የነጻ ገበያ ሥርዓቱ መደላድል

ኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ በነጻ ገበያ ሥርዓት ለመመራት በሽግግር ዋዜማ ላይ ትገኛለች፡፡ በዚህ ወሳኝ ጊዜ መጪውን የገበያ ሁኔታ ማስተዳደር የሚችሉ ተቋማትና ሥርዓቱን መምራት የሚችሉ ብቁ ባለሙያዎች ያስፈልጋሉ፡፡

የመጪው ጊዜ ባለሙያዎች፣ ተቋማት እና የሕግ ማዕቀፉ ምን መምሰል አለባቸው? እንዲሁም የትኞቹስ ተቋማት ቀድመው ሊዘጋጁ ይገባል? የሚለው ፈጣን ምላሽ የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ከነጻ ገበያ ሥርዓቱ ውጪ ልትሆን እንደማትችል፣ ውሳኔውም የዘገየ መሆኑን እና እየተወሰዱ የሚገኙ ውሳኔዎችን ተከትሎ በቂ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባ ዝግጅት ክፍሉ ያነጋገራቸው የሕግ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

በኢትዮጵያ የግልግል እና የማስማማት ማዕከል ዳይሬክተር ጠበቃና የሕግ አማካሪው ሚካኤል ተሾመ እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የሽያጭ ውሎች በምን አይነት መልኩ መሠራት እንዳለባቸው የሚደነግገውን የኒውዮርክ ስምምነት አፅድቃለች፤ በአዋጅም አውጥታለች፡፡

ወደነጻ ገበያ የሚደረገው ሥራ የተጀመረው እ.አ.አ በ2018 እንደነበር አስታውሰው፤ በቅርቡ ተከታታይ ሕጎች መውጣታቸው እና የውጭ ምንዛሬ ገበያ መር መሆኑ የበለጠ ትኩረት እንዲሰጠው አደረገ እንጂ በቅርበት ለሚከታተለው ቀድሞ የሚገነዘበው ነገር ነው ይላሉ፡፡

ኢትዮጵያ ከነጻ ገበያ ሥርዓቱ ውጪ ልትሆን አትችልም የሚሉት የሕግ አማካሪው ሚካኤል፤ ዓለም አቀፍ የንግድ ድርጅት (WTO) እና የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና እየመጡ መሆኑን መሠረት በማድረግ ተቋማቱን የሚያንቀሳቅሷቸው ባለሙያዎች ብቁና ዓለም አቀፍ ሁኔታን በመገንዘብ የሚጓዙ መሆን አለባቸው ሲሉ ይመክራሉ፡፡

ጠበቃና የሕግ አማካሪው አቶ ወይናለም ወልደሰንበት በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ በገበያ የሚመራ ሥርዓት ትግበራ በጣም ዘግይቶ የተወሰነ ቢሆንም፤ በመንግሥት እየተወሰዱ ያሉ ርምጃዎች እና እንቅስቃሴዎች የሚደገፉ መሆናቸውን ይጠቁማሉ፡፡

የነጻ ገበያ ሥርዓትን ተከትለው የፖሊሲ ዝግጅቶች፣ የሕግ ማዕቀፎች፣ በዘርፉ ላይ ተዋናይ የሆኑ ተቋማት እና ባለሙያዎች ውሳኔዎቹን የመቀበል እና የማስፈጸም አቅማቸው በዛው ልክ ማደግ እንዳለበትም ያሳስባሉ፡፡

የፍትህ ተቋማቱን በምሳሌነት በማንሳት፤ የነጻ ገበያ ሥርዓት የበለጠ ወደ ተግባር እንዲለወጥና እንዲስፋፋ ፍርድ ቤቶች እንዲሁም የግልግል ማዕከላት መጠናከር፣ መስፋፋት እና አዳዲስ እንዲፈጠሩ መደረግ ይኖርበታል ባይ ናቸው፡፡

ፍርድ ቤቶች በንግድ ዙሪያ የሚመጡላቸውን ጉዳዮች የመዳኘት የንድፈ ሃሳብና የተግባር አቅማቸው የዳበረ ሊሆን ይገባል፡፡ በሂደቱም ፍርድ ቤቶች በቂ ዝግጅት ሊያደርጉ ይገባል ነው የሕግ አማካሪ አቶ ወይናለም የሚሉት፡፡

