መስከረም በኢትዮጵያውያን ዘንድ አቆጣጠር አዲስ ዓመት ‹‹አሃዱ›› ብሎ ቁጥር የሚጀምርበት ነው። ክረምት እና በጋ ከፍተኛ ሽኩቻ ውስጥ፤ የክረምቱ ጭቃ ጥለኸኝ አትሂድ! እያለ የኋሊት የሚጎትተው፤ ፀደይ ደግሞ እባክህ ወደ እኔ ናልኝ! የሚልበት፤ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ትርጉም እና እሴት ያላቸው በዓላት የሚበዙበት ወር ነው።
መስከረም የክረምቱን መውጣት ተከትሎ ምድሪቱ ከቆላ እስከ ደጋ ልምላሜ የሚላበስበት፤ አንገቱን ደፍቶ የከረመ የቄጠማ ሣር የክረምቱን ማለፍ የሚያረጋግጠው፤ ከአጎነበሰበት ቀና ብሎ ‹ወፌ ቆመች› እንደሚል ሕፃን ለመቆም የሚውተረተረው በመስከረም ወር ነው።
የወፎች ኅብረ ዝማሬ ደመቅ የሚልበት፤ ሰፈራቸውን ትተው የተሰደዱ የአዕዋፋት ዝርያዎች ወደ ቀያቸው ተመልሰው ሥነ-ምሕዳሩን ውበት የሚያላብሱበት፣ በማለዳ ጫጫታቸው የተኛን ፍጡር የሚቀሰቅሱበት ወቅት ነው መስከረም።
በእኔ አተያይ እንደ እንቁጣጣሽ የተጨበጨለት የተዘፈነለት፤ እንደመስቀልም የተደመረለት በዓል አይገኝም። መስከረም ነገረ ብዙ፤ ሐሳበ ብዙ ነው፤ መልከ ብዙም ነው። ከዚህም ባሻገር በዚህ ወር ያለፈውን ዓመት ረስቶ በአዲስ ተተክቶ ሌላ ሕይወት ለመጀመር ሰዎች ደፋ ቀና የሚሉበት ነው። በርካታ በዓላትም የሚከበሩበት ነው። በዚህ ወር ከሚከበሩ በዓላት ታዲያ ከእንቁጣጣሽ ተከትሎ የበርካቶች መድመቂያ በዓል መስቀል ነው። መስቀል በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል በተለያዩ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ትውፊቶችን በማስታከክ ከሚከበሩ በዓላት መካከል አንዱ ነው።
የታሪክና የሃይማኖት ድርሳናት እንደሚያመለክቱት፤ የመስቀል በዓል ከአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን (327 ዓ.ም) ጀምሮ ይከበራል። በዓሉ ሃይማኖታዊ ትውፊት የተላበሰ ሲሆን፤ በዘመኑ የነበረችው ንግሥት እሌኒ እየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀል አስቆፍራ ካስወጣችበት ጊዜ ጀምሮ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ሃይማኖታዊ ይዘት ተላብሶ ይከበራል።
ንግሥቲቱ መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ ‹‹ቂራቆስ›› በተባሉ አባት ጠቋሚነት ለማግኘት ደመራ አስደምራ ፍለጋ የጀመረችው መስከረም 17 ቀን እንደሆነ የክርስትና ሃይማኖት ድርሳናት ያስረዳሉ። ንግሥት እሌኒ የሃይማኖት አባቶችን አሰባስባ በፀሎት እንዲረዷት ጠይቃ፤ ከደመራው በሚወጣው ጢስ ጠቋሚነት መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ አግኝታለች። መስቀሉም ከወራት ቁፋሮ በኋላ መጋቢት 10 ቀን ወጥቷል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ መስከረም 16 ቀን ‹ደመራ› እና መስከረም 17 ቀን ‹የመስቀል በዓል› እየተባለ ይከበራል።
ከአራተኛው ምዕተ ዓመት ጀምሮ እንደሚከበር የሚነገርለት ይህ በዓል በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) የማይዳሰሱ ቅርሶች መዝገብ ላይ በዓለም ቅርስነት በኢትዮጵያ ሥም እንዲመዘገብ ተደርጓል።
