ኢሬቻ የምስጋና፣ የአንድነት እና የመቻቻል በዓል

ኢሬቻ የምስጋናና የአብሮነት በዓል ነው። የኦሮሞ ሕዝብ ከፈጣሪው ጋር የሚገናኝበት፣ አምላኩን የሚያመሰግንበት የተማጽኖ ክብረ በዓል ነው። በማህበረሰቡ ወግና ሥርዓት በሚመራ የአባቶች ምርቃትና ቡራኪ የመስቀል በዓልን ተከትሎ በመዲናችን አዲስ አበባ ሆራ ፊንፊኔ፣ በቢሾፍቱ ከተማ ደግሞ የሆራ ሀር ሰዲ ከፍተኛ ሕዝብ በታደመበት ይከበራል። ላለፉት ስድስት ዓመታት ባሕላዊ እሴቱን ሳይለቅ እንዲህ ባለው የጋራ መንፈስ ሲከበር ሰንብቷል።

ኢሬቻን በትክክል ሊገልጹት ከሚችሉ ሃሳብና ቃላት መካከል የመጀመሪያው ‹የምስጋና በዓል› የሚለው ነው። መነሻና መድረሻውን ምስጋና ያደረገው ኢሬቻ በማህበረሰቡ ዘንድ አንድነትን ፈጥሮ ስለሀገርና ሕዝብ የሚጸለይበት የተማጽኖ እሴት ነው። ከዚህ እውነት በመነሳት ኢሬቻ ፍቅርና አንድነት ወንድማማችነትም የሚጸኑበት የእርቅና የተግባቦት ሥርዓት እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡

ማስረጃ ካስፈለገ ደግሞ በማህበረሰቡ ዘንድ በታሪክ ተመራማሪነታቸው አንቱታን ያተረፉ እንደ ዲሪቢ ደምሴ እና ገመቹ መገርሳ (ዶ/ር) የመሳሰሉ ምሁራኖችን መጥቀስ ይቻላል። እንደምህራኖቹ ገለጻ ኢሬቻ ማለት ዋቃ ‹ፈጣሪ› ማለት ሲሆን የክብረ በዓሉ አላማ ይሄን ፈጣሪ ማመስገን እንደሆነ ይናገራሉ። ኢሬቻ እኩልነትም እንደሆነ የሚገልጹ ብዙ ናቸው። የኑሮ ደረጃ እድሜና ጾታ ልዩነት ሳይደረግበት ለዘመናት በአንድ ሃሳብ ሲከበር እንደቆየ የሚመሰክሩ አሉ፡፡

ምሁራኖቹ ኢሬቻን ከጨለማ ወደ ብርሃን ወይም ደግሞ ከመንጋት ጋር ያያይዙታል። ከክረምት መገባደድ በኋላ የኢሬቻ በዓል የሚከበርበት ዋነኛው ምክንያት ትላንትን ላሳለፈን፣ ጨለማውን ላሻገረን፣ ክረምቱን ወደ በጋ ለለወጠ ፈጣሪ ምስጋና መቸሪያ እንደሆነ ያስረዳሉ። ጠቅለል ሲደረግ የኦሮሞ ሕዝብ ሰማይና ምድርን ለፈጠረው ለሁሉ ጌታ ፈጣሪው ‹ዋቃ› ክብርና ምስጋና ለመቸር ሲል የሚያከብረው በዓል ነው፡፡

ምሁራኑ አያይዘውም የኢሬቻ በዓልን ለማክበር የሚመጣ ታዳሚ እንደ ሳርና አበባ ያሉ እርጥብ ነገሮችን ይዞ ይመጣል። ይሄም ‹አንተ ያጸደከው ነው አብቦ ያፈራው› በሚል ሃሳብ የፈጣሪን በጎነት እያሰበ አሜን የሚልበት እንደሆነ ያስረዳሉ። ከዚህ ጎን ለጎን ኢሬቻ የኦሮሞ ሕዝብ ለመላው የሰው ልጅ ሰላምና ደህንነት፣ ፍቅርና አብሮነት የሚለምንበት የተማጽኖ በዓልም ነው ሲሉ ያክላሉ፡፡

