ትኩረት ያልተሰጠው የአዕምሮ እድገት ውስንነት

አስናቀ ፀጋዬበዓለም አቀፍ ደረጃ ከአንድ ቢሊዮን በላይ ወይም 15 ከመቶ የሚሆነው ሕዝብ በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ መንስኤዎች ምክንያት አካል ጉዳተኛ እንደሆነ ይነገራል። ከዚህ ውስጥ 70 ከመቶ ያህሉ በታዳጊ ሀገራት ውስጥ ይኖራል። በኢትዮጵያም ከ23 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ወይም 17 ነጥብ 6 ከመቶ የሚጠጉ ሰዎች አካል ጉዳተኛ ስለመሆናቸው መረጃዎች ያሳያሉ። ከዚህ ውስጥ 82 ከመቶ ያህሉ በድህነት ውስጥ ይኖራሉ።

የአእምሮ እድገት ውስንነትም /intellectual dis­ability/ አንዱ የአካል ጉዳት ዓይነት ሲሆን ለእድገት አስፈላጊ የሆኑ አካባቢያዊና ማህበራዊ ግብዓቶች ባለመሟላታቸው ምክንያት በግላዊና ማህበራዊ ክንዋኔዎች ረገድ መዘግየት መሆኑ የዘርፉ ህክምና ባለሞያዎች ይናገራሉ። ይሁንና አስፈላጊው ድጋፍ ከተሟላ የአእምሮ እድገት ውስንነት ሊሻሻል የሚችል መሆኑን አያይዘው ይጠቁማሉ።

በኢትዮጵያ በቂ ጥናት ባለመደረጉ ከአእምሮ እድገት ውስንነት ጋር የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ በትክክል አይታወቅም። ነገር ግን የዓለም ጤና ድርጅት በአእምሮ እድገት ውስንነት ላይ ባወጣው መረጃ መሠረት በኢትዮጵያ ካለው 110 ሚሊዮን በላይ ከሚሆን ሕዝብ ውስጥ ከሰባት ሰዎች ውስጥ አንዱ የአእምሮ እድገት ውስንነት እንዳለበት አመልክቷል። ዩኒሴፍ እ.ኤ.አ በ2018 ባወጣው ሪፖርት መሠረት ደግሞ 7 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሰዎች በተለያዩ የአእምሮ እድገት ውስንነት እንደተጠቁ አሳይቷል። ይህም ኢትዮጵያ ካላት ሕዝብ ወደ 9 ነጥብ 3 ከመቶ ያህሉ በዚህ ህመም ውስጥ እንዳለ ያሳያል።

የአእምሮ እድገት ውስንነት ከፅንሰት ጀምሮ እስከ አስራ ስምንት ዓመት እድሜ ክልል ድረስ ሊከሰት እንደሚችልም ነው የዘርፉ ጤና ባለሞያዎች የሚያስረዱት። ከአስራ ስምንት ዓመት በኋላ የሚከሰተው የአእምሮ እክል ግን የአእምሮ ህመም እንጂ የአእምሮ እድገት ውስንነት እንዳልሆነ ይገልፃሉ። ከዚህ ቀደም በነበሩት ጊዚያት የአእምሮ እድገት ውስንነት የአእምሮ ግንዛቤ አቅም /intelligence/ ውጤትን ብቻ መሠረት በማድረግ አሻሚና በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት የማያገኙ መረጃዎች የነበሩ ሲሆን በአሁኑ ዘመን ግን የአእምሮ እድገት ውስንነት በትክክል ለመረዳት ራስን የማስማማት ክህሎቶችንና ብስለትን በሚገባ መረዳት እንደሚያስፈልግ እየተነገረ ነው።

የእእምሮ እድገት ውስንነት መንስኤዎች እስካሁን በሳይንሳዊ መንገድ የተረጋገጡት በዘር፣ ውርስ/ሀረግ የሚመጡና የሚተላለፉ፣ በወሊድ ጊዜና ከወሊድ በኋላ የሚከሰቱ ናቸው። የልጆችን አካላዊና አእምሯዊ ጤንነት ከሚወስኑ ሁኔታዎች ውስጥ አንዱ የዘር ውርስ ሀረግ ነው። በዚህ መልኩ በሰዎች ላይ የአእምሮ እድገት ውስንነት ሊያስከትሉ የሚችሉ አንዳንድ ሁኔታዎች በዘር ሀረግ ሳቢያ ሊፈጠሩ ይችላሉ።

