ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ ከሚኖሩ የዳያስፖራ ማህበራት የተሰበሰበ አጀንዳ ተረከበ

አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በኢትዮጵያ ከሚኖሩ የዳያስፖራ ማህበራት የተሰበሰበ አጀንዳ እና በአርቲስት ዘለቀ ገሰሰና በሙያ አጋሮቹ “እንመካከር” በሚል ርዕስ የተሠራውን የሙዚቃ ክሊፕ በትናንትናው ዕለት ተረከበ። ኮሚሽኑ በአፋር ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱንም በትናንትናው እለት አስጀምሯል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት፤ ኮሚሽኑ በሀገሪቱ የማያግባቡ ጉዳዮችን በምክክር እና በሠለጠነ መንገድ ለመፍታት እየሠራ ይገኛል።

በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን የሀገራዊ ምክክሩ ቁልፍ ተሳታፊዎች በማድረግ እየሠራ ይገኛል ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ፤ ቀደም ሲል በአፍሪካ፣ በመካከለኛው ምስራቅ፣ በአውሮፓ፣ በካናዳ፣ በሰሜን አሜሪካ እና በሌሎች ሀገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር ስለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ዓላማ ከ10 በላይ የበበይነ መረብ ውይይት ማደረጉን አውስተዋል።

በኢትዮጵያ ጉዳይ ይመለከተኛል የሚል የማንም ጥያቄ አይቀርም ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ፤ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሀገራዊ ፋይዳ አላቸው የሚሏቸውን ጥያቄዎች በአጀንዳ መልክ ቀርጸው በጋራም ሆነ በተናጥል ለኮሚሽኑ መላክ ይችላሉ ነው ያሉት።

በውጭ ሀገር ያሉ ኢትዮጵያውያን በተደራጀ መልኩ ጥያቄያቸውን ማቅረብ ብቻ ሳይሆን ኮሚሽኑ ወደ ተወሰኑ የውጭ ሀገራት በአካል በመሄድ ስለሀገራዊ ምክክሩ ጽንሰ ሃሳብ፣ እየተሠሩ ስላሉ ሥራዎች እና የወደፊት አካሄዱን በተመለከተ በሀገራቱ ከሚገኙት ኢትዮጵያውያን ጋር ውይይት እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።

በውይይቱም ለሚነሱ ጥያቄዎች፣ ብዥታ ፈጥረው እስካሁን በቆዩ ጉዳዮች እና ሀገራዊ ምክክርን በተመለከተ ተገቢውን ገለጻ እናደርጋለን ሲሉ አስረድተዋል።

ለሀገራዊ ምክክሩ ግብዓት የሚሆኑ አጀንዳዎች በተለያዩ ክልሎች ሲሰበሰብ እንደነበር አስታውሰው፤ በትናንትናው ዕለት ደግሞ በኢትዮጵያ ከሚኖሩ የዳያስፖራ ማህበራት የተሰበሰበ አጀንዳ መረከባቸውን ገልጸዋል።

ከወረዳ ጀምሮ የማያግባቡ ጉዳዮች በማዕከል ደረጃ ወደ ኮሚሽኑ እየቀረቡ ያሉበት ምዕራፍ መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይ ጊዜ ግለሰቦች አጀንዳቸውን በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን እና በቀጥታ ወደ ኮሚሽኑ የሚያቀርቡበት እንዲሁም ከወረዳ እስከ ማዕከል እና በፌዴራል ደረጃ አጀንዳቸውን ለኮሚሽኑ ያቀርባሉ ብለዋል።

ኮሚሽኑ በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሚያቀርቡትን አጀንዳ በማንኛውም ጊዜ ለመቀበል ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሀገራዊ ምክክሩ እየሠራው ስላለው ሥራ እና ስለወደፊት አካሄዱ ግንዛቤ ሊኖራቸው እንደሚገባ እና ንቁ ተሳትፎ ሊያደርጉ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ዲያስፖራ ማህበር ፕሬዚዳንት አርቲስት ዘለቀ ገሰሰ እንመካከር በሚል ርዕስ አዘጋጅቶ ለምክክር ኮሚሽኑ ከዚህ በፊት በድምጽ ቅጂ ብቻ ያበረከተውን የሙዚቃ ክሊፕ ያስረከበ ሲሆን፤ ለአርቲስት ዘለቀና የሙያ አጋሮቹ ምስጋና አቅርበዋል።

ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ከዚህ ትምህርት በመውሰድ በሚሠሩበት የሙያ መስክ ሀገርና ሕዝብን ሊያገለግሉ እንደሚገባም ተናግረዋል።

በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚገኙ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ስለሰላም መሥራት ዋና ኃላፊነታቸው ሊሆን እንደሚገባም ጨምረው ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ዲያስፖራ ማህበር ፕሬዚዳንት አርቲስት ዘለቀ ገሰሰ በበኩሉ፤ ኪነጥበብን በመጠቀም በሀገሪቱ ያሉትን ግጭቶችና አለመግባባቶች በመፍታት ለሰላም፣ ለፍቅር እና ለአንድነት መሥራት ይገባል ብሏል። በዚህም ከሙያ አጋሮቹ ጋር በመሆን በህብረተሰቡ መካከል ሰላም፣ ፍቅር፣ መግባባት እና ሀገራዊ አንድነትን የሚሰብክ ሙዚቃ ሠርቼ ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር አስረክቤያለሁ ሲል ተናግሯል።

ኪነጥበብ የህብረተሰብ መስታወት በመሆኑ በቀጣይም ሌሎች የኪነጥበብ ባለሙያዎች በዚህ ሥራ እንዲሳተፉ ጥሪ እናቀርባለን ሲል አስታውቋል።

በተያያዘም የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአፋር ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክን ትናንት አስጀምሯል።

የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ ማስጀመሪያ መርሃግብር ላይ ንግግር ያደረጉት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነር አምባሳደር አይሮሪት መሐመድ (ዶ/ር) እንደገለፁት፤ ኮሚሽኑ ትናንት ተጀምሮ ለቀጣዮቹ ስድስት ቀናት በሚቆየው አጀንዳ የማሰባሰብ ተግባር ተሳታፊዎች ከሚያደርጉት ንግግር እና ምክክር ሀገራዊ መግባባት ላይ ልንደርስባቸው ያስፈልጋል ብለው የሚያምኑባቸውን የዳበሩ አጀንዳዎች ይሰበስባል።

የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን እና ባለድርሻ አካላትን በመወከል የሂደቱ ተሳታፊ የሚሆኑ ተወካዮች የሚያፀባርቋቸው ሃሳቦች በአፋር ክልል ብሎም በሀገር ደረጃ መግባባትን ለማስፈን ቁልፍ ሚና እንደሚኖራቸው የጠቆሙት ኮሚሽነሯ፤ ተሳታፊዎች በሃላፊነት ስሜት የአጀንዳ ሃሳቦቻቸውን እንዲያቀርቡ ጠይቀዋል።

አክለውም፤ የሀገራችን ኢትዮጵያ ችግሮች ዘርፈ ብዙ መሆናቸው የሚታወቅ ቢሆንም እኛው ኢትዮጵያውያን በሰከነ መንፈስ የሃሳብ ልዩነቶቻችን ላይ ለመነጋገር መፍቀዳችን ለችግሮቻችን ለዘለቄታው የሚበጁ መፍትሔዎችን ለማስቀመጥ ያግዘናል፤ የጋራ ቤት ለመገንባትም ያስችለናል ብለዋል።

አካታችነት ከኮሚሽኑ መርሆዎች አንዱ መሆኑን አመላክተው፤ ከተሳታፊዎቹ ውስጥ ሴቶች 30%፣ አካል ጉዳተኞች 10%፣ ወጣቶች 20% እንዲሆኑ የኮሚሽኑ የአሠራር ሥነ ዘዴ በሚያዘው መሠረት ተሳታፊዎች በወካዮቻቻቸው አማካይነት ተመርጠው የምክክር ሂደቱ መጀመሩን ነው ኮሚሽነሯ የተናገሩት።

በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ በአፋር ክልል ከሚገኙ ከ49 ወረዳዎች የተመረጡ ከ800 በላይ የሕብረተሰብ ክፍል ወኪሎች እንዲሁም በክልልሉ የሚገኙ ከ700 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች፣ የመንግሥት ተወካዮች፣ የተለያዩ ተቋማትና ማህበራት ተወካዮች እንዲሁም ታዋቂ ግለሰቦች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ በተገኙበት የተጀመረው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት በሀገር ሽማግሌዎች ቡራኬ እና በሃይማኖት አባቶች ፀሎት የተከፈተ ሲሆን፣ የሴቶች እና ወጣቶች ተወካዮችም መልዕክት አስተላልፈዋል።

ኮሚሽኑ እስካሁን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላ፣ በሐረሪ፣ በሲዳማ እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ እና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች የአጀንዳ ማሰባሰብ መድረኮችን አካሂዷል።

ሄለን ወንድምነው

አዲስ ዘመን ረቡዕ መስከረም 22 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You