አዲስ አበባ፡- አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት ክፍሎች እና አካባቢዎች ያሉ ነባር ህንጻዎቹን በአዲስ ለመቀየር ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ገለጹ፡፡
ፕሬዚዳንቱ ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሀና ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት፣ ዩኒቨርሲቲው በህንጻ ግንባታ በኩል በጣም ኋላ ቀርና ያረጁ በመሆናቸው ለመማር ማስተማር ምቹ አልነበሩም፡፡በዩኒቨርሲቲው በቅርስነት ከሚቀሩት በስተቀር ሌሎቹ በአዳዲስ ግንባታዎች ይተካሉ።
በአሁኑ ወቅት በሁሉም ካምፓሶች ያሉት የዩኒቨርሲቲው መምህራን ቢሮዎች በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ የተጎዱና ያረጁ ናቸው ፤ ከዚህ አንጻር ባለፉት ሶስትና አራት ዓመታት ዩኒቨርሲቲው የአዳዲስ ህንጻ ግንባታዎች ያስፈልጉታል ተብሎ ወደ ሥራ መገባቱን ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል።
እንደ ፕሮፌሰር ጣሰው ገለጻ ዩኒቨርሲቲው የተማሪዎቹ ቁጥር እያደገ ከመሆኑና የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎችን ቁጥር በእጥፍ ለማሳደግ ካለው እቅድ አንጻር በሁሉም ካምፓሶች ያሉትን ቪላ ቤቶችና ሌሎችን ለቅርስነት ከሚፈለጉት በስተቀር ሁሉንም በአዲስ የመቀየር እቅድ መያዙን ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅትም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ ውስጥ እየተሰራ ያለው ህንጻ ሲጠናቀቅ የማህበራዊ ሳይንስ ትምህርት ክፍሎች በሙሉ ህንጻው ውስጥ ይገባሉ ፣ ይህ ደግሞ የመማር ማስተማር ሥራውን ምቹና ሳቢ ያደርገዋል እንደ ፕሮፌሰር ጣሰው ገለጻ።
መንግሥት “ድባብ “ ተብሎ የሚጠራውን በዩኒቨርሲቲው ፊት ለፊት ያለውን ቦታና በሲኤም ሲ 12 ሄክታር መሬት ሰጥቷል በእነዚህ ቦታዎች ላይ ትምህርት ክፍሎችን የማስፋፋትና ደረጃቸውን የጠበቁ ለሠራተኞች መኖሪያ የሚሆኑ ህንጻዎችን ለመገንባት እቅድ መኖሩን አብራርተዋል ።
ፕሬዚዳንቱ “አሁን ያለው የዩኒቨርሲቲው መሰረተ ልማት በጣም ያረጀ ፤ትምህርትን በዘመናዊ መንገድ ለመስጠት የማያስችል በመሆኑ ግንባታዎችን በተቻለ ፍጥነት በማጠናቀቅ ጥሩ የመማሪያ የምርምርና ለሠራተኞች የተመቻቸ መኖሪያ ቤት እንዲኖሩ ይደረጋል “ ብለዋል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 3/2011
እፀገነት አክሊሉ