ኢሬቻ ከምስጋና ጎን ለጎን የዘመን መለወጫም በዓል ነው። በተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች እንደሚከበረው የአዲስ ዓመት ማብሰሪያ ማለት ነው። በክረምት ወራት ሳይገናኝ የቆየ ዘመድ አዝማድ በአዲስ ዓመት መጀመሪያው መስከረም ላይ ይገናኛል። ማህበረሰቡም ክረምቱን በሰላም ላሳለፈ ፈጣሪው ምስጋና ያቀርባል፡፡

አባገዳዎችና ሀዳ ሲንቄ በኦሮሞ ባሕላዊ አልባሳት ደምቀው፣ የበዓሉ ተሳታፊዎችም ሥርዓቱን በሚያጎሉ የተለያዩ ዓይነት የጸጉር አሰራርና መዋቢያ አምረው ሲመርቁና ሲመረቁ፣ ሲያመሰግኑና ሲመሰገኑ ማየት በእውነቱ ደስ ይላል። ዓለም ከሰውነት ጀምረው በሰውነት ያበቁ ብዙ ሰዋዊ ክብረ በዓላት አሏት። ለፈጣሪ የሚሆን የምስጋና በዓልን ስታከብር ግን እምብዛም ናት። ቀን ቆጥሮና ቀምሮ ለፈጣሪው ምስጋና ሲያቀርብ የሚታወቀው የኦሮሞ ማህበረሰብ ነው። ይሄ ባሕላዊና ታሪካዊ ልማድ ከሀገር ዘልቆ አፍሪካን፣ ከአፍሪካም ዘሎ ዓለም አቀፍ ሰዋዊ ልማድ ቢሆን ምስጋና ካጣው ፈጣሪ ዘንድ ብዙ ያተርፍልን ነበር፡፡

ኢሬቻ እና የገዳ ሥርዓት የአንድ ሳንቲም ሁለት መልኮች ናቸው። ተወራርሰውና ተሰባጥረው ከትላንት ወደ ዛሬ የመጡ የሥርዓትና የምስጋና ጥምረቶች ናቸው። የገዳ ሥርዓት ሁሉን አቃፊ የእርቅና የሰላም የአብሮነትም ሥርዓት እና እሳቤ ነው። ኢሬቻ ደግሞ የምስጋና በዓል። እኚህ ሁለት የሥርዓትና የውዳሴ ጥምረቶች ከሁሉም ለላቀው ፈጣሪ ቅድሚያ ሰጥተው ኢሬቻ በሚል ስም የፈጣሪ የምስጋና ቀን ላይ አርፈዋል።

መስከረም በርከትከት ያሉ በዓላት የሚከበሩበት መሆኑ ይታወቃል። በተለየ መልኩ የዘንድሮው አዲስ ዓመት በርከት ያሉ የአደባባይ በዓላትን አሳይቶናል። የአደባባይ በዓላት ፍቅርንና አንድነትን፣ እርቅንና ሰላምን ከማውረድ ጎን ለጎን ታሪክን የሚያድሱ፣ አብሮነትን የሚመልሱ ናቸው። እንዲህ ዓይነት ሀገራዊ በዓላት በአሉባልታና መሠረት በሌለው ወሬ መደብዘዝ የለባቸውም።

መልካም እሴቶች ሀገርና ትውልድ ማነጫዎች ናቸው። ከክብረ በዓልነት ባለፈ ትውልዱ ልብ ውስጥ ገብተው ፍቅርና ትህትናን፣ አንድነትንና ይቅርባይነትን ቢያስተምሩት ለመነጋገርም ሆነ ተግባብቶ አብሮ ለመኖር ሃሳብ አናጣም ነበር። ገዳ የሥርዓት ቤት ነው። ፍቅርን አስቀድሞ አንድነትን ያስከተለ አስተሳሰብ። ኢሬቻ ደግሞ ከዚህ ሥርዓት ውስጥ የተጸነሰሰ የምስጋና ክብረ በዓል። ሁለቱም አሁን ላለችው ኢትዮጵያ የተሃድሶ መንፈስን በማዋጣት ረገድ ሚናቸው የጎላ ነው። በገዳ ወደ ፍቅር እንሄዳለን በኢሬቻ ከፈጣሪ ጋር እንታረቃለን፡፡

