መስቀል አበባ ውብ አበባ…

 

የመስቀል በዓል በወርኃ መስከረም አጋማሽ የሚከበር ሲሆን በዚህ ወቅት በተለይም በገጠሩ የሀገራችን ክፍል አንዳንድ የሰብል ዓይነቶች ማሸት የሚጀምሩበት እና የበቆሎ እሸት የሚደርሱበት ፤ የጎመን ድስት ወጥቶ የገንፎ ድስት የሚጣድበት ፤ አደይ አበባ የሚፈካበት ነው። አርሶ አደሩም በባለፈው ዓመት የመርኸር እርሻ ከዘራው ምርት መቅመስ የሚጀምርበት ፤ ጎተራው ተሟጦ የነበረው አርሶ አደር ጎተራውን ከጓሮው የሚያደርግበት፤ ልጅ ከብቱ የሚጠግብበት የሽግግር ጊዜ በመሆኑ ልዩ ስሜትን ይሰጣል። በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ንብ አናቢዎችም ማር መቁረጥ የሚጀምሩበት መስከረም 17 ነው። በዚህ ቀን የተቆረጠን ማር እንደመድሃኒት ይቆጥሩታል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አማኞች ዘንድ የአሌክሳንድሪያው ፓትርያርክ በመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያ ገዢ ለነበሩት ዐፄ ዳዊት ክርስቶስ የተሰቀለበትን ግማደ መስቀል ስላበረከቱላቸው ግማደ መስቀሉ በሀገራችን ኢትዮጵያ ይገኛል የሚል እምነት አላቸው። በመሆኑም የዓሉ አከባበር በኢትዮጵያ ልዩ ድባብ ያለው ነው።

እንደሊቃውንት ገለጻ፤ መስከረም 17 ቀን የሚከበረው የመስቀል በዓል ለሦስት መቶ ዓመታት ተቀብሮ እና ቆሻሻ ሲጣልበት የቆየውን ክርስቶስ የተሰቀለበትን ግማደ መስቀል ለመፈለግ ንግሥት እሌኒ ቁፋሮ ያስጀመረችበት ቀን ነው። መስቀሉን ለመፈለግ መስከረም 17 ቀን ቁፋሮው ይጀመር እንጂ የተገኘው መጋቢት 10 ቀን ነው። ነገር ግን መጋቢት 10 ቀን በየዓመቱ ጾመ ኢየሱስ ላይ የሚውል በመሆኑ መስቀሉ ለማውጣት ቁፋሮ በተጀመረበት መስከረም 17 ቀን እንዲከበር ተደርጓል፡፡

ደመራ የሚደመረውና የሚለኮሰው መስቀሉን በመፈለግ ሂደት ውስጥ የተከናወኑ ተግባራትን ለማመላከት ነው። የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ጉባዔም በድህረ ገፁ ባወጣው አንድ መረጃ ኢትዮጵያውን የሚያከብሩት የመስቀል በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት ትክክለኛው መስቀል ተቆፍሮ የተገኘበትን ቀን ለመዘከር እንደሆነ ያስረዳል፡፡

የበዓሉ አከባበር እንደየቦታው ወግ ፣ ባህል፣ ዕሴት፣ ትውፊት በተወሰነ ደረጃ ይለያያል። በአንዳንድ አካባቢዎች የመስቀል ደመራ በዋዜማው እንዲበራ ሲደረግ በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ በመስቀል ቀን ጠዋት ደመራ ተደምሮ እንዲበራ ይደረጋል። በመስቀል ደመራ ላይ አደይ አበባና ለምለም ቄጠማ ጣል ጣል ማድረግ የተለመደ ነው። በሕዝቡ ዘንድም መስቀልን ከአደይ አበባ ጋር የማያያዝ ነገርም ይታያል። በቤተክርስቲያን ዝማሬም

