የግሉን ዘርፍ ኢኮኖሚያዊ ድርሻ የሚያሳድገው አጋርነት

በበርካታ የዓለም ሀገራት የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ ውስጥ በየጊዜው እያደገ የመጣ ሚናን መጫወት የቻለው ‹‹የመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነት›› (Public Private Partnership – PPP)፣ ብዙ ሀገራትም መንግሥታዊ አገልግሎቶችን በግሉ ዘርፍ በኩል እንዲያቀርቡ እድል ፈጥሯል። ይህ አጋርነት መንግሥት በራሱ ማቅረብ የሚገባውን አገልግሎት ከግሉ ዘርፍ ጋር በመቀናጀት እንዲያቀርብ የሚያደርግበትን አሰራር እንዲዘረጋ አስችሏል።

የመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነት ሁሉንም የምጣኔ ሀብትና የፖለቲካ ጥናት ባለሙያዎች የሚያስማማ ትርጓሜ አልተገኘለትም። የመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነት እንዲጠናከር ድጋፍ ከሚያደርጉ ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው የዓለም ባንክ (World Bank)፣ የመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነት ‹‹መንግሥትና የግሉ ዘርፍ በረጅም ጊዜ የውል ስምምነት አገልግሎቶችን ለማቅረብ በትብብር የሚተገብሩት አሰራር›› እንደሆነ ይገልፃል።

የዓለም የገንዘብ ድርጅት (International Mon­etary Fund – IMF) በበኩሉ፣ የመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነትን፣ ‹‹በተለምዶ መንግሥት ያቀርባቸው የነበሩ አገልግሎቶች በግሉ ዘርፍ በኩል እንዲቀርቡ የሚያስችል አሰራር›› ብሎ ይተረጉመዋል። በድርጅቱ ትርጓሜ መሰረት በመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነት አሰራር ስርዓት፣ መንግሥት የሚያቀርባቸው አገልግሎቶች በግሉ ዘርፍ ሲቀርቡ የግሉ ዘርፍ የአገልግሎቶቹን የፋይናንስ፣ የግንባታና የአስተዳደር/አመራር ኃላፊነቶችን ይረከባል።

የመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነት ‹‹የአገልግሎት አቅርቦትንና ተደራሽነትን ዓላማቸው ባደረጉ የመንግሥት ተቋማት እና ትርፍን ታሳቢ ባደረጉ የግል ዘርፍ ተዋንያን መካከል የሚደረግ የአገልግሎት አቅርቦትና አስተዳደር ስምምነት ነው›› የሚል ብያኔ የሚሰጠው ደግሞ የምጣኔ ሀብት ትብብርና ልማት ድርጅት (Organization for Economic Co-Operation and Development – OECD) የተሰኘው በይነ-መንግሥታዊ ተቋም ነው።

ሀገራትም ለመንግስትና የግል ዘርፍ አጋርነት የሚሰጡት ብያኔ እንደየሀገራቱ ነባራዊ ሁኔታዎች ይለያያል። ሀገራት የሚከተሏቸው የምጣኔ ሀብትና የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለሞች በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ አጋርነት በሚደረጉ ስምምነቶችም ሆኑ በአጠቃላይ አስፈላጊነታቸው ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድሩ እንደሚችሉ ይገመታል። ርዕዮተ ዓለሞቹ መንግሥትና የግሉ ዘርፍ በገበያ ውስጥ የሚኖራቸውን ተሳትፎ ስለሚወስኑ፣ በሁለቱ አካላት አጋርነት የሚከናወኑ ተግባራት ዓይነትና ወሰን የርዕዮተ ዓለሞቹ ጫና ሰለባ መሆናቸው አይቀርም።

በአጠቃላይ ‹‹የመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነት›› በሀገር ልማትና እድገት ውስጥ ዋነኛ ተዋንያን በሆኑት በመንግሥትና በግል ዘርፎች መካከል የሚደረግ የአገልግሎት አቅርቦትና የልማት ትብብር እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል። የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት መገለጫ ከሆኑት ባህርያት አንዱ የግሉ ዘርፍ መንግሥት ለሕዝብ አገልግሎት ማቅረብ በሚገባው ዘርፍ ውስጥ መሳተፉ ነው። ቀጣይ ጊዜን ታሳቢ ያደረጉ የረጅም ጊዜ ስምምነቶች እና የሀብት፣ የክህሎትና የኪሳራ ክፍፍሎችም የአጋርነቱ ሌሎች መገለጫዎች ናቸው። አንዳንድ ሀገራት የመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነት የውል ጊዜ እስከ 25 ዓመታት ድረስ መዝለቅ እንዳለበት ደንግገዋል። የመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነት ወደፊት ሊመጣ የሚችለውን ኪሳራ ለሁለቱ ወገን ያከፋፍላል፤ ሁለቱ ተዋንያን ከኪሳራ በተጨማሪ ሀብትና ክህሎትንም ይጋራሉ።

