ኢትዮጵያ በዓለም የጫት አቅርቦት የመሪነትን ደረጃ እንደመያዟ ከዓለም ከፍተኛ የጫት ተጠቃሚ ከተባሉ ሀገሮችም ከእነየመን፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ መካከል ትመደባለች። በሌላ በኩል በኢትዮጵያ የጫት ሱስ ተቀዳሚውን ሥፍራ ከሚይዙ የሱስ ዓይነቶች አንዱ ነው። የጫት ተጠቃሚዎች ቁጥር በጨመረ መጠን፣ የሱሰኞችም ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ በተለያዩ አጋጣሚዎች ይነሳል። በቀደምት ጊዜያት የጫት ተጠቃሚነት በውስን የሀገራችን ክፍሎችና በተወሰኑ አካባቢዎች ይዘወተር የነበረ ቢሆንም፣ አሁን አሁን ግን የተጠቃሚው ቁጥር በተለይም በከተማዎች አካባቢ በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል። ዕድሜ፣ የትምህርት ደረጃና ባሕል ሳይገድበው በየአካባቢያችን በበርካታ ሰዎች ሲዘወተር ማየት የተለመደ ሆኗል። በተለይ በወጣቱ አካባቢ አሁን አሁን ይህ ሁኔታ ጎልቶ ይታያል። በዚህም ቁጥራቸው ጥቂት የማይባሉ ዜጎች በጫት ሱሱ ምክንያት ለማኅበራዊ፣ ለኢኮኖሚው ቀውስ እየተዳረጉ ሲሆን በጫት የሚደርሰው የአዕምሮ ጤና ጉዳትም ከፍተኛ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በዩኤንኦዲሲ በተደረገ ዳሰሳ ላይ እንደተቀመጠው፣ እ.ኤ.አ. በ1993 በአማኑኤል ሆስፒታል አልጋ ይዘው የአዕምሮ ሕክምና ከሚከታተሉ ታካሚዎች መካከል 43 በመቶው የአዕምሮ ሕመማቸው ከሱስ ጋር የተገናኘ ነበር። የጫት ሱስ ቀዳሚውን ሥፍራ ከሚይዙት መነሻ ምክንያቶችም ይመደባል። ይህም ችግሩ ማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እያስከተለ መሆኑን አመላካች ይሆናል።
እንደ ሀገር ይህን ችግር ለመከላከል የሁሉንም ማኅበረሰብ የነቃ ተሳትፎ ይጠይቃል። ከዚህ አንጻር ላግዛት የበጎ አድራጎት ድርጅትም በሀገራችን በተለይ አምራቹን የኅብረተሰብ ክፍል እየጎዳ ያለውን የአደንዛዥ ዕፅ ሱስ በመከላከል የድርሻዬን መወጣት አለብኝ በማለት እንቅስቃሴ ጀምሯል። ከሰሞኑ ድርጅቱ ‘ትውልድን ከአደንዛዥ ዕፅ ሱስ እንታደግ’ በሚል ሀሳብ የሐረሪ ክልል መሠረት አድርጎ የሚተገበር ፕሮጀክት ይፋ አድርጓል። በዚህ ወቅት የላግዛት በጎ አድራጎት ድርጅት መሥራች እና ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ጽዮን አለማየሁ እንደተናገሩት፣ ላግዛት የበጎ አድራጎት ድርጅት በ2014 ዓ.ም የተቋቋመ እና በቦርድ የሚመራ ሀገር በቀል የበጎ አድራጎት ድርጅት ነው። በድርጅቱ ተግባራዊ የሚደረገው ፕሮጀክቱ በዋነኝነት ቅድመ መከላከል ላይ ትኩረቱን ያደርጋል።
ድርጅቱ መነሻውን ሐረር ላይ አድርጎ የተቋቋመ እንደመሆኑም የፕሮጀክቱ ጅማሮውን በክልሉ ሊያደርግ ችሏል የሚሉት ወይዘሮ ጽዮን፣ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ሱስ አስያዥ ዕፅዋት መካከል አንዱ የሆነው ጫት በስፋት እየተዘወተረ እንደሆነ መረጃዎች ይናገራሉ። በተለይ በከተሞች አካባቢ የጫት ዕፅ ተጠቃሚው ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑን ጠቅሰው፤ የዚህ ተፅዕኖ ከሚስተዋልባቸው መካከል ሐረር ከተማ ተጠቃሽ መሆኗን ተናግረዋል። በከተማው ችግሩ የሚታይበት የማኅበረሰብ ክፍል በእድሜ የገፉ፣ ጎልማሶች እና ወጣቶች ላይ ብቻ ሳይሆን በታዳጊ የእድሜ ክልል ላይ በሚገኙት ብሎም በነፍሰጡር ሴቶች ጭምር የሚታይ ነው ብለዋል።
