ተፈጥሮ ጀርባን ባትሠራ ምን ነበር

ተፈጥሮ ግን መሰሪ ናት..የማንደርስበትን ጀርባ ከኋላችን አስቀምጣ ከራሳችን ጋር ትንቅንቅ ውስጥ ያስገባችን። ጀርባዬ ላይ ሌላ ነፍስ ያለ ይመስለኛል..አርፌ እንዳልቀመጥ የሚያቅበዠብዥ ነፍስ። ከመላው ሰውነቴ ተለይቶ ጀርባዬ ላይ እንደእንሽላሊት የሚሄድ፣ የሚቧጥጥ፣ የሚያቅራራ፣ የሚውረገረግ ብል አለ..ላከው ስል የሚጠፋ። ደሞ እኮ ብቻዬን ሳለሁ በዝምታ ሰንብቶ ፕሮቶኮል የሚፈልግ ቦታ ላይ መንቃቱ ነው። ሽክ ብዬ ፍቅረኛዬን ላገኝ ወይም ደግሞ ለሆነ ትልቅ ጉዳይ ሰው መሀል ስገኝ ጠብቆ የሚበላኝ ነገር ነው የሚያስቆጣኝ። ከሰውነት ጋር አብሮ የተሰጠን የሆነ ነገር እማ አለ..እንደጀርባ ከኋላ አድብቶ እንከናችንን ሊገልጥ በስውር የሚከተለን፡፡

በሰውነት ላይ በፉክክርና በእኔ እበልጥ ጣውንታሞች ሆነው ጎራ የፈጠሩ ሁለት ሃሳቦች አሉ..

ሰው በስላሴ ሃሳብ ከአፈር ተሠራ…

ሰው በዝግመተ ለውጥ ከዝንጀሮ ወደሰውነት ተቀየረ..የሚሉ፡፡

ዳርዊን ወይስ እየሱስ ማናቸው ናቸው ልክ? ብዬ አልጠይቅም። ፍጡርን ከፈጣሪ ጋር ማወዳደረወ ሆኖ አይደለም ሲታሰብ የሚነዝር ድርጊት ነው። እኔ ለእየሱስ አድልቼ በረጅም ዘመን ስልሳሌ የሚሆነኝን መርጫለው። በበኩር እማኝ ምስክር ሰውነቴን በጸጋ ተቀብያለው። ግን ጀርባ ላይ እከክ ከየት መጣ? ታላቅ ሃሳብ ውስጥ እከክ ምን ይሠራል? ከአፈር ተሠርተህ ድሮስ እንከን ላይኖርብህ ነው? የሚል መልስ መሳይ ሃሳብ አእምሮዬ ውስጥ በቀለ። ደግሞ ሌላ አደመጥኩ..‹አታብል..ከአፈሩ ሰሪው ይልቃል። ሰሪው አፈሩን የመረጠበት ምንም መሆናችንን በመናገሩ ውስጥ ሌላም ትርጉም አለው› የሚል። ሁለት የማላውቃቸው ጎራዎች በራሴ ውስጥ ግብ ግብ ፈጠሩ። ወደየትኛው እንደምወግን መላ ጠፋኝ፡፡

ሁለተኛው መንፈሴ በእልህ ንግግሩን ቀጠለ ‹ምንም ነው ያልከው አፈር የሕይወት ማህጸን ነው። ዘርተን የምንበላው በአፈር ነው። መነሻና መድረሻችን መሬት ነው። የሚበልጠው አብሯቸው እስካለ ድረስ ትናንሾቹ ባለሃይል ናቸው። አፈር የሕይወት ቀለም የሆነው በአስገኚው በኩል ነው። ጎልያድና ዳዊትን አስታውሳቸው..ዳዊት አፈር ነው..ጎልያድ ደግሞ ባለሞገስ..መቼም ማን የክብር ኒሻን እንዳጠለቀ ታውቀዋለህ። አየህ የሚበልጠው አብሮህ ሲሆን እንደዚህ ነው። በአፈር ውስጥ የእኔና የአንተ ሰው መሆን ሊገርምህ አይገባም። ልክ የማትሆነው የሚበልጠው አብሮህ ያልሆነ ጊዜ ነው። አንዳንድ ጊዜ አልመን እንዳንስታቸው ግዙፍ ጥላዎች በዙሪያችን ያንጃብባሉ..ብዙሃን ፈርተው ሲያፈገፍጉ ደቂቃን ቀስታቸውን ይወረውራሉ..ወርውረውም አይስቱም..ይሄ የእኛ አቅም ሳይሆን የሚበልጠው ተራዳይነት ነው፡፡

