ዜና ትንታኔ
ግብፅ ኢትዮጵያን ከጎረቤት ሀገራት የማግለል እሳቤዋን ተግባራዊ ለማድረግ ከሶማሊያና ከኤርትራ ጋር ከምታደርጋቸው ግንኙነቶች ባሻገር በቅርቡ ሠላም አስከባሪ በማስመሰል ወታደሮቿን ወደ ደቡብ ሱዳን ለማሠማራት ማቀዷን ይፋ ማድረጓ ይታወቃል። የግብፅ እንቅስቃሴ ለሠላም አስተዋፅዖ ማድረግ ወይስ ኢትዮጵያን ለመክበብ እና ም ሥራቅ አፍሪካን ለማተራመስ ?
ኢትዮጵያ የዓባይ ግድብ የሀገራዊ ልማት ስትራቴጂዋ ቁልፍ አካል መሆኑን በተደጋጋሚ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ስታሳውቅ በግድቡ ምክንያት በታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ላይ ምንም አይነት ጉዳት እንደማያደርስ ማስተማመኛ በመስጠት ጭምር እንደሆነ በርካቶች ዘግበውታል።
ዘ ኒውዮርክ ታይምስ እኤአ በ2020 ይዞት በወጣው ዘገባ እንዳመላከተውም፤ የዓባይ ግድብ ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ትልቅ የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ረገድ ትልቅ ተስፋን የሰነቀችበት መሆኑን ይጠቅሳል። እንግሊዛዊው የፖለቲካ ተንታኝ አሌክስ ደ ዋል ይህንኑ ሀሳብ በማጠናከር ግድቡ ለኢትዮጵያ የመልማት መብትን የሚያረጋግጥ ነው ማለታቸው አይዘነጋም።
ይህ የኢትዮጵያ የልማት ፍላጎት ግን የግብፅን ፍራቻ ከፍ እንዳደረገው ይጠቀሳል። ካይሮ የኢትዮጵያን ኃያልነት በሰሜን ምሥራቅ አፍሪካ ለግብፅ ታሪካዊ የበላይነት ፈተና ሊሆን እንደሚችል ታያለች። እኤአ በ2020 በአልጀዚራ በኩል የወጣ ዘገባ የግብፅ ባለሥልጣናት፤ ኢትዮጵያ በዓባይ ግድብ የቀጣናውን የኃይል ሚዛን ልትቀይር ትችላለች በሚል ስጋት የኢትዮጵያን “መነሳት” በከፍተኛ ስጋት ይመለከቱታል” ብሏል።
ኢትዮጵያ ፕሮጀክቱን ወደፊት ስትገፋ፣ ግብፅ በድብቅ እርምጃዎችን በመውሰድ የተለያዩ ተፅዕኖ በማሳደር ተፎካካሪዋን ለማተራመስና ሠላም ለመንሳት ጥረት እንደምታደርግም ተመላክቷል። በቅርቡ ከሶማሊያ እና ከኤርትራ ጋር እያደረገች ካለው ግንኙነት ባሻገር ኢትዮጵያን የመክበብ አዝማሚያ በሚታይበት መልኩ በደቡብ ሱዳን ሠላም አስከባሪዎችን ለመላክ ማሰቧ የተለየ አንድምታ እንዲኖረው አድርጓል። የግብፅ አሉታዊ እንቅስቃሴዎች ለአካባቢው አለመረጋጋት አስተዋፅዖ እንደሚያደርጉም ባለሙያዎች ይናገራሉ።
የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የውጭና ዓለም አቀፍ ዘርፍ ኃላፊ፤ እንዲሁም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት መብራቱ ዓለሙ (ዶ/ር) እንደሚያብራሩት፤ የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና አሁን ላይ አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል። የዓባይ ግድብ ግንባታ እየተጠናቀቀ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ “ዓባይ የእኛ ነው” በሚል ትርክት ግብፅ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረገች ትገኛለች። የኢትዮጵያ መንግሥት የባሕር በር ጉዳይን በሚመለከት ከሶማሌላንድ ጋር ያደረገውን ስምምነት አስመልክቶ አሉታዊ ጎን በመያዝ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ግንኙነት እየፈጠረች ነው። አጠቃላይ ቀጣናው ላይ ችግር እንዲፈጠር ፍላጎቷን በጉልህ እያሳየች ነው።
