ኢሬቻ፣ የአብሮነት እሴት! የኦሮሚያ ኮሙኒኬሽን ቢሮ

መግቢያ

ኢሬቻ ከገዳ ሥርዓት ተቋማት አንዱ ሲሆን ለፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብበት በዓል ነው፡፡

ኢሬቻ በሰውና በፈጣሪው እንዲሁም በሰውና በፍጥረታት መካከል ለሚኖረው የተፈጥሮ ሕግ በአፋን ኦሮሞ “ሰፉ” ተገዥነቱን የሚገለፅበት ክብረበዓል ነው፡፡ የተፈጥሮ ሕግ እንዳይዛባ እስካሁን ላቆያቸው ፈጣሪ በጋራ ሆነው ለዋቃ ምስጋና የሚያቀርቡበት ነው፡፡ ከተፈጥሮ ጋር ያለውን ግንኙነት ወይም ትስስር የሚያድሱበት በዓል እንጂ በራሱ ሃይማኖት አይደለም። ኢሬቻ ከእርቅ፣ ከይቅርታ፤ ከኅብረት፣ ከፍቅርና ከሠላም ጋር ይመሳሰላል፡፡

  • ኢሬቻ በዓመት ሁለት ጊዜ ይደረጋል፡፡ እነሱም፡-
  • ኢሬቻ መልካ፡- ይህ ኢሬቻ በወርሐ መስከረም በመልካ ላይ የሚከበር በዓል ነው፡፡ የመልካ ኢሬቻ የተፈጥሮ ሕግ ሳይዛባ ለመቆየቱ ወደ ፊትም ሚዛኑ እንዲጠበቅ ለዋቃ ቶኪቻ (ለአንድ ፈጣሪ) ለምለም ሳር ተይዞ ምስጋና የሚቀርብበት እለት ነው፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ በክረምት ወራት ዝናብ ለሰጠው ዋቃ/ፈጣሪ ምስጋና ያቀርባል፡ ፡ በቀጣይም ቡቃያው ከየትኛውም የተፈጥሮ አደጋ ተጠብቆ፤ በሠላም ወደ ጎተራው እንዲገባ ፈጣሪን የሚማጸንበት ነው፡፡
  • ኢሬቻ ቱሉ፡- ይህም የሚከናወነው የበጋው ወራት ተገባዶ በልግ/አርፋሳ ሲገባ ነው፡፡ በአቅራቢያ በሚገኙ ተራራማ ቦታዎች ላይ በመውጣት ለመጪው ክረምት ዝናብ ስጠን፣ ወራቱን የአዝመራ ጊዜ አድርግልን፣ በማለት ፈጣሪን ይለምናሉ፡፡
  • ኢሬቻ ለምን ይከበራል?

 

ኢሬቻ ለሁለት ትላልቅ ምክንያቶች ይከበራል፡፡ ፈጣሪ ለሰው ልጅ ላደረገው መልካም ነገር ምስጋና ለማቅረብ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ወደ ፊት እንዲሆን ለሚፈለግ ነገር ለመማጸን ነው፡፡ በዚሁ መሠረት የኦሮሞ ሕዝብ ከባዱን የክረምት ወራት ላሳለፈ ዋቃ/ፈጣሪውን፣ ወደ መልካ በመውረድ ያመሰግናል፡፡ ሁሉን የፈጠረውን አምላክ፣ ሁሉን አሳልፎ ለዚያ ያበቃውን ፈጣሪ፣ በንጹሕ ልቦና በማመስገን ይቅርታን ይጠይቃል፡፡ ዓመቱም የሠላም፣ የፍቅር፣ የስኬትና የብልፅግና ይለምናል፡፡ በዚህ ወቅት ርስ በርስም እንኳን ለብራ /ፀደይ ወቅት/ አደረሳችሁ በመባባል ደስታውን ይገልጽበታል፡፡ ኢሬቻ የምስጋናና የልመና እሴት ስለሆነ ለምለም ሳርና አደይ አበባ ይዞ፣ ከየአቅጣጫው ተሰባስቦ በመልካ /ወንዝ/ ያመሰግናል፡፡ ሴቶችም የሚከተለውን ዜማ እያዜሙ ለምስጋና ይሄዳሉ።

