አስተሳሰብን በአዲስ የመቀየር ጥበብ

የአዕምሮን እንደ አዲስ የማስተካከል ጉዳይ በጣም ወሳኝ ነው። ፈረንጆቹ ጋር ደግሞ ይህ በጣም የተለመደ ሀሳብ ነው። እንደውም /reprogram your mind/ or /reprogram your sub conscious mind/ እያሉ የተለያዩ ሀሳቦችን ያነሳሉ። ለመፍትሄዎችም የተለያዩ መፅሃፎችን ይፅፋሉ። ሴሚናሮችን ያዘጋጃሉ። ቪዲዮዎችን ይሰራሉ። በዚህም ሰዎች አዕምሯቸውን እንደ አዲስ ይቀይራሉ።

ለምን መሰላችሁ? ኑሮ ያደክመናል። ሕይወት ተደጋጋሚና አሰልቺ ትሆናለች። አዕምሯችን ብዙ መጥፎ ነገሮችን ይሸከማል። ቁጭት፣ ጭንቀት፣ ፍርሃት አለብን። በቃ! መጥፎ ስሜቶች በውስጣችን አሉ። ታዲያ እነዚህ ስሜቶች ከአእምሯችን ውስጥ መራገፍ አለባቸው። እንደ ልጅ ጥርት ያለ ሃሳብ ማሰብ አለብን። ንፁህ አዕምሮ ያስፈልገናል። አዕምሯችንን እንደ አዲስ ለማስተካከል ታዲያ ምን ማድረግ አለብን?

የመጀመሪያው አዕምሮህ እንዴት እንደሚሰራ ማወቅ አለብህ። ለምሳሌ ስልክ ነክቶ ለማያውቅ ሰው ዘመኑ የደረሰበትን የመጨረሻውን የስልክ ምርት አይፎን ሰርቲን ፕሮ ማክስ ገዝተህ ብትሰጠው ‹‹እንዴት የሚያምር የከበረ ድንጋይ ነው? ደሞ እኮ ልስላሴው›› ብሎ ቤቱ እንደተራ እቃ ሊያስቀምጠው ይችላል። ለምን አያውቀውማ! አዕምሮህ ለምን እንደሚሰራና እንዴት እንደሚሰራ ካላወክ አጠቃቀሙን አታውቅበትም።

አንዳንዴ አእምሯችን እንዴት እንደሚሰራ ስለማናውቅ ስንጨነቅ መድሃኒት እንውጣለን። ትንሽ ነገር ሲገጥመን ‹‹ምነው ፈጣሪዬ ምን አደረኩህ›› እንላለን። ትንሽ ነገር ሲፈጠርና መጥፎ ስሜት ሲሰማን ፈጣሪን እናማርራለን። በቃኝ እንላለን። ተስፋ እንቆርጣለን። እኔ እኮ አበቃልኝ እንላለን። ሕይወትን ትርጉም እናጣበታለን። ለምን? የአእምሯችን አሰራር አልገባንም። አዕምሯችን ነው የተጎዳው። እኛ ግን በአካል ሁሉ ነገራችን ይጎዳል።

አያችሁ የአእምሯችን አሰራር በጣም ወሳኝ ነው። ስለዚህ አንተ ሕይወትህን እየጠላሃት ያለኸው ምን አልባት አዕምሮህ እንዴት እንደሚሰራ ስላላወክ ነው። ከዚህ በኋላ ግን መጨነቅ ማቆም አለብህ። መፍራት ታቆማለህ። መጥፎ ስሜቶችና ሃሳቦች አዕምሮህን አይቆጣጠሩትም። አዕምሮህ እንዴት እንደሚሰራ ማወቅ ብቻ ነው ካንተ የሚጠበቀው።

ሁለት አይነት የአእምሮ ክፍሎች አሉ። ንቁ /con­scious/ እና ድብቅ /sub-conscious/ ይባላሉ። ንቁ /conscious የአእምሮ ክፍል በጣም ንቃት ውስጥ ሆኖ ነው የሚያገለግለው። ለምሳሌ አንድ ነገር አዲስ ከሆነ ንቁ ሆነን ነው የምንሰማው። አዲስ ነገር ስንለምድ ነቃ ብለን ነው የምናዳምጠው። ለመጀመሪያ ግዜ ምግብ ያበሰላችሁ ግዜ እያንዳንዱን ሂደት በንቃት ነው የምንከታተለው። ኪ ቦርድ ለመጀመሪያ ግዜ ስንተይብ (ታይፕ ስናደርግ) እያንዳንዷን ፊደል እየመረጥን ነው።

