በምግብ ራስን መቻል ሌላው ሉዓላዊነት

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻልና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋጋት እየሠራች እንደሆነ ይገለጻል። ለመሆኑ የምግብ ሉዓላዊነት ስንል ምን ማለታችን ነው? የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እየተሠራ ያለው ሥራስ ምን ውጤት እያስገኘ ነው? በሚሉት ጉዳዮች ዙሪያ የዘርፉ ምሁራን አስተያየታቸው ሰጥተውናል።

በግብርና ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ሥርዓተ ምግብ ሽግግርና ኒውትሬሽን ዋና አስተባባሪና የሚኒስትሩ ከፍተኛ አማካሪ ጌታቸው ድሪባ (ዶ/ር) እንደሚሉት፤ አንድ ሀገር ሕዝቦችን ከአደጋ፣ ከረሀብና ከርዛት የሚወጡበትን መንገድ ካላዘጋጀ ሙሉ በሙሉ ሉዓላዊ ነው ለማለት አይቻልም። የምግብ ሉዓላዊነት የአንድ ሀገር ሉዓላዊነት መሠረታዊ አካል ነው።

የምግብ ሉዓላዊነት ስናነሳ የምግብ መብት የሚባል ነገር አለ። ይህ የአንድን ግለሰብ፣ ቤተሰብ፣ ማህበረሰብና ሕዝብ በልቶ የማደር መብት እንዳለው የሚገልጽ መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ የራሷን የሆነን የግብርና እርሻ የፈጠረች ሀገር እንደመሆኗ መጠን የምግብ ሉአላዊነቷን ማረጋገጥ የግድ ይላል ነው ያሉት።

ይህን እውን ለማድረግም የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ገልጸው፤ ከዚህ ውስጥ የኢትዮጵያ የሥርዓተ ምግብ ሽግግር ተብሎ እየሠራ ያለው ሥራ ተጠቃሽ መሆኑን ያነሳሉ። ዘላቂነት ሌላኛው የምግብ ሉአላዊነት ማረጋገጫ መንገድ ነው። ይህም ኢትዮጵያ የምታመርተው የምግብ አይነትና መጠን ለሕዝቦቿ የሚዳረስ፤ የህብረተሰቡን የንጥረ ምግብ ፍላጎት መሠረት ያደረገና ዘላቂነት ያለው አሠራር መዘርጋትን ይጠይቃል ሲሉ ያብራራሉ።

የምግብ ሉአላዊነት ስንል ተደራሽነትና ፍትሐዊነት ያለው መሆንም ይጠበቅበታል።ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2015 ዓ.ም 17 የልማት ግቦች እና 169 ትልሞች የያዘውን ዘላቂ የልማት ግብ ተቀብላለች ያሉት ዶክተር ጌታቸው፤ መሠረታዊ እሳቤው ረሀብን ከዓለም ዙሪያ ማጥፋት ነው። ከዝቅተኛ ደረጃ ድህነት ውስጥ ያሉ ሰዎችን ማውጣት፣ የተፈጥሮ ሀብቶችን መንከባከብና ሰላምንና ትብብርን የሚያጠናክር ነው። በራሷ በኩልም የ10 ዓመት የልማት ግቦችን ቀርጻ እየሠራች መሆኑን ጠቅሰዋል።

ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ የስንዴ ልማት፣ የሌማት ቱርፋትና አረንጓዴ አሻራን ጨምሮ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ጠቁመው፤ በእነዚህ መርሃ ግብሮችም ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እየተገኙ ነው። ለአብነትም ስንዴን ከውጭ ሀገር ከማስገባት በመላቀቅ በአንጻሩ የሀገር ውስጥ ፍላጎትን በማሟላት ለውጭ ገበያ ማቅረብ መቻሉን ያነሳሉ። አነስተኛ አርሶ አደሮችን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግና ቴክኖሎጂን በስፋት እንዲጠቀም ለማድረግ የፋይናንስ አቅርቦት ትኩረት ተሰጥቶታል።የተመረተው ምግብም ተደራሽነትና ይዘት ላይ ትኩረት አድርጎ በመሥራትም ሕፃናት ላይ የሚስተዋለውን መቀንጨር ለማስቀረት በትኩረት እየተሠራ ነው ያሉት።