የመጀመሪያው መንፈሴ..በዝምታ ተዋጠ፡፡

እኔ ውስጥ ሁለት ጎራ የመፈጠሩ ነገር በየትኛውም ነገር ላይ እርግጠኛ አለመሆኔን ጠቆመኝ። ሕይወት ሰፊ ናት ሳይገባኝ እንደገባኝ የተቀበልኩት ይኖራል..ገብቶኝም እንዳልገባኝ የሆንኩትም፡፡

ዝም ያለው መንፈሴ ግን እኮ ሲል አደመጥኩት..‹ግን እኮ አፈር ሕይወት ብቻ ሳይሆን ሞትንም ያበቅላል። አንተ ራስህ ይሄ ገብቶህ ነው የምትናገረው? የሕይወት እከክ ከአፈር ካልበቀለ ከየት መጣ ልትል ነው? አለው ሁለተኛውን መንፈሴን። አሁን ሲገባኝ ጠያቂና መላሽ ሆነው እኔን ወደእውነተኛ መንገድ ሊወስዱኝ የተቃረኑ መሰለኝ፡፡

‹አፈር የሕይወት መብቀያ ነው..አለመኖር በዚህ ስም አይጠራም እናም ከአፈር አልተነሳም። የሕይወት እከክ የሰው ልጅ በመኖር ውስጥ ከአፈር የጣለው ኋላም እሾህ ሆኖ በቅሎ ራሱን ያደማው እንጂ ተፈጥሮ ያበቀለው አይደለም። አንተ የምትለውን ያለመኖር እንክርዳድ የሰው ልጅ ራሱ ነው ዘርቶ ያጸደቀው› ሲል መለሰለት፡፡

ጠያቂው መንፈሴ ወደዝምታው አዘቅት ተመለሰ

አክሎም ‹ሰው ንጹህ ዘር ነው..ነገዱም ሀሳበ ሥላሴ ነው። ንጹህ ሃሳብ ውስጥ ብላሽ ታሪክ የለም..ዘራችን አንዱአምላክ ነው። ከምርጥ ሃሳብ ስር ካለ ዘር በቅለን አበባ መሆን ሲገባን በራሳችን ላይ የሃጢያትን እከክ ፈጠርን። ይሄ እከክ ብልና ጠዝጣዥ ሆኖ ከራሳችን ጸጉር እስከ እግራችን ጣቶች ድረስ ቅማልና ጮቅ ሆኖ መጣ። እከክ የሌለበት አካል የለንም። ምርጥ ዘራችንን በነውር ለውጠን ቤተመቅደስ ሰውነታችንን የባዕድ መፈንጫ አድርገናል። ራስ ለዘውድ አንገት ለድሪ መሆኑ ቀርቷል። ደረት ለግማድ፣ ክንድ ለአልቦ መሆኑ ዘበት ነው። ወለባና አሸክታቦቻችን የክብር ሥፍራ አጥተው በእከክ ተመንዝረዋል። ራሳችን ዘውድ መጫን ሲገባው የተባይ መናኸሪያ ሆኗል። ክብሮቻችን የሉም..

ጽንፍ የረገጡ ጥንድ መንፈሶቼን ለዝምታ ጥዬ ወደራሴ የጀርባ እከኬ ተመለስኩ። ጀርባ ባልተፈጠረ ከተፈጠረም ቧጠን ብንደርስበት ምናለ የሚለው ተቀዳሚ ምኞቴ ሆነ። ከኋላ በኩል ዓይንና ጀርባችንን መቧጠጫ ሶስተኛ እጅ ቢኖረን የሚለው ምኞቴ በከንቱነት ዘላለማትን ጠብቷል። በጽሞና ሰንብቶ ቀጠሮዬ ከእሷ ጋር የሆነ እለት ያቁነጠንጠኛል። ጀርባ ሲበላና አይነምድር ሲመጣ ስሜቱ አንድ አይነት ነው። ያቁነጠንጣል፣ መግቢያ ያሳጣል፣ የምንይዘው የምንጨብጠው እስኪጠፋን፡፡

እከክ መንፈሴ እንደሚለው በሕይወት ለም መሬት ላይ ያበቀልነው የሃጢያት ዛር ውላጄ የፈጠረው ይሆን? ነው ወይስ ተፈጥሮ ራሷ ብጉራም ሆና ከተፈጠርንበት አፈር የጸነሰችው? የቱም ይሁን ግድ የለኝም..ብቻ ጀርባዬ ላይ ፊጥጥ ከሚል እከክ የሚታደገኝ ባገኝ ለቱም ግድ አይኖረኝ።

