ባለፈው የአፍሪካ ዋንጫ ከ24 አገራት 630 ያህል ተጫዋቾች ብሔራዊ ቡድኖቻቸውን ሲወክሉ ከነዚያ ተጫዋቾች መካከል 200 ያህሉ የተወለዱት ወይም የእግር ኳስ ክህሎታቸውን ያጎለበቱት ከአፍሪካ ውጪ ነው። 104ቱ በፈረንሳይ የተወለዱ ወይም በሀገሪቱ የሥልጠና መንገድ የተገሩ ናቸው። 24 ተጫዋቾች በስፔን፣ 15 በእንግሊዝ፣ 13 በኔዘርላንድስ፣ 10 ደግሞ በፖርቹጋል።
በ2022 የዓለም ዋንጫ ግማሽ ፍፃሜ በመድረስ የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት አገር የሆነችው ሞሮኮ መሠረታቸው አውሮፓና ሌሎች ሀገራት ያደረጉ 18 ያህል ተጫዋቾች በስብስባ መካተታቸው ትልቅ አስተዋፅዖ ነበረው። ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን ያላቸው እንደ አልጄሪያ፣ ሴኔጋል፣ ናይጄሪያ፣ ኮትዲቯርና ሌሎችም በርካታ ሀገራት ወሳኝ የሆኑ በርካታ ተጫዋቾቻቸው የእግር ኳስ መሠረታቸው ከአፍሪካ ውጪ ነው። በዚህም ውጤታማ እየሆኑ ይገኛሉ። ተጫዋቾች ከታዳጊነት አንስቶ የዳበረ የእግር ኳስ ባሕል፣ በዘመናዊ ሥልጠናና ሳይንሳዊ መንገድ መገራታቸው ለየቡድኖቻቸው የተሻለ ነገር እንዲያበረክቱ ማድረጉ አያከራክርም።
ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ዕድለኛ አይደለችም። የእግር ካስ ሥርዓቷ ከመሠረተ ልማትና ከሥልጠናው ጀምሮ ወይ አልዘመነ ወይም ሌሎቹ የአፍሪካ አገራት የሚጠቀሙትን ዕድል አልተጠቀመች በተለመደው መንገድ መጓዟን ቀጥላለች። ለዚህም ነው ለመጨረሻ ጊዜ በተሳተፈችበት አፍሪካ ዋንጫ ከ24 ሀገራት መካከል አንድም ተጫዋች ከሀገር ውጪ የተወለደ ወይም ውጪ ቀመስ ያላካተተች ብቸኛዋ ሀገር የነበረችው። ለዚህም ሕገ መንግሥቱ ጥምር ዜግነት አለመፍቀዱ ዋነኛው ምክንያት ነው። ለዚህ ግን አንድ መፍትሔ አለ፣ ተሰጥዖ ያላቸው ታዳጊ ኢትዮጵያውያንን መልምሎ የተሻለ መሠረተ ልማትና የእግር ካስ ሲስተም ባላቸው የውጪ ሀገራት እንዲጎለብቱ ማድረግ። ግን እንዴት?
ይህን ጥያቄ ለመመለስ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያውያን ባለተሰጥዖ ታዳጊዎች ዓለም አቀፍ ተፈላጊነት እንዲያገኙ መንገድ የሚጠርጉ ፕሮጀክቶች ብቅ ማለት ጀምረዋል። በቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንና የኢትዮጵያ የቡና ተጫዋች አሠልጣኝ ዕድሉ ደረጄ የሚመራው ዕድሉ አካዳሚ (ኢዲዋይ አካዳሚ) አንዱ ነው።
አካዳሚው ታዳጊዎችን በመመልመል ሥልጠና መስጠት ከጀመረ ሁለት ዓመት አስቆጥሯል። ከዛ በፊት ግን በተቆራረጠ መልኩም ቢሆን ሥልጠና ይሰጥ እንደነበር መሥራቹ አሠልጣኝ ዕድሉ ደረጄ ይናገራል። ባለፈው ዓመት በሀገር ውስጥ በምድብ አንድ ወደ ኢትዮጵያ ቡናና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ያቀኑ ተጫዋቾችን አፍርቷል። በቀጣይም ፕሮፌሽናል ተጫዋች ለማፍራት ጠንካራ የውጪ ግንኙነት መሥርቷል። በዚህም መሠረት ኢዲዋይ አካዳሚ ከወራት በፊት አንድ ዓለም አቀፍ ስምምነት አድርጓል። ይህ ስምምነት ቲኤፍ ኤ ኢሊት ከሚባል በዱባይ የሚገኝ ፕሮፌሽናል የእግር ኳስ ክለብ ጋር ነው። ቲኤፍ ኤ በዱባይ ሊግ በሦስተኛ ዲቪዚዮን ይወዳደራል። ከዚህ በተጨማሪ ተጫዋቾችን እየመለመለ ሥልጠናም እየሰጠ ወደ አውሮፓ መላክ ላይ ትኩረት አድርጎ ይሠራል። ይህ አካሄድ ለተስፈኛ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች መልካም ዕድል ሆኗል።
