የኢሬቻ በዓልን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ለማሳደግ

ኢትዮጵያ የበርካታ እሴቶች መገኛ ነች። በዓለም አቀፍ ቅርስነት የተመዘገቡ 16 የሚደርሱ መስህቦችን በዩኔስኮ በማስመዝገብ ያህን ካደረጉ ጥቂት ሀገሮች ተርታ ተመደባለች። ሀብቶቹ የሰው ልጆችን ቀደምት ስልጣኔ፣ የኑሮ ዘይቤ፣ የማህበረሰብ ባሕላዊ እሴት፣ ታሪክ እንዲሁም የሰው ዘር አፈጣጠርን የሚያሳዩ የአርኪዮሎጂካል መካነ ቅርሶችን ጭምር ያካተቱ ናቸው።

የቱሪዝም በረከቶቹን ለመመልከት ወደ ሀገሪቱ በርካታ ጎብኚዎች ይመጣሉ። ሀብቶቹን በሚፈለገው ልክ አልምቶ፣ አስተዋውቆ የቱሪስት ፍሰትን አሁን ካለው ቁጥር በተሻለ ማሳደግ ከተቻለ ከኢትዮጵያዊ እሴትነት ባሻገር ለሀገሪቱ ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ አቅም ለመገንባትም የገዘፈ ሚና እንደሚኖራቸው የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በመስከረም ወር ከፍተኛ ቁጥር ያለው ጎብኚ ከሚገኝባቸውና ኢትዮጵያዊ የሆኑ ባሕላዊ እሴቶች ከሚታዩባቸው ክብረ በዓሎች መካከል የኦሮሞ ማህበረሰብ ባሕል፣ ወግና የኑሮ ዘይቤ በከፍተኛ ደረጃ የሚንፀባረቅበት የኢሬቻ በዓል አንዱ ነው። በዓሉ ማህበረሰቡ በየዓመቱ ስለ ልምላሜ፣ ስለ ሰላም እና ከዓመት ወደዓመት ስላሸጋገረው ፈጣሪው ምስጋና የሚያቀርብበትና ከፍተኛ ቁጥር ያለው ታዳሚ ልዩ ልዩ ባሕላዊ እሴቶቹን የሚያሳይበት ነው።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በዚህ ተወዳጅ ባሕላዊ ፌስቲቫል ላይ ዓለም አቀፍ ጎብኚዎች፣ ከኢትዮጵያ የተለያዩ ክፍሎች በክብረ በዓሉ ላይ ለመታደም የሚሹ ኢትዮጵያውያን፣ በውጭ የሚኖሩ የማህበረሰቡ ተወላጆች የሚገኙበት እየሆነ ነው። ከጊዜ ወደጊዜም ከባሕላዊ ከበረ በዓሉ ባሻገር የቱሪዝምና የኢኮኖሚ ምንጭ በመሆን እየታወቀ ነው።

አቶ ነጋ ወዳጆ የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ ኮሚሽኑ ከምስረታው አንስቶ በክልሉ የሚገኙ የቱሪስት ሀብቶችን በማስተዋወቅ፣ በማልማት ሀገሪቱ ከቱሪዝም የምታገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን ይገልፃሉ። የቱሪዝም አቅም መሆናቸው ከታመነባቸው ሀብቶች መካከልም ባሕላዊ ሀብቶች እንደሚጠቀሱ ገልጸው፣ ከእነዚህ ውስጥም የኢሬቻ ዓመታዊ ክብረ በዓል አንዱ መሆኑን አመልክተዋል።

‹‹የኢሬቻ በዓልን በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ አደባባይ በመውጣት ያከብረዋል›› የሚሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ የዓለም አቀፍና የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ትናንት በተከበረው ሆራ ፊንፊኔ፣ እንዲሁም ዛሬ እየተከበረ በሚገኘው ሆራ ሀርሰዲ ቢሾፍቱ ክብረ በዓል ላይ ከማህበረሰቡ ጋር በጋራ ለማክበር እንደሚገኙ ይገልፃሉ።

