መስቀል እና ሽምግልና

ሃይማኖታዊ በዓላት ሃይማኖታዊ ብቻ አይደሉም። ባህላዊና ሞራላዊ እሴት አላቸው። ባህላዊ እሴቶች የልጃገረዶችንና የወጣቶችን መንፈስ ያድሳሉ። አዲስ ተስፋን ያበስራሉ። ሞራላዊ እሴቶች የህብረተሰቡን አብሮ መኖርና መተጋገዝ ያጠነክራሉ። ይሄ በኢትዮጵያ ምድር የተለመደ ነው። ጎዳና ላይ የወደቁ ወገኖች እንኳን ጎብኚ የሚያገኙት በበዓላት ቀን ነው። በዓላትን ብቻ ጠብቆ ማድረጉ ትክክል ባይሆንም (የሀገሪቱን የኢኮኖሚ አቅም እናስብና) በበዓላት ቀን ራሱ ማሰቡ ግን የሞራል ልዕልናን ይጠይቃል።

ሌላው የበዓላት ውበት የማህበራዊ ሕይወት ልዕልና መሆናቸው ነው። አንድ አባካኝ፣ ዕቅድ የለሽ፣ ለሰው የማይጨነቅ… የሚባል ሰው ሳይቀር ለበዓላት ሰዋዊ ዝግጅት ያደርጋል። ከወዳጅ ዘመድ ይገናኛል። በአጠቃላይ በዓላት ማህበራዊ ሕይወትን ያጠናክራሉ።

በዓላት የየራሳቸው ባህላዊና ሃይማኖታዊ ይዘት አላቸው። ከመስቀል በዓል የማስታውሰው የሽምግልና ሥነ ሥርዓት ነው።

በአካባቢ አወዛጋቢ ነገር ሲያጋጥም ችግሩ የሚፈታው በሽማግሌ ነው። የተጣላ ሰው የሚታረቀው በሽማግሌ ነው። ለመስቀል ደግሞ እርቅ የግድ ነው። መስቀል በ 17 ይሁን እንጂ፤ የመስቀል በዓል ግን እንደየአካባቢው ባህል እስከ 20 ምናምን ሁሉ ይቆያል። በቡድን የሚከበርባቸው አካባቢዎች ይኖራሉ። ይህ የመስቀል በዓል እንዲህ ጎረቤት ተሰባስቦ መከበሩ አንድ ልዩ ባህሪ እንዲኖረው አድርጎታል።

የመስቀል በዓል የቤት ውስጥ በዓል አይደለም፤ ጎረቤት ተሰባስቦ ሜዳ ላይ በጋራ የሚከበር በዓል ነው። በዚህ በዓል ውስጥ ታዲያ አንድ የማውቀው ባህል የመስቀል በዓል በመጣ ቁጥር ትዝ ይለኛል። ይሄውም በመስቀል ሰሞን ሽማግሌዎች በእርቅ ሥራ የሚጠመዱት ነው። ምንም አይነት ጠብ ይሁን በአካባቢ የተቀያየመ ሰው ካለ ለመስቀል በዓል የግድ መታረቅ አለበት። የተኮራረፉ ሰዎች እያሉ በዓሉ በፍጹም ሊከበር አይችልም። እዚህ ላይ በጣም የምታስደስተኝ ሽማግሌዎች የሚጠቀሟት የማግባቢያ ስልት ናት። በእርቅ የድርድር ሥርዓቱ ውስጥ ከተደራዳሪዎች አንዱ ወይም ሁለቱም ለመታረቅ ፈቃደኛ ካልሆኑ ሽማግሌዎች እንዲህ ይላሉ።

