የደመራ በዓል መንፈሳዊና ባሕላዊ እሴቶች

የኢትዮጵያ የመስቀል በዓል አከባበር በተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ የትምህርትና ባሕል ማዕከል በዓለም ቅርስነት ተመዝግቧል። ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ካስመዘገበቻቸው ዓለም አቀፍ ቅርሶች በተጨማሪ የመስቀል ደመራ ባሕላዊ ክብረ በዓል አስረኛውና የመጀመሪያው የማይዳሰስና የማይጨበጥ (ሕሊናዊ) ቅርስ በመሆን ለመመዝገብም በቅቷል። የደመራ በዓል መስከረም አስራ ስድስት ቀን በመስቀል ዋዜማ የሚከበር ሲሆን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ በታላቅ ናፍቆትና አክብሮት ከሚከበሩ በዓላት መካከልም አንዱ ነው።

የደመራ በዓል እንደ መሆኑ በመላው ሀገሪቱ በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ ከሀይማኖታዊ ስርዓት ባለፈ የተለያዩ ባሕላዊ ክንዋነዌችም የሚፈጸሙበት ነው። የደመራ የአደባባይ በዓል እንደመሆኑ ሁሉ በርካታ ሀይማኖታዊና ባሕላዊ ክንዋኔዎች የሚካሄዱበትም ነው። እኛም ለዛሬው ዝግጅታቸን የደመራ በዓል መንፈሳዊና ባሕላዊ እሴቶች ምን ይመስላሉ ስንል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅና የብዙኃን መገናኛ ቴሌቪዥን መርሐ ግብር አዘጋጅ ከሆኑት መጋቤ ምስጢር ሣህሉ አድማሱ ቆይታ አድርገናል። እንደሚከተለውም አቅርበነዋል።

አዲስ ዘመን ፤ ደመራ ምን ማለት ነው ታሪካዊ አመጣጡስ እንዴት ነው ?

መጋቢ ምስጢር ሣህሉ ፤ ደመራ የሚለው ቃል ደመረ፣ ጨመረ፣ አንድ አደረገ፣ አዋሀደ ከሚለው የግእዝ ቃል የተወሰደ መሠረታዊ ቃል ሲሆን መሰብሰብን፤ መከመርን፤ መጨመርን ያመለክታል። ጥንታውያን አባቶች ሕዝባዊ አንድነትን ለመግለጽ፣ ብሔራዊ ኅብረትን ለመስበክ የተጠቀሙበት ትውፊታዊ ቃል ነው። ኢትዮጵያዊ አንድነት ኦርቶዶክሳዊ ኅብረት እጅግ ተዳክሞ በነበረበት ወቅት ሕዝባዊ ስሜትን ብሔራዊ ፍቅርን ሃይማኖታዊ እሴትን ለማጠናከር የተጠቀሙበት የመቀስቀሻ ዘዴ እንደሆነ ይነገራል።

የደመራ በዓል ታሪካዊ አመጣጥንም ስንመለከት እንደሚከተለው በታሪክ ተዘግቦ እናገኛለን። እየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ከወደቀበት መርገም ያድነው ዘንድ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ በሰላሳ ሶስት ዓመቱ በራሱ ፈቃድ በመስቀል ላይ ተሰቀለ። ከፍተኛ ወንጀል የሠሩ ሰዎች ብቻ ይሰቀሉበት የነበረው መስቀል ከጌታ ስቅለት በኋላ የመዳን ምልክት ሆነ። ዳሩ ግን ጌታ የተሰቀለበት መስቀል ተአምራትን በማድረጉ የታወኩ አይሁድ መስቀሉን ከሰዎች እይታ ለመሠወር በመወሰን ጉድጓድ ቆፍረው ቀበሩት። መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ ለ300 ዓመታት ያህል የቆሻሻ መጣያና ማከማቻም አደርገውት ቆይተዋል።