ትግላችን እኮ ፍቅር የሚያውቅ ትውልድ መፍጠር ነው። ትግላችን እኮ በምክክር ሰላሙን ያጸና ማህበረሰብ መሥራት ነው። ታዲያ እንዲህ ያሉ ሰላም እና ፍቅርን ምስጋናንም ሰባኪ እሴቶች ከሌሉን ኖረውም ካልተጠቀምንባቸው ልፋታችን ምን ይረባናል? መጀመሪያ ያሉንን እንወቅ። መጀመሪያ ባሉን እንድመቅ። ያሉንን እሴቶች በአግባቡ መጠቀም ከቻልን ከምንም በላይ ሰላም ፈጣሪዎቻችን መሆን ይችላሉ፡፡

ሥርዓት የጥበብ መጀመሪያ ነው። ሥርዓት በሌላት ሀገር ላይ ጥበብ ቤቷን አትሰራም። ጥበብ ቤቷን እንድትሰራ ትውልድ ቀራጭ፣ ማህበረሰብ አናጭ በጎ እሴቶች ያስፈልጉናል። እኛ ኢትዮጵያዊነት ጨዋነት የጀመረባቸው ብዙ መልካም እሴቶች አሉን። እያንዳንዱ ብሔረሰብ ግብረገብነትን የተማረበት የጨዋነት መክሊት አለው። ኢትዮጵያዊ የሆነው በዚህ ውስጥ ነው። ግብረገብነትን ባስቀደመ ከስም ሁሉ ባማረው አብሮነት ውስጥ የቆምነው በዚህ በኩል ነው።

እንደ ሀገር ትልቁ ድክመታችን ያሉንን አለማወቃችን ብናውቅም አለመጠቀማችን ነው። ያሉንን በበጎ መንፈስ ከተቀበልን በቂዎቻችን ናቸው። የሌሉንን ከምንሻ ወዳሉን ማየቱ ሀገር ከማቅናት አኳያ የተሻለ አቅምን ይፈጥሩልናል የሚል የግል ምልከታ አለኝ። ኢሬቻ ከኦሮሞ ማህበረሰብ ይነሳ እንጂ መሰረቱ ኢትዮጵያዊነት ነው። ፍቅርና አንድነትን ይቅር ባይነትንም የምንማርበት የሁላችን የጋራ በዓል ነው። ሌሎች በዓላትም ተመሳሳይ መልክ ያላቸው ናቸው። በኢትዮጵያዊነት ጀምረው በኢትዮጵያዊነት የሚያበቁ።

ታሪክ ከየትም ይነሳ በጎ እስከሆነ ድረስ የሁላችን ነው። መልካም እሴቶች የማንም ይሁኑ እስከጠቀሙን ድረስ የጋራችን ናቸው። እንደ አስታራቂ በዓላት ያሉ ከግለኝነት የምንወጣበት፣ እውነት የጸነሰው ስለፍቅር የሚለፋ የጋራ ታሪክ ያስፈልገናል። የማይጥሉን..ከወደቅንም የሚያነሱን፣ የትላንትን እዳ ፍቀው ዛሬን ፍቅር የሚያስተምሩ፣ ወደ ነገ የሚወስዱ የአንድነት ምርኩዞች ያስፈልጉናል፡፡