ቲኤፍ ኤ ኢሊት ምስራቅ አፍሪካን ጨምሮ በመላው ዓለም ላይ ልዩ ችሎታ /talent/ ያላቸው ታዳጊ ተማሪዎች ከመመልመል ባሻገር የአካዳሚውን ደረጃ /standard/ እንዲያሟሉ ሥልጠናዎችን በመስጠት ወደ አውሮፓ ክለቦች ይልካል። የኢዲዋይ አካዳሚ መሥራች አሠልጣኝ ዕድሉ ከቲኤፍ ኤ ኢሊት ጋር ባደረገው ዓለም አቀፍ የታዳጊዎች ምልመላ ስምምነት የ18 ዓመት ወጣት የሆኑት ናትናኤል አረጋዊና ቢንያም ደስታው ዕድል የተፈጠረላቸው ተጫዋች ናቸው። ናትናኤል ከዓመት በፊት ወደ ቲኤፍ ኤ አካዳሚ ገብቶ ከሠለጠነ በኋላ ከመላው ዓለም ከ10 አገራት ከመጡ ተጫዋቾች አንደኛ በመሆን ነበር ለመፈራረም የበቃው። ቢንያምም በተመሳሳይ። አሁን ላይ የሁለቱ ወጣቶች ፍሬ በአጭር ጊዜ መታየት ጀምራል።
የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በቅርቡ በሚያደርገው የአፍሪካ ዋንጫ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ላይ በአሠልጣኝ ሥዩም ከበደ ጥሪ ከተደረገላቸው ተጫዋቾች መካከል ሁለቱ የኢዲዋይ አካዳሚ ፍሬዎች ይገኙበታል።
‹‹ወደ ዱባይ ያቀናሁት በአሠልጣኝ ዕድሉ አማካኝነት ነው›› የሚለው ናትናኤል እዚያ ካቀና በኋላ ከኢትዮጵያ የተለየ ነገር ያገኘው በዋናነት በሥልጠና አሰጣጡ ላይ መሆኑን ይናገራል። ‹‹እዚያ ሁሉም ነገር ፕሮፌሽናል ነው፣ ከሜዳ ጀምሮ እስከ አመጋገብ ምንም የሚጓደል ነገር የለም፣ ከእኛ የሚጠበቀው አቅማችንን አውጥተን ማሳየት ነው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ አንዱ ችግር የሜዳ ነው፣ ታዳጊዎች ደግሞ የተሻለ ደረጃ እንዲደርሱ ምቹ ሜዳ የግድ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ታዳጊዎች ላይ ትኩረት አይደረግም›› ያለው ናትናኤል፣ እሱ ያገኘውን አይነት ዕድል ቢያገኙ አቅሙና ብቃቱ ያላቸው በርካታ ኢትዮጵያውያን ታዳጊዎች በእድሜያቸው መሠረት ተመልምለው የኢትዮጵያን እግር ኳስ መቀየር እንደሚችሉ እምነት አለው። ቢንያምም በዚህ ረገድ ከናትናኤል የተለየ ሀሳብ የለውም።
ኢዲዋይ አካዳሚ የፈጠረለትን ትልቅ ዕድል ተጠቅሞ በዱባዩ ክለብ የሙከራ ጊዜውን በስኬት በማጠናቀቅ ከስምንት ወር በፊት መፈረሙን የሚያስታውሰው ቢንያም፣ የኢትዮጵያን እግር ኳስ ወደ ኋላ እየጎተተው የሚገኘው ከመሠረተ ልማት ጀምሮ እስከ ሥልጠና ያለው ችግር በዱባዩ ቆይታው አልገጠመውም። እንደ ኢዲዋይ አካዳሚ ሌሎችም ለታዳጊዎች የእሱ አይነት ዕድል በስፋት መፍጠር ከቻሉ የኢትዮጵያን እግር ኳስ የመለወጥ አቅሙ እንዳላቸው ጥርጥር የለውም።
አሠልጣኝ ዕድሉ እነዚህ ወጣቶች በዱባይ ባገኙት ዕድል ከአካል ብቃት ጀምሮ ብዙ እድገት ማሳየታቸውን ይናገራል። ኢትዮጵያ ውስጥ ከመሠረተ ልማት ጀምሮ ታዳጊዎቹ ወጥ በሆነ መንገድ አቅማቸውን ለማሳደግ ብዙ ፈተናዎች እንዳሉባቸው በማስታወስም፣ በዱባይ ቆይታቸው በዋናነት የፕሮፌሽናል አስተሳሰብ እንዲያዳብሩ ከማድረጉ በተጨማሪ ፉክክር በበዛበት ሂደት ውስጥ ጎልተው ለመውጣት ጠንክረው እንዲሠሩ ማድረጉን አስረድተል። በዚህ ሂደት አልፈው ለወጣት ብሔራዊ ቡድን መጠራታቸውም ለሌሎች ተነሳሽነትን ይፈጥራል ባይ ነው።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሐሙስ መስከረም 16 ቀን 2017 ዓ.ም