በርካታ ቁጥር ያለው ታዳሚ በሚገኝባቸው በእነዚህ ቀናት የኢኮኖሚ ጥቅምን የሚፈጥሩ፣ የሆስፒታሊቲ ዘርፉን የሚያነቃቁ እንቅስቃሴዎች እንደሚፈጠሩ የሚናገሩት አቶ ነጋ፤ የማረፊያ፣ የመስተንግዶና ሌሎችም ባሕላዊ ቁሳቁስ ላይ ፍላጎቱ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጨምር ይገልፃሉ። ይህን መሰል ፌስቲቫል ሀገሪቱ በቱሪዝም ዘርፉ በኢኮኖሚዋ ላይ በጎ ተፅእኖ ለመፍጠር የምታደርገውን ጥረት እንደሚያግዝ ያስረዳሉ። በአዲስ አበባና በቢሾፍቱ ከተማዎች ለሁለት ቀናት ወጪ የሚደረገው መዋለ ንዋይ ለአገልግሎት ዘርፉ ከፍተኛ ጥቀሜታን እንደሚያስገኝም ይናገራሉ።

ምክትል ኮሚሽነሩ እንደሚገልፁት፤ የኢሬቻ በዓል ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ጎን ለጎን ማህበረሰብን ለማቀራረብ ከፍተኛ ድርሻ አለው። ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚመጡ፣ ከጎረቤት ሀገራት እንዲሁም ከመላው ዓለም የሚመጡ የሰው ልጆችን በማቀራረብ ረገድ አስተዋጽኦው ጉልህ ነው።

በተለይ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ለበዓሉ የዘገባ ሽፋን ለመስጠት ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል፡፡ ይህም ይህን ታላቅ ፌስቲቫል በቀላሉ በተለያዩ ሀገራት ለበርካታ ሚሊዮን ሰዎች ለማድረስ፣ ባሕሉን ለማስተዋወቅና ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣውን የቱሪስት ቁጥር ለመጨመር ያግዛል። ኮሚሽኑም ይህንን አቅም ከዓመት ወደ ዓመት ለማሳደግ እየሰራ ነው።

የኢሬቻ ፌስቲቫል ከባሕላዊ ክብረ በዓልነቱ ባሻገር ኢኮኖሚያዊ አቅሙ እያደገ እንዲመጣ ኮሚሽኑ የተለያዩ አማራጮችን በመፍጠር ላይ እንደሆነ የሚገልፁት አቶ ነጋ፤ ከእነዚህ ስልቶች መካከል ከበዓሉ ቀናት አስቀድሞ ልዩ ልዩ ባዛሮችና ኤግዚቢሽኖች መዘጋጀታቸውን ያስረዳሉ። ከዚህ መካከል በስካይ ላይት ሆቴል የተካሄደው የ2017 ዓ.ም የኦሮሚያ የቱሪዝም ሳምንት ኤግዚቢሽን እና ሌሎች መሰል ሁነቶች ተጠቃሽ መሆናቸውን ይናገራሉ።

በእነዚህ ዝግጅቶች ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ አስጎብኚ ድርጅቶች፣ ሆቴሎች፣ ባንኮች፣ የቴሌኮምና የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች እንዲሁም የቱሪዝም ዘርፍ ባለድርሻዎች እንደተሳተፉ ይገልፃሉ። ዓለም አቀፍ ተደራሽነቱን ለማስፋትም ዘንድሮ ከቡሩንዲ፣ ኡጋንዳ፣ ኬኒያ፣ ሩዋንዳ፣ ኔፓል ከመሳሰሉት ሀገራትም ምርትና ሀብቶቻቸውን ለማስተዋወቅ የተለያዩ አካላት መገኘታቸውን ይገልፃሉ።

ኢሬቻን ከባሕ ባሕላዊ ክብረ በዓልነቱ ባሻገር የሚያስገኘውን የኢኮኖሚ አቅም ለማጠናከር በየጊዜው ማሻሻያዎች ማድረግ ተገቢ መሆኑን የሚያነሱት አቶ ነጋ፤ በምሳሌነት በብራዚል የሚካሄደውን ዓመታዊ ካርኒቫል ይጠቅሳሉ። ይህ በዓል በአሁኑ ሰዓት በዓመት በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር የሚገኝበት መሆኑንም አስታውቀዋል።

ወደ ኢሬቻ ተመልሰውም በዓሉ ተመሳሳይ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ማስገኘት እንዲችል በበዓሉ ላይ የሚታደመው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ሊዝናና፣ ለማስታወሻ ሊገዛው እንዲሁም ሌሎች ወጪዎችን ፈሰስ ሊያደርግ የሚችልባቸው የገበያ አማራጮችን መፍጠር እንደሚገባ ይናገራሉ። ኮሚሽኑም ይህንን ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ብራዚልን ከመሳሰሉ በካርኒቫሎቻቸው ከፍተኛ የኢኮኖሚ ምንጭ ከሚፈጥሩ ሀገራት ተርታ አሁን ላይ አልደረስንም የሚሉት አቶ ነጋ፤ በጊዜ ሂደት ግን ኢሬቻ እዚያ ደረጃ መድረሱ እንደማይቀር ይናገራሉ። ይህንን እቅድ እውን ለማድረግ የሚያስችሉ መሠረታዊ የማልማት፣ የማስተዋወቅ፣ የኢኮኖሚ የገበያ አማራጮችን የማስፋት ተግባራት መጀመራቸውን በመግለጽም ሥራዎቹ ከጊዜ ጋር ወደዚያኛው ራዕይ የሚያቀርቡ እንደሆነ ነው የሚናገሩት።