ሀገር ማለት የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች አስተሳሰብ፣ ታሪክ፣ ባሕልና ወግ ሥርዓትም ጭምር ነው የሚል የቆየ መረዳት አለን። እንዳረዳዳችን የሆነ የኑሮ ዘይቤ ግን የለንም። አንዳንድ ጅብ የሚገባባቸውን ሰፋፊ ቀዳዳዎች የሚፈጥሩት እንዲህ ያሉ ክፍተቶች ናቸው። እንደ አረዳዳችን የሆነ የኑሮ ዘይቤ አብሮነትን ለማስቀጠል ወሳኙ መንገድ ነው፡፡

በዓላት ዘርፈ ብዙ መልክ አላቸው። በእያንዳንዱ ብሔረሰብ ጉያ ውስጥ ያሉ ወግና ሥርዓቶች የሆነ ጠቃሚ መነሻ አላቸው። ልክ እንደዚህ ሁሉ ኢሬቻም ፈጣሪን ማመስገኛ ነው። ፈጣሪን ማመስገኛ ብቻ ብለን የምናበቃው ግን አይደለም። በአዲስ ዓመት መጀመሪያ ላይ ከፊታችን ላሉ አስራ ሁለት ወራትና 365 ቀናቶች ፈጣሪን አደራህን የምንልበት፣ ስለሀገራችን፣ ስለሕዝቡ፣ ስለእንስሳቱ የምንጸልይበት፣ በአንድነትና በአብሮነት የምንጸናበት የአዲስ ተስፋ ጅማሬም ነው፡፡

ኢሬቻ ሰፊ ነው… በእድሜውን እንዥርግ..አንቱ ነው። ሲያስታርቅና ሲያመሰግን፣ ሲመርቅና ተስፋ ሲሰጥ ከርሟል። አሁን ደግሞ ከአንድ ብሔረሰብ በዓልነት አልፎ ሀገራዊ ቀለም ያለው ሆኖ በዩኒስኮ በኩል የዓለም ቅርስ በመሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተከበረ ይገኛል። እኛም እንዳለፈው ጊዜ አዲሱን ዓመት በአባቶች ምርቃት በአዲስ ልብ የምንጀምርበት፣ መጠላላትን ትተን በአብሮነት የምንቆምበት እንዲሆን በቀናነት ልናከብረው ግድ ይለናል፡፡

ከቱሪዝም እና ከገጽታ ግንባታ አኳያም እንዲህ ያሉ የአደባባይ በዓላት ሚናቸው ላቅ ያለ ነው። አብሮነትን ከመፍጠርና ወንድማማችነትን ከማጽናት አኳያ የማይናቅ ሚና አላቸው። ኢትዮጵያዊነት ትስስር ነው ስንል ዝም ብለን አይደለም በምክንያት ነው። የብዙሀነትን ቅይጥ ቀለም የፈጠሩልን ባሕልና ወጎቻችን እንዲህ ካለው የአደባባይ በዓል የሚነሱ ናቸው። የሁላችን ያለፈ ዳና በብዙሀነት ባሕልና ሥርዓት የደመቀ ነው። ማናችንም ለብቻችን ቆመን አልደመቅንም። ድምቀቶቻችን የሕዝብ በዓላት ናቸው፡፡

በዓላት ትስስር መፍጠሪያ ገመዶች ናቸው። እንዳንላላ ሆነን የጠበቅነው፣ እንዳንወይብ ሆነን የጸናነው እንዲህ ባለው የጋራ ሥርዓት ነው። አንዱ የአንዱን በዓል ሲያከብር መለያየት እየጠፋ ኢትዮጵያዊነት እየጎላና እየደመቀ ይሄዳል። አሁን ላለው ሕዝባዊ መንፈስ አንድነትን ከሚፈጥሩ የትስስር ገመዶች ውስጥ እንደ ኢሬቻ ያሉ በዓላት ቀዳሚዎቹ ናቸው። በጋራ ለመቆም የጋራ ሥርዓት ያስፈልገናል። በአብሮነት ለመጠራት ብቻነት የሌለው ኢትዮጵያዊ መንፈስ ያሻናል፡፡