ከዚህ በኋላ ግን የታላቁ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት እሌኒ ከቁስጥንጥንያ የዛሬዋ (ኢስታንቡል) ተነሥታ የጌታችን የመድኃኒችን የእየሱስ ክርስቶስን መስቀል ከተቀበረበት ለማውጣት ወደ እየሩሳሌም ሔደች። እየሩሳሌም በደረሰች ጊዜ የጌታችን የመድኃኒታችን መስቀል ተአምራትን እንዳያደርግ አይሁድ በምቀኝነት ጉድጓድ ቆፍረው ቀብረውት ነበርና የተቀበረበትን ቦታ የሚያሳያት አጥታ በመፈለግ ብዙ ጊዜ አሳለፈች። በኋላ ግን አንድ ኪራኮስ የሚባል አረጋዊ አካባቢውን ነግሯት ደመራ አስደምራ ዕጣን አጢሳ ወደ ፈጣሪዋ ብትማፀን የዕጣኑ ጢስ ወደ ሰማይ ከወጣ በኋላ መንበረ ጸባዖት ደርሶ ተመልሶ መስቀሉ የተቀበረበትን ስፍራ (ጎልጎታ) እንዳመላከታት ተገልጿል።

እርሷም በምልክቱ መሠረት መስከረም አስራ ሰባት ቀን ቁፋሮው እንዲጀመር አዘዘች። ሰባት ወር ያህል ከተቆፈረ በኋላ መጋቢት አስር ቀን የጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ክቡር መስቀል አገኘች፤ ከእርሱ መስቀል ጋር ሁለት ወንበዴዎች የተሰቀሉበትን መስቀልም አብራ አግኝታው ስለነበር የጌታችንን መስቀል ለይታ ያወቀችበት መንገድ ግን ድውያንን በመፈወሱ፣ አንካሳ በማበርታቱ፣ ጎባጣን በማቅናቱ፣ ሽባን በመተርተሩ፣ የዕውራንንም ዐይን በማብራቱ ነው። ስለዚህም በየዓመቱ የመስቀልን በዓል ስናከብር ደመራ የምንደምረውና የምናበራው ንግሥት ዕሌኒን አብነት በማድረግ ነው።

አዲስ ዘመን ፤ የደመራ በዓል ማክበር መቼ ተጀመረ ?

መጋቢ ምስጢር ሣህሉ፤ ንግሥት ዕሌኒ መስቀሉን ባገኘች ጊዜ የደስታዋን መልዕክት ለልጇ እንዲደርሰው ለማድረግ እንዳሁኑ ዘመን ስልክና ሬድዮ ስላልነበር በዚያን ጊዜ መልዕክትን ሩቅ ሥፍራ ለማስተላለፍ ሲፈልጉ የሚጠቀሙበት መንገድ ነበር። ይህም በየተራራው ቃፊሮችን (መልእክተኞችን) መድበው መልዕክቱን ከሚተላለፍበት አቅራቢያ ተራራ ላይ ችቦ በማብራት ከርሱ በኋላ ተራራ ላይ ላለው መልዕክተኛ ምልክትን በማሳየት ነው። ቀጣዩም መልዕክተኛ ችቦን እያበራ፣ ለሌላኛው መልዕክተኛ በማሳየት መልዕክቱ መድረስ የሚገባው ቦታ እንዲደርስ በዚህ መልኩ ያስተላልፉ ነበር።

ንግሥት ዕሌኒም ይህንን ዘዴ በመጠቀም የመስቀሉ መገኘት ወሬ (የምሥራች ዜና) ቁስጥንጥንያ እንዲደርስ አደርጋለች። ልጇ ቆስጠንጢኖስም መልዕክቱ እንደደረሰው ወደ እየሩሳሌም ሂዶ እናቱን አግኝቶ ብዙ ስጦታ አበርክቶላታል። እርስዋም የቤተክርስቲያኑም መሠረት ወዲያው እንዲጣል ያደረገች ሲሆን የደመራ ማብራት ሥርዓትም ከዚህ ግዜ አንስቶ ሲያያዝ የመጣና ዛሬ የደረሰ ነው።

አዲስ ዘመን፤ የደመራ በዓል ከሃይማኖታዊ ስርዓቶች ባለፈ በየአካባቢው የተለያዩ ባሕላዊ ክንዋኔዎች አሉት እነዚህን ቢያብራሩልን ?