ከዚህ ዓይነት መንስኤዎች ውስጥ የዘር/ውርስ ሀገር ተሸካሚዎች መዛባት፣ ጉድለት፣ ማፈንገጥ /chromo­somal aberrations/፣ የክሮሞዞሞች ቁጥር ጥንድ መሆን ሲገባው አንዳንድ ጊዜ ሶስት መሆን፣ ያልተለመደ የክሮሞዞሞች እድገት፣ የሰውነት ንጥረ ነገሮች ሂደት /ሜታቦሊስም/ መቃወስና በዘር/ ውርስ/ የሚፈጠሩ የአንጎልና የነርቭ ህመሞች ይገኙበታል።

የአእምሮ እድገት ውስንነት በወሊድ ጊዜም ሊከሰት እንደሚችል ሳይንሱ ያረጋገጠ ሲሆን በተለይ ፅንስ በማህፀን ውስጥ መቆየት የሚገባውን ያህል ጊዜ ሳይቆይና የማህፀን እድገቱ ሳያበቃ ያለ ጊዜው የሚከሰት መወለድ፣ በምጥ ጊዜ ምጥ ከሚፈለገው ጊዜ በላይ በቆየት በህፃኑ ላይ እስከሞት የሚያደርስ የመተንፈስ ችግር፣ ሕፃናትን ለማዋለድ ጥቅም ላይ የሚውሉ መሳሪያዎች ሳቢያ በአንጎል ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን ለመቀነስ በባለሞያዎች በቂ ጥንቃቄ ካልተደረገ የአእምሮ እድገት ውስንነት ሊከሰት ይችላል።

በተመሳሳይ ከወሊድ በኋላም የአእምሮ እድገት ውስንነት ሊከሰት የሚችልበት እድል እንዳለ በባለሞያዎች ይገለፃል። ሕፃናት ከተወለዱ በኋላ ጉልህ የአካልና የአእምሮ እድገት የሚያሳዩት በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ዓመታት ውስጥ ነው። በነዚህ አራትና አምስት ዓመታት ውስጥ የሰው ልጅ አንጎልና የስሜት ህዋሳት ከፍተኛውን እድገት የሚያሳዩት። ለዚህ ከፍተኛ እድገት የተሳካ መሆን ታዲያ ሕፃናት ከተለያዩ አደጋዎች፣ ብክለቶችና ኢንፌክሽኖች መጠበቅ ይኖርባቸዋል። ሕፃናት ከተወለዱ በኋላ የሚከሰቱ አደጋዎች፣ ብክለቶችና ኢንፌክሽኖች ለምሳሌ መውደቅ፣ መመታት፣ የሚጥል ህመም፣ ማጅራት ገትር፣ የአንጎል ቁስል፣ የሰውነት ጉዳትና የደም መፍሰስ ለአእምሮ እድገት ውስንነት መከሰት ከወሊድ በኋላ መንስኤ ሊሆኑ ይችላሉ።

የአእምሮ እድገት መቼ እና እንዴት ሊከሰት እንደሚችል አይታወቅም። ከዚህ አንፃር ሁሉም የአእምሮ እድገት ውስንነት ጉዳይ የሁሉም ህብረተሰብ ክፍል ጉዳይ እንደሆነ ይታመናል። የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸውን ሰዎች የመንከባከብና ጤናቸውን የማሻሻል ኃላፊነት የአንድ የተወሰነ አካል ብቻ ኃላፊነት ሳይሆን የሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነት ነው።

ወይዘሮ ምህረት ንጉሴ በፍቅር ኢትዮጵያ የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ብሔራዊ ማህበር ፕሬዚዳንት ናቸው። እርሳቸው እንደሚናገሩት ማህበሩ የተመሰረተው በ87 የአእምሮ እድገት ያለባቸው ልጆች ወላጆች አማካኝነት በ1987 ዓ.ም ሲሆን በቀጣዩ ጥቅምት ወር 30 ዓመቱን ይይዛል። በጊዜው ማህበሩ ሲመሰረት ተመሳሳይ ማህበር፣ የወላጆች ስብስብና የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ልጆችን የሚደግፉ ማዕከላት አልነበሩም። በጊዜው ለልጆቹ የሚጠቅም ሥራ መሥራት የሚችል ማዕከላት አለመኖራቸውና ለልጆቻችን ራሳችን መልስ እንስጥ በሚል ማህበሩ ተመስርቷል።

