የፋሽን ኢንዱስትሪ በዓለም ላይ ትልቅ የኢኮኖሚ አቅም መገንባት ከቻሉ ዘርፎች አንዱ ነው። በዚህም ዘርፉን አጎልብተው ትልቅ ደረጃ ማድረስ የቻሉ ሀገራት ከግለሰብ አልፎ ኢኮኖሚያቸውን የሚደግፍበት ደረጃ ማድረስ እንደቻሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ኢትዮጵያ በፋሽን ኢንዱስትሪው ትልቅ አቅም እንዳላት ቢታመንም በሚገባው ልክ አድጓል ለማለት እንደማያስደፍር ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ሲጠቁሙ ይስተዋላል። ለዚህ አንዱ ምክንያት መንግሥትና በዘርፉ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች በጋራ መሥራት አለመቻላቸው መሆኑ ይታመናል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የኢትዮጵያ የፋሽን ዘርፍ በጥቂት ግለሰቦች ጥረት አበረታች ለውጥ እየታየበት እንደሚገኝ መካድ አይቻልም። ዘርፉን ወደ ተሻለ የእድገት ደረጃ ለማድረስ በጋራ የመሥራትና አብሮ የመምከር ጥረታቸው እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ተብለው የሚወቀሱት የፋሽን ባለሙያዎችና መንግሥታዊ መዋቅሮችም በጋራ ለመሥራት ጥረት ሲያደርጉ ማየት እየተለመደ ነው። ለዚህም አንዱ ማሳያ በቅርቡ የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ከማፊ ፋሽን አካዳሚ ጋር አብሮ ለመሥራት ያደረጉት ስምምነት ነው።
በሁለቱ አካላት መካከል የተደረገው ስምምነት በፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ውስጥ የፋሽን ስልጠና ማዕከል ለመክፈት የሚያስችል መሆኑ ተጠቁሟል። የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር (ዶ/ር) ከማፊ ፋሽን አካዳሚ ባለቤት ዲዛይነር ማህሌት አፈወርቅ (ማፊ) ጋር የመግባቢያ ስምምነቱን በፈረሙበት ወቅት እንደተገለፀው፣ የፋሽን ማሰልጠኛ ማዕከሉ የአጭር እና የረጅም ጊዜ ስልጠናዎችን ይሰጣል።
የፋሽን ማሰልጠኛ ማዕከሉ በአጫጭር እና በረጅም ጊዜ ዜጎችን በማሰልጠን ለሀገራችን ፋሽን ኢንዱስትሪ ትልቅ አቅም እንደሚሆን ዶ/ር ብሩክ በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ገልፀዋል።
“ከኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት በጋራ ለመሥራት ትልቅ ስምምነት መፈፀማችንን ስንገልፅ በፍፁም ደስታ ነው! ስምምነቱ በጋራ ሆነን የኢትዮጵያን የፋሽን ኢንዱስትሪ የትምህርት ጥራት በማላቅ እንደ አፍሪካም ዘርፉን ወደፊት የሚያራምድና ትልቅ ተፅዕኖ የሚያሳርፍ የፋሽን ጥናትና ምርምር ለማድረግ ያስችለናል።” በማለት ስምምነቱን በተመለከተ አካዳሚው በማህበራዊ ትስስር ገፁ አስታውቋል።
የፋሽን አካዳሚው አክሎም፣ በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ ማንኛውም ሰው በየትኛውም ቦታና ባለው አቅም ጥራት ያለው የፋሽን ትምህርት እንዲያገኝ ማስቻል ዓላማው መሆኑን ጠቁሞ፣ ስምምነቱ በፋሽን ኢንዱስትሪው ምቹ ምህዳር በመፍጠርና በማጠናከር እንዲሁም ፈጠራን በማበረታታት ድንበር ተሻጋሪ የእድገት ጎዳና ለመዘርጋት እንዳለመ አብራርቷል። የመጪውን ዘመን የፋሽን ኢንዱስትሪ መሪዎች በመፍጠርና በማበረታታት የኢትዮጵያን የፋሽን ኢንዱስትሪ ገፅታ ለመቀየር የጀመረውን ታላቅ ጉዞም በርካቶች እንዲቀላቀሉት ጠይቋል።