የምግብ ሉዓላዊነት ስለተመኘነው ብቻ አይመጣም የሚሉት ዶክተር ጌታቸው፤ በፌዴራል ደረጃ 14 ሚኒስትሮችን ያካተተ የምግብ ሥርዓት ሥነምግብ ስትሪንግ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየሠራ መሆኑን ያስታወሱት ዶክተር ጌታቸው፤ ይህም የሚያጋጥሙ ከፍተኛ ችግሮችን የሚፈታና አቅጣጫዎችንም ያስቀምጣል። በክልሎችም በተዋረድ እየተዋቀረ ሲሆን ያሉ ሀብቶችን ማቀናጀትና ማሰባሰብ ላይ ይሠራል።

የምግብ ሉዓላዊነት የሰብዓዊ ክብር ጥያቄን እንደሚያስከትል ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት በሚያጋጥሙ ችግሮች ምክንያት በርካታ ዜጎች በምግብ እርዳታ ይኖራሉ። ይህ የምግብ እርዳታ በአብዛኛው ከውጭ ለጋሾች የሚመጣ ነው። ይህ ደግሞ ውስጣዊ ጉዳዮች ላይ ጣልቃ ለመግባት እድል የሚፈጥር መሆኑን ነው ያስረዱት።

አንድን ሀገር የሚያስከብረው ወታደራዊ አቅሙ በአንድ በኩል የመንግሥት ጥንካሬና የሕዝቦች ደህንነት በልቶ አድሮ በሀገራቸው መኩራትም ጭምር ሲኖር መሆኑን ጠቅሰው፤ ብዙ ዜጎቻችን እርዳታ ላይ የሚመሠረቱ ከሆነ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሉዓላዊነትን ጥያቄ ውስጥ ማስገባቱ የማይቀር ነው። እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ይህንን ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ያለሙ ናቸው።

የምግብ ሉዓላዊነት መንግሥት በሚሠራው ብቻ የሚረጋገጥ ስላልሆነ የግል ዘርፉ ፣ አርሶ አደሩና መላው ኢትዮጵያውያን ርብርብ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ሲያጋጥም እርዳታ የትም ሀገር ተለመደ መሆኑን አስታውሰው፤ ይሁን እንጂ እንደ ማህበራዊ ረድኤት ሆኖ መቀጠል የለበትም።

ስለሆነም ሁላችንም የምንወዳትን የሀገራችንን አንድነትና ሉዓላዊነት የሚፈታተን ኃይል ሆኖ የሚመጣ እድል መኖሩን ተገንዝበን የዜጎችን ክብር ለማስጠበቅና የሀገራችንን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ መሥራት ይኖርብናል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአካባቢ ጥበቃና ዘላቂ ልማት ፕሮፌሰሩ በላይ ስማኔ በበኩላቸው፤ የምግብ ሉዓላዊነት አለማረጋገጥ ብዙ ፖለቲካና የፋይናንስ ጫና ያስከትላል። ምክንያቱም የምግብ ሉዓላዊነት ለሀገር ውስጥ ፍጆታ በበቂ ሁኔታ እና በተመጣጣኝ ዋጋ በሀገር ውስጥ አምርቶ ማቅረብና ራስን መቻል ማለት ነው ይላሉ።

በብዙ የሀገራችን ፖሊሲዎች፣ በግብርና ሰነዶች እና በሌሎችም ጉዳዮች ውስጥ የምግብ ዋስትና ቁልፍ ሀገራዊ ሥራ መሆኑ ይገለጻል። በእርሻ ምርምር፣ በግብርና ኤክስቴንሽን ማሻሻል፣ በቴክሎጂ አቅርቦትና የግብርና ምርት ማሳደጊያዎችን በወቅቱ ከማቅረብ አንጻር የተለያዩ ሥራዎች ይሠራሉ። ብዙ ለውጦችም ተመዝግበዋል።

ምርትና ምርታማነትን ከማሻሻል አኳያም በጥራጥሬ፣ በሰብል፣ በእንስሳት ልማት ዘርፎች ለውጦች አሉ። ነገር ግን ይህ ለውጥ ካለው የሕዝብ ቁጥር አኳያ በበቂ ሁኔታ የኢትዮጵያን የምግብ ዋስትና ሊያረጋግጥ እንዳልቻለ ይገልጻሉ።

