ዓለም ወደ አንድ መንደር እየሆነች ባለችበት በዚህ ዘመን አፍሪካውያን አገራት አንድነት ሃይል፤ ህብረትም የድል ምስጢር መሆኑ በቅጡ የገባቸው አይመስልም። ለእዚህም ያላቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስተጋብር እጅግ ደካማ በምክንያትነት ሊጠቀስ ይችላል።
በአሁኑ ወቅት የድህነት ተምሳሌትነቷ ተቀይሮ የተስፋ ምድርነት መገለጫ በመሆን ላይ በምትገኘው አፍሪካ አገራቱ ከማበር ይልቅ የግል ብልጽግናቸውን መሻታቸው በተለይ የአህጉሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት በሚጠበቀው ልክ እንዳይፈጠን ቀፍድዶ ይዞታል።
ለዚህ የአገራት የጋራ ትስስር ጉድለትም የተለያዩ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ።ከእነዚህም መካከል በኢኮኖሚ ግንኙነት ረገድ አገራቱን ለማስተሳሰር የሚያስችል ተቋም አለመኖሩ ከሁሉ ልቆ ይጠቀሳል።
በእርግጥ የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ የተለያዩ የህብረት ተቋማት፤ ያልተቀናጀ ጉዞ ለማስወገድ ድንበር አልባ አፍሪካን በመፍጠር በአህጉሪቱ ዜጎች መካከል ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስርን ለማጠናከር ብዙ ደክመዋል። ከእነዚህም ተቋማት መካከል አንዱ የምዕራብ አፍሪካ አገሮች የኢኮኖሚ ማህበረሰብ / ኤኮዋስ/ የሚባለው ይጠቀሳል።
ኢኮዋስ የተመሰረተው እኤአ በ1975 በ15 መልክአ ምድራዊና ባህላዊ ትስስር ባላቸው አገራት ነው። አባል ሀገሮቹም ቤኒን፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ጊኒ ቢሳው፣ ኮትዲቭዋር፣ ማሊ፣ ኒጀር፣ ሴኔጋል፣ ጊኒ፣ ጋና፣ ጋምቢያ፣ ኬፕ ቨርዲ፣ ላይቤሪያ፣ ናይጄሪያ፣ ሴራሊዮንና ቶጎ ሲሆኑ፣ በጥቅሉ 385 ሚሊዮን ህዝብ የሚኖርባቸው ናቸው።
ከእነዚህ አገራት መካካል ስምንቱ ማለትም ቤኒን፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ጊኒ ቢሳዋ፣ኮትዲብዋር ፣ ማሊ፣ ኒጀር፣ ሴኔጋል፣ ቶጎ በጋራ “ሲኤፍኤ ፍራንክ›› የተባለ የጋራ የመገበያያ ገንዘብ ተጠቃሚዎች ናቸው። ናይጀሪያ፣ኬፕ ቨርዲ፣ጊኒ፣ጋና፣ ጋምቢያ፣ ላይቤሪያና ሴራሊዮንም የየራሳቸውን መገበያያ ሲጠቀሙ ቆይተዋል።
የኤኮዋስ አባል አገራት መሪዎችም ትስስራቸውን ይበልጥ ለማጠናከር «አንደኛው መንገድ» ያሉትን ወጥ የሆነ የመገበያያ ገንዘብ እውን ለማድረግ ላለፉት ሶስት አስርት ዓመታት የተለያዩ ተግባራትን ሲፈፅሙ ቆይተዋል።
ከቀናት በፊት በናይጄሪያ አቡጃ በተካሄደው የህብረቱ ጉባኤ ላይም ይህ የዓመታት ድካማቸው ፍሬያማ ሆኖ ታይቷል። 15 አባል አገራት በተገኙበት ስብሰባ፣ «ኢኮ» ተብሎ የተሰኘ የጋራ መገበያያ ገንዘብ ይፋ አድርገዋል። ይህ የጋራ መገበያያ ገንዘብም አስፈላጊ የሆኑ ቅድመ ዝግጅቶች ተጠናቀውለት እስከ እኤአ 2020 ባለው ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ እንደሚደረግ ታውቋል።