ብዙ ግዜ ግን በቀን ውስጥ አዲስ ነገር የምንለምደው ለጥቂት ሰዓታት ነው። ብዙ ሰዓት ንቁ አይደለንም። ስለዚህ ንቁ /conscious/ የሚባለውን የአእምሮ ክፍል ብዙ ግዜ አንጠቀምበትም። ስለዚህ በጣም ወሳኙ ሁለተኛውና ድብቅ /sub-conscious/ የሚባለው የአእምሮ ክፍል ነው። ይህ የአእምሮ ክፍል ደጋግመን የምናደርጋቸውን ነገሮች የሚቆጣጠር የአእምሮ ክፍል ነው። በሰውነታችን ውስጥ ከሚካሄዱ እያንዳንዱ ሂደቶች ጀምሮ ለምሳሌ የምግብ ልመትና መተንፈስን ጨምሮ ማንኛውንም የሰውነት ስርአቶችን ይቆጣጠራል።

ይህን ብቻ ሳይሆን ልማዶቻችንን፣ ደጋግምን የምናደርጋቸውን ነገሮች በሙሉ ድብቅ /sub-conscious/ ነው የሚቆጣጠረው። ለምሳሌ የኮምፒዩተር ኪቦርድ ላይ ስትፅፍ የሆነ ሰዓት ላይ መልመድ ትጀምራለህ። ስለዚህ ይህ ድብቅ /sub-conscious/ የሚባለው የአእምሮ ክፍል ማስታወሻዎችን ይመዘግባል። ስለሆነም በኪቦርዱ ላይ ኤ የቱ ጋር እንደሆ ታውቃለህ። ወዲያው ሌሎቹንም ፊደሎች ትነካካለህ። ብዙ ነገሮች ላይ ፈጣን የምትሆነው ድብቁ የአእምሮ ክፍልህ ስለለመደው ነው። ስለዚህ ድብቁ የአእምሮ ክፍል ደጋግመን ያደረግነውን፣ ተደጋግሞ የሰማነውን፣ የተነገረንን፣ ደጋግመን ያየነውን ሕይወታችን ላይ መዝግቦ ያስቀራል። ዋናው የአእምሮ ማስታወሻ ክፍል ነው። በእሱ መንገድ እንድንጓዝ ያደርገናል።

ለዛ ነው አንዳንድ ልጅ በልጅነቱ አትችልም እየተባለ ተደጋግሞ ከተነገረው ትንሽ ከፍ ሲል አልችልም የሚል ስሜት ይሰማዋል። ስለዚህ አይሞክርም። አዲስ ነገር ላይ አይደፍርም። አንዳንድ ልጅ በልጅነቱ እንተ ጎበዝ ነህ ! ጀግና ነህ እየተባለ ያደገ ልጅ ደግሞ ደፈር ይላል። ብዙ ነገር ይሞክራል። ደጋግሞ የሰማውን በሕይወቱ ላይ ይገልጠዋል። በልጅነት ግዜ ብቻ ሳይሆን ከፍ እያልን ስንሄድ አብረናቸው የምንውላቸው ጓደኛዎችን የሚነግሩን ነገሮች በእኛ ድብቁ የአእምሮ ክፍል ውስጥ ተመዝግበው ይቀራሉ። ድብቁ የአእምሮ ክፍል አብዛኛውን የሕይወታችን ክፍል ይወስናል።

