የቱሪዝም ዘርፉ ፈተናዎች እና ተስፋዎች

ባለፈው የፈረንጆቹ ዘመን በ2023 በዓለም በቱሪዝም ዘርፍ የላቀ አፈፃፀም በማግኘት እና በሰፊው በመጎብኘት ከፍተኛ ገቢ በማግኘት ታዋቂነትን ከተረፉ ሀገራት መካከል ቀዳሚዋ ፈረንሳይ ናት። ፈረንሳይን ተከትላ ስፔን በመቀጠል አሜሪካን፣ ቻይና፣ ጣሊያን፣ ቱርክ፣ ሜክሲኮ ፣ ታይላንድ እና ጀርመን ተጠቃሾች ናቸው። እነዚህ ሀገራት ምንም እንኳ ቀድሞም በቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ ገቢን በማግኘት እና በመጎብኘት ታዋቂነትን ያተረፉ ቢሆኑም፤ በዓለም ላይ ተከስቶ የነበረው የኮረና ወረርሽኝን ተከትሎ የቱሪዝም ዘርፋቸው በእጅጉ ክፉኛ በመጎዳቱ ገቢያቸው ተቀዛቅዞ የጎብኚ ቁጥራቸውም ቀንሶ ነበር።

ባለፈው 2023 ግን ገቢያቸው ከኮረና በፊት ወደነበረበት ደረጃ መመለስ ችሏል። ፈረንሳይ፣ ስፔን እና አሜሪካን የመሳሰሉ ሀገራት፤ እያንዳንዳቸው 100 ሚሊየን የሚጠጉ ጎብኚዎችን ወደ ሀገራቸው በመሳብ እና እንዲጎበኙ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ከፍተኛ ገቢ ሲያገኙ ኢትዮጵያ ግን አንድ ሚሊየን ቱሪስት ለመሳብ ተቸግራለች። እነሳዊዲ አረቢያን የመሳሰሉ ሀገራት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቱሪዝም ዘርፍ ላይ ከፍተኛ ሥራን በማከናወናቸው የተሻለ ገቢ ማግኘት እና የተሻለ ቁጥር ያለው ጎብኚን መሳብ ችለዋል። ኢትዮጵያ ግን በተባበሩት መንግሥታት የዓለም የቱሪዝም ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በማክሮ ኢኮኖሚ ችግሮች ብትፈተንም የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ ትግሏን ቀጥላለች። እ.ኤ.አ. ከ 2022 የሰላም ስምምነት በኋላ በቱሪስቶች መጎብኘቷን ቀጥላለች። ነገር ግን ከሌሎች ሀገሮች ጋር ተፎካክራ የጎብኚዎችን ቁጥር በሚሊየን ማስቆጠር እና ከፍተኛ ገቢ ማግኘት አዳግቷታል።

ለምን የኢትዮጵያ የቱሪዝም ዕድገት በሚፈለገው መጠን መሆን አልቻለም ለሚለው ዘርፉን የሚመሩ ኃላፊዎች እና ባለሞያዎች የሚሉት አላቸው። የቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሺ ግርማ እንደሚገልፁት፤ ለአንድ የቱሪዝም እንቅስቃሴ አስፈላጊ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል ዋነኛዎቹ መሠረተ ልማቶች ናቸው። ለምሳሌ የትራንስፖርት ሁኔታው ላይ መንገድ፣ ቴክኖሎጂው ላይ የቴሌኮም አገልግሎቶች መሻሻል አለባቸው። ከእነዚህ በተጨማሪ የጤና አገልግሎት ላይ ብቁ የሰው ኃይል መኖር፣ የሠራተኞች አቅም፣ የሰላም እና የፀጥታ ጉዳይ፣ የፖሊሲ ጉዳዮች እና ሌሎችም በጣም አስፈላጊ የሆኑ የዘርፉን ተወዳዳሪነት የሚወስኑ ጉዳዮች አሉ።