የግልግል እና የማስማማት ማዕከላት ገላጋይ ብለው የዘረዘሯቸው ባለሙያዎቻቸውን የማብቃት ግዴታ ይኖርባቸዋል፡፡ የሕግ ቢሮዎች፣ ጠበቆችና የሕግ አማካሪዎች ከጊዜው ጋር ተራማጅ የሆነ እውቀትን ሰንቀው መዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል ሲሉም ያክላሉ፡፡

ጠበቃና የሕግ አማካሪ ሚካኤል የወጡ ሕጎችን ባግባቡ ማስፈጸም የሚችሉ ተቋማት መኖር እንዳለባቸው በመጠቆም፤ ለተግባሩ ትኩረት ተሰጥቶት መሠራት አለበት፣ ስለተባለው ጉዳይ የሚገነዘቡና ወደ ተግባር መለወጥ የሚችሉ ብቁ ባለሙያዎችም መኖር አለባቸው ይላሉ፡፡

አያይዘውም፤ ኢንቨስተሮች በአንድ ሀገር ውስጥ ሥራ ለመጀመር ሲያስቡ ቀድመው የሚያናግሩት የሕግ ባለሙያዎችን ነው፡፡ በመሆኑም የሕግ ባለሙያዎች ራሳቸውን ሊያበቁ ይገባቸዋል፡፡ ፍርድ ቤቶች አካባቢም ቀደም ብሎ ሊሠራ የሚገባ ተግባር አለ፡፡ ችግር ሲፈጠር መብት የማስከበሪያ ሕጉን የሚተረጉሙት ዳኞች በመሆናቸው ቀድመው ሕጎቹን ማወቅ አለባቸው ነው የሚሉት፡፡

ዳኞች ከተጻፈው አልፎም ዓለም አቀፍ ግንዛቤ ያላቸው ቢሆኑ ይመረጣል የሚሉት ጠበቃና የሕግ አማካሪው፤ ነጻ ገበያን ብሔራዊ ባንክ ብቻ፣ ወይንም ንግድ ሚኒስቴር፣ ገቢዎች ሚኒስቴር እና ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በተናጥል የሚወጡት አይደለም፡፡ እያንዳንዳቸው የየራሳቸው አስተዋጽኦ እና ሚና ያላቸው በመሆኑ በቅንጅት ተናብበው መሥራት አለባቸው ባይ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉን የንግድ ድርጅት (WTO) እንድትቀላቀል አጋዥ የሕግ ማዕቀፎች ዝግጅት አስፈላጊ መሆኑን የሚገልጹት አቶ ወይናለም፤ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ፈራሚ ሀገር እንደመሆኗ የባንክ ዘርፉ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ሲሆን የግድ የበቃ ተቋምና ባለሙያዎችን ማዘጋጀት ይገባል ነው የሚሉት፡፡ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣንም የተዘጋጀ አስተሳሰብ አደራጅቶ መገኘት እንደሚጠበቅበት ይጠቁማሉ፡፡

መንግሥት የፖሊሲ ለውጦችን አድርጓል፡፡ ይህንን ተከትሎም የተለያዩ ሕጎች ወጥተዋል፡፡ የግልግል ማዕከልን በምሳሌነት ብንወስድ ራሱን የቻለ የግልግል አሠራር አዋጅ ያለው አካሄድን የሚደነግግ ዝርዝር ሕግ ወጥቶለታል፡፡ ይህ ይበል የሚያሰኝ ነው ይላሉ አቶ ወይናለም ፡፡

የአክሲዮን ሽያጭም እየመጣ ነው፡፡ ይህም ራሱን የቻለ የውጭ ሀገር ባለሀብቶችን የሚስብ እንደሚሆን ስለሚገመት በጋራ እስካልሠሩ ድረስ ስኬታማ መሆን አይቻልም፡፡

የባለሙያዎች ዝግጅት በበቂ ሁኔታ የማይኖር ከሆነ ሂደቱ ላይ ተጽእኖ ሊፈጥር ይችላል፡፡ ስለጉዳዩ በብዙሃን መገናኛም ሆነ በሌሎች መንገዶች በአጀንዳነት ተይዞ ቀጣይነት እና ተከታታይነት ባለው መንገድ በስፋት ውይይት ሊደረግበት ይገባል ሲሉም ያሳስባሉ፡፡

