የግብጽ የመሣሪያ ድጋፍ ለሶማሊያ ወይስ ለአልሸባብ?

ዜና ትንታኔ

ባሳለፍነው ሳምንት ግብጽ ለሶማሊያ የተለያዩ የጦር መሣሪያዎችን ለሶማሊያ መላኳ ይታወሳል። ሆኖም ይህ ራሷን ለመከላከል በቂ አቅም ለሌላት ሶማሊያ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እንደሚያመዝን እየተነገረ ነው። እንዲህ አይነት የመሣሪያ ድጋፍ በቀላሉ በአልሸባብ እጅ ሊገባና ሶማሊያ ሙሉ ለሙሉ በአልሸባብ እጅ ልትወድቅ ብሎም ለቀጣናው ሰላም ስጋት ሊሆን እንደሚችል ምሁራን ይገልጻሉ።

የሰላምና ደህንነት ባለሙያና የኢንተራክሽን ፎር ቼንጅ ኢን አፍሪካ ዳይሬክተር ወርቁ ያዕቆብ (ዶ/ር) እንደሚገልጹት፤ ሶማሊያ ክልሎቿን እንኳን በማዕከላዊ መንግሥት የማስተዳደር አቅም አጥታለች፤ እንዲሁም ከግብጽ መንግሥት ጋር ያደረጋቸውን ወታደራዊ ስምምነት የፓርላማ አባላትም ተቃውመውታል። በዚህ ሁኔታ ላይ እያለች የግብጽ መንግሥት ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎችን መስጠቱ መሣርያዎቹ በቀላሉ በአልሸባ እጅ እዲወድቁ በማድረግ ለቀጣናው ሰላም ስጋት ሊሆን ይችላል።

በቀጣናው ግብጽ፣ ሶማሊያ፣ ኢትዮጵያና ኤርትሪያ የየራሳቸው ውስጣዊ ችግሮች ያሏቸው በመሆኑ ሰጥቶ የመቀበል መርህን በመከተል በጋራ መልማት ተመራጭ ነው። እነኚህ ሀገራት ቆም ብለው በችግሮቻቸው ዙሪያ በማሰብ ዲፕሎማሲያዊ አማራጮችን በመጠቀም ከጠብ አጫሪ ንግግሮችና ተግባራት መቆጠብ እንዳለባቸውም ዶክተር ወርቁ ይገልጻሉ።

ግብጽ በአሁኑ ወቅት ጠብ አጫሪ ተግባር በማከናወን ኢትዮጵያን የመክበብ አይነት ሁኔታ ውስጥ እየገባች ነው። ከህዳሴው ግድብ ጋር ተያይዞ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለረጅም ጊዜ ስትከስ መቆየቷን የሚያነሱት ባለሙያው፤ ይህንንም በዲፕሎማሲ ማሸነፍ ሲያቅታት ሰሞኑን በኢትዮጵያ ዙሪያ የምታደርገው እንቅስቃሴና የምታወጣው መግለጫ በሃይልና በውክልና ጦርነት ነገሮችን ለማሳካት ፍላጎት እንዳላቸው ማሳያ ነው ይላሉ።

እንደ ዶክተር ወርቁ ገለጻ፤ ግብጽ ኢትዮጵያን ለጦርነት ለማነሳሳት አደገኛ አካሄድ እየሄደች በመሆኑ ኢትዮጵያ በተቀናጀ ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ ግብጽ እያደረገችው ካለው ጠብ አጫሪ ተግባር እንድትቆጠብ ማድረግ ያስፈልጋታል። እንዲሁም ይህን ተግባር ለዓለም አቀፉ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብና ሚዲያዎች ማስረዳት፣ የግብጽን እንቅስቃሴ ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ መከታተልን ይሻል።