ይህን የአባል አገራቱ የአንድ ገንዘብ የመጠቀም ውሳኔ በሚመለከትም የተለያዩ መገናኛ ብዙኃንና የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ሰፊ ሃተታ እያሰፈሩ ይገኛሉ። እንደ ዘገባዎቹና ባለሙያዎቹ አስተያየትም፤ ውሳኔው ሁለት አይነት ስሜቶች ተንጸባርቀውበታል። ደጋፊዎችን የማፍራቱን ያህል ተቃዋሚዎቹም ብዙ ብለው ተስተውለዋል።
የውሳኔው ደጋፊዎች፤ በአባል አገራቱ መካከል ያለውን የንግድ አጋርነት ይበልጥ የሚያጎለብት፣የፋይናንስ ዘርፍ ትብብርና የአከፋፈል ስርዓቱን የሚያስተሳስር እንዲሁም የተለያዩ ገንዘቦችን ለመመንዘር የሚወጣውን ከፍተኛ ወጪ የሚያስቀርና የገንዘብ ምንዛሬ ስጋቶችንም ለማስቀረት ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንዳለው አመላክተዋል።
በተለይ እኤአ 2022 በአፍሪካውያን አገራት መካከል ነፃ የንግድ ልውውጥ በእጥፍ በማሳደግ የአህጉሪቱ የድህነት ተምሳሌትነት ተቀይሮ የተስፋ ምድር መሆኗን ለማስመስከር ለሚደረገው ጥረት አጋዥ መሆኑንም አስምረውበታል። በተለይም እኤአ በ«2063 ግብ የተጣለለት በድንበር ያልታጠረችና የተሳሰረች አፍሪካን የመፍጠር አጀንዳ እውን ለማድረግ ወሳኝ እርምጃ» ሲሉም አሞካሽተውታል።
አሉታዊ መዘዞች እንዳሉት የሚያስረዱት በሌላ በኩል እንደሚያስረዱት፤ አገራቱ ምንም እንኳን አሁን ላይ የጋራ ገንዘቡን ይፋ ማድረጋቸው እንደ ስኬት ቢቆጥሩትም ከሁሉ ቀድሞ በርካታ ጥያቄዎች መመለስና የቤት ስራቸውን መስራት ግድ ይላቸዋል።
በአባል አገራቱ መካከል ጠንካራ አጋርነት በሌለበት፣ የተለያዩ የንግድ ፍሰቶችን የሚያስተሳስሩና የሚያቀላጥፉ ጠንካራ ፖሊሲዎች ተቀምረው ተግባራዊ ባልሆኑበት አንድ የጋራ ገንዘብ ለመጠቀም መወሰናቸው አደጋው እጅግ የከፋ ነው ሲሉም ተደምጠዋል።
ለዚህ እሳቤአቸው ማጠናከሪያም የአውሮፓ ህብረት አባል አገራት በጋራ ገንዘብ ለመጠቀምና ለ44 ዓመታት ተደራድረው የመሰረቱትን ‹ዩሮ ዞን› በዋቢነት አቅርበዋል።አገራቱ ‹ዩሮ ዞን› በሚባለው የገንዘብና የኢኮኖሚ ጥላ ስር ትስስር የፈጠሩና የጋራ መገበያያ ገንዘባቸውን ዩሮ ያደረጉት አገራት በአንድ የዞኑ አባል አገር ድክመትም ይሁን በሌላ ምክንያት የገንዘብና የኢኮኖሚ ቀውስ ለሌላውም ማህበርተኛ ሲተርፍ መስተዋሉን አስታውሰዋል።
ይህም በተለይ እ.አ.አ. በ2008 የተከሰተው ከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ ግሪክ፣ ስፔን፣ ፖርቱጋልና ጣሊያንም በከፍተኛ ዕዳና የበጀት ድጎማ ስር እንደጣላቸውም በመጠቆም፤በወቅቱ ለባለ ጠንካራ ኢኮኖሚ ባለቤቶቹ ጀርመንና ፈረንሳይ እንዲሁም ዓለምአቀፉ የገንዘብ ድርጅት ለዞኑ ምርኩዝ ባይሆኑ ኖሮ ያስክትል የነበረው አደጋ የከፋ እንደነበርም አስረድተዋል።
ይህን ከአስር ዓመት በፊት የሆነ ክስተት ወደ ኋላ ተመልሰው የሚያስታውሱ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ታዲያ፤ በጋራ ገንዘብና በአህጉራዊ ማዕከላዊ ባንክ የተመሩትን የ‹ዩሮ ዞን› አገሮች የኢኮኖሚ ቀውስ ዋቢ በማድረግ አጣዳፊ ውሳኔ ላይ መድረስ ተገቢ አለመሆኑን በመወትወት ላይ ይገኛሉ።
በዚህ ረገድ ለአልጀዚራ አስተያየቱን የሰጠው በናይጄሪያው የፐብሊክ ስትራቴጂና ሚዲያ ግሩፕ ጌት ፊልድ የፖሊሲ ባለሙያ አድውሚ አማሮዋ፤ ‹‹የአንድ መገበያያ ገንዘብ ቀጣናዊ የእርስ በእርስ የንግድ ትስስር ችግሩን ለመፍታትና የንግድ አጋርነትን ለማቀላጠፍ እንዲሁም ቀለል ለማድረግ አቅም የለውም» ብሏል።
