ኢሬቻ- የምስጋና ቀን

ኢሬቻ በየዓመቱ የሚከበር ዓመታዊ የምስጋና ቀን ነው። ኢሬቻ የሚከበረው ክረምት ሲወጣ በወንዞች ወይም በሐይቆች ዳርቻ ነው። በሀገር አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ኦሮሞዎች ከየአካባቢያቸው ተሰብስበውና ባህላዊ አልባሳት ለብሰው፣ ቄጤማና አደይ አበባ ይዘው በሐይቆች እና ወንዞች ዙሪያ ታድመው ያከብራሉ።

ቢሾፍቱ በሚገኘው ሆራ አርሰዲ ሐይቅ በተለየ ሁኔታ ይከበራል። ሐይቁ ክብና ስፋት ያለው መሆኑ፣ ሁሉም ተሰብስቦ ሐይቁን ዙሪያውን ከበው ሲታይ የሐይቅ ዳርቻው ኢሬቻ የጨለማው ክረምት መሰናበቻ የ‹‹ብራ›› ወቅት ወይም የብርሃናማው መስከረም መባቻ ስለሆነ ነው በልዩ ድምቀት ይከበራል።

በኦሮሞ ትውፊት ይህን የምስጋና ቀን የሆነውን ኢሬቻ አንዳንድ ኦሮሞዎች ኢሬሳ ከፊሎቹ ደግሞ ዲባዩ ‹‹Dhibaayyuu›› በማለት ይጠሩታል ሲል “Advocacy Oromia“ ድረ ገጽ የተገኘ መረጃ ያሳያል። ኢሬቻ የሚለው ቃል በአፋን ኦሮሞ ለምለምና እርጥብ ሣር ወይም ቄጠማ የሚል ፍች እንዳለው ጥናታዊ ጽሑፎች ያሳያሉ። እርጥብ ሣር ወይም ቄጠማ በአፋን ኦሮሞ ጂዳ (jiidha) ይባላል። ይህም ፍሬያማነትን እና ሕይወት በፈጣሪ ጥበቃ እያበበች እየጎመራች ነው የማለት ትዕምርት (symbole) ነው።

ኢሬቻ ሲከበር ሰዎች ለምለም ቄጠማና አደይ አበባ ይዘው ‹‹ቢራን በሪኤ አባቦን ደራሬ›› እያሉ ይዘፍናሉ ይጨፍራሉ። ግርድፍ ትርጉም መስከረም ጠባ፤ አበቦችም ፈኩ እንደማለት ነው። ኢሬቻ የሚከበረው ጭጋግ ደመናው ተገፎ ሰማዩ ሲጠራ፣ ፀሐዩ ሲያበራ፣ ድፍርስ ወንዝ ንጹህ ሲሆን ነው።

መስከረም ሲጠባ አደይ ሲፈነዳ የሚከበረው ኢሬቻ፤ ‹‹ኢሬቻ ቢራ›› (የመፀው ኢሬቻ) እና ‹‹ኢሬቻ መልካ›› ማለትም የወንዝ ዳርቻ ኢሬቻ አንዳንዶች ደግሞ ኢሬቻ ጂደ (ለምለም ኢሬቻ) ኢሬቻ ደራራ ማለትም የአደይ አበባው ኢሬቻ በሚል ስያሜዎች ይጠሩታል። አባ ገዳዎች እና ሐዳ ሲንቄዎች በዓሉን በመምራት በማመስገን አዲሱ ዘመን ያማረ የሰመረ እንዲሆን ያመሰግናሉ።

በበጋው ወቅት የሚከበረው ኢሬቻ ቱሉ ‹‹Irreecha Tuulluu›› ነው። ከአካባቢው ከፍ ያለ ተራራ ሥፍራ የሚከበር ሲሆን፤ በጋው ተጠናቆ ክረምት መግቢያ ወራት ላይ የሚደረግ ምስጋና ነው።