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለፃ፤ በኢትዮጵያም የኮረና ወረርሽኝ በቱሪዝም ዘርፉ ላይ ከባድ ጫና ፈጥሮ ማለፉ የሚዘነጋ አይደለም። ሌሎች ሀገሮች ከኮረና በፊት የነበራቸውን የቱሪዝም ዘርፍ ገቢ ማግኘት ችለዋል። በኢትዮጵያ በኩል ግን ከኮረና በኋላም የሰሜኑ ጦርነት ቀጥሎ የመጣ በመሆኑ እና በጦርነቱም ምክንያት ሰዎች በቀላሉ ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱበት ሁኔታ በመገደቡ እንዲሁም የኤምባሲ ማስፈራሪያዎች እና ክልከላዎች ከፍተኛ ጫና በመፍጠራቸው ከኮረና በኋላም የቱሪዝም ዘርፉ ፈተና ቀጥሏል።

በሌላ በኩል የአገልግሎት ጥራት አሁንም ፈተና ውስጥ ነው። የአገልግሎት ጥራት እንዲሻሻል የሆቴሎችን ደረጃ መመደብ፤ ከዚህ በፊት የተመደቡትንም ዳግም ደረጃ መስጠት ያስፈልጋል። ሬስቶራንቶችን እና አስጎብኚ ድርጅቶችን እስከ አሁን ድረስ ጥራታቸውን መቆጣጠር እና ደረጃ መመደብ ላይ አልተደረሰም። አሁን መመሪያ በመፅደቁ ወደ ምደባ ይገባል። ስለዚህ መሠራት ካለበት አንፃር ብዙ መሥራት ይጠበቃል። ነገር ግን ኮረና እና የሰሜኑን ግጭት ተከትሎ የቱሪዝም ዘርፍ ላይ የሚደረሰውን ጉዳት ለመቀነስ በርካታ ኮንፈረንሶች ወደፊት እንዲመጡ በማድረግ ዘርፉን ለመደገፍ ጥረት ተደርጓል ብለዋል።

በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የባሕል ጥናት እና የሥነ ጽሑፍ መምህሩ ዶክተር መስፍን ፈቃደ በሚኒስትር ዴኤታው ሃሳብ ይስማማሉ። በበኩላቸው ምንም እንኳ ኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፉ ላይ ፈተናዎች ያሉባት ቢሆኑም፤ ብዙ ተስፋዎች እና ዕድሎች እንዳሏት ይናገራሉ። በተለይ ከወቅቱ ጋር በማያያዝ ከሚዳሰሱ ቅርሶች በተጨማሪ ለቱሪስቱ መስህብ ሊሆኑ የሚችሉ የሚከበሩ በዓላት መኖራቸውን በማስታወስ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከበዓላት አከባበር ጋር ተያይዞ ባሕሉን ይዞ የቆየ መሆኑ በራሱ ቱሪዝምን ለማሳደግ አመቺ መሆኑን ያብራራሉ። ይህንን ሲያስረዱ በኢትዮጵያ በተለያዩ ማህበረሰቦች ውስጥ የተለያዩ በዓላት አሉ። በበዓላቱ የሚለበሱት ልብሶችም ሆኑ ማጌጫዎቹ ሀገር በቀል መሆናቸው የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ በእጅጉ ይጠቅማሉ።

በነሐሴ እና በመስከረም ወር የሚከበሩ በዓላትን ተከትሎ ማህበረሰቡ የተለየ የፀጉር አሰራር፤ አልቦ እና ሌሎችም ማጌጫዎችን ይጠቀማል። ልብሱም የባሕል ነው። በዓላት ሲከበሩ ባሕሉን ጠብቆ መቆየቱ በቀጣይም ቱሪስትን ለመሳብ የሚያግዝ ትልቅ መሣሪያ ነው። ይህንን በመረዳት ወላጆች ለልጆቻቸው በዓላቸውን ከእነባህላቱ ማሳወቅ አለባቸው። ይህ በቀጣይም የኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ አንደኛው ተስፋ ነው።

