«የግብጽ አካሄድ፤ በጥባጭ ካለ ጥሩ አይጠጣምና…»

በገጠር አካባቢ ውሃ ከምንጭ ሲቀዳ ከአቆተው ቀስ ብሎ በጣሳ ወይም በቅል ተደርጎ ወደ እንሥራ ነው የሚገለበጠው እንጂ፣ እጅ እንዳመጣ ወደ አቆተው ውሃ አይጠለቅም፡፡ ምክንያቱም ውሃው ስለሚበጠበጥ ይደፈርሳል፡፡ ይህን ሥርዓት ተከትለው አብዛኞቹ የገጠር እናቶች የሚበቃቸውን ያህል ይቀዳሉ፤ ቀጣይ ለምትቀዳውም በማሰብ እንዳይደፈርስ ይጠነቀቃሉ፡፡

አንዳንድ ጊዜ ግን ከአቆተው ለራሳቸው ቀስ ብለው ቀድተው ከጨረሱ በኋላ ለቀጣይ ሰው ባለማሰብ የጠለለውን ውሃ የሚያደፈርሱ አሉ፡፡ ‹‹እኔ ከበላሁ ሰርዶ አይብቀል›› እንዳለችው አህያ ዓይነት መሆኑ ነው፡፡ ለሌላው መብትና ጤና ሳያስቡ ውሃውን በጥብጠውት ይሄዳሉ፡፡ እንዲህ የሚያደርጉት አብዛኛውን ጊዜ ሰው ሳያያቸው ነው፡፡ በእርግጥ ሰው እያያቸውም ቢሆን፣ ተረኛ አጠገባቸው እየተጠባበቃቸውም ቢሆንም ግድ የሌላቸውም አሉ፡፡ ዋናው ዓላማቸው ማደፍረስ ሌላው ንፁህ እንዳይጠጣ ማድረግ ነው፡፡

እንዲህ አድርገው የሚያደፈርሱ ሲገኙ፣ ሌሎች ውሃ ቀጂዎች በቅድሚያ እንዴት ተደርጎ እንደሚቀዳ ከማሳየትና ከመምከር በመጀመር፤ አልስተካከለም የሚሉትን በህብረት ሆነው እስከመጣላት ይደርሳሉ፡፡ በዚህ አግባብ የማይስተካከሉትን ደግሞ ማህበረሰቡ ውሃው አጠገብ እንዳይደርሱ ያግዳቸዋል፤ ይከታተላቸዋል፤ በጥባጭ ካለ ጥሩ ስለማይጠጣ፡፡

ግብጽም ‹‹እኔ ከበላሁ ሰርዶ አይብቀል›› እንዳለችው አህያ ሆና፣ ባገኘችው አጋጣሚ ሁሉ ኢትዮጵያ ጥሩ እንዳትጠጣ ታደፈርሳለች፣ ትበጠብጣለች፡፡ የህዳሴ ግድቡ ሲገነባ ማንኛውም አካል ምንም እንከን እንዳያጋጥመው በማሰብ ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ ጥረት አድርጋለች፡፡

በተለይ ኢትዮጵያ ከግብጽና ከሱዳን ጋር የሦስትዮሽ ውይይት ለማድረግ በሙሉ ልብ ተንቀሳቅሳለች፡፡ ይሁንና ግብጽ ሱዳንን በማስተባበር ውይይቱ መስመር እንዳይዝ ብሎም ግድቡ እንዳይገነባ የተለያዩ እርስ በእርሳቸው የሚቃረኑ ሃሳቦችን ስትደረድር ቆይታ በስተመጨረሻ ውይይቱን አቋርጣ ወጥታለች፡፡

ኢትዮጵያ ግን አሁንም ቢሆን ሁሉን ሊያግባባ የሚችል ሥምምነት ላይ ለመድረስ ያላትን ቁርጠኝነት እያሳየች ነው፡፡ በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር ወይም በአጠቃላይ የትብብር ሕግ ማዕቀፍ ስር የሦስትዮሽ ድርድሩን ለመቀጠልና የሁሉንም ተጠቃሚነት የሚያረጋጋጥ ስምምነት ላይ ለመድረስ ቁርጠኝነት አላት፡፡