Mareehoo, mareehoo, mareehoo; ዞሮ መጣልን (3)

Alaa mana nuuf toli yaa ayyoleehoo; ከውስጥም ከውጪም መልካም ሁሉ ይሁንልን

Mareehoo, mareehoo, mareehoo; ዞሮ መጣልን(3)

Mee nutti araarami yaa ayyoleehoo; እባክህ ታረቀን እያሉ ለምስጋና ወደ መልካው ይሄዳሉ፡፡

ወንዶችም ከኢሬቻ ሲመለሱ /Gabbisayyoo/ ገብሰዮ እያሉ እያዜሙ ይመለሳሉ፡፡

Gabbisayyoo hoo…hoo… roobee biyya gabbisee Gabbisayyoo hoo..hoo… roobee biyya gabbisee Gabbisayyoo hoo…hoo roobii lafa nuuf ga’i,

Gabbisayyoo hoo…hoo yaa Waaqi ati nuuf nahi… ይላሉ፡፡

ይህም ተሳካልን፤ በሠላም ተመለስን የሚል መልእክት አለው፡፡

  1. የኢሬቻ ወግና ሥርዓት

 

የኢሬቻ በዓል በታላቅ ድምቀትና ሥርዓት የሚከበር በዓል ነው። በዚህ በዓል ላይ መደረግ ያለባቸውና የሌለባቸው ሥርዓቶች አሉ፡፡

  • ቂም እና ጥላቻ ይዞ ለምስጋና መውጣት የተከለከለ ነው፡፡
  • ከአባ መልካ ቀድሞ ወደ ኢሬቻ ስፍራ ገብቶ ማመስገን የተከለከለ ነው፡፡
  • የኢሬቻ ስፍራ ክቡር ነው፤ ቆሻሻ አይጣልበትም፤
  • በሌሊት ለኢሬቻ አይወጣም፣ ሥርዓት አይደለም/ የተከለከለ ነው፡፡
  • በደፈረሰ ወንዝ፣ ክረምት ውስጥ ለኢሬቻ አይወጣም፤ ሥርዓት አይደለም /የተከለከለ ነው፡፡
  • ወንዶች ዛጎል አያደርጉም፤ ሥርዓት አይደለም / የተከለከለ ነው፡፡
  • ልጃገረዶች ሲንቄ አይዙም፤ ሥርዓት አይደለም / የተከለከለ ነው፡፡
  • ያለ ለምለም ሳር ለምስጋና ወደ ኢሬቻ አይኬድም፤ ሥርዓት አይደለም /የተከለከለ ነው፡፡
  • ኢሬቻ፣ የአብሮነት እሴት!

 

ኦሮሞ ለአብሮነትና ለወንድማማችነት ትልቅ ስፍራ አለው። በባሕሉም በሞጋሳና ጉዲፈቻ አማካይነት ባዳ አስጠግቶ ባሕሉን በማውረስ፣ ሀብትና ንብረቱን በማካፈል አብሮ ይኖራል፤ ዝምድናውንም ያጠናክራል፡፡ በዚህ መሠረት ትልቅ ትንሹን እንዲያከብር፣ በወንድማማችነት አብሮ እንዲኖር ያደርጋል፡፡ የኢሬቻ በዓልም ይህንን ወግና ባሕል በማጠናከር ለአንድ ዓላማ የወጡ ሰዎች በንጹሕ ልብና አዕምሮ ፈጣሪያቸውን አመስግነው እንዲመለሱ፣ አንድነታቸውንና ወንድማማችነታቸውን እንዲያጠናክሩ ያበረታታል፡፡ እንደ ኢሬቻ ወግና ሥርዓት ከተለያየ ስፍራ የሚመጡ ተሳታፊዎች ያለምንም ልዩነት፣ በፍቅርና በአንድነት ፈጣሪን ያመሰግናሉ፡፡ አብሮ ማመስገንና በጋራ መሳተፍ፣ መዝናናትና ጊዜን ማሳለፍ ደግሞ ርስ በርስ ለመተዋወቅና ባሕል ለመለዋወጥ ይረዳል፤ ወንድማማችነትንና አንድነትንም ያጠናክራል።