መጋቢ ምስጢር ሣህሉ፤ የመስቀል በዓል ሃይማኖታዊ በዓል ቢሆንም ኢትዮጵያውያን የተለያዩ ባህሎቻቸውን እና እሴቶቻቸውን በማሳየት የሚያከብሩት በዓል ነው። የውኃ በዓል ከሚባሉት ውስጥ በዓለ ጥምቀትና ቃና ዘገሊላ ተጠቃሽ ሲሆኑ፤ በዓለ እሳት ከሚበሉት ውስጥ ደግሞ ደብረ ታቦርና የደመራ በዓል ተጠቃሽ ናቸው። በዋናነት ሀይማኖታዊ ስርዓቱ ሲታይ በመስከረም አሥራ ስድስት ቀን በዘጠኝ ሰዓት አካባቢ ለመስቀል መታሰቢያ ሰው ሁሉ በየመንደሩ በየቀበሌው ቀጠን ያለ ርጥብ አጠናን ይዞ ዕንጨትን እየሰበሰቡ መደመርና በማቃጠል ነው። ይህም ሆኖ እንደ ጎንደር ፤ አክሱምና ላሊበላ ባሉ አካቢዎች ደመራ የማብራት ስነስርዓቱ የሚከናወነው በአስራ ሰባት ነው።

አዲስ አበባም የመስቀል ደመራ በዓል በደምቀት ከሚከበርባቸው ቦታዎች አንዷ ናት። በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የሚከበረውን የደመራ በዓል ለማክበር የሚታደሙት የሀይማኖቱ ተከታዮች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎችም ናቸው። በዓሉ በሚከበርብት ወቅትም ከፓትርያርኩ ጀምሮ በርካታ የሀይማኖት አባቶች የሚገኙ ሲሆን ከየአድባራቱ የሚመጡ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችና ሌሎች ዘማሪዎችም የሚታደሙበት ይሆናል። ከየቤተክርስቲያናቱ ከሚመጡት አገልጋዮች በተጨማሪም በርካታ የእምነቱ ተከታዮችም በተመሳሳይ ሀይማኖታዊ ስርዓቶችን ይታደሙበታል።

በተለመደው አካሄድ በዓሉ በሚከበርበት ቦታ የሚገኙ ምእመኖችም ሆኑ የቤተክርስቲያን አገልጋዮች ከሌላው ግዜ በተለየ የሚለብሷቸው አልባሳት አሉ። ከቅርብ ግዜ ወዲህ ደግሞ በየሰፈሩ ያሉ ወጣቶች የተለያዩ ሀይማኖታዊ ይዘት ያላቸው ተመሳሳይ ልብሶችን በማዘጋጀት በመስቀል አደባባይ የሚታደሙ ሲሆን የሚያሰሟቸው ዝማሬዎችና ምስጋናዎችም አሉ። የደመራ በዓል በዋናነት በመስቀል አደባባይ የሚከበር ቢሆንም በየሰፈሩና በየቤቱም ችቦ በማዘጋጀት ደመራ ተደርጎ ይበራል።