ኢሬቻ ለኦሮሞ ማህበረሰብ የምስጋና በዓል ከሆነ እንደ ሀገር ያለውን ሁለንተናዊ ፋይዳ መረዳት ይከብዳል ብዬ አላስብም። ለምስጋና ሩቅ ለሆነ ማህበረሰብ፣ ከመተቻቸትና ከመናናቅ ላልወጣ ትውልድ የምስጋና በዓል መኖሩ እንደ አንድ ትልቅ እድል ልንወስደው የሚገባ ነው። አብዛኞቹ ልዩነቶቻችን ወደ ሌላው ከማያዩ ዓይኖቻችን የተነሱ ናቸው። ምስጋና ሌላውን የምናይበት፣ ስለሌላው የምንጨነቅበት ሀገር መፍጠሪያ ልማድ ነው። እንደዚህ ዓይነት በጎ ልማዶች ዳብረውና ሰፍተው ስንመራረቅና ስንወዳደስ ነው የጋራ ታሪክ የምናበጀው፡፡

ከሆነ ብሔረሰብ በቅለው በጋራ የሚከበሩ እልፍ የአደባባይ በዓላት አሉን። ጊፋታን፣ ያዮዴን፣ ዮ መስቃላን የመሳሰሉ የዘመን መለወጫ በዓላት ከአደባባይ ባለፈ የአብሮነትን ትርጉም የሚፈጥሩ ቀለሞቻችን ናቸው። እኚህ ባሕሎች የአንድ ወገን ይመስላሉ እንጂ አይደሉም። ከሁላችን በሁላችን የሁላችን ናቸው። አዲሱ ትውልድ በእንዲህ ባለ አንድነትንና አብሮነትን በሚያጠነክር የጋራ በዓል ካልታነጸ በምንም ቢበረታ መዛሉ የማይቀር ነው፡፡

አሁን ላይ ከየት እንደለመድናቸው ብንጠየቅ መልስ የማናገኝላቸው ከኢትዮጵያዊነት የሚያርቁ አንዳንድ የብቻነት ልማዶች እየተጠናወቱን ነው። ከለመድነውና አቅፎ ከያዘን ሰፊ እጅ ሸሽተን መድረሻችን የት እንደሚሆን ለማወቅ ጠቢብ መሆን አይጠይቅም። በሌላው ውስጥ በቅዬ፣ ሌላውም በእኔ ውስጥ በቅሎ… ኢትዮጵያ የምትባለውን ሀገር ፈጥረናል። በባሕልና በታሪክ፣ በወግና ልማድ ተወራርሰን የጋራ የሚል አብሮነትን አበጅተናል፡፡

ትውልድ የማህበረሰብ መልክ ነው። ማህበረሰብ የባሕሉና የሥርዓቱ ነጸብራቅ ነው። እኚህ ሁሉ ሀገር ወደምትባል የጋራ እውነት ይመሩናል። ሀገር ደግሞ ሁሉም ባሕልና ሥርዓቶች በፍቅርና በአንድነት የሚከበሩባት የሁላችን ሰፊ ሜዳ ናት። ተጀምረን ያበቃነው በማህበረሰብ ሥርዓት ውስጥ ነው። ለዚህ ማህበረሰብና ለሥርዓቱ በጎ ማሳየት የወጣንበትን ከማክበር ጎን ለጎን ሀገር ማጽኚያ አውዳችንም ነው፡፡

የእኔ የአንተ የምንባባልባቸው የብቻ ታሪኮች አቆርቁዘውናል። ወደኋላ ከመጎተትና ያሉንን የጋራ እሴቶች ከማደብዘዝ ባለፈ ጥቅም አልሰጡንም። አሁን የሌላውን የእኔ ብለን የምንነሳበትና ኢትዮጵያን በአዲስ ቀለምና ሸራ ላይ የምንስልበት ነው። ገባንም አልገባንም ሁላችንም አንድ ነን። አንዳችንም ብዙ ነን። በዓሉን አብረን እናክብር.. ስለ በዓሉም አብረን እንቁም።

ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)

አዲስ ዘመን መስከረም 25/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You