በርካታ የጥናት ውጤቶች እንደሚያሳዩት፣ የመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነት ለኢንቨስትመንት ዘርፍ እድገት ትልቅ ሚና አለው። የባባሳሄብ አምቤድካር ዩኒቨርሲቲ (ሕንድ) መምህራኑ ጓራቭ ሲንግ እና መሐመድ ካሃን የመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነት በማኅበረሰብ ግንባታና በሀገር እድገት ላይ የሚኖረውን ሚና በዳሰሱበት ‹‹The Role of Public Private Partnership (PPP) in Building Society›› በተሰኘው ጥናታቸው፣ ብዙ የዓለም ሀገራት፣ በተለይም ታዳጊዎቹ፣ በመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነት በኩል የመሰረተ ልማት ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት በርካታ ተግባራትን እንደሚያከናወኑ ጠቁመዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነት የመልካም አስተዳደር ስርዓትን ለማስፈን ሁነኛ ግብዓት ሆኖ እያገለገለ እንደሚገኝም አመላክተዋል። ይህ አሰራር በተለይም የማኅበራዊ አገልግሎቶችን ተደራሽነት ለማስፋት ለሚያስፈልገው ፋይናንስ ተጨማሪ ምንጭ በመሆን ለኢንቨስትመንት ዘርፍ ማደግ ከፍተኛ ሚና እንዳለው የባለሙያዎቹ ጥናት ያስረዳል። በአጠቃላይ፣ የመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነት የአገልግሎቶችን ተደራሽነትና ጥራት በማሳደግ ለኢንቨስትመንት ዘርፍ እድገት ምቹ መደላድሎችን የሚፈጥር ግብዓት ነው።

የዓለም ባንክ፣ ሀገራት የመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነትን እንዲተገብሩና አሰራሩ እንዲጠናከር ድጋፍ ከሚያደርጉ ተቋማት መካከል በግንባር ቀደምነት ይጠቀሳል። የባንኩ የጥናት መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ ከ134 በላይ የዓለም ሀገራት የመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነት አሰራርን በተግባር ላይ አውለዋል። ከ15 እስከ 20 በመቶ የሚሆነው የእነዚህ ሀገራት የመሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት (Infrastructure Investment) የተገነባውም በዚሁ አጋርነት አማካኝነት ነው።

ባንኩም ይህን የአሰራር ስርዓት ለሚተገብሩ ሀገራት በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን (International Finance Corporation – IFC) እና በባለብዙ ወገን የኢንቨስትመንት ዋስትና ድርጅት (Multilateral Invest­ment Guarantee Agency – MIGA) በኩል ከፍተኛ የፋይናንስ ድጋፍ የሚያደርግ ሲሆን፣ የአሰራሩ ትግበራ የሃገራቱን የመሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት ተደራሽነትና ጥራትን ለማሳደግ ላቅ ያለ አስተዋፅዖ እንዳበረከተ ባንኩ በክትትልና ድጋፉ ምስክርነቱን ሰጥቷል።

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መንግሥትም በተለያዩ ጊዜያት ከተለያዩ የግል ድርጅቶች ጋር በጥምረት የመሠረተ ልማት አውታሮችን የመገንባት ተግባራትን ሲያከናውን ይታወቃል። እንዲህ ዓይነቱ አሠራር በተለያዩ ጊዜያት በወጡት የኢንቨስትመንት አዋጆች ውስጥም እውቅና ያገኘና የተደነገገ ነው።

የአጋርነቱን ትግበራ የተሻለ ውጤታማ ለማድረግና በትግበራው ሂደት የሚታዩ ክፍተቶችን ቅርፅ ለማስያዝ ያስችላል የተባለው ‹‹የመንግሥትና የግል አጋርነት አዋጅ›› (1076/2010) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መፅደቁ ይታወሳል። የመሠረተ ልማት ሥርዓቱን ጨምሮ የአገሪቱን የልማት ግቦች ከማሳካት አንጻር የግሉ ሴክተር ወሳኝ ስትራቴጂያዊ አጋር መሆኑ በአዋጁ ላይ የተመላከተ ሲሆን፤ አዋጁ ግልጽነትን፣ ፍትሐዊነትን እና ዘላቂነትን ለማስፈን እና በግሉ ዘርፍ የፋይናንስ አቅም የሚገነቡ የመሠረተ-ልማት ፕሮጀክቶችን ለማበረታታት የሚረዳ አመቺ የሕግ ማዕቀፍ እንደሆነም ተጠቁሟል።

የመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነት እንዲጠነክር ምቹ ሁኔታ ከሚፈጥሩ አሰራሮች መካከል አንዱ በሁለቱ ዘርፎች መካከል የሚደረግ የጋራ ምክክር (Public-Private Dialogue) ነው። የጋራ ምክክሩ የግሉ ዘርፍ ያሉበትን ችግሮች ለመንግሥት በማቅረብ የግሉ ዘርፍ ጠንካራና ተወዳዳሪ ሆኖ በመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነት ፕሮጀክቶች ላይ እንዲሳተፍ ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራል።

በኢትዮጵያም የግሉ ዘርፍ ከመንግሥት አካላት ጋር ምክክር እንዲያደርግ እድል የፈጠረው ብሔራዊ የመንግሥትና የግል ዘርፍ የምክክር መድረክ (Nation­al Public-Private Dialogue)፣ የግሉ ዘርፍ ያሉበት ችግሮች በጥናት ተለይተው ለመንግሥት ሲቀርቡበት ቆይቷል።

የግሉ ዘርፍ ወኪል በሆነው የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የሚዘጋጀው ይህ የምክክር መድረክ፣ በወቅቱ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና በምክር ቤቱ መካከል በተደረገ ስምምነት፣ በ2002 ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን፣ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ መካከል ያለውን የልማት ግንኙነትና አጋርነት ለማጎልበት እንዲሁም ለንግድና ኢንቨስትመንት ማነቆ የሆኑ ችግሮች እልባት እንዲያገኙና ለአፈፃፀማቸው ክትትል የሚደረግበት ስርዓት እንዲኖር ታስቦ የተቋቋመ መድረክ ነው።

ይህ መድረክ በ2007 ዓ.ም በዓለም አቀፍ ደረጃ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ የምክክር መድረኮችን በሚደግፈውና በየዓመቱም ክንውኖቻቸውን በሚገመግመው ዓለም አቀፉ የግልና የመንግሥት ምክክር መድረክ ኮሚቴ ‹‹ለረዥም ጊዜ ዘላቂ የሆነ የምክክር መድረክ በማካሄድ›› እውቅና እንደተሰጠውም ይታወሳል።

አራተኛው ሀገር አቀፍ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ የምክክር መድረክም በኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት እና በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ትብብር የግሉ ዘርፍ ተዋንያንና የመንግሥት አካላት ተወካዮች በተገኙበት በቅርቡ መካሄዱ ይታወሳል። በመድረኩ ላይም የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚደንት አቶ ሰብስብ አባፊራ፣ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ የምክክር መድረክ መንግሥትና የግሉ ዘርፍ ስለንግዱ ማኅበረሰብ ችግሮች የሚወያዩበትና ቀጣይ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን የሚያስቀምጡበት መድረክ እንደሆነ ይገልጻሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት፣ የምክክር መድረኩ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ መካከል ውይይትን፣ ትብብርንና ስትራቴጂካዊ አጋርነትን ለማጎልበት ወሳኝ መድረክ ሆኖ ያገለግላል። በግሉ ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እንዲሁም በማክሮ ኢኮኖሚው የለውጥ ሂደት የግሉ ዘርፍ የሚጠበቅበትን እንዳያበረክት እንቅፋት የሆኑ ተግዳሮቶችን በመለየት መፍትሄ ለማበጀት የላቀ ሚና ይኖረዋል።

‹‹የአጋርነት መድረኩ በጥናት የተለዩ የግሉ ዘርፍ ችግሮችና የመፍትሄ አቅጣጫዎች ይቀርቡበታል። በመንግስትና በግሉ ዘርፍ ምክክር መደረጉ በንግድ ሥርዓት ውስጥ የሚያጋጥሙትን ክፍተቶች በጋራ ተወያይቶ ለመሙላት ከማገዙም ባሻገር፤ የንግድ ስርዓቱን ለማዘመን፣ በዘርፉ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት፣ የልማት አጋርና አብሮ የመስራት ባህልን ለማዳበር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል›› በማለት ይገልፃሉ።