በዓሉ በገጠራማው የሀገራችን ክፍል ከሀይማኖታዊ ስርዓትነቱም ባለፈ የጥሩ ነገር ጅማሮ እየተደረገም ይወሰዳል። የመስቀል ደመራ በዓል የሚከበርበት የመስከረም ወር ጨለማ የሚባለው ክረምት አልፎ የብርሃን ወቅት የሆነው የሚጀምርበት ነው። በዚህም የወንዝ ሙላትን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ለወራት ሳይገናኙ የከረሙ የማኅበረሰብ ክፍሎችን በማገናኘቱ ረገድ የመስቀል በዓል የራሱ አዎንታዊ ሚና አለው። በዚህም የተነሳ በዓሉ ለበርካቶች የተነፋፈቀ የሚገናኝበት፤ ቤተሰብ የሚሰባሰብበት በመሆን ለብዙዎች የደስታ ምንጭም ነው።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የደመራ በዓል ለበርካታ ሰዎች የገቢ ምንጭ በመሆንም ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለው በዓል ነው። በከተሞች ለደመራ በዓል እንደ ሌሎች አውደ አመቶች ሁሉ አዲስ ልብስ መልበስ የተለመደ በመሆኑ ከልብስ ሽያጭ ጀምሮ በየአካባቢው የደሩ ገበያዎችን ማየት የተለመደ ትእይንት ነው። በገጠርም እንደ አካባቢው ባሕል የደመራን በዓል ታሳቢ በማድረግ የሚዘረጉ ገበያዎች ያሉ ሲሆን ለደመራ በዓል ተብለው የሚቀርቡ ምርቶችም አሉ።

አዲስ ዘመን፤ በኢትዮጵያ በተለያዩ ቦታዎች ያለው የደመራ በዓል አከባበር ምን ይመስላል ?

መጋቢ ምስጢር ሣህሉ የደመራና የመስቀል በዓል በሁሉም አካባቢዎች የሚከበር ቢሆንም በደቡብ የሀገራችን ክፍል በተለየ ድምቀትና ባሕላዊ ሁነት ይከበራል። በደቡብ የመስቀል በዓል ከሃይማኖታዊ ገፅታው በተጨማሪ በተለያዩ ባሕላዊና ማኅበራዊ እሴቶች ታጅቦ ይከበራል። የበዓሉ አከባበር እንደ አካባቢው ይለያያል። በጉራጌ፣ በከንባታ እና በዶርዜ የመስቀል በአል ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ይከበራል።

ለምሳሌ የመስቀል በዓል በቤተ ጉራጌ ከወትሮው የተለየ ቦታ አለው። በሥራ ምክንያት ተለያይተው የቆዩ ቤተሰቦች የሚገናኙበት ብቻም ሳይሆን በጋራ እየበሉና እየጠጡ የሚያከብሩት በዓል ነው። ለምሳሌ በቤተ ጉራጌ የመስቀልን በዓል ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ እንስሳትም ጭምር ያከብሩታል። ለወትሮው ወደ ግጦሽ ሜዳ ወጥተው የዕለት ጉርሳቸውን ያገኙ የነበሩ የቀንድም ሆኑ የጋማ ከብቶች ታጭዶ በተዘጋጀላቸው መኖ ከቤት ሳይወጡ በዓሉን እንዲያሳልፉ ይደረጋሉ። በቤተ ጉራጌ የመስቀል በዓል ለአንድ ቀን ብቻ ተከብሮ የሚያልፍ አይደለም።

በጉራጌ ብሔረሰብ ተወዳጅ የሆነው የመስቀል በዓል በቀናት ተከፋፍሎ የሚከበር በዓል ነው።

በቤተ ጉራጌ የመስቀል በዓል ከመስከረም አስራ ሁለት እስከ ጥቅምት አምስት ቀን ይከበራል። በእነዚህ ግዜያትም ከሕፃናት ጀምሮ ወጣቶች እና አዛውንቱ የብሔረሰቡን ባሕላዊ ምግብ ክትፎና ሌሎችን በመመገብ፣ በጭፈራና በፈንጠዝያ ያከብራሉ።