እሳቸው እንዳስታወቁት፤ ይህንን መሰል ራዕይ በኢሬቻ ላይ ብቻ ሳይሆን በመስቀል፣ ጥምቀትና በሌሎች በኢትዮጵያ ውስጥ በሚከበሩ ሃይማኖታዊና ባሕላዊ ፌስቲቫሎች ላይ ተግባራዊ ማድረግ ይገባል፡፡ እነዚህ ኢትዮጵያዊ እሴቶች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸው ከፍተኛ ነው፤ በጋራ ሁሉንም በሚጠበቀው ደረጃ በማልማትና ዓለም አቀፍ ተደራሽነታቸውን በማስፋት የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት ያስፈልጋል። ለዚህም የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀትና ንቅናቄዎችን በመፍጠር ወደ ተግባር ይገባል፡፡

በዘንድሮው በዓል ላይ ትናንት በአዲስ አበባ በተከበረው ሆራ ፊንፊኔ እንዲሁም ዛሬ በሆራ ሀርሰዲ ቢሾፍቱ የሚከበረውን ጨምሮ በበዓሉ ላይ እስከ 10 ሚሊዮን የሚደርስ ሕዝብ እንደሚገኝ የጠቆሙት አቶ ነጋ፤ ታዳሚዎች በሁለቱም ከተሞች ለማረፊያ፣ ለምግብ፣ ለባሕላዊ አልባሳትና ለልዩ ልዩ ጉዳዮች ከ10 እስከ 25 ቢሊዮን ብር ኢኮኖሚያዊ ፈሰስ ይደረጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ያስረዳሉ። ከዚህ መነሻ አገልግሎት ሰጪዎች፣ አምራቾች እዚህ ፌስቲቫል ላይ ትኩረት አድርገው በየዓመቱ አዳዲስ የገቢ አማራጮችን ቢፈጥሩ ውጤታማ መሆን አንደሚችሉም ጠቁመዋል።

‹‹በርካታ ሀገራት ኢትዮጵያውያን ያሏቸው ባሕላዊ እሴቶች እንዲኖራቸው ይመኛሉ›› የሚሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ ምክንያቱም መሰል መስህቦች ከባሕላዊ እሴትነት ባሻገር ከፍተኛ የኢኮኖሚ አቅም በመፍጠራቸው እንደሆነ ይገልፃሉ። ኢትዮጵያም በመስህብ ሀብቶች ብዛት የታደለች እንደመሆኗ ከሀብቱ ተጠቃሚ ለመሆን መዘናጋት እንደማይገባ ይናገራሉ። ማህበረሰቡ እሴቶቹ ብቻ ሳይሆኑ የሕዝብ ቁጥሩ ትልቅ የገበያ አቅም እንደሚፈጥር ጠቅሰው፣ ይህንን አማራጭ በሚገባ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚያስፈልግ ያስረዳሉ።

እንደ ምክትል ኮሚሽነሩ ማብራሪያ፤ የኢሬቻ ከብረ በዓል በሚፈለገው ደረጃ እንዲከበር ለማድረግ ልዩ ልዩ ዝግጅቶች ይደረጋሉ፤ ከዚህ ውስጥ ዋናውን ድርሻ የሚወስደው የአገልግሎት ዘርፉ የሚያደርገው ዝግጅት ነው።

ከውጭም ሆነ ከሀገር ውስጥ በክብረ በዓሉ ላይ ለመታደም የሚመጡ እንግዶች ተገቢውን መስተንግዶ፣ እንክብካቤና ደህንነቱ የተጠበቀ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችሉ ሥራዎች ተሰርተዋል። ለእዚህም በተለይ ከሆቴል ባለቤቶች ጋር ውይይቶች ተደርገዋል፡፡

