የወጣት ብሔራዊ ቡድኑ ለሴካፋ ዋንጫ ዝግጅቱን አጠናክሮ ቀጥሏል

የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ (ሴካፋ) የወንዶች ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ ከመጪው ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ በታንዛኒያ ዳሬሰላም ከተማ አዘጋጅነት ይካሄዳል። ይህ ውድድር በቀጣዩ የፈረንጆቹ ዓመት ለሚካሄደው ከ20 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ዞኑን ወክለው የሚካፈሉ ሁለት ሀገራትን ለመለየት እንደ ማጣሪያ የሚያገለግልም ነው። የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድንም ለሴካፋ ዞን ከ20 ዓመት በታች አፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ውድድር ዝግጅት በማድረግ ላይ ይገኛል።

በውድድሩ ተሳታፊነታቸውን ያረጋገጡት የዘጠኝ ሀገራት ብሔራዊ ቡድኖች በሁለት ተከፍለው የሚፎካከሩ ይሆናል። በመጀመሪያው ምድብ አዘጋጇ ታንዛኒያ ከሱዳን፣ ርዋንዳ፣ ጅቡቲ እና ኬንያ ጋር የተደለደሉ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ በምትገኝበት ቀጣዩ ምድብ ደግሞ ቻምፒዮና ዩጋንዳ፣ ደቡብ ሱዳን እና ብሩንዲ ይገኛሉ። ለሁለት ሳምንታት ያህል የሚደረገው ውድድር መስከረም 26 ጥቅምት 10/2017 ዓ/ም የሚቆይም ይሆናል፡፡

በዚህ ውድድር የሚካፈለውን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለማዘጋጀትም በዋና አሠልጣኝነት ስዩም ከበደ፣ በረዳት አሠልጣኝነት ደግሞ ዐቢይ ካሳሁን እንዲሁም አምሳሉ እስመለዓለም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከቀናት በፊት መሾማቸው ይታወቃል። ጥሪ የተደረገላቸው ተጫዋቾችም ከመስከረም 07/2017 ዓ/ም አንስቶ በመሰባሰብ ወደ ዝግጅት ገብተዋል። መቀመጫውን ካሌብ ሆቴል ያደረገው የኢትዮጵያ ወጣት ቡድን በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ዝግጅቱን አጠናክሮ በማከናወን ላይም ይገኛል።

ባለፉት የዝግጅት ቀናት ጥሪ ተደርጎላቸው ከቡድኑ ጋር ሲሠሩ የቆዩ አራት ተጫዋቾች እንዲሁም ሶስት ግብ ጠባቂዎች የተቀነሱ ሲሆን፤ በምትካቸው ሌሎች አራት ተጫዋቾች ማለትም አለልኝ ሙሉነህ እና ዳዊት ካሳው ከስሪ ፖይንት አካዳሚ፣ መድህን ተክሉ ከወልቂጤ ከተማ እንዲሁም ይበልጣል ኤልያስ ከስፔኑ ቢ ዋን አካዳሚ ስብስቡን ተቀላቅለው ልምምዳቸውን እያከናወኑ መሆናቸውም ታውቋል። በመጀመሪያው ጥሪ ላይ ያልተገኙት የድሬዳዋ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ተጫዋቾችም ወደ ዝግጅት ገብተዋል። በዚህም መሠረት የመጨረሻው የቡድኑ ስብስብ በመጪው እሁድ መስከረም 19/2017 ዓ/ም የሚታወቅ መሆኑን ፌዴሬሽኑ ጠቁማል።

ዋና አሠልጣኝ ስዩም ከበደ በሥራቸው ካሉ ወጣት አሠልጣኞች ጋር በመሆን ለተጫዋቾች የመጀመሪያ ጥሪ ማድረጋቸውን በማስታወስ፣ ተጫዋቾቹም ከ20 ዓመት በታች ሊግ እንዲሁም ባላቸው ብቃት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጫወት ዕድል ያገኙ ወጣቶች ሲሆኑ፤ ኢትዮጵያን ለመወከል ይመጥናል የሚባል ቡድን ለመመስረት ተሰባስበዋል። በመጀመሪያው ጥሪም ከ40ዎቹ 33 የሚሆኑት ተገኝተዋል። ባለው አጭር የዝግጅት ጊዜም ጠንካራ ቡድን ይዞ ውድድሩ ላይ ለመቅረብ እንዲሁም ዋናውን ብሄራዊ ቡድን ሊረከቡ የሚችሉ ወጣቶች በመሆናቸው ይህንን ያማከለ ዝግጅት በመደረግ ላይ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

ውድድሩ እአአ ከ1971 አንስቶ በመካሄድ 53 ዓመታትን ያስቆጥር እንጂ በወጥነት ከመካሄድ ይልቅ በተለያዩ ጊዜያት እየተደረገ አሁን ካለበት ደርሷል። በዚህ ውድድር ዩጋንዳ ለ5 ጊዜያት ዋንጫውን በማንሳት ስኬታማ ሀገር ስትሆን ከሁለት ዓመት በፊትም አሸናፊ መሆኗ የሚታወስ ነው። ኢትዮጵያ በበኩሏ እአአ በ1995፣ 1996 እና 2005 ለሶስት ጊዜያት ቻምፒዮን ለመሆን ችላለች።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ዓርብ መስከረም 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You