በሌላ በኩል ዶክተር መስፍን ዘርፉ እንዲያድግ እና ሀገር በቀል ሊጎበኝ የሚችሉ በዓላት እንዲያድጉ መንግሥታዊ የሆኑ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በስፋት መሥራት አለባቸው። በትምህርት ዘርፉም ላይ መካተት ይገባዋል። በዚህ ደረጃ መሥራት እና በዓላትን፣ ባሕሎችን እንዲሁም ቅርሶችን መጠበቅ ከተቻለ ወደፊት ኢትዮጵያ እንደሌሎቹ ሀገሮች ከቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ ገቢ ማግኘት ትችላለች። ይህ በራሱ ትልቅ ተስፋ ነው ብለዋል።

የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት አሰልጣኙ አቶ ዐቢይ ንጉሴ በዶክተር መስፍን ሃሳብ ይስማማሉ። የቱሪዝም ዘርፍ ዕድገት ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዳለው በመጠቆም፤ ከውጪ ምንዛሪ ግኝት ባሻገር፣ ሰፊ የገንዘብ እንቅስቃሴ እንዲኖር በማስቻል፣ የሥራ ዕድል በመፍጠር እንዲሁም ማህበረሰቡ የሚታወቅበት ለምሳሌ ቡና፣ ማር እና ሌሎችም የማህበረሰብ ምርቶችን ለማስተዋወቅ ያስችላል የሚሉት አቶ ዐቢይ፤ በውጪ ገበያ እንዲኖራቸው እንደሚያግዝ ያመለክታሉ።

ወቅቱን ተከትሎ የአደባባይ በዓላት በስፋት መኖራቸውን በመጠቆም፤ በዓላቱ መኖራቸው በራሱ ሌሎች አካባቢዎች እንዲጎበኙ ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራሉ። የሚሉት አሰልጣኙ፤ ለምሳሌ መስከረም በዓል ላይ የተሳተፉ ጎብኚዎች ስለበዓላቱ ለሌሎች ስለሚናገሩ ሀገርን ለማስተዋወቅ እና የቱሪዝም ዕድገትን ለማፋጠን ያመቻል ይላሉ። ክረምትን ተከትሎ በተለይ የገጠሪቱ አካባቢዎች መልከዓ ምድራቸው የሚያምር በመሆኑ፤ በተጨማሪ የፏፏቴዎቹም አቅም ስለሚጨምር ቱሪስቶች በተለይ በዚህ ወቅት የሚጎበኙበትን ሁኔታ ማመቻቸት ቢቻል መልካም ነው። ይህ መኖሩን ማሰብ በተለይም በዓላቱ ብቻ ሳይሆኑ ኢትዮጵያ በክረምትም ጭምር ልትጎበኝ እንደምትችል ማሰብ እና በዛም ላይ መሥራት ከተቻለ ትልቅ ውጤት ማግኘት ይቻላል ይላሉ።

ሚኒስትር ዴኤታው በበኩላቸው፤ በርግጥም በዓላቱ በራሳቸው ለቱሪዝም ዘርፍ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አላቸው። ነገር ግን አሁን ላይ በስፋት እየተሠራ ያለው ሥራም የዘርፉ ትልቅ ተስፋ መሆናቸውን ያብራራሉ። ገበታ ለሸገር እና ገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶችን በመጥቀስ፤ በጣም ጥሩ ውጤት መጥቷል የሚል እምነት እንዳላቸው ያብራራሉ።

እንደ አቶ ስለሺ ገለፃ፤ ምንም እንኳ የሚቀሩ ብዙ ጉዳዮች ቢኖሩም አሁን ላይ ሊታዩ እና ሊገለፁ የሚችሉ ትልልቅ ለውጦች አሉ። በማለት ለምሳሌ ገበታ ለሸገርን ያነሳሉ። እንጦጦ፣ ወዳጅነት ፓርክ እና አንድነት ፓርክን ያየ ማንኛውም የቱሪዝም ዘርፍ ባለሞያ በቱሪስት መዳረሻነትም ሆነ የገንዘብ ምንጭ በመሆን ዘርፉ ትልቅ ተስፋ እንዳለው መገንዘብ አያዳግተውም ይላሉ።