ግብጽ ግን ድርድሩ ውስጥ የምትገባው በሙሉ ልብ ሳይሆን የውስጥ ችግር ሲያጋጥማት ወይም የአጋሮቿን ድጋፍ ላለማጣት ለይስሙላ ነው፡፡ ጉንጭ አልፋ ውይይት በሚደረግባቸው ባለፉት ዓመታት ውስጥ ግድቡ እንዳይገነባ ያልሸረበችው ሴራ፣ ተባባሪ ሆነው እንዲያግዟት ያልተማፀነችው አካል የለም፡፡ አሁን የታላቁ ህዳሴ ግድብ የግንባታ ሥራው ተጠናቆ በከፊል ሥራ በመጀመሩ በህዳሴ ግድቡ መገንባትና አለመገንባት ላይ መጨቃጨቁ እንደማያዋጣ ተረድታ የመበጥበጥና የማደፍረስ ስልቷን ወደ ሌላ አቅጣጫ አዙራለች፡፡ ዋና ግቧ ደግሞ ከህዳሴ የሚገኘውን ሀገራዊ ሀብት ኢትዮጵያ በአግባቡ እንዳትጠቀም ማድረግ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት በሚል ከሶማሌላንድ ጋር የተፈራረመችውን ስምምነት ተከትሎ በሞቃዲሾ ሶማሊያ እና በአዲስ አበባ መካከል ፖለቲካዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ውዝግብ ሲካሄድ መክረሙን ግብጽ እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ስትቋምጥለት የነበረውን የማደፍረስ ሥራዋን ለማከናወን ስትውተረተር ትታያለች። በቅድሚያ ግብጽ ከሶማሊያ ጋር ወታደራዊ ስምምነት አደረገች፤ ከዚያም የጦር መኮንኖችን እና ወታደራዊ አቅርቦቶችን የጫኑ ሁለት የግብጽ ወታደራዊ አውሮፕላኖች ሞቃዲሾ አስገባች፡፡

ኢትዮጵያ ይህ ጉዳይ አሳሳቢ ነው በማለት ስታመለክት፤ ግብጽ ጉዳዩ ወደ ሌላ አቅጣጫ እንዳይሄድባት በማሰብ በሶማሊያ ውስጥ የየትኛውም ሀገር መንግሥት ወታደሮች አልገቡም፤ ‹‹ያያችሁበት ዓይን ግንባር ያድርገው›› በሚል ሁኔታ እንዲስተባበል አድርጋለች፡፡

የወታደሮቹን መግባት ያስተባበሉት ደግሞ የሶማሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዛ አብዲ ባሬ ማክሰኞ ጳጉሜን 5 ቀን 2016 ዓ.ም ሞቃዲሾ ውስጥ ባደረጉት ንግግር ነው፡፡ በንግግራቸው የትኛውም ሀገር ወደ ሶማሊያ ወታደሮቹን እንዳላስገባ ገልጸዋል። ሶማሊያ የውጭ ኃይሎችን ወደ ግዛቷ እንዲገቡ መፍቀዷ የአካባቢውን ሰላም እንደሚያናጋ በመግለጽ እርምጃውን ኢትዮጵያ በይፋ ተቃውማለች። ለሚመለከታቸውም አሳስባለች፡፡

የጦር መኮንኖችን እና ወታደራዊ አቅርቦቶችን የጫኑ ሁለት የግብጽ ወታደራዊ አውሮፕላኖች ሞቃዲሾ ማረፋቸው በስፋት ከተዘገበ በኋላ፤ ከኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ከሶማሊያውን ጭምር ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡ የሶማሊያ የተለያዩ ግዛቶች ባለሥልጣናት እና የፌዴራል መንግሥቱ ፓርላማ አባላትም መንግሥት የግብጽ ወታደሮች ወደ ሶማሊያ እንዲገቡ መፍቀዱን በይፋ ተቃውመዋል።

ለሶማሊያ መንግሥት መጠናከር እንዲሁም ለሶማሊያ ሕዝብ ሰላም መከበር ኢትዮጵያ የምትችለውን ያህል ድጋፍ ከማድረግ በተጨማሪ እስከ ህይወት መስዋዕትነት የሚደርስ ዋጋ ከፍላለች፡፡ ከ15 ዓመታት በላይ ወታደሮቿን በሶማሊያ አሰማርታ የሀገሪቱን መንግሥት ስትደግፍ ቆይታለች። ሰላም ወዳዱና ቤተሰባዊ የሆነው የሶማሊያ ሕዝብ የተከፈለለትን መስዋዕትነት ባለመዘንጋት ለድርጊቱ ያሳየውን ተቃውሞ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ የሚያደንቁት ነው፡፡

ድሮም ቢሆን የሶማሊያ እና የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሰፊ በሆነ ድንበር ላይ ሲኖሩ የሚያመሳስላቸው ቋንቋ፣ ባህል እና ሃይማኖት ስላላቸው ተዋደውና ተቻችለው በሰላም የሚኖሩ ናቸው፡፡ ሊያለያዩዋቸው የሚሞክሩ አካላት ሲመጡ እንኳን በችግር ጊዜ ሲረዳዱ የሚስተዋሉ ናቸው፡፡ ቢሆንም በጥባጭ ካለ ጥሩ አይጠጣምና በሁሉም መስክ ጠንቀቅ ብሎ መጠበቁ ተገቢ ነው።

ስሜነህ ደስታ

አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You