ድብቁ /sub-conscious/ የአእምሮ ክፍል አንድ የተለየ ባህሪ አለው። ሞኝ ነው። ደጋግሞ የተነገረውን ነገር ያስቀራል። መቼም ሞኝ ታውቃላችሁ። የሆነ ነገር ካደረጋችሁት ‹‹እሱ እኮ እንዲህ አድርጎኝ›› ይላል። ቂም ነው የሚይዝባችሁ። ልክ ‹‹ሞኝና ወረቀት የያዘውን አይለቅም›› እንደሚባለው። ሞኝ ውለታ ከዋላችሁለትም የሆነ ቀን አስታውሶ ‹‹እሱ እኮ እንደዚህ አድርጎልኝ›› ይላችኋል። በቃ! ድብቁ የአእምሮ ክፍል ልክ እንደሞኝ የሰበሰበውን፣ ደጋግሞ የሰማውን መዝግቦ ያስቀራል።

እንግዲህ ለዚያ ነው አንተም የምትጨነቀው። አየህ! የሚያስጨንቁ ጉዳዮችን ደጋግመህ ትሰማለህ። ስለዚህ በሕይወትህ ትጨነቃለህ። የዘራኸውን ታጭዳለህ። የምትዘራው መጥፎ ጭንቀት፣ መጥፎ ሀሳብ፣ መጥፎ ነገር ከሆነ እሱ በሕይወትህ ይገለጣል። አሁንም የምትጨነቀው ለዚያ ነው። ደስ የሚለው ነገር ግን ይህ ድብቁ የአእምሮ ክፍልህን መቀየር ትችላለህ። እንዴት አድርገህ? እየደጋገምክ ለአእምሮህ ጥሩ ጥሩ ነገሮችን በመንገር። አዳዲስ ነገሮችን በአእምሮህ ውስጥ በመዝራት።

አይምሯችን እንደመሬት ነው። የሚዘራበትን መምረጥ አይችልም። መሬት አፍ አውጥቶ ስንዴ ዝሩብኝ አይልም። እኛ ሰዎች ነን መሬቱ ላይ የምንዘራው። ግን ደግሞ ስንዴ ፈልገን ስንዴ ከዘራን መሬቱ ስንዴ ያበቅላል። አይምሮህ አንተ የምትፈልገውን ነገር ነው የምትጭንበት። የምትሰማው ነገር ወሳኝ ነው። ጥሩ ነገር ከሰማህ በአእምሮህ ውስጥ ጥሩ ነገር እየዘራህ ነው።

አየህ! ከዚህ በኋላ አይምሮህን አዲስ ማድረግ አይደል ዓላማህ? ስለዚህ አይምሮህን የሚያስተካክል ነገር መስማት ትጀምራለህ። የምትሰማው ነገር መንፈሳዊ ነገር ሊሆን ይችላል። መልካም ነገር፣ ተስፋ የሚሰጥ ነገር ሊሆንም ይችላል። ከዚህ ውጪ ግን ሌላ ነገር አትሰማም። ሌላ ነገር አታደርግም። ትጠነቀቃለህ። ለምትዘራው ነገር ተጠንቀቅ። የአይምሮ በርህን ጠብቅ። አየህ! ከዚህ በኋላ መጥፎ ዜና መስማት የለብህም። ለምን? መጥፎ እንድታስብ ያደርግሃላ።

በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በትዝታ መኖር ማቆም ይኖርብሃል። ምን አልባት ስለትናንት እየደጋገምክ ታስብ ይሆናል። ትላንት ስለደረሰብህ መጥፎ ነገር፣ ስለገጠመህ ቁጭት፣ በጣም የሚያስቆጩህን አጋጣሚዎች ታስባቸዋለህ። ጭንቀትህ ስለትናንት ነው። ስለዚህ ትላንትን በዛሬ ውስጥ እየኖርክ ነው ማለት ነው። አይምሮህ ደጋግመህ የምታስበውን ነው የሚሰጥህ። ትላንትናን ካሰብክ ትላንትናን ዛሬም ትደግመዋለህ። ሕይወት ተደጋጋሚ ትሆናለች። አሰልቺ ትሆናለች። የትናንቱን ዛሬም ትኖረዋለህ።

ታዲያ ምን ይሻላል? ነገን በዛሬ ውስጥ መኖር መጀመር አለብህ። ነገን እያሰብክ ዛሬ ላይ ጠንክር። ነገ በሕይወትህ ይገለጣል። አየህ! መልካም ነገሮችን ደጋግመህ ስታስብ መልካም ነገር በአይምሮህ ውስጥ እየዘራህ ስለሆነ መልካም ነገር በሕይወትህ ትገልጣለህ። የቀንም የሌሊትም ሕልመኛ መሆን አለብህ። የቀን ሕልመኞች መሆን በራሱ ሕይወታችንን ይቀይረዋል። ቀን ላይ ዝም ብለን ስንቀመጥ መልካም ነገሮችን ብናስብ ‹‹እንዲህ ባደርግ፣ ይሄን ባሳካ፣ ይሄ ቢኖረኝ›› ብንል አይምሯችንን መልካም ነገር እየመገብነው ነው።

ድብቁ የአእምሮ ክፍል አንተ ተኝተህም ይለፋል። አንተ የምትፈልገውን ነገር ለመስጠት የማያደርገው፤ የማይቆፍረው ጉድጓድ የለም። አንዳንዴ ቁጭ ስትሉ ከሰው ጋር እያወራችሁ የሆነ ሃሳብ ብልጭ ብሎላችሁ አያውቅም? እርግጠኛ ነኝ ያውቃል። ምክንያቱም ድብቁ አይምሮ ደጋግሞ እያሰበ ነበር። አንተ ሌላ ነገር ውስጥም ብትሆን አይምሮህ መልሱን ሲያገኝ መስራት ይጀምራል።

አየህ! ስለነገ ሕልምህና መልካም ነገር ካሰብክ የሆነ ሰዓት ላይ በሕይወትህ ድብቁ የአእምሮህ ክፍል ይገልጠዋል። ፈጣሪህም ተአምሩን የሚያሳይህ በድብቁ የአይምሮ ክፍልህ ነው። ታዲያ የቀን ሕልመኛ ብቻ ሳይሆን የሌሊትም ሕልመኛ መሆን አለብህ። ልትተኛ ስትል በጣም የምትፈልገውን ነገር አጥብቀህ እያሰብክ መተኛት አለብህ። እውቁ የሳይንስ ሊቅ አልበርት አንስታይን ‹‹ልተኛ ስል በጣም ልፈታው የምፈልገውን ሳይንሳዊ ችግር እያሰብኩት እተኛለሁ። እኔ ግን የማስበው ፈትቼዋለሁ ብዬ ነው። ጠዋት ስነሳ ግን ያን ችግር ፈትቼው፤ መፍትሄውንም አግኝቼው እነቃለሁ›› ይላል።

ስለዚህ የትኛውንም የዚህ ዓለም ችግር እንደፈታኸው አስበህ ምትኖር ከሆነ የሆነ ሰዓት መፍትሄው በሕይወትህ ይገለጣል። ድብቁ የአይምሮ ክፍል ስራውም ይህ ነወ። ለዛ ነው የቀንም የሌሊትም ሕልመኛ መሆን ያለብህ።

በሶስተኛ ደረጃ ውስጥህ ነው ወሳኙ። ወዳጄ! ውጫዊ ነገሮችና ውጫዊ ሁኔታዎች ያንተን ውስጣዊ ሰላምና ደስታ ሊወስኑት አይገባም። መፍቀድ የለብህም። ምክንያቱም ለምሳሌ ሰዎች ሲያደንቁህ ደስ የሚልህ ከሆነ፣ ፊት ሲነሱህ፤ የልባቸውን አውጥተው መጥፎ ነገር ሲናገሩህ አንተ የሚከፋህ ከሆነ ያንተን ውስጥ እየተቆጣጠረው ያለው ውጫዊ ዓለም ነው። ዓለም ስትገላበጥ ውስጥህ መገላበጥ የለበትም። ከውጪ ወደ ውስጥ መኖር ማቆም አለብህ። ከውስጥ ነው ወደውጪ መኖር ያለብህ።

ውስጥህ ሰላምና ደስታ ካለ ዓለም አብራህ ትስቃለች። አብራህ ትደምቃለች። ሕይወትህን የሚወስነው ውስጣዊ ነገር ነው። አየህ! መለወጥና መቀየር የምትጀምረው ከውስጥ ወደ ውጪ መኖር ስትጀምር ነው። አለበለዚያ ይች ዓለም አትሞላም። ስለዚህ ዓለም በተቀየረች ቁጥር ውስጥህ የሚቀየር ከሆነ መቼም ደስተኛ አትሆንም። ሕይወትህ ላይ ጭንቀቶችና መጥፎ ሀሳቦች የሚቆጣጠሩህ ውጫዊ ነገሮችን እያየህ ነው።

አየህ! እንደዛ እንዲሆን መፍቀድ የለብህም። አንተ ሁልግዜም የሰው ልጅ ነኝ ብለህ ማመን አለብህ። ‹‹እኔ ሁልግዜም ደስተኛ ነኝ፤ በፈጣሪዬም ደስተኛ ነኝ፤ ጤና ሰጥቶኛል›› በል። ያለህን እያየህ በውስጥህ እርካታ ሊኖርህ ይገባል። ያኔ ውጪህም ያምራል።

በአራተኛ ደረጃ አካባቢህን ምረጥ። አንዳንዴ አንተ በጣም አቅም አለህ። በጣም ትችላለህ። ሕይወትህ ላይ የጎደለህ ነገር የለም። ፈጣሪህ የሰጠህ ብዙ ችሎታዎች አሉህ። ብቃትህን እንዳታወጣው ያደረገህ በአካባቢህ ያሉ ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ። አካባቢህም ሊሆን ይችላል። ታዲያ አይምሮህን እንደ አዲስ ማስተካከል የምትፈልግ ከሆነ መቆረጥ ያለብትን ቁረጥ። መቀጠል ያለበት ነገር ካለ ደግሞ ቀጥል። ከጥሩ ሰዎች ጋር ዋል።

አካባቢህ አንተን ይወስንሃል። ለምሳሌ ማድቤትህ ውስጥ ምግብ እያበሰልክ አንድ ሰው መጥቶ ቆሻሻ ቢደፋብህ ትተናነቀዋለህ። ለምን? ምግቡ ሆድህ ውስጥ ስለሚገባ ለምትበላው ታስባለህ። አይምሮህ ውስጥ ለሚገባው ነገርም ማሰብ መጀመር አለብህ። አይምሮህ ውስጥ መጥፎ ነገር፣ ቆሻሻ ለሚበትኑ ዜናዎች፣ ሃሳቦች፣ መጥፎ ሰዎች፣ እንደማትችል ለሚነግሩህ ሰዎች ቦታ መስጠት የለብህም።

አካባቢህን በደምብ አጥናው። ላንተ የሚመጥን ከሆነ አይምሮህ እንደ አዲስ መሰራት ይጀምራል። የምትሰማው ነገር በጣም ወሳኝ ነው። ሕይወትህ ላይ የሚገለጠውም ደጋግመህ የሰማኸው፣ ያደረከው፣ የምትውለው ቦታ ነው። የዛሬ አምስት ዓመት ያደረካቸው ነገሮች አሁን ያለህበትን ወስነዋል። የዛሬ አምስት ዓመት የምትደርስበትን የሚወስኑት ደግሞ አሁን የምታደርጋቸው ነገሮች ናቸው። ስለዚህ አካባህን ምረጥ።

አምስተኛውና የመጨረሻው ደረጃ የመደጋገም ኃይል ሲሆን ይህም ወሳኝ ነው። ከባድ ነገሮች ቀላል የሚሆኑት ከደጋገምናቸው ብቻ ነው። አንድን ነገር ደጋግመን ስናደርገው አይምሯችን ያንን ነገር ቀለል አድርጎ ለመስራት የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም። በአይምሯችን እየደጋገምን አንድን ነገር ስንሰራ በቀላሉ ነገሩን ዕንድንከውን ጥርጊያ መንገድ ያመቻቻል።

ስለዚህ የመደጋገም ኃይል ወደሕይወታችን እንዲገባ ማዳበር አለብን። አንተ የምትደጋግመውን ነው ሕይወትህ ላይ ምታገኘው። ደጋግመህ የምትሰማውና የምታየው ነገር በጣም ወሳኝ ነው። ስለዚህ በእጅ በእግርህ ብለህ አይምሮ ማሰብ ያለበትን እንዲያስብ አድርግ። እየደጋገምክ ለአይምሮህ ጥሩ ነገር ንገረው።

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን መስከረም 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You