በሴራሊዮን የዜና መረብ ዘ ፓትሪዮቲክ ቫንጋርድ ላይ የፃፉት ኮርቶር ካማራ በበኩላቸው፤ ከሁሉም በላይ የአንድን አገር ሉዕላዊነት የሚፃረር ነው ሲሉ ገልጿል።በተለይ በማዕከላዊ ተቋሙ ውሳኔ አገራት የራሳቸውን የብድር ምጣኔ እንዳይወስኑ ሊጫናቸው ይችላል፤ በኢኮኖሚያቸው ለፈረጠሙት ሲጠቅም፤ ዝቅተኞቹን ይበልጡን ይጎዳልም።›› ሲል አስነብቧል።
ከዚህ ሁሉ ቀድሞ የኢኮዋስን የንግድ ስምምነት ተግባራዊነት ስለማሻሻል ማጤን እንደሚገባ የሚያስገነዝቡ ባለሙያዎችም በርካታ ሆነዋል። ከዚህ እሳቤ አራማጆች አንዱ የሆኑት የዓለም አቀፍ የንግድ ግንኙነት አማካሪው ተቋም ፒ ደብሊው ሲ የምዕራብ አፍሪካው አንድሪው ኔቪን በበኩላቸው፤ ናይጄሪያ ተጨማሪ ቀረጥን በማስወገድ አንድ የጋራ ገበያን በመመስረት ሂደት ሆነኛ መፍትሄ ነው የተባለለትን የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነትን ለመቀላቀል ፈጥና አለመንቀሳቀሷ አስታውሰዋል።
ሁለት ሶስተኛ የሚሆነውን የቀጣናውን ኢኮኖሚ የምትሸፍነው ናይጄሪያ የንግድ ትስስሩን ሳትቀላቀል ስለአንድ የመገበያያ ገንዘብን ማሰቧ የማያስኬድ ስለመሆኑ አስረድተዋል። የኢኮዋስ የንግድ አጋርነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ባልሆነበት አባል አገራት የጋራ ገንዘቡን ቀዳሚ አጀንዳቸው ማድረጋቸው አግባብ አለመሆኑን አስገንዝበዋል።
ይሁንና ናይጄሪያ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነትን ለመቀላቀል መወሰን በኒጄር ዋና ከተማ ኒያሚ እየተካሄደ በሚገኘው የአፍሪካ ህብረት ልዩ ስብሰባ ላይ ይፋ አድርጋለች። ይህም ምናልባት ስጋቶችን የማቃለል አቅም እንዳለውም ተመላክቷል።
ውሳኔውን ከመደገፍና ከመወረፍ በዘለለ አንዳንድ መገናኛ ብዙሃንና የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ከመሪዎቹ ውሳኔ ጀርባ ያለው አንድነትን የማጠናከር ፍላጎት አሊያም ኢኮኖሚያዊ እድገትን መሻት ሳይሆን ይበልጡኑ ፖለቲካዊ አጀንዳን ያነገበ ስለመሆኑም አትተዋል።
በሌላ በኩል፤ የመገበያያ ገንዘብ እውን የማድረግ ውሳኔውን የተቀበሉት አብዛኞቹ የምዕራብ አፍሪካ አገራት ቀደም ሲል የፈረንሳይ ቅኝ ተገዥዎች መሆናቸውን በማስገንዘብ፤ የምዕራብ አፍሪካ አገራቱ መሪዎች አንድ የመገበያያ ገንዘብ እውን የማድረግ ውሳኔም፤ ከጥገኝነት ይልቅ በራሳቸው መቆም እንደሚችሉ ለማሳየት የወጠኑት ስለመሆኑም አስረድተዋል።
የምዕራብ አፍሪካ አንድ የመገበያያ ገንዘብ በዚህ መልክ የየቅል እሳቤዎችና ሁለት መልኮችን ማስተናገዱን የቀጠለ ሲሆን፣ ምንም እንኳን የአባል አገራቱ መሪዎች ውሳኔ ድጋፍ ባይነፈገውም፤ በርካቶች ግን ከተግባራዊነቱ ቀድሞ በአግባቡ ሊጤን እንደሚገባው አፅእኖት እየሰጡበት ይገኛል።
በአይ.ኤም.ኤፍ ውስጥ በምጣኔ ሀብት ባለሙያነት ያገለገሉት አብዱረማን ሳር እንዳሉትም፤ የአባል አገራቱ መሪዎች አንድ የጋራ የመገበያያ ገንዘቡ ተግባራዊ የሚሆንበትን ቀነ ቀጠሮ ከማራዘም አንስቶ በርካታ ምርጫዎች እንደተቀመጡላቸው ይገልጻሉ። ነገም ለሁሉ መልስ ይሰጣል።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 2/2011
ታምራት ተስፋዬ