እያንዳንዱ ቀናትም የየራሳቸው ሥያሜና ባሕላዊ ክዋኔዎች አሏቸው። በዚህም መሰረት መስከረም አስራ ሶስት ቀን «ወሬት የኸና » ይባላል። ይህም ማለት በብሔረሰቡ ቋንቋ እንቅልፍ ከልካዩ ቀን የሚል ትርጓሜን የያዘ ሲሆን ለዚህም በምክንያትነት የጉራጌ ሴቶች ለበዓሉ ዝግጅት ለማድረግ የሚጓጉበት ቀን ከመሆኑ ጋር በተያያዘ እንደሆነ ይነገራል። በዚህ ቀን ለበዓሉ ለመመገቢያነት የሚያገለግሉ ባሕላዊ ቁሳቁሶች ለዓመት ከተሰቀሉበት ቦታ ወርደው በጥንቃቄ ተጣጥበው ዝግጁ ይሆናሉ። የፅዳት ተግባሩ ከአጥንት የተሰሩ ባሕላዊ የመመገቢያ ማንኪያዎች፣ ከሸክላ የተሰሩ ጣባዎች እና ሌሎችንም ይጨምራል። በተጨማሪ ቤቶች ከአፈር በተዘጋጁ ቀለማት ያሸበርቃሉ፤ አዳዲስ የኬሻ ጅባዎች ተነጥፎባቸው ለበዓሉ ዝግጁ ይሆናሉ። ይኸው ቀን በሶዶ ክስታኔ ጉራጌዎች «የወልቀነ» ወይም የሴቶች ቀን በመባል ይታወቃል።

መስከረም አስራ አራት ቀን «ደንጌሳት» ይባላል። ይህ ቀን ልጆች እና ሕፃናት ደመራ ደምረው ባሕላዊ ጭፈራዎቻቸውን የሚጫወቱበት ነው። «ደንጌሳት» ወይም የልጆች ደመራ/እሳት የሚል ትርጓሜን የያዘ ሲሆን ልጆች ቀኑን በተለያዩ ባሕላዊ ዘፈኖች ለቀኑ ስላበቃቸው ፈጣሪያቸውን ያመሰግኑታል።

ከደመራው በኋላም ሴቶች የጎመን ክትፎ በማዘጋጀት በእያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ውክልና በተዘጋጀ ጣባ በማድረግ ለምግብነት ያዘጋጃሉ። ባለትዳር የሆኑ የቤተ ጉራጌ አባላት በአንድ ጣባ የጎመን ክትፎው ተዘጋጅቶ ይሰጣቸዋል። ተምሳሌትነቱም የትዳር አጋሮች አንድ አካል አንድ አምሳል ናቸው ተብሎ ስለሚታመን የሚፈፀም ነው።

መስከረም አስራ አምስት «ወኸመያ» በቤተ ጉራጌ ዋናው የመስቀል በዓል የሚከበርበት ቀን ነው። «ወኸመያ» ወይም ዓመት በዓል የሚል ትርጉም አለው። በዚህ ቀን በሁሉም የብሔረሰቡ አካባቢዎች የእርድ ቀን ነው። በዕለቱም የሚታረደው በሬም ሆነ ወይፈን ሽማግሌዎች ፊት ቀርቦ ስለ ሃገር ሰላም እንዲሁም ስለ በዓሉ መልካሙን የመመኘት ምርቃት የሚወርድበት ነው። የቤተሰቡ አባላትም በእያንዳንዱ ምርቃት መጨረሻ ላይ ሶስት ጊዜ “ኬር ይሁን” በማለት ምርቃቱን ይቀበላሉ። ‘ኬር ይሁን’ ትርጉሙ ሰላም ይሁን እንደማለት ነው።