እንጦጦም በስፋት እየተጎበኘ መሆኑን በማስታወስ፤ ብዙ ሰው የሚሳተፍበት ስፖርት እየተካሔደበት እንደሚገኝ እና በተለይ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ዕድገት ትልቅ መሆኑንም ይናገራሉ። ከእንጦጦ እና አንድነት በተጨማሪ ወዳጅነት ፓርክም ቢሆን የተለያዩ ፕሮግራሞች እና ብዙ ሰርጎች እየተካሔዱበት መሆኑን ጠቅሰው፤ ቀን እና ማታ ሰዎች ስፖርት የሚሰሩባቸው እና ወላጆችም ልጆችን ይዘው የሚዝናኑባቸው ሁኔታዎች በስፋት ተፈጥረዋል ብለዋል። ይህ በቀጥታ ከቱሪዝም ጋር እንደሚገናኝ በማውሳት፤ የቱሪዝም ዘርፉ ዕድገት ከውጪ ብቻ ሳይሆን የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችንም ያካተተ መሆን እንዳለበት ሊዘነጋ አይገባም ይላሉ።

ከውጪ ጎብኚዎች አንፃር ገበታ ለሸገር፣ እንጦጦ፣ አንድነትም ሆነ ወዳጅነት ገፅታን በመገንባት እና በበርካታ ሰዎች በመጎብኘት በገቢ ደረጃ በሚሰበሰብ ገንዘብ ሌሎች መዳረሻዎችን ማልማት ተጀምሯል። ይህ ትልቅ ተስፋ ሰጪ ጅምር ነው የሚል እምነት እንዳላቸውም አመላክተዋል።

ከቱሪዝም አንፃር ኢትዮጵያ ውስጥ ቱሪዝም ገና አዲስ ጅምር ነው። ዘርፉ የፖለቲካ ድጋፍ እና ትኩረት ማግኘት የጀመረው ገና አሁን ነው። አሁን ያለው ትኩረት ከቀጠለ ብዙ መዳረሻዎች እና መሠረተ ልማቶች መሠራት ይቻላል። ኢትዮጵያም ግብርና መር እና ኢንዱስትሪ መር ብቻ ሳይሆን ቱሪዝም መር የሆነ ትልቅ ኢኮኖሚን የምትገነባበት ሁኔታ ይፈጠራል ብለዋል።

በሌላ በኩል የዘርፉን ውጤታማነት ለመግለፅ ያህል ሚኒስትር ዴኤታው እንደተናገሩት፤ ብዙ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል። የውጪ ምንዛሪ እየተገኘ ነው። በተጨማሪ አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና ናት እየተባለ ከሌሎች ከተማ ጋር ስትወዳደር የነበረችበት የሚታወስ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ እየኖሩ ያሉ የሌሎች ሀገሮች ሰዎች ማለትም የውጭ ዜጎች ሊዝናኑባቸው እና ሊኖሩባቸው የሚችሉባቸው ቦታዎች አልነበሩም፤ አሁን ግን በእግራቸው ሊንቀሳቀሱባቸው እና ሊዝናኑባቸው የሚችሉባቸው ቦታዎች ተፈጥረዋል። ይህም በራሱ ለቱሪዝም ዘርፉ ትልቅ ተስፋ ነው ብለዋል።

ከገበታ ለሸገር በተጨማሪ ገበታ ለሀገርም ወንጪ፣ ኮይሻ እና ሃላላ ኬላ በጣም በጥራት የተሰሩ ናቸው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ አሁን ላይ አንዳንዶቹ ምናልባት በቀላሉ ሰው ሊደርስባቸው የማይችሉባቸው ቢሆኑም፤ ለምሳሌ ጎርጎራ፣ ጨበራ እና ወንጪ ብዙ ሰው በቀላሉ ሊሔድ እና ሊጎበኛቸው ያሉበትንም ሁኔታ ማረጋገጥ እንደሚቻል ተናግረዋል። ሌሎቹም ቢሆኑ አንዳንድ የሰላም እጦት ያሉባቸው ቦታዎች እንዳሉ ሆነው የሰላም ሁኔታው ሲስተካከል ደግሞ በጣም በሰፊ ቁጥር መጎብኘት የሚቻልበት ሁኔታ እየተመቻቸ መሆኑን ተናግረዋል።