የፕሮጀክቱ ተልዕኮ የማኅበረሰቡን የተለያዩ አካላት በማስተባበር የአደንዛዥ ዕፅ ሱስ በኅብረተሰቡ ላይ የሚያደርሰውን አስከፊ ውጤት መቀነስ ብሎም ማጥፋት ነው የሚሉት ወይዘሮ ጽዮን፣ ፕሮጀክቱን ተግባራዊ ለማድረግ በክልሉ ከሚገኙ ከሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት ጋር የጋራ ስምምነት መፈራረማቸውን ገልጸዋል። በዋነኝነት የክልሉ ጤና ቢሮ፣ የክልሉ ትምህርት ቢሮ፣ የክልሉ ሴቶች እና ሕጻናት ቢሮ፣ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን፣ የክልሉ ፋይናንስ እና ኢኮኖሚ ቢሮን የፕሮጀክቱ ባለድርሻ አካላት አድርጎ በአብሮነት እንደሚሠራም አስታውቀዋል ።
ፕሮጀክቱ ሐረርን መነሻ አድርጎ ይጀምር እንጂ በመላው ኢትዮጵያ ተደራሽ ለማድረግ ይሠራል የሚሉት የላግዛት በጎ አድራጎት ድርጅት የኘሮጀክት አማካሪ አንዱአለም አባተ (ዶ/ር)፣ በድርጅቱ ተግባራዊ የሚደረገው ፕሮጀክቱ በዋነኝነት ቅድመ መከላከል ላይ ትኩረቱን እንደሚደረግ ተናግረዋል። የችግሩ መስፋት አንዱና ዋነኛው ምክንያት ከግንዛቤ ክፍተት የመነጨ እንደሆነ ይታመናል። ስለዚህ በስፋት የሚስተዋለውን ችግር ለመቅረፍ ግንዛቤ መፍጠርን ዋነኛ መሣሪያ አድርጎ ሊነሳ መቻሉን አስረድተዋል።
በክልሉ በሚገኙ የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች፣ መምህራን እና የተማሪ ወላጆች እንዲሁም ከትምህርት ቤቶች ውጪ የሚገኘውን የኅብረተሰብ አደንዛዥ ዕፅ ሱስ ምንነትና አስከፊነት በገጽ ለገጽ የሥልጠና መርሐ ግብሮች ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ይሠራል።
በሌላ በኩል ከትምህርት ቤቶች ውጪ የሚገኘውን አካል በተለያዩ የጽሑፍ፣ የራዲዮ፣ የቴሌቪዥን መገናኛ ብዙኃን ስለ አደንዛዥ ዕፅ ሱስ አስከፊነት ግንዛቤ መፍጠር፤ በአደንዛዥ ዕፅ ሱስ የተያዙ ተማሪዎችን በሥነ ልቦና ባለሙያዎች እገዛ ከሱስ እንዲላቀቁ የሚታገዙ ይሆናል። እንዲሁም ወጣቶች እና በሱስ የተጠቁ ዜጎችን ከሱስ እንዲያገግሙ ማገገሚያ ማዕከል ማቋቋም ከሱስ አገግመው ብዙ ዜጎች እንዲሆኑ የሚያግዝ መሆኑን አብራርተዋል።
በማኅበረሰቡ ልምድ የሆነና ወደ ባሕልነት የተጠጋ ከመሆኑ አንፃር፤ በአንድ ጊዜ የሚቀረፍ ችግር አይሆንም። ለዘመናት የተገነባው አስተሳሰብ ለመቀየር እና ለማረም ዓመታትን እንደሚወስድ አክለው ገልጸዋል። በዚህ ረገድ ሊገጥሙ የሚችሉ ፈተናዎች እንደሚኖሩም የሚጠበቅ ሲሆን፤ ስለዚህ ፕሮጀክቱ ተቀርፆ ወደ ተግባር ሲገባ ይሄንኑ ታሳቢ በማድረግ ነው ሲሉ ዶክተር አንዱዓለም ተናግረዋል ።
በሀገራችን የጫት ተጠቃሚዎች ቁጥር ከዕለት ዕለት እየጨመረ እንደመምጣቱ የጫት ጥገኝነት (ዲፔንዳንሲ) እና ሱስም አብረውት ከፍ እያሉ እንደሆነ ይስተዋላል። በሀገር ደረጃም የችግሩ ስር መስደድ አንጻር ትውልዱን ለማዳን ሰፊ ሥራ መሥራትን ይጠይቃል። ስለዚህ ችግሩን ለመቅረፍ እንደ ላግዛት በጎ አድራጎት ድርጅቶችን ማበረታታት እና መደገፍ እንዲሁም ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ተሳትፎ ማድረግና በጋራ ርብርብ በማድረግ ዓላማው በማሳካት ሀገርን መታደግ ይገባል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሐሙስ መስከረም 16 ቀን 2017 ዓ.ም