የወሊሶ ከተማ የኢንቨስትመንት ጥሪ

ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንቱ ዘርፍ በሰጠችው ትኩረት የኢትዮጵያ ባለሀብቶች እንዲሁም የውጭ ባለሀብቶች በዘርፉ በስፋት የተሰማሩበትና እየተሰማሩ ያሉበት ሁኔታ ይታያል:: ሀገሪቱ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን/አሁን ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ተብለዋል/፣አግሮ ኢንዱስትሪዎችን ገንብታ የመስሪያ ሼዶችንና የለሙ ቦታዎችን በማመቻቸት የውጭና የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ገብተው እንዲሰሩ እያደረገች ትገኛለች::

ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮችም በበኩላቸው ለኢንቨስትመንት የሚሆን መሬት በማዘጋጀት፣ መሰረተ ልማት በማሟላት የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች በዘርፉ እንዲሰሩ ምቹ ሁኔታዎች ፈጥረዋል፤ እየፈጠሩም ናቸው:: በዚህም በርካታ የክልል እና የከተማ አስተዳደር ከተሞች ሰፋፊ የኢንዱስትሪ ማዕከላት ለመሆን የበቁበት ሁኔታም ተፈጥሯል::

የኢንዱስትሪ ልማቱ ሀገሪቱ ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች ለመተካት፣ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኙ የወጪ ምርቶችንም በሀገር ውስጥ ለማምረት ምቹ ሁኔታ ፈጥሮላታል:: በዚህም ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በስፋት ማምረት ተጀምሯል:: ባለፈው በጀት ዓመት ከሁለት ቢሊየን ዶላር በላይ የሚያወጡ ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች መተካት የተቻለበትን ሁኔታ ለእዚህ በአብነት መጥቀስ ይቻላል:: የወጪ ምርቶችን በልዩ የኢኮኖሚ ዞኖቿ በኩል እያመረተች ለውጭ ገበያ እያቀረበች ትገኛለች::

የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴው በተለይ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ልማት በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ተጠናክሮ ቀጥሏል:: በርካታ የክልል ከተሞችም ያላቸውን እምቅ የኢንቨስትመንት አማራጮች በመለየት፣ እነዚህን እምቅ ሀብቶች ባለሀብቶች ማልማት የሚችሉባቸውን ምህዳሮች በመፍጠርና ለባለሀብቶች ጥሪ በማቅረብ የበኩላቸውን ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ:: በቀጣይም በዘርፉ ብዙ ርቀት ለመጓዝ አቅደው እየሰሩም ናቸው::

የኦሮሚያ ክልሏ ወሊሶ ከተማ ከእነዚህ ከተሞች አንዷ ናት:: ከአዲስ አበባ ጅማ በሚወስደው ዋና መንገድ ከአዲስ አበባ 114 ኪሎ ሜትር ላይ የከተመችው ይህች ከተማ ከተመሰረተች 98 ዓመታት መቆጠራቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ:: በአየር ጸባይዋና በተፈጥሮ ሀብቶቿ የምትታወቅ ሲሆን፣ በተለይ በግብርና ልማቱ የሚታወቀው የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን መቀመጫ ከተማ ናት::

ከተማዋ ለተለያዩ የኢንቨስመንት ሥራዎች ተመራጭ የሚያደርጓት አቅሞች እንዳሏት የከተማዋ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል:: ተጠሪነታቸው ለኦሮሚያ ክልል መንግሥት ከሆኑ በርካታ የክልሉ ከተሞች መካከልም አንዷ ናት::

ከተማዋ የግብርና ምርቶች ማቀነባበርን/አግሮ ፕሮሰሲንግን/ጨምሮ ለግብርና፣ ለማኑፋክቸሪንግና ለአገልግሎት ዘርፎች ኢንቨስትመንት ምቹ ስለመሆኗ ይገለጻል:: በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ከለሙት የቱሪዝም መዳረሻዎች አንዱ ከሆነው የወንጪ ሀይቅ በ34 ኪሎ ሜትር ላይ መገኘቷ ሌላው በቱሪስት አገልግሎት ዘርፍ መሰማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች ምቹ ስፍራ እንድትሆን የሚያስችላት ሆኗል::