ከዛን ጊዜ የአእምሮ እድገት ውስንነት ባለባቸው ልጆች ላይ የተለያዩ የጉልበት ብዝበዛዎች፣ ፆታዊ ትንኮሳ፣ አስገድዶ መድፈር፣ አድሎና መገለል ይደርስባቸው ነበር። ከዚህ አንፃር እነዚህ ችግሮች ለመቅረፍና የአእምሮ እድገት ውስንነት ላለባቸው ልጆች ደህንነቱ የተጠበቀ ቦታ ለመፍጠር በሚል ፍቅር ኢትዮጵያ የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ብሔራዊ ማህበር በወላጆች ተመስርቷል።

ፕሬዝዳንቷ እንደሚያብራሩት፣ የአእምሮ እድገት ውስንነት ሲባል የአእምሮ ብስለትና ብቃት መጓደልና እንዲሁም ለማህበራዊና ግላዊ ክንዋኔዎች የብቃት መጓደል ነው። አዕምሮ የሚያከናውናቸው ተግባራት በሚፈለገው ልክ አለመሆን ወይም ብቃትና ብስለት ሲያጋጥመው የአእምሮ እድገት ውስንነት ይከሰታል። ከግላዊ ክንዋኔ ጋር በተያያዘ ደግሞ አንድ ሰው ከተወለደበት ጊዜ አንስቶ የሚጠበቅበት ሊያደርጋቸው የሚገቡ ነገሮች አሉ። ለምሳሌ ሲወለድ ማልቀስ፣ ከዛ ቁጭ ማለት ከዛ ደግሞ መዳህ ይጠበቅበታል። እንግዲህ እነዚህ ነገሮች ሲቀሩ ነው የብቃት መጓል ናቸው ተብሎ የአእምሮ እድገት ውስንነት ነው ሊባል የሚችለው።

ማህበሩ ባለፉት ሰላሳ ዓመታት ውስጥ በተለይ የተደበቁ የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸውን ልጆች በማውጣትና የተሻለ የሕይወት እንቅስቃሴ እንዲኖራቸው በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሥራ ሲሰራ ቆይቷል። ይሁንና አሁንም ድረስ ያልተቀረፉለት በርካታ ችግሮች አሉበት። ማህበሩ ካሉበት ችግሮች አንዱና ቀዳሚው ግንዛቤ ችግር ነው። በማህበሩ አባላት ላይ የሚደርሱ የተለያዩ አድልዎና መገለሎች አሉ። ይህ ደግሞ የሚያጋጠመው በማህበረሰቡ ዘንድ በአእምሮ እድገት ውስንነት ዙሪያ ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ መሆን ነው። ይህ ግንዛቤ እጥረት የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ልጆች በትምህርት፣ በጤና፣ በሥራና በተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች እኩል ተጠቃሚ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል።

ከዚሁ ጎን ለጎን ግን ማህበሩ በሙሉ አቅሙ እንዳይንቀሳቀስ እንቅፋቶች አሉበት። ለማህበሩ አባላት ማድረግ የሚፈልጋቸውን ነገሮች ለምሳሌ በገጠር አካባቢ ውስጥ ድረስ ገብቶ መሥራት እንዳይችል የፋይናንስና የባለሞያዎች እጥረት አለበት። በእነዚህ አካባቢዎች ማህበሩ ተደራሽ ሳይሆን በመቅረቱ በቤት ውስጥ ተዘግቶባቸው የተቀመጡ በርካታ የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸውን ልጆች ማውጣት አልቻለም። ማህበሩ አሁን ላይ በአዲስ አበባ ከተማ ያለበትን ቦታ የግንባታ ፍቃድ አለማግኘትም በሥራው ላይ ተጨማሪ እክል ፈጥሯል። የግንባታ ፍቃድ ቢያገኝ ቢያንስ ከተረጂነት ወጥቶ ሥራውን በራሱ ሕንፃ ላይ በተሟላ ሁኔታ ለማከናወን ይረዳዋል።