ተፈጥሮ ለም መሬት ናት ብንል..እረ አይደለችም..አራሙቻ አብቃይ መሬት ናት ብንል ወደልኩ የምንጠጋው ምን ይዘን ነው? ሁሉም የመሰለውን የሚሰነዝርባት ነጻ ዓለም ላይ ነን.. እንደዚህ መሆኑ ደግሞ ያላስታራቂ በየፊናችን እንድንቆም አድርጎናል። እንዲህ ጎራ የለየ ውንብድና ካልታከለበት መኖር ብቻውን አይጣፍጥ ይሆን?

ተናጋሪው መንፈሴ እንደሚለው የሕይወት ለምጽ የኩነኔ እፍታ ይሆን? ነው መሰል..ካልሆነ እንደሂሳብ ሊቅ አስልቶና ቀምሮ ጥሩ ጊዜዬ ላይ ለምን ይመጣል? ለዛውም እሷ ፊት ስቆም..ለዛውም እንከን በማይፈልግ ከፍታ ላይ፡፡

የሆነ ቦታ አለ..ተፈጥሮ ከሰውነት ስሪቷ የተረፋትን ጭቃና ብናኝ ያጎረችበት ጉሬ..ይሄ ቦታ ጀርባ ይመስለኛል። ካልሆነ እንዳይታይ ተከልሎን በፊትና ኋላ ለምን ቆምን? የሆነ ቦታ አለ ተንጠራርተንና ወደዚያ ወደዚህ ተንፈራግጠን የማንደርስበት ከሰውነት የራቀ ቦታ..ይሄን ሥፍራ የጀርባ ላይ ደሴት እለዋለው። እከክ ያቆረ..የሕይወት ቤርሙዳ። ልጅነቴ ጀምሮ ያበቃው ለአያቴ የጀርባ ማከኪያ ጉልጥምት እያቀበልኩ እንደሆነ የማልዘነጋው ትውስታ አለኝ። አያቴ ለምን ጀርባ ማከኪያ መቁያና ማማሳያ አቀብለኝ እንደምትለኝ አሁን ነው የገባኝ። መቼም በራስ ካልደረሰ አናውቅ..። ቆይ ግን በልጅነቴ ጀርባ አልነበረኝም..? ለአያቴ ጀርባ ማከኪያ ሳመላልስ በልቶኝ የማያውቀው! ነው ወይስ ከምናምንቴ ጋር እየታከኩ እከኬን አስታግሼው ይሆን?

ግራና ቀኝ እጄን በጎን ብልከው፣ በማጅራቴ በላይ ብሰቅለው፣ በታች በመቀመጫዬ በኩል ብሰደው ጀርባዬን አልደርስ አልኩበት። የበላኝን ቦታ አላገኝ አልኩት። ጀርባዬ አጠገቤ ቢሆን በጥፊ አላጋው ነበር። ሰክኜ እና አደብ ገዝቼ በምወዳት ሴት ፊት እንዳልታይ ያደረገኝ ባላንጣዬ፡፡

እሷ ፊት መጽዳት ነበር ፍላጎቴ..የበቃ መሆን። ግን ነጻ አልሆንም፣ ከጀርባዬ ጀምሮ አጓጉል ቦታ ላይ ያሳክከኛል። ብብቴ ውስጥ፣ መራቢያ አካላቴ ስር..እርምጥምጥ ቦታ ላይ። የሰላ ነገር ላይ እንዳረፈ መቀመጫ እንዲችው ስቁነጠነጥ እቆያለው። ልብሴ ተባይ አለው እንዳልል የጸዳ ነው ለበስኩት፡፡

አርፋ መቀመጧ ያስቀናኛል። ወለሉ ላይ የተሰተረው ጥላዋ እንኳን ዝማሜ የለውም። በስክነቷ ተፈጥሮን በሃይሏ የምትገዛ ትመስላለች። በርጋታዋ በጸጥታዋ ለተፈጥሮ ሥልጣኔን የምታስተምር ነው የምትመስለው። እዚች ሴት ፊት እከካም መሆን ምን እንደሚመስል ሳሉት፡፡ እንደእሷ ነበርኩ..እንደእሷም መሆን እፈልጋለው።

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን ዓርብ መስከረም 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You