የመስቀል በዓል ሃይማኖታዊ ይዘቱ እንደተጠበቀ ሆኖ በየአካባቢው እንደ ማኅበረሰቡ ባሕልና ወግም ይከበራል። በተለይም ደግሞ በሀገሪቱ ደቡባዊ ክፍል ከሃይማኖታዊ ይዘቱ በተለየ ትርጉም ሰጥተው ያከብሩታል። ይህ በዓል በአንዳንድ አካባቢዎችም የዘመን መለወጫ ተደርጎም ይወሰዳል። የመስቀል በዓል በዘመናት መካከል ነባር ትውፊቶቹን ጠብቆ የዘለቀ ደማቅ በዓል ነው። መስቀል በዓል እንደ ዘመን መለወጫ ከመታየቱም በተጨማሪ የተጣሉ ሰዎች የሚታረቁበት ወሳኝ ወቅት ሲሆን ማኅበራዊ እሴትን በማጠናከርና ሠላምን በመስበክ ትልቅ ሚና አለው።
ንግስት ዕለኒ መስቀሉን ለማግኘት ብዙ የለፋች በኋላም የተሳካላት ስለመሆኑ ይነገራል። እንግዲህ ብዙ የተለፋበት ፆም ፀሎት የተደረገለት ሂደት ውስጥ ያለፈ በመሆኑ ከትውልድ ወደ ትውልድ መተላለፍ ያለበትም በዚሁ ጠንካራና ያልተበረዘ ዓውድ መሆን አለበት። በዓሉ ውበት እንዲኖረው የጎብኚዎችንም ቀልብ እንዲይዝ እና ከሃይማኖታዊ ይዘቱም በዘለለ ምጣኔ ሃብታዊ ጠቀሜታ እንዲኖረው ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል።
መስቀሉን ለማግኘት የተከማቸውን ክምር አፈር ለማስወገድ ብዙ ቁፋሮ ተካሂዷል፤ ረጅም ጊዜም ወስዷል። ይህ የሚያሳየው አንድ ነገር ለማግኘት ዕምነት፤ ፅናት እና ትዕግስት የሚፈልግ መሆኑ ነው። በአጭሩ መስቀል በዓል የምንፈልገውን ለማግኘት የማንፈልገውን የምናስወግድበት ሂደት የምንረዳበት ነው።
እኛም በዓሉን ስናከብር፤ እንደ ሀገር ሊጠቀሙን የሚችሉ ግን በርካታ ውጣ ውረዶችና የሚጠይቁ ጉዳዮች መኖራቸውን በመረዳት፤ ለዚህ መከባበር፣ መተባበር እንደሚያስፈልጉን በማጤን ሊሆን ይገባል። መስቀሉን ለማግኘት የማይፈለገውንና ለዓመታት የተከመረውን ቆሻሻ ማስወገድ ግድ እንዳለ ሁሉ፤ እኛም የምንፈልገውን እስክናገኝ ድረስ የምንፈልገው ነገር የተሸፈነበትን ቆሻሻ ማስወገድ ይጠበቅብናል። መስቀሉን ለማግኘት ሲባል በነበረው ቁፋሮም በርካታ የእምነቱ ተከታዮች የተሳተፉ ሲሆን፤ ከፍተኛ ልፋትና ፀሎት የታከለበት ነው። በመሆኑም የምንፈልገውን ለማግኘት ብዙ የተጋን፤ ነገም የምንተጋ መሆናችንን ማስመስከር አለብን።
የደመራ ወይንም መስቀል በዓል በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) የማይዳሰሱ ቅርሶች መዝገብ ላይ በመላው ኢትዮጵያ ስም በዓለም ቅርስነት መመዝገቡ፤ ከክርስትና እምነት ተከታዮች ባለፈ፤ ለሌሎች እምነት ተከታዮች የብሔራዊ ኩራት ምንጭ ነው። መስቀል በዓል ከመንፈሳዊ በዓልነት ባለፈ የሕዝቦች አንድነትና መተሳሰር የሚጠናከርበት፣ ተስፋ እና ቀጣይ ዕቅድ የሚነደፍበት ወቅት ነው። በመሆኑም መስቀልን የመንፈሳዊ ይዘት ብቻ ሳይሆን ሥነልቦናዊ ትስስር የሚጠናከርበት በመሆኑ አብሮነታዊነትን ለማጉላት ፋይዳው ላቅ ያለ ነው።
በዓሉ ብሔራዊ ክብራችንን፤ የመዋደዳችንና የመከባበራችን ዓርማ፣ ብሔራዊ አንድነታችንን፤ ለሠላም እና ለአብሮነት ያለንን ማኅበረሰባዊ ማንነት በአደባባይ የምናስመሰክርበት መልካም አጋጣሚ በመሆኑ ከፍ ባለ የኃላፊነት መንፈስ ልናከብረው ይገባል። ይህንን ማድረግ ደግሞ የእያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነት ነው። መልካም በዓል።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ሐሙስ መስከረም 16 ቀን 2017 ዓ.ም