የአየር ንብረት ለውጥን፣ የሕዝብ ብዛታችንም እንዲሁም ዘላቂ ሰላም ማስፈን አለመቻል የምግብ ዋስትናን እንዳናረጋግጥ መሰናክል ፈጥሮብናል የሚሉት ፕሮፌሰር በላይ፤ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ግብርና ብቻ በቂ አይደለም የሚባለውም ለዚህ ነው። በመሆኑም በጤና፣ በቤተሰብ ምጣኔና በሌሎችም መስኮች ላይም ሥራዎች መሠራት እንዳለባቸው ያመለክታሉ።

በተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጠሩ ጦርነትና ግጭቶች የሚያስከትሉት የማህበራዊ አለመረጋጋት የምግብ ዋስትናችንን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት በከፍተኛ ደረጃ ጎድቶታል የሚሉት ምሁሩ፤ ከዚህም በተጨማሪ የዩክሬንና የሩስያ ጦርነት እንዲሁም በመካከለኛው ምሥራቅ የሚስተዋሉ ችግሮች የራሳቸውን አሉታዊ አስተዋጽኦ አበርክተዋል ይላሉ።

አብዛኞቹ የግብርና ምርት ማሳደጊያ ግብዓቶች ከውጭ የሚመጡ ናቸው። ይህ ደግሞ ከውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር በተገናኘ የሚያጋጥም ሌላኛው እንቅፋት ነው።በጥቅሉ ምንም እንኳን ሰፊ ጥረት ቢደረግም አሁንም ድረስ ሙሉ በሙሉ የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ አልተቻለም ነው ያሉት።

የተቀረጹ ፖሊሲዎችን ለመተግበር ብዙ ርቀት መሄድ ይኖርብናል። ከዚህ ውስጥ የሚጠቀሰው ማህበረሰብን ያማከለ ፖሊሲ ማውጣትና አስተዳደራችንን ማዘመን እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ ከዚህ በተጨማሪ ምርምርና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን በስነምህዳርና በግብርና ሥርዓት የተማከሉ ቴክኖሎጂዎችን በብዛት እንዲያፈልቁ መሥራት ያስፈልጋል። የኤክስቴንሽን ሥራውን ከፖለቲካ ሥራው መለየትና ግብርናን ማዘመን ላይ ሙሉ ጊዜውን የሚያውል የግብርና ኤክስቴንሽን ባለሙያ እንዲኖር መሥራት ይገባል።

አርሶና አርብቶ አደሮች ያላቸውን ሀብት በአግባቡ እንዲጠብቁና ቴክኖሎጂዎችን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር እንደሚገባ ጠቅሰው፤ የግል ዘርፉ በግብርናው ዘርፍ ያለውን ተሳትፎ ማሳደግ እና ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በስፋት እንዲጠቀም ማድረግም ያስፈልጋል። አጋር አካላት የሚሰጡትን ድጋፍ በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ ይጠበቃል።

መሥራት ያለብንን የቤት ሥራ በአግባቡ ከሠራን ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አልፋ የምግብ ሉዓላዊነቷን ማስጠበቅ የሚያስችል አቅም እንዳላት ጠቁመው፤ ሰላም ማስጠበቅ፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት የሚያከናውኑትን ሥራ በአግባቡ መከታተልና መቆጣጠር ላይም ትኩረት አድርጎ መሥራት እንደሚገባ አመላክተዋል።

እንደ ምሁራኑ ገለጻ፤ ኢትዮጵያ በምግብ ራስን ለመቻል ብሎም የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እየሠራች ነው።ይሁን እንጂ ሀገራዊ ሰላምን ማስፈን፣ አሠራርና አስተዳደርን ማዘመን ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት ያስፈልጋል።ለዚህ መሳካት ደግሞ መንግሥት የሚያደርገው ጥረት በቂ ስላልሆነ ሁሉም ባለድርሻዎች በትብብር መሥራት ይኖርባቸዋል ሲሉ ምክረ ሃሳባቸው ይሰጣሉ።

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን መስከረም 19 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You