ይህን ተከትሎም ከ15 እስከ 45 በመቶ የሚሆን ቅናሽ በማድረግ ጭምር እንግዶችን ተቀብለው እያስተናገዱ የሚገኙ ሆቴሎች መኖራቸውን ምክትል ኮሚሽነሩ ይናገራሉ። ይህም የውይይቱና የቅድመ ዝግጅቱ ውጤት መሆኑንም ያስረዳሉ። እንግዶች ሳይጉላሉ የበዓሉን እሴቶች በሚገባ ጎብኝተውና ተሳታፊ ሆነው መመለሳቸው ለፌስቲቫሉ እያደገ መምጣት ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረውም ይገልፃሉ።

መንግሥት ኢሬቻን ከመሰሳሉ ፌስቲቫሎች ላይ ቀጥተኛ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዳልሆነ የሚገልፁት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ ይሁን እንጂ ከግብርና መሰል ጉዳዮች በተዘዋዋሪ ገቢዎች እንደሚያገኝ ያስረዳሉ። ሆኖም ግን ከቱሪዝም ዘርፍ ዋንኛው ተጠቃሚው የግሉ ዘርፍ መሆኑን በማንሳት ይህንን በመሳሰሉ ፌስቲቫልና ክብረ በዓሎች ላይ ንቁ የሆነ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚገባው ይገልፃሉ። በተለይ በዓሉን በዓለም አቀፍ ደረጃ በማስተዋወቅ፣ የተለያዩ ኢንቨስትመንቶችን በማድረግ ኢሬቻ ላይ የሚታደሙ ጎብኚዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲጨምሩና ኢኮኖሚያዊ አማራጩም እንዲሰፋ ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የሌሎች ሀገራት ልምድ የሚያሳየው ካርኒቫሎቻቸው ተከብረው በተጠናቀቁበት ማግስት ለቀጣይ ዓመት ዝግጅት እንደሚጀምሩ ነው ያሉት አቶ ነጋ፤ በኢትዮጵያ መሰል ልምድ ደካማ እንደሆነ ይናገራሉ። ይህንን ባሕል ለመቀየር የግሉ ዘርፍ በልዩ ትኩረት በቅንጅት ለጋራ ጥቅም መሥራት እንደሚገባው ይናገራሉ።

በተለይ ኢሬቻ ለማክበር ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ጎብኚዎች ቆይታቸውን አራዝመው ሌሎችንም የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች እንዲጎበኙ፤ ይዘውት የመጡትን ሀብት በሚገባ አውጥተው እንዲሄዱ ሊሰሩ ይገባል ይላሉ። ለዚህም ቱር ኦፕሬተሮች፣ አስጎብኚ ባለሙያዎች እንዲሁም በቱሪዝም ሆስፒታሊቲ ላይ የተሰማሩ ባለድርሻዎች ቀደም ብለው በመዘጋጀት ተግባራዊ ለውጥ ማምጣት እንዳለባቸው ይገልፃሉ።

‹‹የኢትዮጵያ አየር መንገድን የሚያክል ትልቅ አቅም አለን። ሆቴሎቻችን እንግዶችን ማስተናገድ የሚያስችል ቁመና አላቸው›› የሚሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ እነዚህን ማቀናጀት ብቻ ትልቅ ለውጥ ይዞ እንደሚመጣ አስታውቀዋል። ይህንን አቅድ ተግባራዊ ከማድረግ አንፃር የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ከቱር ኦፕሬተሮች፣ ሆቴሎች እና የግሉ ዘርፍ ላይ በኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለቤቶች ጋር ግንኙነት በመፍጠር በጋራ ለመሥራት ውይይት እንደሚደረግ ይገልፃሉ።

የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን የኢሬቻ ክብረ በዓልን ጨምሮ በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ መስህቦች እንዲተዋወቁና ሀገርም ከዚያ ተጠቃሚ እንድትሆን እንደሚሰራ የሚናገሩት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ ይህን መሰል ሥራ በአንድና በሁለት ተቋም ብቻ የሚሰራ እንዳልሆነም አመልክተዋል፡፡ ሥራው የሁሉም ኢትዮጵያዊ ኃላፊነት መሆኑን ጠቁመው፣ እያንዳንዱ ዜጋ ስለ ሀገሩ ባሕል፣ የመስህብ ሀብት ሊሞግት፣ ሊያስተዋውቅ እና አምባሳደር ሊሆን ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል። ይህ መሆን ከቻለ የታለመው የኢትዮጵያ የቱሪዝም እድገት በቅርብ ጊዜ ውስጥ እውን እንደሚሆን አስታውቀዋል።

ዳግም ከበ

አዲስ ዘመን እሁድ መስከረም 26 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You