንድ ዘጠኝ ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር መመደቡንም አስታውቀዋል።

በዘርፉ ላይ የሥራ ተቋራጮች አቅም ውስንነት፣ የወሰን ማስከበር ችግር፣ የዲዛይን ጥራት መጓደል፣ የግንባታ ግብዓቶች እጥረት እና ዋጋ ንረት፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ ኢንዱስትሪው በበቂ ደረጃ በምርምር አለመደገፉ እንዲሁም አጠቃላይ የአቅም እና ከአሠራር ሥርዓት ጋር የተያያዙ ክፍተቶች በዋናነት እንደተግዳሮች ይጠቀሳሉ ብለዋል።

ይህም የመንገድ ኘሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ፣ በጀት እና የጥራት ደረጃ እንዳይጠናቀቁ ከማድረግ ባለፈ በዘርፉ በየጊዜው እየጨመረ የመጣ የዋጋ ንረት እንዲከሰት አድርጓል። በመሆኑም በ2017 በጀት ዓመት የግንባታ ፕሮጀክቶችን በጥራት፣ በወቅቱ እና በብቃት ተግባራዊ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።

በዚህም በግንባታ ሂደት ላይ እና ግንባታቸው ለዘገየ ፕሮጀክቶች አፈፃፀም ማሻሻያ ስትራቴጂ ቀርፆ ተግባራዊ ማድረግ፣ የተቋረጡ ፕሮጀክቶችን ደረጃ በደረጃ ማስጀመር ሥራ የሚሠራ መሆኑን አቶ ተወዳጅ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ከተጀመሩ ረጅም ጊዜ ለሆናቸው ፕሮጀክቶች ግልጽ የማጠናቀቂያ ስትራቴጂና እቅድ አውጥቶ ማጠናቀቅ፣ ውላቸው ተፈርሞ በተለያየ ምክንያት ያልተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ተገቢውን ክትትል በማድረግ ተግባርም እንደሚተገበርም  አስታውቀዋል።

ማሕሌት ብዙነህ

አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You