የወሊሶ ከተማ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አበበ ድሪባ ጅግሳ እንዳሉት፤ የከተማዋ መሬት አቀማመጥ ሜዳማነት፤ ለአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ መገኘቷ፣ ይህም ባለሀብቶች ምርቶቻቸውን ለሀገር ውስጥ ገበያም ሆነ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑ ከተማዋን በተለያዩ ኢንቨስትመንቶች መሰማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች ምቹ ያደርጓታል::

መንግሥት ልዩ ትኩረት ለሰጠው ለአምራች /ለማኑፋክቸሪግ/ኢንዱስትሪ ዘርፍም የከተማዋን ኢንቨስትመንት ምቹ ለማድረግ ጽህፈት ቤቱ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸው፣ በዚህ ዘርፍ ለሚሰማሩ ፕሮጀክቶች ሰፊ የሰው ኃይል እንዳለም ጠቁመዋል:: ለኢንቨስትመንት ዘርፉ የሚያስፈልጉ መሰረተ ልማቶች የተሟሉ መሆናቸውንም ጠቁመዋል::

እሳቸው እንዳሉት፤ ለከተማዋ አዲስ የኤሌክትሪክ ማከፋፈያ እየተገነባ ይገኛል፤ ይህም ለዘርፉ የሚያስፈልገውን የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል:: ለኢንቨስትመንት የሚውል መሬት ዝግጁ በማድረግ በኩል ተሰርቷል፤ በውሃ መሰረተ ልማትም በኩልም ከከተማዋ አልፎ በአቅራቢያዋ ለሚገኘው የገጠር አካባቢዎች ሕዝብ ጭምር ሊውል የሚችል አዲስ የውሃ መሰረተ ልማት ዝርጋታ እየተካሄደ ነው::

ጽህፈት ቤቱ የከተማዋን የኢንቨስትመንት ፍሰት የሚጨምርና የሚያስፋፋ ተግባር እያከናወነ መሆኑንም አስታውቀው፣ 144 ሄክታር መሬት በማዘጋጀት ባለሀብቶችን እየተጠባበቀ ያለበትን ሁኔታ ለእዚህ በአብነት አመልክተዋል::

በከተማዋ በአሁኑ ወቅት በአገልግሎት፣ ማኑፋክቸሪንግ እና እርሻ ኢንቨስትመንት 215 ባለሀብቶች ተሰማርተው እየሰሩ መሆናቸውን አቶ አበበ ጠቅሰው፣ ኢንቨስትመንቶቹ ለአምስት ሺ 500 ዜጎች የሥራ እድል መፍጠራቸውንም ተናግረዋል::

እሳቸው እንዳሉት፤ እስከ አሁን በከተማዋ በኢንቨስትመንት በኩል እየተሰራ የቆየው በብዛት በአገልግሎት ላይ ነበር:: ማኑፋክቸሪንግና እርሻ ላይ በጥቂቱ ነበር:: አሁን የመንግሥት አቅጣጫ ማኑፋክቸሪንግ እንደመሆኑ ጽህፈት ቤቱም በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል::

ይህ ማለት ግን አገልግሎትና ግብርና አያስፈልግም ማለት አይደለም፤ ይበልጥ ትኩረት የሚሰጠው ለማኑፋክቸሪግ ኢንዱስትሪ መሆኑን ለመግለጽ ነው:: ከተማዋ ለወንጪ ሀይቅ ያላት ቅርበት በአገልግሎት በተለይ በሆቴል ልማት ላይ በትኩረት መስራትን ይጠይቃል፤ ይህ ሥወራም ቢሆን ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ተደርጎ መሰራት ያለበት እንደመሆኑ በእዚህም ዘርፍ ላይ በትኩረት ይሰራል::

አገልግሎትን በተመለከተ የወንጪ ሀይቅ መልማት ከተማዋም ወደዚህ የቱሪስት መዳረሻ የሚሄዱትንና ከመዳረሻው የሚመጡትን ቱሪስቶች የሚመጥን የሆቴልና መሰል አገልግሎቶች እንዲኖሯት ማድረግ ላይ እንደሚሰራም ተናግረዋል::