‹‹በሉ እንግዲያውስ በዓሉ ይቅርላችሁ! እኛንም የእንጨት ሽበት አድርጋችሁናል። የዘንድሮን በዓል እንግዲህ የሰው መሳቂያ አድርጋችሁን እናሳልፈው። ‹በአካባቢው ሽማግሌ እንኳን የለም እንዴ!› እየተባልን እንሰደብ። እግዜር ዓመት ዓመቱ አድርሶ ለዚህ ያበቃንን በዓል መብራት ሲወጣ እኛ በእናንተ የተነሳ እንተወው…›› እያሉ ሽማግሌዎች ሲፈርዱ ከተደራዳሪዎች ደግሞ ‹‹እናንተ ለምን ትተውታላችሁ? እናንተ ደምሩ!›› በማለት ሁለቱም የተኳረፉት ሰዎች ‹‹እኔ እቀራለሁ እሱ አብሯችሁ ይደምር፤ እኔ እቀራለሁ እሱ አብሯችሁ ይደምር›› ይባባላሉ። አሁንም ግን ሽማግሌዎች አይበገሩም። ጭራሽ የምጸት ሳቅ እየሳቁ ‹‹የኛ ባልንጀሮች የደም እርቅ ያስታርቃሉ ‹ጎረቤት ማስታረቅ ያልቻሉ› እየተባልን ደግሞ እዚህ ደመራ ላይ ልንታይ?›› እያሉ ተራ በተራ ‹‹እኔማ የዚያን ዕለት እዚህ አካባቢ አልታይም፤ እኔም አልታይም›› እያሉ ተደራዳሪዎችን ያስፈራሯቸዋል።

የዚህን ጊዜ እንግዲህ የሚታረቁት ሰዎች የግድ መታረቅ እንዳለባቸው ያምናሉ። እርቁን እምቢ ቢሉ እንደ ጀግና ሳይሆን የሚታዩት እንደ ባለጌ ነው። በባህሉ ውስጥ ከሽማግሌ ቃል መውጣት ነውር ነው። በዓሉን ጎረቤትን አስከፍቶ መዋል በአካባቢው ያስተዛዝባል፣ በዕድርም ሆነ በሌሎች ማህበራዊ ግንኙነቶች ላይ ‹‹እሱ ደግሞ ባለጌ›› ያሰኛል። ምክንያቱም ሽማግሌ ብዙ ነገር ነው። ነገ በራሱ ላይ የሆነ ነገር ቢደርስ ከሽማግሌ አያልፍምና የሽማግሌን ሀሳብ መቀበል የግድ ነው። በዚህም ምክንያት ለመስቀል በዓል ክረምቱን ሙሉ ተኮራርፎ የከረመ ሁሉ ይታረቃል።

የእርቅ ሁኔታው እንደየቅሬታቸው ይለያያል። ቀላል የሚባል መቀያየም ከሆነ ከጎረቤት ሽማግሌዎች አያልፍም፤ ብዙ የተነጋገሩና የመደባደብ ደረጃ ላይ የደረሰ ከሆነ ደግሞ ራቅ ካለ አካባቢ ሽማግሌ ይመረጣል። የሚመረጡ ሽማግሌዎችም ብዙ የማስታረቅ ልምድ ያላቸውና የሃይማኖት አባቶች ናቸው። በዚህ በማስታረቅ ሥራ ውስጥ የሚታወቁ የአካባቢው ሽማግሌዎች ዛሬም አሉ። እስከሩቅ አካባቢ ድረስ ሰዎችን ለማስታረቅ ይሄዳሉ።