ፕሬዝዳንቷ እንደሚያብራሩት፣ ማህበሩ ባለፉት ሰላሳ ዓመታት ከአእምሮ እድገት ውስንነት ጋር በተያያዘ ባከናወናቸው ሥራዎች በርካታ ለውጦች መጥተዋል። የመጀመሪያው ማህበሩ ሥራውን በመጀመሩ በርካታ የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ልጆች ከታሰሩበትና ከተደበቁበት ቤት መውጣት ችለዋል። በዚህም የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ልጆች ወላጆች እፎይታ አግኝተዋል። ከዚህ ባሻገር በኢትዮጵያ የሚታየው የልዩ ፍላጎት ትምህርትና ሌሎችም አካታችነትን ለማረጋገጥ የተሞከሩ በርካታ ሥራዎች አሉ። እነዚህ ሥራዎች በአብዛኛው የተከናወኑት ማህበሩ ከተቋቋመ በኋላ ነው።

አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ኮከበ ፅባህ ትምህርት ቤት ብቻ ነበር የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸውን ልጆች ተቀብሎ ለብቻቸው ሲያስተምር የነበረው። እንደዚህ ዓይነት ሙከራዎች የተጀመሩትም ይህ ማህበር ከተቋቋመ በኋላ ነው። ብቸኛ የነበረውን አእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ትምህርት ቤት በማበልፀግ፣ የትምህርት መርጃ መሳሪያዎችን በማቅረብ፣ ለመምህራን ስልጠና በመስጠት፣ የልዩ ፍላጎት ለትምህርትን በሰርተፊኬት ደረጃ በማስጀመር ረገድም ማህበሩ ጉልህ ሚና ተጫውቷል። አንድ ብቻ የነበረውን ትምህርት ቤትም ወደ 21 ከፍ እንዲል ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል። እነዚህም በሀገር አቀፍ ደረጃ አእምሮ እድገት ውስንነት ዙሪያ የመጡ ትላልቅ ለውጦች ናቸው።

ማህበሩ በአሁኑ ጊዜ ከአፋር፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝና ጋምቤላ በስተቀር በሁሉም ክልሎች ላይ በሚገኙ 18 ከተሞች ላይ ሥራው ያከናውናል። 15 ሺ አባላትንም ይዞ እየተነቀሳቀሰ ይገኛል። በአዲስ አበባ ከተማ ደግሞ ሁለት የሞያ ማሰልጠኛ ማዕከላት አሉት። የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሞችን ለወላጆች ይሰጣል። በዚህም በድህነት ውስጥ ያሉና የአእምሮ እድገት ውስንነት ላለባቸው ልጆች ወላጆች ቅድሚያ በመስጠት በርካቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል። ይህ ሥራ ታዲያ በክልሎችም ጭምር የሚከናወን ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ ማህበሩ በሥነ ተዋልዶ ጤና ዙሪያና በሌሎችም ጤና ነክ ጉዳዮች ላይ የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ልጆች ራሳቸውን እንዲጠብቁ የማድረግ ሥራ ያከናውናል። ከሆስፒታሎች ጋር በጋራ በመሆን ደግሞ መድኃኒት የሚያገኙበትን ሁኔታ ያመቻቻል። ልጆቹ ጤናቸውን እንዲጠብቁ በበጎ ፍቃደኛ ሐኪሞች አማካኝነትና በስፔሻል ኦሊምፒክ ፌዴሬሽን ጋር በመሆን ልየታና ምርመራ ዘመቻ ይካሄዳል። በዚህም በርካታ የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ልጆች ተጠቃሚ ሆነዋል።

ይህ በአእምሮ እድገት ውስንነት ዙሪያ በፍቅር ኢትዮጵያ የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ብሔራዊ ማህበር እየተከናወኑ ያሉ ጥቂት ሥራዎች ናቸው። ከዚህ አንፃር የአእምሮ እድገት ውስንነት ጉዳይ በመንግሥትና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራበት ይገባል። እያንዳንዱ የማህበረሰብ ክፍልም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል።

 

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን መስከረም 25/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You