ማኑፋክቸሪንግ የመንግሥት የልማት አቅጣጫ ነው፤ መንግሥት የማኑፋክቸሪግ ኢንዱስትሪው እንዲስፋፋ፣ ያሉበት ችግሮች በመፍታት የሚጠበቅበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ ለማድረግ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን እያካሄደ እንደሚገኝ አቶ አበበ ጠቅሰው፣ ‹‹እኛም ኢትዮጵያ ታምርት ንቃናቄን ተቀላቅለናል፤ በዚህም በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የሚሰማሩ ባለሀብቶችን የማነቃቃት ሥራ ሰርተናል፤ እኛ በብዛት ለመቀበል የምንፈልገው በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ የሚሰማሩትን›› ሲሉ አስገንዝበዋል::

በዚህም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች ለመተካት፣ ከውጭ ለሚገቡ ምርቶች የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ ለማስቀረት፣ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ለማምረት እንዲሁም የሀገር ውስጥ ጥሬ እቃዎችን ለመጠቀም እንዲሁም በወጪ ምርቶች ላይ እሴት ጨምሮ ለመላክም እየተሰራ መሆኑ ይታወቃል::

ይህን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ማኑፋክቸሪንግ ላይ መሰማራት የሚፈልጉ ባለሀብቶች የፕሮጀክቱን አይነት ሊመርጡ ይችላሉ:: ባለሀብቶች ከልምዳቸው፣ ከካፒታላቸውና ከመሳሰሉት አኳያ የሚመርጡን ዘርፍ እነሱ ያውቃሉ:: እኛ ግን በየትኛውም የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸውን እንቀበላለን ሲሉ አብራርተዋል::

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በከተማዋ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው ባለሀብቶች ብዙም አልነበሩም ሲሉም ጠቅሰው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ፍላጎቱ ያላቸው ባለሀብቶች እየታዩ መምጣቸውንም ኃላፊው ገልጸዋል::

ባለሀብቶች የምስማርና ቆርቆሮ፣ ሳሙና ያሉት ፋብሪካዎች፤ የቆዳ ኢንዱስትሪዎችን እያቋቋሙ እንደሚገኙ አመልክተው፣ ዘርፉ በጣም አዋጭ መሆኑን በመገንዘብ በርካቶች እየገቡበት መሆናቸውን ገልጸዋል:: አዋጭነቱን እየተመለከቱ ሌሎች ፍላጎት እያሳዩ መምጣታቸውን፣ በከተማዋ በጥቃቅንና ኢንዱስትሪ ተደራጅተው ሲሰሩ ከቆዩት መካከል ወደማኑፋከቸሪንግ ኢንዱስትሪው እየገቡ እንደሚገኙም አቶ አበበ አስታውቀዋል::

ጽህፈት ቤቱ የከተማዋን የኢንቨስትመንት አማራጮችና የተፈጠሩ ምቹ ሁኔታዎች በማስተዋወቅ በኩልም በስፋት እየሰራ ይገኛል:: አቶ አበበ በተያዘው በጀት ዓመት በከተማ ደረጃ የኢንቨስትመንት ፎረም ተዘጋጅቶ እንደነበርም አስታውሰው፣ ፎረሙም በመገናኛ ብዙሃን ሽፋን እንዲያገኝ መደረጉን ገልጸዋል:: ይህን ተከትሎም በርካታ ባለሀብቶች በከተማዋ የተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ተሰማርተው ለመስራት ፍላጎት እያሳዩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል::

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን ስንቀላቀል ትኩረታችን በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ላይ ሆኗል:: በዚህም ላይ በመስራት ባሉት ባለሀብቶች ላይ ግንዛቤ ፈጥረናል ያሉት ኃላፊው፣ ሌሎች ሲመጡም በማኑፋክቸሪንግ እሳቤ እንዲመጡ ለማድረግ በቂ መሬት አዘጋጅተን እየጠብቅናቸው ስለመሆናችን እያስተዋወቅን ነው፤ በዚህም ባለሀብቶቹ ወደ ከተማዋ ቢመጡ የመሥሪያ ቦታ፣ ለዘርፉ የሚያስፈልጉ የኤሌክትሪክ፣ የውሃና የመሳሰሉት መሰረተ ልማቶች ችግር እንደማይገጥማቸው ጭምር እየነገረን ነው ሲሉም አብራርተዋል::