‹‹ መስቀል አበባ ነህ ውብ አበባ

አደይ አበባ ነሽ አበባ

መስቀል አበባ ተቀብሮ ሲኖር

አደይ አበባ ሥነ ስቅለቱ

መስቀል አበባ እሌኒ አገኘች

አደይ አበባ ደገኛይቱ …

መስቀል አበባ ወንዙ ጅረቱ አደይ አበባ ሸለቆው ዱሩ

መስቀል አበባ አሸብርቀው ደምቀው አደይ አበባ ላንተ መሰከሩ። …›› እያሉ ይዘም ራሉ፡፡

ከአስር ዓመት በፊት በመስቀል አደባባይ ደመራ ወጣቶቹ ሲዘምሩ በብዛት በወረቀት የተሠራ አደይ አበባ ይዘው በዝማሬና በዝማሜ ስለነበር፤ ዛሬ በየቦታው ለምናየው ለሴቶች የጆሮና የፀጉር ጌጥ ፣ ለአልባሳት፣ ለመኖሪያ ቤቶች መስኮትና የግድግዳ ጌጥ እንዲሆኑ አዎንታዊ ተፅዕኖ ፈጥሯል። ዛሬ እንደ ጌጥ የሚያገለግለው አሪቲፊሻሉና ትልልቁ አደይ አበባ ገበያው በመስከረም ሲብት እንዲህ ሊደራና በሰዉ ዘንድ ሊወደድ የቻለው በሰንበት ተማሪዎች በመስቀል ዝማሬ በፈጠሩት ኩነት ነው።

መስቀል ለአንድንድ ብሔረሰቦችም እንደመታወቂያ ምልክትም ነው። ለምሳሌ መስቀል በጉራጌ ብሔረሰብ የተለየ ድባብ ያለው ነው። የጉራጌ ብሔረሰብ ዓመቱን ሙሉ በአዲስ አበባ እና ሌሎች ትልልቅ ከተሞች ከላይ ታች ወጥቶና ወርዶ፤ ነግዶ ሠርቶ ያገኛትን ገንዘብ ቋጥሮ ወደ ቤተሰቦቹ ቀየ ገጠር ድረስ ሄዶ እርድ አርዶ፣ ቆጮውን ፣ የጎመን ክትፎውንና የስጋውን ክትፎውን አዘጋጅቶ የሚያከብረው በዓል ነው።

መስቀል የሚከበረው መስከረም ጠባ አዲስ ዓመት ገባ በሚል ድባብ ስለሆነ ፤ ዓመቱን ሙሉ ሠርቶ የደከመ መንፈሱን ያድስበታል። የተለያዩ ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ ክንዋኔዎችን ይፈጽምበታል። በመስቀል በዓል ተያይተው የተዋደዱ ለአቅመ አዳም እና ለአቅመ ሄዋን የደረሱ ወጣቶችም ሦስት ጉልቻቸውን ይመሠርቱበታል። አጋጣሚውን ‹‹በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ›› አድርገው ይጠቀሙበታል፡፡

በዓሉ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ፓትርያርክን ጨምሮ ጳጳሳት ፣ ቀሳውስት ሌሎች የሃይማኖት አባቶች ፣ ዲፕሎማች እና ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት እንዲሁም ቱሪስቶችና የከተማው ነዋሪዎች የሚታደሙበት ነው። በዓሉ ሃይማኖታዊ ይሁን እንጂ ባህላዊ ዐውድና ድባብ ያለው ነው። በዓሉ በአደባባይ በተለያዩ መንፈሳዊ ዝማሪዎች እና ትእይንቶች ደመራ በማብራት በልዩ ድምቀት የሚከበር ነው። ቄሳውስት እና ዲያቆናት እንዲሁም የሰንበት ትምህርት ቤት ዘማርያን ለአእምሮ ደስታን የሚፈጥሩ የያሬድ ዝማሬዎች የሚያቀርቡትን ነው።

‹‹ መስቀል ብርሃን ለኩሉ ዓለም

መሠረተ ቤተክርስቲያን

ወሃቤ ሰላም መድሃኒዓለም

መስቀል ኃይልነ ለእለ ነአምን›› እያሉም ይዘምራሉ። ትርጓሜውም

መስቀል ብርሃን ነው ለመላው ዓለም

መሠረት ነው ለቤተክርስቲያን

ሰላምን ሰጪ ነው መድሃኒዓለም

መስቀል ኃይል ነው ለእኛ ለምናምነው፡፡›› ማለት ነው።

በነገራችን ላይ መስቀል በሚከበርበት መስከረም 17 ቀን በየዓመቱ የዓለም የቱሪዝም ቀንም ታስቦ ይውላል። ይህ ደግሞ በዩኔስኮ የተመዘገበውን የመስቀል በዓል በቱሪስቶች ዘንድ ልዩ ቦታ እንዲሰጠው እድል ይፈጥራል። ሀገራችን ከቱሪዝም የምታገኘውን ገቢ ከፍ ለማድረግ ያግዛል፤ ለብዙ ወጣቶችም የሥራ እድል ፈጥራል። ስለሆነም አጋጣሚውን ለመጠቀም እኛ ኢትዮጵያውያን ከመነቃቀፍ ወጥተን በመተቃቀፍ ከቱሪዝሙ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ እጅ ልእጅ እንያያዝ! መልዕክቴ ነው።

ኃይለማርያም ወንድሙ

አዲስ ዘመን መስከረም 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You