ግብር በአግባቡ መሰብሰብ ፍትሐዊነትን ለማስፈን ዋነኛ መንገድ ነው

አዲስ አበባ፡በከተማዋ ከሚገኙ ግብር ከፋዮች በአግባቡ ግብር መሰብሰብ ፍትሐዊነትን ለማስፈን ዋነኛ መንገድ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ፡፡

ከንቲባዋ ከከፍተኛ ግብር ከፋዮች እና ከሸማች ማኅበራት እንዲሁም የቢሮው የሥራ ኃላፊዎች ጋር ባደረጉት ውይይት እንደተናገሩት፤ ግብር በሀብታም እና በድሃ መካከል ያለው ልዩነት ለማጥበብ እና ፍትሐዊ የኑሮ ደረጃ በመፍጠርም ፍትሐዊነትን ለማስፈን ያግዛል፡፡

ከፍተኛ ገቢ ያለው የማኅበረሰብ ክፍል በሚከፍለው ግብር በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኘው ማኅበረሰብ የድጎማ እና የልማት ሥራዎች በማስፋት ሚዛናዊ የኑሮ ሁኔታ ለማስተካከል እና ፍትሐዊነት ለማረጋገጥ የሚረዳ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

‹‹ግብር የውዴታ ግዴታ የምንለው የኃላፊነት መወጫ መንገድ በመሆኑ ነው።›› ያሉት ከንቲባዋ፤ ሁሉም ዜጋ የግብርን አስፈላጊነት ተረድቶ በፈቃደኝነት ቢከፍል ሌብነት እንደሚጠፋ ጠቅሰዋል፡፡ እስከ አሁን ለተፈጠረው ክፍተት ዋነኛ ምክንያት ግብርን በፈቃደኝነት ባለመክፈል መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ግብርን በአግባቡ በመክፈል ከተረጂነት ከመላቀቅ ባሻገር የኢኮኖሚ ነፃነት ማስጠበቅ እንደሚቻል ጠቅሰው፤ የኢኮኖሚ ነፃነት ካልተረጋገጠ በልመና እና በተረጂነት ምክንያት የሚደርሰው ተፅዕኖ እየጨመረ እንደሚመጣ ተናግረዋል፡፡

ሠላም የሚያስጠብቅ አካል በተገቢው መንገድ ለማደራጀት፣ የሕዝብ ትራንስፖርት አቅርቦት በዝቅተኛ ዋጋ ለማቅረብ፣ እንዲሁም ውሃ ለከተማዋ ነዋሪ በዝቅተኛ ዋጋ ለማቅረብ የሚቻለው ሁሉም በአግባቡ ግብር ሲከፍል መሆኑን አስረድተዋል፡፡

እንደ ከንቲባዋ አገላለጽ፤ ኅብረተሰቡ መብቱ በማስጠበቅ ግብር ከፋዩም ግዴታውን በመወጣት ግንዛቤ ሊኖረው ይገባል፡፡ የሚፈለገው አገልግሎት እንዲሟላ ለማድረግ በትብብር መሥራት ከሁሉም በላይ ሊቀድም ይገባል፡፡

ሔርሞን ፍቃዱ

አዲስ ዘመን መስከረም 26 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You