ባለሀብቶቹ እነዚህን ምቹ ሁኔታዎች ተጠቅመው ራሳቸውንም ከተማዋንም እንዲጠቅሙ ጽህፈት ቤቱ በፎረሙ ላይ ጥሪ ማቅረቡን ጠቅሰው፣ በዚህም ባለሀብቶች ፍላጎት አሳይተው ጥያቄዎች መጥተዋል፤ ሌሎችንም በዚሁ መልኩ ለማስተናገድ ዝግጁ ነን ይላሉ::

በክልል ደረጃ በሚዘጋጁ የኢንቨስትመንት ዘርፉ መድረኮች ላይ በመገኘት ከተማዋ ያላትን እምቅ አቅም እያስተዋወቅን እንገኛለን፤ እኛ ብቻ ሳንሆን ሌሎችም ይህንኑ እያደረጉ ናቸው ያሉት አቶ አበበ፣ እንደ በፌዴራል ደረጃ ግን ይህን አላደረግንም:: በሚዲያ ያደረግነው የማስተዋወቅ ሥራ በቂ ነው ባይባልም አንደ ሀገር መልዕክት ያስተላልፋል የሚል እምነት አለን ብለዋል::

በ2017 በጀት ዓመት 60 ባለሀብቶችን ለመሳብ ታቅዶ እንደነበር ጠቅሰው፤ ይህን ለመፈጸም በቂ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል:: ከእነዚህ ውስጥ ባለፉት ወራት ወደ 23 የሚጠጉ ባለሀብቶችን ተቀብለናል ብለዋል:: ቀሪውን እቅድ ለማሳካት ደግሞ እስከ አሁን የተከናወኑት የፕሮሞሽን ሥራዎች እንዳሉ ሆነው በተለያዩ ማስታወቂያዎች ለባለሀብቶች ጥሪ እንደሚቀርብ ጠቁመዋል:: የሕዝብ ተሳትፎ በሚታይባቸው መድረኮችና በስብሰባዎች ላይ በመገኘት የምናካሂደውን የማስተዋወቅ ሥራ እናጠናክራለን ብለዋል::

እነዚህ ባለፉት ወራት ወደ ኢንቨስትመንቱ መጥተዋል የተባሉት ፕሮጀክቶች ለዜጎች ምን ያህል የሥራ እድል ፈጥረዋል፤ አጠቃላይ ካፒታላቸውስ ስንት ነው በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽም ወደ 2000 ለሚሆኑ ሰዎች የሥራ እድል ይፈጥራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸው፣ የፕሮጀክቶቹ ካፒታል ወደ አንድ ቢሊየን ብር እንደሚጠጋም አስታውቀዋል:: የፕሮጀክቶቹ መምጣት ለከተማዋ ገቢና እድገትም አስተዋጽኦቸው ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፣ እኛም በእዚህ ሁሉ እሳቤ መሰረት እየሰራን ነው›› ብለዋል::

አካባቢው የግብርና አካባቢ መሆኑን ጠቅሰው፣ አግሮ ፕሮሰሲንግ ላይ ወደ ሥራ የገቡ የዱቄትና መኮሮኒ ፋብሪካዎች እንዳሉ ገልጸዋል:: ገና እየጀማመሩ ያሉ ኢንዱስትሪዎች እንዳሉም አመልክተዋል::

በከተማዋ ኢንቨስትመንት ለመሰማራት ፍላጎት አሳይተዋል ካልኳቸው መካከል የተወሰኑት በእዚህ በአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ የሚሰማሩ ናቸው ሲሉ፣ ጠቅሰው፣ ከወተት ልማት ጋር በተያያዘ እስከ አሁን የተሰራ ባይኖርም አሁን ፍላጎት ያሳዩ ተገኝተዋል ብለዋል::