በተመሳሰይ በተለያዩ አካባቢዎችም የሚከወኑ ባሕላዊ ስርዓቶች አሉ። እነዚህን ስርዓቶች በሙሉ አንድ የሚያደርጋቸው ነገር አለ። በዓሉ ሁሉም ስለሰላም የሚመክሩበት ;ሁሉም ስለሰላም የሚሰባሰቡበትና የሚሰሩበት ነው። አንዳንዶቹ ዝግጅቶች ለወራት የሚደረጉ ናቸው። እንግዲህ በእነዚህ ግዜያት ውስጥ ሁሉ አንዱ ሌላውን እያሰበ እንዴት ሊያስደስተው ሊያሰትናግደው እንደሚችል ለፍቅሩ እየተጨነቀ ይቆያል ማለት ነው። ቤተሰብ በዚህ ደረጃ እንደሚዘጋጀው ሁሉ ብዙ ልጆችም ወላጆቻቸውን በዚህ ቀን ደስተኛ ለማድረግ ገንዘብ ከማስቀመጥ ጀምሮ በርካታ ስጦታዎችንም ሲያዘጋጁ ይቆያሉ። በዚህ አይነት በአብዛኛው ከአዲስ አበባ ወደተለያዩ አካባቢዎች የደመራ በዓልን ለማክበር የሚንቀሳቀሱ ሲሆን የደመራና የመስቀል በዓልን ታሳቢ በማድረግ ከተለያዩ የዓለም ሀገራት ወደኢትዮጵያ የሚመጡትም በርካቶች ናቸው። እነዚህ ሁሉ ነገሮች ከቤተሰብ ጀምሮ በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለው ሰላማዊ ግንኙነት እንዳይላላ ትልቅ ፋይዳ ያላቸው ናቸው።

አዲስ ዘመን፤ በኢትዮጵያ የሚከበረው የደመራ በዓል በሀገር ገጽታ ግንባታ ረገድ የሚኖረው ፋይዳ እንዴት ይታያል።

መጋቢ ምስጢር ሣህሉ፤ የመስቀል ደመራ በዓል በ2006 ዓ.ም በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት ተመዝግቧል:: ይህም በዓሉ ከሀገራችን አልፎ በሌሎች ልዩ ሥፍራ እንዲሰጠው ምክንያት ሆኗል። ከዚህ ግዜ ጀምሮም የበዓሉ አከባበርም በርካታ የውጭ ሃገር ቱሪስቶችን ቀልብ የሳበና የደመራው በዓል በሚከበርበት ወቅት በርካቶቹ ወደ ሀገራችን በመምጣት ታዳሚ መሆን ከጀመሩ ሰነባብተዋል። በበዓሉ የሚታደሙት የውጪ ዜጎች በአንድ ወገን ከየሀገራቸው ይህንን በዓል ለማክበር እቅድ ይዘው የሚታደሙ ሲሆን ፤ ሌሎች ደግሞ የስራ ጉዳይን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ናቸው። እነዚህ የውጪ ሀገር ዜጎች ለየትኛውም ጉዳይ ተገኝተው ቢሆን እንደ ሀገር የሚያስገኙልን ጠቀሜታ ሰፊ ነው።

እንደሚታወቀው በዓሉ በሚከበርበት ወቅት የሀገር ውስጥም ሆነ የውጪ በርካታ ሚዲያዎች ለዘገባ መገኘታቸው አይቀርም። ነግር ግን የበዓሉን አከባበር አስመልክቶ በእነዚህ የመገናኛ ብዙሀን ከሚተላለፈው ባላነሰ በበዓሉ የታደሙ የውጪ ዜጎች ስለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በርካታ በጎ ነገሮችን ለዓለም ተደራሽ የሚያደርጉበት እድልም ሰፊ። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በአንዳንድ አካባቢዎች ያሉ ችግሮች እንዳሉ ይታወቃል። እነዚህ ችግሮች የሀገርን ገጽታ የሚያጠለሹና ቀሪው ዓለም ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ያለውን ቀና እሳቤ የሚያበላሹ ናቸው። በተለይም እኛ ኢትዮጵያውያን እንግዳ በመቀበል ረገድ በጣም የሚያኮራ ታሪክ ያለን ሕዝቦች ነን። በየትኛውም ዘመን ቢሆን በኢትዮጵያ የነበሩ ነገስታትም ሆነ ሕዝቦቿ የትኛውንም በሰላም የመጣ እንግዳ አሳፍረው የመለሱበት ግዜ የለም። እንግዳ በመቀበልና በማስተናገድ ረገድ ያለው ታሪካችን ዛሬም ይኸው ነው። ይህንን አስጠብቆ በመቀጠል ረገድ የደመራ በዓል ይህንን የራሱ ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል።