አቶ ሚካኤል እንደሚናገሩት፤ የባለሙያዎችም ሆነ የሕዝቡ ግንዛቤ እንዲሰፋ መደረግ አለበት፡፡ ዓለም ላይ እየተፈጠሩ ያሉ ነገሮች በደንብ መታወቅ አለባቸው፡፡ ለዚህም ባለሙያዎችን ለማብቃት የተለያዩ ሥልጠናዎች መዘጋጀት አለባቸው፡፡

ኢትዮጵያ የኒውዮርክ ስምምነትን መቀበሏ የውጭ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ላይ ያላቸውን እምነት ከፍ የሚያደርግ፣ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንቱንም በመጨመር መልካም አጋጣሚን የሚያሰፋ መሆኑን አቶ ወይናለም ያነሳሉ፡፡

እነዚህ እና ሌሎች በርካታ አዳዲስ የሕግ ማእቀፎችን ለማውጣት በመንግሥት የተወሰዱ ርምጃዎች ይበል ያሰኛሉ፡፡ ነገር ግን የሕጎቹ መውጣት ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ የተቋማቱ መጠናከር፣ የግለሰቦቹ ዝግጅትም ይጠበቃል ነው የሚሉት፡፡

ከነጻ ገበያው ጋር ተያይዞ እየተወሰዱ ያሉ ርምጃዎች ለማህበረሰቡ፣ ለሕግ አውጭው፣ ለጠበቃው፣ ለመንግሥት፣ ለፖሊሲ አውጭውም ሆነ ለንግዱ አካላት አዲስ ሃሳብ ናቸው፡፡ ስለዚህም የሚጠበቀውና ትግበራው ሊለያይ፣ ያልታሰቡና ያልተዳሰሱ ነገሮች ሊከሰቱ የሚችሉበት ዕድል ሊኖር ይችላል ሲሉም ያስጠነቅቃሉ፡፡

ሌሎችም ስጋቶች እንደሚኖሩ ጠብቆ በደንብ መዘጋጀት ያስፈልጋል የሚሉት አቶ ወይናለም፤ የሕግ ክፍተት ካጋጠመም ለማረምና ለማስተካከል የሚያስችል ርምጃዎችን ለማድረግ መዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ይገልጻሉ፡፡

ከማስፈጸምና ከመፈጸም አቅም ጋር የሚያያዝ የግለሰቦችና የተቋማት አቅምን እየገነቡ መቀጠል ተገቢ እንደሆነ እና ቀድመው የተገበሩ ሀገራትን ልምድና ተሞክሮ መቅሰምም እንደሚያስፈልግም ይጠቁማሉ፡፡

አቶ ሚካኤል ሌሎች ሀገራት በኢትዮጵያ እንደተደረገው አይነት የፖሊሲ ለውጥ ሲያደርጉ በብዙኋን መገናኛ ሕዝቡ እንዲያውቀው ተደርጎ፣ የመንግሥት የፖሊሲ ውሳኔ የእያንዳንዱ ሰው ሕይወት ላይ ምን ሊያደርግ እንደሚችል ውይይት እንደሚደረግ ይጠቅሳሉ፡፡

በመሆኑም ተሞክሮውን በመቀመር በቂ የግንዛቤ ፈጠራ መሠራት ይኖርበታል፡፡ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው ሰዎች ይበልጥ ተሳታፊ እንደሚሆኑ ታሳቢ በማድረግ የውይይት መድረኮችን ማዘጋጀት ይጠበቃል ነው የሚሉት፡፡

በጉዳዩ በቂ እውቀት እና የውጭ ቋንቋዎች እውቀት ያላቸው ኢትዮጵያውያንን በመጠቀም ጉዳዩን በደንብ ማዳበር እንደሚገባ ነው የሚመክሩት፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ኢኮኖሚውን ለማሳደግ የነጻ ገበያ ሕግጋትን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንደሚያደርግ ይፋ ያደረገው መስከረም 28 ቀን 2011 ዓ.ም የሁለቱ ምክር ቤቶች መክፈቻ ላይ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ዘላለም ግዛው

አዲስ ዘመን ማክሰኞ መስከረም 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You