ከቱሪዝም ዘርፍ ጋር ተያይዞ ሚኒስትር ዴኤታው በደንብ መታወቅ አለበት ያሉት፤ የቱሪዝም አቅርቦት ለዘመናት የተዘነጋ ክንፍ መሆኑን ነው። ‹‹ብዙ ጊዜ ምን ያህል ቱሪስት መጣ ይባላል። ይህ የፍላጎት ጉዳይ ነው። ትልቁ ሥራ ግን አቅርቦት ነው። መጀመሪያ የሚጎበኝ መስዕብ፣ ወይም መዳረሻ ምን ያህል ተሠራ? የሚል ጥያቄ መጠየቅ ያስፈልጋል። ቱሪስቱ የሚፈልገውን ነገር በቅርቡ ያገኛል? አስፈላጊው መሠረተ ልማት ተሟልቷል? በዘመናዊ መልኩ የሠለጠነ፣ የበቃ፣ ዕውቀት እና ሥርዓት ያለው የሰው ኃይል አለ? በየቦታው ምቹ የጉብኝት ሥርዓት አለ? ›› የሚሉት ጉዳዮች ተረስተው ቆይተዋል ብለዋል።

ዘርፉ ላይ በአቅርቦት ላይ በስፋት ባለመሠራቱ ፈተናው ውስብስብ ሆኖ ቆይቷል። ነገር ግን አሁን ብዙ ገንዘብ የሚጠይቁ እነዚህ ጉዳዮች በስፋት እየተሠራባቸው መሆኑን አመላክተዋል። የቱሪዝም አቅርቦቶች ረዥም ጊዜ ይወስዳሉ። ከፍተኛ አቅም እና እውቀት የሚፈልጉ ናቸው። ነገር ግን አቅርቦቶች ከተሟሉ መዳረሻዎች በቀላሉ በቱሪስቶች የመመረጥ ዕድል እንደሚኖራቸው ተናግረዋል።

የጎበኙ ሰዎች ደግሞ ተደስተው ሌሎች እንዲያዩት ለመናገር የሚችሉበት ዕድል ይፈጠራል። ስለዚህ አሁን እየተሠራ ያለው ሥራ ከማስተዋወቅ ጋር ተያይዞ በቀላሉ ውጤት ለማምጣት የሚያስችል ነው ማለት ይቻላል ብለዋል። አገልግሎት ላይ በዓይነት፣ በጥራት በጣም በተቀናጀ እና በተደራጀ መልኩ እየተሠራ ነው፤ ስለዚህ ምንም እንኳ የቱሪዝም ዘርፉ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ቢያልፍም አሁን ትልቅ ተስፋ አለው የሚል እምነት እንዳላቸው አመላክተዋል።

እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ ገለፃ፤ ኢትዮጵያ በዩኔስኮ የተመዘገቡትን ቅርሶች ጨምሮ ብዙ ሀብቶች አሏት። ሕዝቡ የሚያከብራቸው ብዙ በዓሎች አሉት፤ በተጨማሪ ባሕሉን ጠብቆ የሚኖር መሆኑም ይታወቃል። እነዚህን ሀብቶች በአግባቡ ማስተዋወቅ ከተቻለ እና መሠረተ ልማቶች በአግባቡ ከተሟሉ እንዲሁም የግጭቶች ጉዳይ መፍትሔ ከተበጀላቸው ሀገሪቱ በብዙ ጎብኚዎች የማትታይበት ምክንያት የለም። አብሮ መዳረሻዎችን በስፋት ማልማት ከቀጠለ እና አቅርቦት ላይ በስፋት ከተሠራ ከቱሪዝም ዘርፉ የሚፈለገውን ገቢ ማግኘት ይቻላል።

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን መስከረም 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You