በሌላ በኩል በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም በያሉበት የደመራ በዓልን ሲያከብሩ እንመለከታለን። እነዚህ ሰዎች የትም ሆነው በዓሉን ቢያከብሩ ኢትዮጵያውያን ሆነው ነው። ማለትም የሀገር ባሕል ልብስ ይለብሳሉ። አቅማቸው በፈቀደ በየእለቱ የሀገር ባሕል ምግቦችን ያዘጋጃሉ። የሚያሰሟቸው ዝማሬዎችና ሌሎች ክንዋኔዎችም በሙሉ ሀገርን የሚያሳዩ ይሆናሉ። ባጠቃለይም ሀገራችን ኢትዮጵያ ያላትን ሀገራዊ ማንነትና ተቀባይነት ለቀሪው ዓለም ለማሳወቅ ተደመራ በዓል ዝግጅቶች የየራሳቸው ድርሻ አላቸው።

ሌላው በሀገር ውስጥ የሚከበሩ ሕዝባዊ የአደባባይ በዓላትን ስናነሳ እንደ ሀገር የቱሪዝም እንቅስቃሴ መጠቀሱ አይቀርም። የደመራ በዓልም በርካታ ቱሪስቶችን በመሳብ ለሀገር ገቢ ከሚያስገኙት መካከል አንዱ ነው። በእርግጥ በአሁኑ ወቅት ያለው የውጪ ሀገራት የደመራ በዓል ታዳሚ ቁጥር ሊደረስበት ከሚገባው አንጻር ሲታይ በጣም ዝቅተኛ ነው ማለት ይቻላል። ይህንን ለማሳደግ በቅድሚያ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ያሉትን የደመራ አከባበር ለሕዝብ ማስተዋወቅ የሚጠበቅ ይሆናል።

አዲስ ዘመን ፤ የደመራ በዓል በሰዎች መካከል ስለሰላም የሚያስተላልፈው መልዕክት ምንድን ነው?

መጋቢ ምስጢር ሣህሉ፤ እንደ ሀይማኖት አስተምህሮ ቤተ ክርስቲያን ሰዎች የሰላም አባት ከሆነው ከእግዚአብሔር ጋር እንደተጣሉ እንዲሁም እርስ በእርሳቸውም በኑሮው ሰላምን ማግኘት እንዳልቻሉ ታስተምራለች። ይህ የታጣው ሰላምም የሰላም አለቃ በሆነው በክርስቶስ እንደገና በመስቀሉ ምክንያት እንደተገኘ ታውጃለች።

ሰላም የሰው ልጅ መሠረታዊ ፍላጎትና የሕልውና መሠረት ነው። ሰላም የሰው ልጆች ሁሉ የጋራ ፍላጎት እንጂ የአንድ ቡድን አመለካከት ወይም ርእዮተ ዓለም አይደለም። ሁሉን የሰው ልጆች ከምናገለግልባቸው ነገሮች አንዱ ሰላምን ለሰው ልጆች ሁሉ መስጠት ነው። ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን የሰላም መገኛ እየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ በማድረግ ለሰው ልጆች ሁሉ ሰላም እንዲሰፍን ትሰራለች። የመስቀል ደመራ በዓል መሠረትም ይህ ነው። ክርስቲያኖች በሙሉ የቤተ ክርስቲያንንም ሆነ የሀገርን ሰላም ለመጠበቅ ኃላፊነታችንን በአግባቡ መወጣት እንደሚጠበቅባቸው ይታመናል። በመሆኑም በደመራ በዓል በሚደረጉ ሀይማኖታዊ ትምህርቶች በሚከናወኑ ምስጋናዎች ሁሉ ሰላም የእግዚአብሔር ስጦታ መሆኑንና የሰላምን አስፈላጊነት ለሰው ልጆች ሁሉ የሚታወጅበትም ይሆናል።