አቶ ሰብስብ ምክር ቤቱ ንግድና ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ እና የግሉ ዘርፍ የኢኮኖሚውን የመሪነት ሚና በአግባቡ እንዲወጣ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፣ በቀጣይም የግል ዘርፍና መንግስት ተቀራርበው እንዲሰሩና ለሚያጋጥሙ ችግሮች አፋጣኝ መፍትሄ እንዲያገኙ ለማድረግ የግሉ ዘርፍ ድምጽነቱን ለማጉላት እንደሚሰራም ተናግረዋል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዶ/ር ካሳሁን ጎፌ፣ የአጋርነት ምክክሩ የግሉ ዘርፍ ተግዳሮቶች የፖሊሲ መፍትሄዎችን እንዲያገኙ፣ የልማት አጋርነት እንዲጎለብትና አብሮ የመስራት ባሕል እንዲዳብር፣ በሀገራዊ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ላይ የጋራ ግንዛቤና መግባባት እንዲፈጠር እንዲሁም ባለሃብቶች ጥራት ያላቸውና ተወዳዳሪ ምርቶችን እንዲያመርቱ እና በወጪ ንግድ ዘርፎች ላይ በስፋት እንዲሰማሩ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር እንደሚያግዝ ያስረዳሉ።

‹‹መድረኩ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ መካከል ድልድይ ሆኖ ያገለግላል። ከተለያዩ ዘርፎች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት እንዲሰባሰቡና ሃሳብ እንዲለዋወጡ እድል በማመቻቸት ለምጣኔ ሀብት መሰናክል የሆኑ ችግሮች መፍትሄ እንዲያገኙ ይረዳል፤ የወል አሸናፊነት እንዲኖር ለማድረግ ያስችላል። በመረጃ ላይ የተመሰረተ ፖሊሲ ለመቅረፅ የሚያስችሉ ገንቢ አስተያየቶችን ለማግኘትም ያግዛል›› ሲሉ ያብራራሉ።

የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚው ውስጥ የላቀ ሚና እንዲኖረው በማሰብ መንግሥት የተለያዩ የምጣኔ ሀብት እርምጃዎችን/ማሻሻያዎችን እየወሰደ እንደሚገኝ የተናገሩት ዶ/ር ካሳሁን፣ በእነዚህ ማሻሻያዎች አማካኝነት የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚው ውስጥ ያለው ድርሻ እያደገ እንደመጣም ይገልፃሉ።

ከ2010 ዓ.ም ሀገራዊ ለውጥ ወዲህ፣ ባለፉት አምስት ዓመታት፣ መንግሥት ዘርፈ ብዙ የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ መርሃ ግብሮችን ተግባራዊ ማድረጉ ይታወቃል። ከእነዚህ መርሃ ግብሮች አንዱ፣ ሀገር በቀል የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ መርሃ ግብር (Homegrown Economic Reform Pro­gram) ነው። የመርሃ ግብሩ ዓላማ አምራች የሆነውን የሠው ኃይል የሚሸከም የሥራ እድል እና የተረጋጋ የማክሮ-ኢኮኖሚ ከባቢ በመፍጠር እንዲሁም የግል ዘርፍ መር (Private Sector-Led) የሆነ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በመገንባት ዘላቂና ፈጣን የምጣኔ ሀብት እድገት ማስመዝገብ ነው።

የኢንቨስትመንት አዋጅና የንግድ ሕግ ማሻሻያዎች፣ ብሔራዊ የንግድና ቢዝነስ ስራ አመቺነት ማሻሻያ መርሃ ግብር (National Ease of Doing Business Initiative) እንዲሁም ከዓለም አቀፍ የግብይት ስርዓት ጋር ዘመናዊ ትስስር ለመፍጠር የፋይናንስ ዘርፉ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት እንዲሆን ተወስኖ ውሳኔውን ለመተግበር እየተደረጉ ያሉ ዝግጅቶች የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ መርሃ ግብሩ አካል ናቸው። ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ በቅርቡ ወደተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር ትግበራ ገብታለች።

እነዚህ ማሻሻያዎች የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚው ውስጥ የሚኖረውን ሚና ለማሳደግ ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርጉ ይታመናል። የግሉ ዘርፍ በምጣኔ ሀብት ውስጥ የሚኖረው ሚና ሲያድግ ደግሞ ለኢንቨስትመንት ዘርፍ ማደግ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥረው የመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነት ይጠናከራል።

አንተነህ ቸሬ

አዲስ ዘመን ሐሙስ መስከረም 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You