ይህ የግብፅ እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ ሠላማዊ ሀገር እንዳትሆንና አንድነቷን እንዳትጠብቅ እንዲሁም ሌሎች የልማት ሥራዎችን እንዳትሠራ የሚካሄድ ሩጫ እንደሆነ ይጠቅሳሉ። “የዓባይ ግድብ ግንባታ ከተከናወነ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ አቅም ያላት ሀገር ትሆናለች” የሚል ስጋት ውስጥ መሆናቸውንም አንስተዋል። በዚህም የኢትዮጵያ ተሰሚነቷ እያደገ እንዳይመጣ ጫና ለመፍጠርና እድገቷንም ለማስተጓጎል ብዙ ርቀቶችን እየተጓዙ ይገኛሉ ነው ያሉት።
ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያን በተለያዩ መንገዶች ለመክበብ ሙከራዎችን ከማድረግ ባሻገር ሀገር ውስጥ የሚስተዋሉትን ግጭቶች ጭምር የማባባስ ሥራ እንደምትሠራ ጠቅሰዋል። በዚህ ምክንያት በአሁን ወቅት በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ያለው የፖለቲካ ትኩሳት እየጎላ መምጣቱን አመላክተዋል። ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላትን ዲፕሎማሲ ይበልጥ ልታጠናክር እንደሚገባም ይመክራሉ።
መብራቱ (ዶ/ር) እንደሚገልጹት፤ ግብፅ በኢትዮጵያ የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎችን በማደናቀፍ ዘላቂ ልማት እንዳይኖር ግጭት እንዲነሳሳና ርስ በርስ ችግሮች ተነስተው ሀገሪቷ ተረጋግታ የልማት ፕሮጀክቶችን እንዳትሠራ የመግታት እንቅስቃሴ ነው እያደረገች ያለችው።
ከዓባይ ወንዝ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ የነበሩ ጥንታዊ ስምምነቶችን በመያዝ ጫና ለመፍጠር እየተንቀሳቀሰች ነው። ከዚህ አኳያም ኢትዮጵያም ከዚህ ቀደም ስታከናውናቸው የነበሩ የዲፕሎማሲ ሥራዎችን አጠናክራ በልዩ ትኩረት መሥራት እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት።
ዘ ኢኮኖሚስት እኤአ በ2021 ይዞት በወጣው ዘገባ በግብፅ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው የዓባይ ውሃ ውዝግብና ግብፅ የምትከተለው ስትራቴጂ እያደገ የመጣውን የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለመግታት ተፅዕኖ እንዳለው ተገልጿል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢትዮጵያ በዓባይ ግድብ ፕሮጀክት ሉዓላዊነቷን እና ቀጣናዊ መሪነቷን ለማስከበር ቆርጣ መነሳቷን እና በአንጻሩ የግብፅ እንቅስቃሴ ወደ ግጭት ሊያመራ የሚችል አዝማሚያ ያለው መሆኑ ተመላክቷል። የዚህ ግጭት ውጤት ለምሥራቅ አፍሪካ መረጋጋት እና የወደፊት እድገት ትልቅ መዘዝ እንዳለውም ነው በወቅቱ የተገለጸው።
የኖርዌይ እውቅ የታሪክ ምሑር ተርጄ ቴቬት እኤአ በ2019 በአልሞኒተር ላይ እንዳስታወቁት፤ በግብፅና በኢትዮጵያ መካከል ያለው የዓባይ ወንዝ ውዝግብ መነሻው በቅኝ ግዛት ዘመን የተደረጉ ስምምነቶችን ተከትሎ ነው ይላሉ። እነዚህ የቅኝ ግዛት ዘመን ስምምነቶች ግብፅ በዓባይ ወንዝ ላይ ያላትን የበላይነት ያጎናፀፉ ሲሆን በተለይም የወንዙን ውሃ አብዛኛውን የምታበረክተውን የላይኛው ተፋሰስ ሀገር የኢትዮጵያን ጥቅም ችላ ያለ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ እነዚህን ያረጁ ስምምነቶች ፍትሐዊ ያልሆኑ እና የዘመናዊ እውነታዎችን እንደማይወክሉ በመቁጠር ስትቃወማቸው መኖሯንና ግብፅም ይህንኑ መነሻ በማድረግ ኢትዮጵያ ላይ ጫናዎችን ለመፍጠር የተለያዩ ሙከራዎችን ስታደርግ መቆየቷን አንስተዋል።
ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ሙሳ ሸኮ በበኩላቸው፤ ግብፅ በኢትዮጵያ የውስጥና የቀጣናዊ ጉዳዮች በተለይም በዓባይ ተፋሰስና በአፍሪካ ቀንድ ጉዳይ ላይ የፈጸመችው የረጅም ጊዜ ጣልቃ ገብነት እንቅስቃሴዋ ሰፋ ያለ ጂኦፖለቲካዊ አንድምታ እንዳለው ይገልጻሉ። የግብፅ በኢትዮጵያን ዙሪያ የመሽከርከሯ ሁኔታ ለራሷ ለግብፅ የሚበጅ እንዳልሆነም ይጠቅሳሉ።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ትልቅ ታሪክና ረጅም የዲፕሎማሲ ገድል ያለው፤ በጦርነትም ሆነ በዲፕሎማሲ የማሸነፍ ልምድ ያለው ነው በማለት፤ ግብፅ በአሁን ወቅት እየሠራች ያለው ኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን መላ አፍሪካውያንን የሚያስቆጣ መሆኑን ተናግረዋል። ግብፅ በሶማሊያ እያደረገች ባለው እንቅስቃሴ ኢንቨስት አድርጋ ከነደፈቻቸው ቡድኖች ውጪ ሌሎቹ እየተቃወሟት ስለመሆኑም አንስተዋል።
ግብጽ አፍሪካ ውስጥ ትሁን እንጂ ጀርባዋን ለአፍሪካውያን ከሰጠች 50 ዓመታት ተቆጥረዋል። ሁሉም እንቅስቃሴዋ ከአፍሪካ ተቃራኒ የሆነ፤ ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ የሚለውን የአፍሪካውያንን አቋም የምትጻረር ናት። ይህ ሁሉ ተደምሮ ሰሞኑን በኢትዮጵያ ዙሪያ እያደረገች ያለው ተገቢ ያልሆኑ እንቅስቃሴዎች የዓለም አቀፍም ሆነ የአፍሪካውያንን ድጋፍ የሚያሳጣት መሆኑ አመላክተዋል።
የተፈጠረው አጋጣሚ ወደ ሶማሊያ ይውሰዳት እንጂ ተልዕኳቸውን የሚያስፈጽሙት ኤርትራን በማዕከላዊ ሥፍራነት በመጠቀም እንደሆነም አቶ ሙሳ አብራርተዋል። ይህም ባለፉት 33 ዓመታት ውስጥ የተንጸባረቀ ነው ብለዋል። ከዚህም ባሻገር በሌሎች ጎረቤት ሀገራት የምታደርገው እንቅስቃሴ ዓላማው ኢትዮጵያን ለማተራመስ እንደሆነ ተናግረዋል።
አቶ ሙሳ፤ “የግብፅ ተግባራዊ እንቅስቃሴና ፕሮፖጋንዳ ሌሎች ሀገራትንም እስከመጠቀም ሊደርስ ይችላል። ራሳቸውን ኃያል በማስመሰል አንዱ ሞቃዲሾ፣ ሌላው ደግሞ አስመራ ሊቆም ይችላል። ነገር ግን ኢትዮጵያ ባላት የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ልምድ ፈተናዎችን ትሻገራለች” ነው ያሉት።
በኒውዮርክ እየተካሄደ ከሚገኘው 79ኛው የተ.መ.ድ ጠቅላላ ጉባዔ ጎን ለጎን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ ከአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳይ ረዳት ሚኒስትር ሞሊ ፊ ጋር የጋራ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።
አምባሳደር ታዬ ለረዳት ሚኒስትሯ በአፍሪካ ቀንድ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ገለጻ ባደረጉበት ወቅት ኢትዮጵያ በቀጣናው ዘላቂ ሠላምና መረጋጋት እንዲሰፍን እያደረገች ያለውን ጥረት ትኩረት ሰጥተው አንስተዋል።
ሚኒስትሩ ሶማሊያን በተመለከተ ሞሊ ፊ ጋር በነበራቸው ውይይት ኢትዮጵያ ሽብርተኞችን በመዋጋት ረገድ በምታደርገው የተጠናከረ ጥረት ዙሪያ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን ከድህረ አትሚስ በኋላ የሚኖረው የኃይል ሥምሪት ተግባራዊ ከመደረጉ አስቀድሞ የስምሪቱ ማዕቀፍ በጥንቃቄ መሠራት እንዳለበት ነው የተናገሩት።
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን መስከረም 16 ቀን 2017 ዓ.ም