የኢሬቻ በዓል የደስታ በዓል ሲሆን ኦሮሞ በዕድሜ፣ በፆታ፣ በሃይማኖት፣ በአመለካከትና በኑሮ ደረጃ ሳይከፋፈል በአንድነት ወጥቶ የሚያከብረው በዓል ነው። ስለዚህ ኢሬቻ ኦሮሞ አንድነቱን፣ ወንድማማችነቱን፣ ፍቅሩን፣ ብሔራዊ ኩራቱን፣ ታሪክና ባሕሉን የሚገልጽበትና የሚያድስበት መድረክ ነው። ለኦሮሞ የሃይማኖትና የባሕል ልዩነት ውበቱና የአንድነቱ መሠረት እንደሆነ ኢሬቻ ዓይነተኛ ማሳያ ነው፡፡ የኢሬቻ በዓል የኦሮሞን አንድነትና የብሔር ብሔረሰቦች ወንድማማችነት ከማጠናከር አንፃር ምቹ መድረክ እየሆነ መጥቷል፡፡

  • ኢሬቻ፡ የእርቅ፣ የምርቃትና የሠላም መድረክ!

 

ኢሬቻ የእርቅና የሠላም መድረክ ነው፡፡ የኢሬቻ እሴቶች ከሠላምና ከእርቅ ጋር ያላቸው ትስስር በዋነኝነት ይጠቀሳል። የኢሬቻ በዓል ከመድረሱ በፊት አባገዳዎችና የሃገር ሽማግሌዎች በየአካባቢው እየሄዱ በማኅበረሰቡ መካከል ቅሬታና አለመግባባት ካለ እንዲፈታ፣ ይቅር እንዲባባሉ፣ ደም የተቀባ ካለ ጉማ /ካሣ/ እንዲከፍል ያደርጋሉ፡፡ እርቅ ሳያወርዱ ቂም ይዞ ለምስጋና ወደ ኢሬቻ መሄድ የተከለከለ (Morally sanctioned) ነው፡፡ ኢሬቻ በንጹሕ ልቦናና በንጹሕ አዕምሮ፣ ያለ ቂምና ቁርሾ ተኬዶ ሠላም የሚሰበክበት ነው፡፡ ኢሬቻ የሚካሄድበት ስፍራ ሁሉ የሠላምና የእርቅ ቦታ ነው፡፡ ለምስጋና መልካ ከተወረደ በኋላም አባገዳዎች እርስ በርሳችሁ ይቅር ተባብላችኋል? እርስ በርሳችሁ ሠላም ናችሁ? ከፍጥረታትና ከፈጣሪ ጋር ሠላም አውርዳችኋል? ብለው ይጠይቃሉ። ምናልባት በየአካባቢው እርቅ ሳያወርድ የመጣ ካለ እንኳን በዚህ ወቅት ይቅርታ በመጠያየቅ ምስጋናውን አቅርቦ ይሄዳል። ስለዚህ ለምስጋና ለምለም ሣር ይዞ የሚወጣ ሰው ቂምና ጥላቻን አስወግዶ፣ ሠላምን፣ ወንድማማችነትን፣ ፍቅርን፣ አንድነትን፣ ተስፋን፣ ብልፅግናንና መልካም ምኞትን ይሰብካል፤ ያውጃል። ከፈጣሪው ለተሰጠው ስጦታ እውቅና ይሰጣል፤ ያመሰግናል። በፍጥረታትና በፈጣሪ መካከል ያለውን ትስስር ያደንቃል፡፡ ሲያመሰግንም ለቤተሰብ፣ ለጎረቤት፣ ለአጠቃላይ ለሰው ልጅ፣ ለሀገር ሠላምና ፍቅር በመመኘት ይዘምራል፤ ያመሰግናል፤ ይለምናል፡፡ ይህ ደግሞ ኢሬቻ የእርቅና የሠላም ተምሳሌት መሆኑን ያመለክታል። ከዚህ የምንረዳው ኢሬቻ የሠላምና የእርቅ መድረክ መሆኑን ነው፡፡ ለዚህ ነው ኦሮሞ ሰው እርስ በርሱ ከተታረቀ ፈጣሪም ይታረቀዋል ብሎ የሚያምነው። ከዚህ በተጨማሪም ኢሬቻ ምርቃት የሚሰጥበትና የሚቀበሉበት ስፍራም ነው፡፡