ኢትዮጵያ በታሪኳ የትኛውም ባዕድ ሀገር ሊያሸንፋትና ሊያንበረክካት እንደማይችል ይታወቃል። ግብጽ በአሁኑ ወቅት ለሶማሊያ አይዞሽ እኔ አለሁሽ ጨዋታ እየተጫወተች ነው። ግብጽ ይህን እያደረገች ያለው ኢትዮጵያ ከህዳሴው ግድብ በሙሉ አቅሟ ሃይል ማመጨት ስትጀምር ኢኮኖሚያዊ አቅሟን ከማሳደግ ባለፈ ለሌሎች ሀገራትም ሃይል በማቅረብ የቀጣናው ተጽዕኖ ፈጣሪነቷ እንዳያድግ በሚል ስጋት መሆኑን ዶክተር ወርቁ ያመላክታሉ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና በአፍሪካና የኤሲያ ጥናት ሶስተኛ ዲግሪያቸውን በመከታተል ላይ ያሉት ዳዊት መዝገበ ጸጋዬ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ የሶማሊያ ፖለቲካ ጎሳን መሠረት ያደረገና የተከፋፈለ ነው። በዚህም ግብጽ የሰጠችው የጦር መሣሪያ ለአልሸባብ አይደርስም ብሎ ማሰብ ከሞኝነት ያለፈ ነው። አልሸባብ መኖር የቻለው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በሶማሊያ መንግሥት ፍላጎት ነው።

ግብጽ በአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ ውስጥ የምትፈልገው በየትኛውም አጋጣሚ የኢትዮጵያን ፖለቲካና የውስጥ ሰላም ማደፍረስ ነው። ከዓባይ ወንዝ ጋር ተያይዞ ግብጽ ስለኢትዮጵያ ያላት የጠላትነት አመለካከት ዛሬ የጀመረ ሳይሆን አባይ ከኢትዮጵያ እንደሚመነጭ ከታወቀበት ጊዜ ጀምሮ ነው የሚሉት መምህሩ፤ ግብጽ ለሶማሊያ የጦር መሣሪያ መስጠቷ የሚያስከትለው ተጽዕኖ በአፍሪካ ቀንድ ብቻ ይወሰናል ብሎ ማሰብ ገርነት ነው ይላሉ።

እንደ መምህር ዳዊት ገለጻ፤ ለዩክሬን የተሰጠው የጦር መሣሪያ ኦዲት የማይደረግ በመሆኑ በጥቁር ገበያዎች እየወጣ በመሸጡ ላልተገባ ተግባር ውሏል፤ የዚህም እጣ ፈንታ ተመሳሳይ ሊሆን የሚችል በመሆኑ ይህም ለመላው ዓለም ስጋት የሚደቅን ነው።

ግብጽ ከሰሞኑ በሶማሊያ ወታደሮቼን አሰፍራለሁ ማለቷ የሚያስደንቅ ነው። ሰላምን አጥብቃ የምትሻ ከሆነ የበርካታ ዜጎች እልቂት ባለበት በጋዛ፣ በሱዳን፣ በሶሪያና በሌሎች ሀገራት ልታሰፍር እንደምችል የሚጠቁሙት መምህር ዳዊት፤ ከልቧ ቢሆን የሶማሊያን ውስጣዊ ችግር በመፍታት ኢኮኖሚያዊ መረጋጋትን መፍጠር ትችል ነበር፤ እንዲሁም ቀደም ሲል ሶማሊያን ከአልሸባብ ለመታደግ በተደረጉ ጥረቶች ተሳትፎ ማድረግ ትችል እንደነበር ያነሳሉ።

ግብጽ ከቅኝ ግዛት ነጻ ከወጣችበት ጊዜ ጀምሮ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋንም ጨምሮ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የኢትዮጵያን ሰላም መንሳት ነው፤ በዚህ የግብጽ ፍላጎት የአፍሪካ ቀንድ ሰላምን ማደፍረስ በመሆኑ የግብጽን የፖለቲካ አካሄድ በማጤን ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሤ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰላም ግንባታና ፖለቲካ ጉዳዮች ረዳት ዋና ፀሐፊ ሮዝማሪ ዲካርሎ ጋር በተወያዩበት ወቅት” በሶማሊያ ባልተረጋጋ የደህንነት ሁኔታ ውስጥ በውጭ ሃይላት የሚደረግ የጦር መሣሪያ አቅርቦት በመጨረሻ ሀገሪቷ አሸባሪዎች እጅ ላይ እንድትወድቅ በር ሊከፍት ይችላል “ ሲሉ ስጋታቸውን መግለጻቸው የሚታወስ ነው።

ቃልኪዳን አሳዬ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You