ለምስጋናው ከየቦታው የሚሰበሰቡ ኦሮሞዎች የየአካባቢያቸውን ባህላዊ አልባሳት ይለብሳሉ፣ ፀጉራቸውን ይሠራሉ፣ የጆሮና የአንገት ጌጥ ያደርጋሉ። ከአርሲ፣ ሐረር እና ባሌ የሚመጡ ኦሮሞ ሴቶች ደግሞ ግንባራቸው ላይ የሚደረግ የወርቅና የብር ልዩ ልዩ ቀለም ያላቸው የጨሌ ጌጥ እንዲሁም በዛጎል የተጌጠ አልባሳት ይለብሳሉ። ባህላዊ አልባሳቱ በራሱ ለኢሬቻ አከባበር ውበትና ድምቀት የሚፈጥር ነው።

ኢሬቻ ባህል፣ እምነት እና ጥበብ የሚታይበት የአከባበር ዓውድ ነው። ኢሬቻ ሲከበር ኦሮሞው ብቻ ሳይሆን ሌሎች የበዓሉ ታዳሚዎች ብሔር ብሔረሰቦች የሚገኙበት ነው። ኢሬቻ ሁሉን አካታች፤ ሁሉን አቀፍ በዓል ነው። ይህም ኦሮሞ በባህሉ አቃፊና ለመሆኑ ማሳያ ነው። በኢሬቻ ምስጋናቸውን በደስታ በባህላዊ ዘፈኖች፣ በግጥሞችና በምሳሌያዊ አባባሎች በባህላዊ አልባሳት ይገልጻሉ።

ክረምትን ወንዞች ይሞላሉ፣ ገበሬዎች በእርሻ ባተሌ ይሆናሉ፣ አንዳንዴ በክረምቱ ቀኑን ሙሉ የሚዘንበው ዝናብ ከቦታ ቦታ እንዲሄዱ አያመችም። ራቅ ያለ ዘመድ አዝማድ ለመጠየቅ፣ ወንዝ ተሻግረው ገበያ ለመገብየትም ሆነ ለመንገድ ወንዞች ስለሚሞሉ ይቸገራሉ። ከባድ ዝናብ፣ ወጨፎ፣ ጭጋጉ፣ ደመናው፣ ብርዱ፣ በረዶው ሲበዛ ደግሞ ወንዞች ሞልተው የአካባቢውን ቦታ ያጥለቀልቃሉ።

የሞሉት ወንዞች የሰዎችን ቤቶች ያፈርሳሉ። በተጨማሪም ሰዎችን ከብቶችን ሊወስዱ ይችላሉ። ለዚህ ነው ከክረምቱ ጨለማ ወደብርሃናማው ብራ ወቅት ላሸጋገረ ፈጣሪ በኢሬቻ ምስጋና በማቅረብ የሚከበረው። ይህን አስቸጋሪ የክረምት ወቅት አሻግሮ ዘመድ ከዘመድ፣ ወዳጅ ከወዳጅ ላገናኘ፤ ምድር በዕጽዋት፣ በአትክልትና በአዝዕርት አብባና ለምልማ፣ አሸብርቃ ደምቃ፣ ለአዲስ ዘመን እንድትበቃ ላደረገ ‹‹ዋቃ›› ምስጋና የሚቀርበው። ዘመኑ የተስፋ የብሩህ ዘመን በመሆኑ ማለት ነው።

ሆራ ሀርሰዲ ኢሬቻ ሲከበር በአራቱ አቅጣጫ ያሉ ኦሮሞዎች ከልሂቅ እስከ ደቂቅ በዓሉን ለማደመቅ ደምቀው ይታደማሉ። ባህላዊ ግጥሙ፣ ዘፈኑ፣ አልባሳቱ ሁሉ ለየት ያለ ድባብ የሚታይባቸው ናቸው። በተለይ እንስቶች ባህላዊ አልባሳት ለብሰው ከፊሎቹ ከሙካሽ ጥቁር ቀሚስ የተሠራ የራሳቸው ቀለም ውበት ባላቸው ዛጎልና ጨሌ ያጌጡና የተንቆጠቆጡ አልባሳትን ለብሰው ለበዓሉ ድምቀትና ውበት የራሳቸውን አበርክቶ ይወጣሉ። እናም በኢሬቻ፣ እምነት፣ ማኅበራዊነት፣ባህላዊነት፣ ጥበብና ውበት የሚጎላበትና የሚታይበት ነው።