ሌላው ከሰላም ጋር በተያያዘ የሚነሳው ጉዳይ ቤተሰብ ለማኅበረሰብ ብሎም ለሀገር መሰረት እንደሆነ ሁሉ በቤተሰብ ውስጥ የሚጀመር ሰላምም ከሰፈርና አካባቢ አልፎ ለሀገር የሚተርፍ ይሆናል። የደመራ በዓል ሲከበር ከላይ እንደተገለጸው ተራርቀው የኖሩ የቤተሰብ አባላት የሚሰባሰቡበት ስጦታ የሚለዋወጡበት መልካም ምኞት የሚገላለጹበት ነው። እንደ ደመራ ያሉ ሀይማኖታዊ በዓላት ሲከበሩ በንጹህ ሕሊና ከቂምና ጥላቻ በጸዳ ልቦና ሊሆን እንደሚገባ በተደጋጋሚ ትምህርት ይሰጣል። በተግባርም እንደምናየው በቤተሰብ ውስጥ ተኳርፎ እና ተቀያይሞ የደመራ እሳትን የሚለኩስ አይኖርም። በመሆኑም በዓሉ ይቅር ለመባባል የሚያስችልም ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ በበርካታ አካባቢዎች ለደመራ በዓል ዝግጅት ሲደረግ ሽማግሌዎች የተቀያየሙ ጎረቤታሞች ወይንም ቤተዘመዶች ካሉ ሰላም እንዲያወርዱ ይጠይቃሉ። የተለመደ ነገር ስለሆነም ብዙ ሰዎች ተቀብለው በይቅርታ አዲስ ግንኙነት የሚጀምሩበት ሁኔታ ይፈጠራል። እነዚህ ነገሮች ሁሉ በሰዎች መካከል የነበሩ ቁርሾዎች እንዲቀሩ ቅይሞች እንዲለዝቡ በማድረግ ሰላምን የሚያበዙ ናቸው።

በሌላ በኩል በተለይም በአዲስ አበባ የደመራ በዓል ሲከበር ከሀይማኖት አባቶችና ከምእመናኑ በተጨማሪ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮችና ሌሎች እንግዶችም የሚታደሙ ይሆናል። የእነዚህ እንግዶች መገኘት በዓሉ በኢትየጵያውያን ዘንድ ያለውን ቦታ ተቀባይነት የሚያመላክት ሲሆን እንግዶቹም የሚያስተላልፏቸው መልእክቶች ሰላምን አንድነትንና ልማትን የሚሰብኩ ናቸው። ይህም እንደ ሕዝበ ክርስቲያኑ ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገር እንደ ሕዝብ ያነበረንን ያለንን ሰላም እንድናጸና የሚጠቅም ነው።

አዲስ ዘመን ፤ በመጨረሻ የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ ?

መጋቢ ምስጢር ሣህሉ፤ እኛ ኢትዮጵያውያን በርካታ ጥሩ ነገሮች ያሉን ሕዝቦች ነን፤ ከገጠሙን ተግዳሮቶች በላይ ብዙ የደስታና የአሸናፊነት ግዜዎችንም አሳልፈናል። ዛሬም ይህንን የደመራ በዓል ስናከብር ትላንት የነበርንበትን ታላቅነት ለመመለስ በሰላም በመተሳሰብና በፍቅር ሊሆን ይገባል። ይህንን ሰላምና ፍቅር የምንገልጸው ደግሞ እርቀን ሳንሄድ በአካባቢያችን ካሉት ጀምሮ ነው። የተቸገሩን መርዳት፤ ለሰው ልጆች ሁሉ ቀና ማሰብ፤ ከክፉ ስራዎች መጠበቅ፤ በበጎ ተግባራት ተባባሪ መሆን እና ሰላምን መስበክ ከእያንዳንዱ ክርስቲያን የሚጠበቅ ይሆናል።

አዲስ ዘመን፤ ስለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን።

መጋቢ ምስጢር ሣህሉ፤ እኔም አመሰግናለሁ።

ራስወርቅ ሙሉጌታ

አዲስ ዘመን ሐሙስ መስከረም 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You