እነዚህ ሽማግሌዎች የማስታረቅ ጥበባቸው ለብዙ ሽማግሌዎች አርዓያ ሆኗል። ሽማግሌዎቹ በአዘቦት ቀን እንኳን አብረዋቸው ሲጫወቱ ብዙ ነገር የሚያስተምሩ ናቸው። ብዙ ጊዜ ነገራቸውን ከሆነ ታሪክ ጋር አያይዘው ነው የሚያወሩት። በእርቅ ጊዜም እንደዚሁ ናቸው። ነገራቸውን በሆነ ገጠመኝ ወይም በቆየ ታሪክ እያጣቀሱ የመጋጨትና የመኳረፍን ነውርነት ያስረዳሉ። የማስታረቅ ጥበባቸው እንደየታራቂዎች ባህሪ የሚመቻቸውን ስልት እየተጠቀሙ ነው። በእርቅ ውስጥ ሁሉም የሚጠቀሟቸው ዘዴዎች ቢኖሩም አንዳንዶቹ ደግሞ የራሳቸውን ስልትም ይጠቀማሉ። ዋሽቶ ማስታረቅ ከሚለው ይልቅ አሳምኖ ማስታረቅን ይችሉበታል። የሚታረቁት ሰዎች ትልቅ ቅሬታ ውስጥ የገቡ ቢሆን እንኳን በሰው ልጅ ውስጥ የሚያጋጥም መሆኑን ያሳምናሉ፤ ከዚህ የከፋ ችግር ያጋጠማቸው ሰዎች እንደነበሩና ታርቀው እንደተጋቡ ወይም በሌላ ወዳጅነት ተሳስረው ትልቅ ነገር ላይ እንደደረሱ የሚያሳይ ታሪክ ይነግሯቸዋል። ባይታረቁ ግን ልጆቻቸው ነገ በሰላም እንደማይኖሩ፣ ይባስ ብሎም ሊገዳደሉ እንደሚችሉ ይነግሯቸዋል።

እንግዲህ የመስቀል በዓል ከሃይማኖታዊ ይዘቱ በላይ እንዲህ አይነት የባህላዊና ማህበራዊ እሴት ይዘትም አለው። በተለይ የተጣሉት ሰዎች ቤተሰቦች በዓሉን በጉጉት ይጠብቁታል፤ ምክንያቱም ቤተሰቦቻቸው ይታረቁላቸዋል። የሚጣሉት ሁለት የጎረቤት አባወራዎች ሊሆኑ ይችላሉ፤ ሁለቱ አባቶች ሲኮራረፉ ልጆች ከብት ጥበቃ አብረው ነው የሚውሉት፤ ግን አባቶቻቸውን እየፈሩ አንዳቸው ሌላኛው ቤት አይሄዱም፤ በዚህ ውስጥ እንግዲህ የአባቶች መታረቅ ለልጆች የሚፈጥረውን ደስታ አስቡት!

ከዚህ አንድ ነገር እንረዳለን፤ የአዋቂዎች አዋቂ አለመሆን በልጆች ላይ የሚፈጥረውን መጥፎ ጫና! ይሄ ነገር ለጎረቤት ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገር ላለው ሁኔታም ትልቅ ትምህርት የሚሆነን ነበር። የተማርን ነን ያሉ ሰዎች በራስ ቡድን ወዳድነት ብቻ ተጠምደው ዘረኝነትን ሲሰብኩ ይውላሉ፤ እነዚህ ተፅዕኖ ፈጣሪ ናቸው የተባሉ ሰዎች ይህን ሲያደርጉ ሌላው ይከተላል ማለት ነው።

እንዲህ ነው እንግዲህ የሽማግሌ ሃይል። የአካባቢው ማህበረሰብ እምነት የሚጥልባቸው። ገበሬዎች የሚጠቀሙት አንድ ሥነ ቃል እንዲህ ይላል።

እንበለውና የመጣው ይምጣ!

ከሽማግሌ ከእርቅም አይወጣ

የዚህ ሥነ ቃል ትርጉም እንበለው፣ እንደባደብ ማለት አይደለም። የሥነ ቃሉ ትልቁ መልዕክት የትኛውም ነገር ከሽማግሌ እንደማይወጣ ነው። በምሳሌያዊ ንግግሮቻችን እንኳን ሽማግሌ የሃሳብ ሃይል እንዳለው የሚያሳዩ ናቸው።

ሽማግሌ በምክሩ አርበኛ በሰናድሩ፣ ሽማግሌ ሳለ ምክር አይጠፋም ጎረምሳ ሳለ ላም አይነዳም፣ ሽማግሌ ካለበት ነገር አይናቅም፣ ሽማግሌ ካልሞተ ስንዴ ካልመረተ፣ ሽማግሌ ይገላግላል የተጠቃ አቤት ይላል፣ ሽማግሌን ከምክር ከመለየት ከምግብ መለየት… የሚሉት ይገኙበታል። ክብር ለሽማግሌዎች!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን መስከረም 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You