ኢሬቻ በሆራ አርሰዲ ብቻ የሚከበር አይደለም። ታዳጊዎች አረጋውያን ከቢሾፍቱ ራቅ ካለ አካባቢ በጤናም ሆነ በአቅም ማነስ መጥተው በዓሉ ላይ ለመታደም የተቸገሩ ኦሮሞዎች በየአካባቢያቸው ኢሬቻን በሐይቅና በወንዞች ዳርቻ ያከብሩታል። ይህም ቀደም ብሎ በትውፊት ኢሬቻ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲከበር የራሳቸው ሚና እንዲጫወቱ ያመቻቸ ነው።

እንደ ዛሬው መጓጓዣ ባልነበረበት ዘመን ኦሮሞዎች በፈረስ እየመጡ በሆራ ሀርሰዲ ኢሬቻ አክብረው ተመራርቀው ዘመኑ እንዲሰምር፣ የተዘራው ዘር ለክረምትና ለመከር እንዲያደርሳቸው፣ ልጆቻቸውን እንዲያሳድግላቸው፣ታላላቆቻቸውን እንዲያሳድርላቸው (ለመጪው ዓመት እንዲያበቃቸው) ለምነው አመስግነው ይለያዩ እንደነበር ሰነዶች ያሳያሉ። በወቅቱ ጭኮ፣ ጨጨብሳ፣እርጎ፣አነባበሮ… ወዘተ ለመንገዳቸው ስንቅ ይዘው ይታደሙ እንደደነበረ በዕድሜ የገፉ አባቶች አውግተውኛል።

ኢሬቻ ሲከበር ዋቄፋታን ጨምሮ የሌሎች የእምነት ተከታዮች የሚያከብሩት ሲሆን፤ የሌላውም ብሔር ተከታዮች በዓሉን ለማክበርና ለመታደም የሚገኙበት ነው። ጥላቻና ሽኩቻ አልባ በዓል ነው። መቃቃርና መናቆር በኢሬቻ አከባበር ቦታ የላቸውም። ሰዎች ኢሬቻ ሲያከብሩ እርቅ ፈፅመው ሰላም ወርዶ ጠብ ተወግዶ ነው። ኢሬቻ ፍቅርና ሰላም የሚታይበት አከባበር ነው።

ኦሮሞ በኢትዮጵያም ሆነ በምሥራቅ አፍሪካ ብዙ ቁጥር የያዘው ሁሉን አቃፊ በመሆኑ እንደነበር የታሪክ ሰነዶች ያስረዳሉ። አባ ገዳዎች ኦሮሞ በሄደበት ሁሉ ሕዝቡን እያቀፈ እየደገፈ ባህሉን እያስተማረ በ‹‹ሞጋሳ›› እና በ‹‹ጉዲፈቻ›› ሥርዓት የኦሮሞ ብሔር አባል እንዲሆኑ ምቹ ሥርዓት እንደዘረጉ የታሪክ ሰነዶች ያሳያሉ።

በኢትዮጵያ ከየብሔሩ ኦሮሞ የሆኑትን ቤት ቆጥሮ አይጨርሳቸውም። ኦሮሞ ከኢትዮጵያ በሕዝብ ብዛት ፊታውራሪ የሆነው አባገዳዎች በቀየሱት የአቃፊነትና የደጋፊነት፣ የጉዲፈቻና የሞጋሳ ስልት መሆኑን የታሪክ ሰነዶች የሚመሰክሩት እውነታ ነው። እያንዳንዱ ብሔር ውስጥ ቢኬድና ዘሩ ቢጠና ከኦሮሞ ያልተዛመደ የለም። የኦሮሞን ባህል የበለጠ ለማጽናት፣ በዓሉን በሰላም ታድሞ ለመሰበናት መትጋት ይገባል። ኢሬቻ የአዲስ ዘመን መባቻ እንደመሆኑ በአፋን ኦሮሞ ምርቃት ‹‹Barri bara nagaa nuu haataa’u››፤ ዘመኑ የሰላም ዘመን ይሁንልን እንላለን።

ኃይለማርያም ወንድሙ

አዲስ ዘመን ዓርብ መስከረም 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You