የወንጪ ሀይቅ ልማት የፈጠረውን እድል ለመጠቀም እንደሚሰራም አቶ አበበ ጠቁመዋል:: ወደ ሀይቁ የሄዱም ሆኑ ከሀይቁ የሚመለሱ ሊያርፉባቸው እንዲሁም ዘና ሊሉባቸው የሚችሉ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች እንዲገነቡ ለማድረግም ለባለሀብቶች ጥሪ እየቀረበ መሆኑን ገልጸዋል::

አቶ አበበ እንዳስታወቁት፤ ከዚህ በኋላ በተለይ በአገልግሎትና ቱሪዝም ዘርፍ የሚሰማሩ ባለሀብቶች ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎችን ብቻ እንዲሰሩ እየተደረገ ይገኛል፤ በቀጣይም በእዚህ አገልግሎት ለመሰማራት ፍላጎት ያሳዩም ይህን ታሳቢ አድርገው እንዲሰሩ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ተካሂዷል:: በዚህ ተስማምተው መሬት የወሰዱ ባለሀብቶችም አሉ::

ቱሪስቶች በልዩ ሁኔታ እንዲስተናገዱ፣ ደረጃቸውን የጠበቁ አገልግሎቶች እንዲያገኙ፣ የጎብኚዎቹንም የኢትዮጵያንም ባህሎች በጠበቀ መልኩ እንዲያገለግሉ ለሆቴል ባለቤቶች ግንዛቤ እንዲፈጠር ተደርጓል፤ ቀጣዩን ኢንቨስትመንትም ይህን ታሳቢ ያደረገ አንዲሆን ይሰራል::

ከተማዋ ለኢንቨስትመንት ምቹ ብትሆንም ብዙም ጎልታ እንዳልወጣች ይነገራልና ይህን ለመቀየር ብቻችሁን ሰርታችሁ ትችሉታላችሁ ወይ? በሚል ለቀረባለቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ እንደተባለው ወሊሶ የእድሜዋን ትልቅነት ያህል ብዙም ኢንቨስትመንት አይታይባትም ሲሉ እሳቸውም ገልጸዋል:: ይህን ገጽታዋን ለመቀየርም በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ያለውን ምቹ ሁኔታ በመግለጽ ባለሀብቶች በኢንቨስትመንቱ እንዲሳተፉ ጥሪ በማቅረብ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል::

በከተማዋ ያሉት ኢንቨስትመንቶችም ቢሆኑ በአነስተኛ ካፒታል እየሰሩ የቆዩ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ አቅሙ ያላቸው ባለሀብቶች በኢንቨስትመንቱ እንዲሰማሩ ለማድረግ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ጥሪ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል:: ‹‹በሚዲያም ማስታወቂያዎችን እያሰራን ነው፤ ለወደፊትም ይሄው ተጠናክሮ ይቀጥላል›› ብለዋል::

እንደ እሳቸው ገለጻ፤ በከተማዋ ኢንቨስትመንት የሚሳተፉት ባለሀብቶች የአካባቢው ባለሀብቶች ብቻ አይደሉም፤ ከሌሎች አካባቢዎች የመጡ ባለሀብቶችም በኢንቨስትመንቱ ተሰማርተዋል:: በተለይ በማኑፋክቸሪንግ ላይ የሚሳተፉት በአብዛኛው ከሌላ አካባቢ የመጡ ናቸው:: የባለሀብቶች ተሳትፎ እንዲጨምር ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል::

የከተማዋ ተጠሪነት በቀጥታ ለክልሉ መንግሥት መሆኑን ጠቅሰው፣ ‹‹በክልል ደረጃ ጥያቄ የሚያቀርቡ ባለሀብቶች ወደ ወሊሶ እንዲመጡ ለማድረግ እድል ይፈጥራል ብለን እናምናለን፤ ያለው ሁኔታም ይህንኑ ያመለክታል›› ብለዋል::

ኃይሉ ሣህለድንግል

አዲስ ዘመን ሐሙስ መጋቢት 11 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You