ማፊ ፋሽን አካዳሚ እና ላቦራቶሪ (ኤምኤፍኤል)የተባለ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ፋሽን ማሰልጠኛ ተቋም በአዲስ አበባ መጀመሩ ከወራት በፊት እንደነበረ ይታወሳል። በታዋቂዋ ዲዛይነር ማህሌት አፈወርቅ የተመሠረተው ኤምኤፍኤል ፤ ጣሊያን ኤምባሲ ፣ የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (ሁኒዶ) በጣልያን ሀገር ታዋቂው የፋሽን ትምህርት ተቋም አካዳሚ ሞዳ ጋር በመተባበር የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ወጣቶች በዓለም አቀፍ የፋሽን ገበያ እንዲገቡ፣ ዓለም አቀፍ ብራንዶች እንዲኖራቸው እና ወደር የለሽ ኤክስፖዠርና እና የትስስር እንዲሁም የኢንቨስትመት እድሎችን እንዲያገኙ የሚያደርግ ተቋም መሆኑ በወቅቱ ተገልጿል።
ኤምኤፍኤል የፋሽን ማሰልጠኛ በጣሊያን መምህራን እና ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች በመጡ አስተማሪዎችና የንግድ አማካሪዎች የሚማሩበት እንዲሁም ዘመኑ ባፈራቸው ቴክኖሎጂ እና ማሽኖች የሚሰለጥኑበት ሆኖ መቋቋሙም ይታወቃል።
ማህሌት አፈወርቅ በኢትዮጵያ ፋሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ “ማፊ ማፊ” የተሰኘውን ብራንድ ላቅ ያለ ደረጃ ለማድረስ ከአስር ዓመታት በላይ እንዳሳለፈች መረጃዎች ያሳያሉ። በዚህ የተነሳም ብራንዱን ዓለም አቀፍ ተሸላሚ ለማድረግ የቻለች ከመሆኑም በላይ የኢትዮጵያን ባህል ያካተቱ የፋሽን ዲዛይኖችን ከሌጎስ እስከ ለንደን በዘለቁ ትልልቅ የፋሽን መድረኮች ላይ ለማቅረብ በቅታለች፡፡
ማፊ በዚህ ኢንዱስትሪ ውስጥ ካሳለፈችው ቆይታ በመነሳት በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ በዘርፉ የሚስተዋለውን ጉድለት በማየት የፋሽን ትምህርት ቤት ለመክፈት አነሳስቷታል። ማፊ ፋሽን አካዳሚና የፋሽን ዘርፍ ቤተሙከራ በሚል የከፈተችው ይህ ማሰልጠኛ ተቋም በኢትዮጵያ ብቻም ሳይሆን በአፍሪካ ጥራት ያለው የፋሽን ስልጠና መስጠትን አቅዶ እንደተነሳ ምስረታው በተበሰረበት ወቅት ማፊ ገልፃለች። ‹‹ሁሌም ህልሜ ጥራት ያለው የፋሽን ሙያ ስልጠና የሚሰጥ አካዳሚ መክፈት ነበር፡፡ ይሁንና በቅርብ ጊዜ ውስጥ ህልሜ ይሳካል የሚል ግምት ግን አልነበረኝም›› የምትለው ማፊ፣ “ማፊ ማፊ” የተሰኘው ብራንድ በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅናው እያደገ መምጣቱ የሰለጠነ የሰው ሃይልን ፍላጎት እየጨመረው እንደመጣ ትናገራለች። ይህም በገበያው ውስጥ ትክክለኛውን የፋሽን ባለሙያ ማግኘት ስለሚያስቸግር ይህንን ክፍተት ለመሙላት በማሰብ አካዳሚውን ለመክፈት ውሳኔ ላይ እንድትደርስ አድርጓታል።
ማፊ ወደ ፋሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ የገባችው ሁለተኛ ሙያዋ አድርጋ ነበር፡፡ በአስራ ስድሰት ዓመቷ የራፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ በመሆን በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ ጥቂት ጊዜ ማሳለፏ ይታወሳል፡፡ ለሙዚቃ ክሊፖቿ ስትል የምታዘጋጃቸው ልብሶች ወደ ፋሽን ኢንዱስትሪው ውስጥ እንድትገባ ምክንያት እንደሆናትም ትገልፃለች፡፡ በዚህ የተነሳ ኢንዱስትሪውን የተቀላቀለችው ማህሌት አሁን በአፍሪካ ትልቁ የመሆን ውጥን የሰነቀውን የፋሽን አካዳሚ ለመክፈት በቅታለች። በአካዳሚዋ የጣሊያንና የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት አስተማሪዎች ስልጠና እንደሚሰጡ አስታውቃለች፡፡
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም