ስነ ተዋልዶ ጤና-ከተደራሽነት ወደ ጥራት

የአፍላ ወጣትነት እድሜ የሕብረተሰቡን የቀጣይ ትውልድ ማፍራት ሁኔታ የሚወስን ነው። በተለይ ደግሞ እንደኢትዮጵያ ባሉ የወጣት ቁጥራቸው ከጠቅላላው ሕዝብ አንፃር ከፍተኛ የሆኑባቸው ሀገራት ለወጣቶች አስቻይ ሁኔታዎች ካልተፈጠሩ፣ ተሳታፊነታቸውንና ተጠቃሚነታቸውን ካልተረጋገጠ ለሚታሰበው ሀገራዊ ለውጥ እንቅፋት ይሆናል። ስለዚህ በአፍላ ወጣቶችና በወጣቶች ዙሪያ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ መስራት አስፈላጊ መሆኑ ሁሉንም ያስማማል።

ወጣቶች አካላዊ፣ ስሜታዊ፣ አእምሯዊና ማሕበራዊ ለውጦች የሚከሰትበት የእድሜ ክልል ላይ የሚገኙ በመሆናቸው የሕይወታቸው ሂደትና ኡደት ልዩ ትኩረት የሚሻ ነው። ምክንያቱም በዚህ እድሜ ክልል በሚፈጠሩ ስሜታዊነት፣ የአቻ ግፊቶች፣ የመረጃ እጥረት የተነሳ አፍላ ወጣቶችና ወጣቶች ለጤናና ለተለያዩ ማሕበራዊ ችግሮች ተጋላጭ ይሆናሉ። የስነ ተዋልዶ ጤና ችግር ደግሞ ለኤች አይ ቪ ኤድስ ሌሎች የአባላዘር በሽታዎች፣ ላልተፈለገ እርግዝና፣ ለጽንስ ማቋረጥ፣ ለአደንዛዥ እፆች፣ ለአልኮል መጠጦች፣ ለአእምሮ ጤና እክል፣ ለአካል ጉዳትና ለሌሎችም ችግሮች ተጋላጭ ያደርጋቸዋል።

ስለዚህ አፍላ እድሜ ላይ ያሉ ታዳጊዎችና ወጣቶች ጤናቸው በተሟላ መልኩ እንዲጠበቅ ሁሉም ክትትልና ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል። ጤናቸው አደጋ ላይ እንዳይወድቅ እርስ በርሳቸው ተቀራርበው የሚወያዩበትና ራሳቸው የመፍትሄ አካል የሚሆኑበት መንገድ መዘጋጀት ይኖርበታል። ወጣቶች በራሳቸው የእድሜ ክልል ውስጥ የራሳቸውን ችግር ሲነጋገሩ ይበልጥ ግንዛቤ ይኖራቸዋል። ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ ነው እስካሁን ድረስ የወጣቶችና አፍላ ወጣቶች ጉባኤ ሲካሄድ የቆየው። አምስተኛው የወጣቶችና አፍላ ወጣቶች ጉባኤም ‹‹ተደራሽነትና ጥራት፤ ምላሽ ሰጪ የጤና ስርዓት ለሁሉም አፍላ ወጣቶች›› በሚል መሪ ቃል በቅርቡ መካሄዱ ይታወሳል።

ወጣት ቶፊቅ እስማኤል ሃኪም በጤና ሚኒስቴር የአፍላ ወጣቶችና ወጣቶች ጤና ካውንስል ፕሬዚዳንት ነው። እርሱ እንደሚለው ካወንስሉ እያከናወናቸው ከሚገኙ ተግባራት ውስጥ አንዱ በየዓመቱ በሚዘጋጀው የአፍላ ወጣቶችና ወጣቶች ጤና ጉባኤ ላይ ወጣቶችና አፍላ ወጣቶች እንዲሳተፉ በማድረግ በስነ ተዋልዶ ጤናና እነሱን በሚመለከቱ ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት እንዲያደርጉ መፍትሄ ሃሳብ እንዲጠቁሙ ማድረግ ነው። በዚህ ጉባኤ ባለፉት አራት ተከታታይ ዓመታት የኢትዮጵያ አፍላ ወጣቶችና ወጣቶች ጤና ጉዳይ ምን ደረጃ ላይ እንዳለ፣ ምን እንደሚያስፈልግና ምን እንደሚያሳስብና በተለይ እንዴት ተደራሽ መሆን እንዳለበት ሲሰራ ቆይቷል።

ዘንድሮ ደግሞ ባለፉት አራት ዓመታት እነዚህን ከማሳካት አንፃር የተሄደበትን ርቀት በመገምገም በወጣቶችና አፍላ ወጣቶች ስነ ተዋልዶ ጤና ጥራትን ለማካተት ታሳቢ ያደረገ ውይይት በጉባኤው ተካሂዷል። እስከዛሬ ድረስ በወጣቶችና አፍላ ወጣቶች ስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት ዙሪያ ተደራሽነት ላይ በስፋት ሲሰራ ቆይቷል። ነገር ግን የስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት ተደራሽነቱ ምን ያህል ጥራት እንደነበረው ቁጭ ብሎ መገምገምና ጥራትን ማካተት አስፈጓል። ለዚህም ነው የዘንድሮው ጉባኤ ትኩረቱን በስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት ጥራት ላይ ትኩረቱን አድርጎ የተካሄደው። በስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት ጥራት በሚፈለገው ልክ ላይኖር ይችላል። ስለዚህ ተጠያቂነትና ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ትልቁ ባለቤት አፍላ ወጣቱና ወጣቱ ነው።

በርካታ ወጣቶች ለጤናና ለተለያዩ ማሕበራዊ ችግሮች ተጋላጭ የሚሆኑት በግንዛቤ እጥረት ምክንያት ነው። ከዚህ አንፃር ካውንስሉ ሚሰራው ነገር ቢኖር በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ለወጣቶችና አፍላ ወጣቶች ግንዛቤ መፍጠር ነው። ግንዛቤ ከመፍጠር ባለፈ ካውንስሉ ከስነ ተዋልዶ ጤና ጋር በተገናኘ አፍላ ወጣቶችና ወጣቶች አገልግሎት የሚያገኙበትን ቦታ ይጠቁማል። የስነ ተዋልዶ ጤና ችግር እንዳያጋጥማቸው አስቀድሞ የመከላከል ስራም ይሰራል። ችግሩን የሚከላከሉበትን ቦታዎች ከመጠቆም ባለፈ በምን አይነት መንገድ ችግሩን መከላከል እንደሚችሉም የሚያሳይበት ስርዓት አለው።

ወጣት ቶፊቅ እንደሚለው ወጣቶች የስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት አሰጣጥ ስርአቱ ጥራት ያስፈልገዋል። ይህን የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል ዘንድሮ በጤና ሚኒስቴር በኩል የተሞከሩ ስራዎች አሉ። ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ላማሻሻል ጥረት ተደርጓል። ሆኖም አሁንም የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራቱን ይበልጥ ማሻሻል ያስፈልጋል። ለአብነት በጤና ተቋማት የሚሰጡ የወጣቶች የጤና አገልግሎቶች አሉ። ነገር ግን አብዛኛዎቹ አገልግሎቶች የሚሰጡት ከሌሎች የጤና አገልግሎቶች ጋር ተደባልቀው ነው። በዚህ ምክንያት ወጣቶች ስለ ስነ ተዋልዶ ጤናና ስለሌሎችም ጤና ነክ ጉዳዮች የማማከር ፍላጎት ኖሯቸው በሃፍረት ምክንያት ወደ ጤና ተቋማት የማይሄዱበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ይህም ከአገልግሎት ጥራት አኳያ ያለውን ጉድለት ያሳያል።

በሌላ በኩል ደግሞ በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እየበዙ መጥተዋል። በነዚህ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ በርካታ ወጣቶች አሉ። ነገር ግን የስነ ተዋልዶ ጤናና ሌሎችም የጤና አገልግሎቶች በበቂ ሁኔታ እየተሰጣቸው አይደለም። ከዚህ አንፃር ወጣቶቹ ባላቸው ግዜ ጤናቸውን እንዲያረጋግጡ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የጤና ማእከል ሊኖራቸው ይገባል። ይህ ባለመሆኑም ነው በርካታ ወጣት ሴቶች ላልተፈለገ እርግዝና የሚጋለጡት።

ልክ እንደ ጤናው አገልግሎት ዘርፍ ሁሉ የኢትዮጵያ የትምህርት ስርአትም አብሮ መሻሻል አለበት። በትምህርት ላይ ከታች ጀምሮ መሰራት አለበት። ስለዚህ ብዙ ነገሮችን ለማስተካከል ግዜው አሁን ነው። ዛሬ ላይ ያልተቀረፈ ችግር ነገ ትውልዱ ይቀርፈዋል ማለት አይቻለም። ፆታዊ ጥቃቶች እየተፈፀሙ ነው። በግጭት ምክንያት በርካታ ወጣቶች ተሰደዋል። በርካታ ወጣቶች በመጠለያ ካምፕ ውስጥ ነው የሚገኙት። በነዚህ አካባቢዎች ላይ የሚገኙ ወጣቶች በጤና የመጠበቅ መብታቸው ሊከበርላቸው ይገባል። ስለዚህ ዛሬ ላይ ጥራት ያለው ምላሽ ሰጪ የጤና ስርአት ሊገነባ ይገባል። ሃይማኖት ተቋማት ላይ ያለው የጤና ስርአትም እንዲጠበቅ ይፈለጋል።

ወጣት ቶፊቅ እንደሚያብራራው በግጭቶች ምክንያት ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች የስነ ተዋልዶና ሌሎችንም የጤና አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ካውንስሉ ለሚመለከተው አካል ጥያቄ ያቀርባል፤ አቅርቧልም። ከሁሉም በላይ ካውንስሉ ሰላም እንዲመጣ ይፈልጋል። ሰላም ሲመጣ የሚፈለገው የጤና አገልግሎት ለወጣቱ እንደሚደርስ ያምናል። ከዛ ውጪ ግን ግጭት በተፈጠረባቸው አካባቢዎች ላይ ያሉ አካላት ቆም ብለው ደጋግመው ሊያስቡ ይገባል። ትውልድ ነው የሚያቀነጭሩት። ጤና ከፖለቲካ ነፃ የሆነ ዘርፍ እንደመሆኑ ማንኛውም ሰው ጤናውን የመጠበቅ መብት አለውና ይህ ነገር እንዲደረግ ካውንስሉ ድምፅ ይሆናል።

እንደዚህ አይነት ቦታዎች ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸው እንዲጎበኙና ምላሽ እንዲሰጣቸው፣ ሕክምና ቁሳቁሶች በፍጥነት ቦታው ላይ እንዲደርሱ፣ ለቀውስ የተጋለጡ ወጣቶች ባሉበት ቦታ ላይ በቶሎ የጤና አገልግሎት ተደራሽነት የሚያገኙበትን ሁኔታ የማመቻቸትና የመወትወት ስራ ይሰራል። ተደራሽነት ሲባል ግን ጥራቱን ጠብቆ ነው። ምንም አይነት የጤና አገልግሎት የለም ማለት የለበትም። አገልግሎቱ የተሟላ ሊሆን ይገባል።

የአፍላ ወጣቶችና ወጣቶች ጤና ካውንስል በጤና ሚኒስቴር ስር ያለ ቢሆንም በኢትዮጵያ ወስጥ ያሉ ማንኛቸውም በአፍላ ወጣቶችና ወጣቶች ዙሪያ ስራ የሚሰሩ አካላት ሁሉ ከካውንስሉ ጋር ይሰራሉ፤ እንዲሰሩም ሕጉ ያስገድዳቸዋል። ካውንስሉም ከነዚህ አካላት ጋር ይሰራል። የኢትዮጵያ አፍላ ወጣቶችና ወጣቶች ካውንስል አባል የሚባሉትም በኢትዮጵያ የሚገኙት ሁሉም የአፍላ ወጣቶችና ወጣቶችን ያካተተ ነው። በአምስተኛው የአፍላ ወጣቶችና ወጣቶች ጉባኤ ላይም ከየክልሉ ከፕሬዚዳንት እስከ ምክትል ፕሬዚዳንትና ፀሃፊ ድረስ ሶስት ሶስት ወጣቶች እንዲሳተፉ ተደርጓል። በጥቅሉ ከ200 በላይ የሚሆኑ ወጣቶች ተሳትፈዋል።

ወጣት ቶፊቅ እንደሚለው በኢትዮጵያ ከ3 ሺ በላይ የወጣት ስብእና መገንቢያ ማእከላት አሉ። የካውንስሉ አጋር አካላት የሴቶችና ማኅበራዊ ሚኒስቴርና ትምህርት ሚኒስቴር እንደመሆናቸው እነዚህ አካላት በወጣቶች ዙሪያ ባለቤት ሆነው ይሰራሉ። በነዚህ 3 ሺ በላይ በሚሆኑ የወጣት ስብእና መገንቢያ ማእከላት ሁሉም የስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎቶች ይሰጣሉ። አገልግሎቶቹ ጥራት ያላቸውና የተሟሉ ናቸው የሚለው ግን ቁጭ ብሎ መፈተሽ ያለበት ጉዳይ ነው።

የዛሬ ዓመት በተሰራ ጥናት እነዚህ 3 ሺ የወጣት ስብእና መገንቢያ ማእከላት ጥራት እንደሌላቸው ሪፖርት ቀርቧል። ጥራት እንደሚያስፈልጋቸው፣ አስፈላጊ መሰረተ ልማቶች ሊሟሉላቸው እንደሚገባ በጥናቱ ተጠቁሟል። እንደዚህ አይነት ጉድለት ያለባቸው የወጣት ስብእና መገንቢያ ማእከላት እንዲዘጉና አቻ ተቋማት እንዲከፈቱ ተደርጓል። በ2017 ዓ.ም ደግሞ እነዚህ የወጣት ስብእና መገንቢያ ተቋማት በአገልግሎት ጥራትና ተደራሽነት በ10 ከመቶ እንዲያድጉ እየተሰራ ይገኛል።

በሌላ በኩል ደግሞ በሁሉም ጤና ተቋማት ላይ የወጣት ጤና አገልግሎት መስጫ ተቋማት እንዲገነቡ መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ስራው ተግባራዊ ይሆናል። አብዛኛዎቹ የስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎቶችም በነፃና በበጎ ፍቃድ አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው። ወጣቶች በጤና ተቋትም ሄደው የስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት ሲያገኙ ክፍያ አይጠየቁም። ስለዚህ ባለፉት አራት ዓመታት በስነ ተዋልዶ ጤና ተደራሽነት ላይ ሰፊ ስራ ሲሰራ ቆይቷል። አሁን ደግሞ ተደራሽነቱን ከማስፋት በዘለለ ምላሽ የመስጠት ስራው እንዳለ ሆኖ በሁሉም የጤና ስርአት የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ላይ ይበልጥ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል።

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን መስከረም 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You