  • ኢሬቻ ከኢኮኖሚ ጠቀሜታ አንፃር

 

የኢሬቻ በዓል ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎች አሉት። የሀገራችንን መልካም ገጽታ ለዓለም ከማስተዋወቅ አልፎ የገቢ ምንጭ እየሆነ መጥቷል፡፡ በተለይ ለባሕል አልባሳትና ጌጣጌጥ አምራቾች መልካም አጋጣሚ ይፈጥራላቸዋል፡፡ እንዲሁም የሥራ ዕድልን በመፍጠር ለሀገር ተጨማሪ ገቢን ያስገኛል፤ እንደ መዝናኛና የመገናኛ ቦታ ሆኖም ያገለግላል። በተጨማሪም ለሀገራችን ቱሪዝም ኢንዱስትሪ ዕድገት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡፡

የባሕል ልብስ ሥራ እየዘመነ መምጣቱ በባሕል “አብዮት” ውስጥ አስተዋፅፆ አለው፡፡ ይህ ደግሞ የግለሰቦችን ገቢ ከማሳደግ አልፎ የኦሮሞን ባሕልና ማንነት ከማስተዋወቅ አንፃርም አስተዋፅፆው የላቀ ነው፡፡

  • ኢሬቻና የባሕል ህዳሴ

የባሕል ህዳሴ የአንድን ሀገር የሥራ ባሕል፣ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ውስጥ በንቃት በመሳተፍ ታዋቂና ተወዳጅ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ እንደ ኢሬቻ ያሉ ፌስቲቫሎች የባሕል ህዳሴ በማምጣት ረገድ ከፍተኛ ሚና አላቸው። የባሕል ህዳሴ ንቅናቄ ውስጥ ኢሬቻም የራሱ ሚና አለው፡፡ ኢሬቻ በርካታ ተሳታፊዎች የሚገኙበትና በተለያዩ አልባሳትና ጌጣጌጦች ተውበው የሚወጡበት በዓል ስለሆነ በባሕል ተቋማት የሚሠሩ ሥራዎችን ለማሳደግና ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር በማዘመን ለማስፋፋትና ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ያግዛል፡፡

  • ኢሬቻ፡ ለውበትና ለብሔራዊ ኩራት!

ኢሬቻ የውበት መገለጫ ነው፡፡ ይህም ሲባል የበዓሉ ዕለት የሚለበሱ አልባሳት፣ የሚጌጡት ጌጣጌጦች፣ የሚያዙ የክብር ዕቃዎች፣ የተሳታፊዎቹ አሰላለፍና አካሄድ፣ መዝሙሮችና ጭፈራዎች በሙሉ ማራኪ ናቸው፡፡ ሴቶች ሲንቄ ይዘው፣ ጫጩ ደርበው፣ ጨሌ አድርገው፣ ጮጮና ለምለም ሳር ይዘው፣ በባሕላዊ አልባሳትና ጌጣጌጦች አጊጠው መሬ ሆ እያሉ ከአባ ገዳዎችና ሌሎች ተሳታፊዎች ፊት ሲሄዱ ማራኪ ውበት አለው። ባሕልና ውበት በአንድነት ሲታይ የራስን ባሕልና ማንነት ለመግለጽ ተነሳሽነትን ይፈጥራል፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢሬቻ በዓል በዚህ ሁኔታ መከበሩ ወጣቶች ባሕላቸውን እንዲያውቁና እንዲያከብሩ፣ በማንነታቸው እንዲኮሩና ሀገራቸውን እንዲወዱ ከፍተኛ አስተዋፅዖ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

አዲስ ዘመን እሁድ መስከረም 26 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You