የስፖርቱ ጉዞ ወደየት እየሄደ ነው ?

የአንድ ሃገር ስፖርት አደገ ሊባል የሚችለው በተለያዩ አቅጣጫዎች ሲመዘን ነው። በዜጎች አሳታፊነት፣ ሕጻናትና ታዳጊዎችን በዘርፉ አሳድጎና አጎልብቶ ብቁ ስፖርተኛ ከማድረግ፣ በአሕጉር እና ዓለም አቀፍ ውድድሮች በሚመዘገብ ውጤት፣ በተገነቡት የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ቁጥርና ጥራት፣ ስፖርቱ ለሃገር ኢኮኖሚ ከሚያበረክተው አስተዋፅዖ ወዘተ አንጻር ሊቃኝም ይችላል። ከዚህ በመነሳት እንደአጠቃላይ የኢትዮጵያ ስፖርት ያለበት የእድገት ደረጃ ቢለካ የት ሊገኝ ይችላል? በእድገት ወይስ በተቃራኒው በቁልቁለት ጉዞ?

ይህንን ጥያቄ ለመመለስ በባለሙያዎች የተሠራ ጥናትን ዋቢ ማድረግ ያስፈልጋል። ነገር ግን በሃገሪቷ ይህንን መሰል ጥናት በየጊዜው የሚሠራ ባለመሆኑ እንዲሁም ስፖርቱ ባለበት ቁመና ለዚህ መሰሉ አሠራር ምቹ ባለመሆኑ አዳጋች ነው። በተለያዩ አጋጣሚዎች የስፖርት ባለሙያዎች ከሚሰጡት አስተያየት እንዲሁም ከሚታየው ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት ግን የትኛውም የስፖርት ቤተሰብ የኢትዮጵያ ስፖርት ጉዞውን የኋሊት ካደረገ መሰነባበቱን መገንዘብ ይችላል።

ከተወዳዳሪነት አንጻር ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የስፖርት መድረክ ስሟን የተከለችበት ስፖርት አትሌቲክስ ወጥ ያልሆነ ውጤታማነት ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው። በዚህ ስፖርት እንደ ዓለም ሻምፒዮና እና ኦሊምፒክ ባሉ ታላላቅ የውድድር መድረኮች ዘመናትን በዘለቀ ውጤታማነት ሃገር ከብራለች፤ ኢትዮጵያውያንም ኮርተናል።

በተጨባጭ መግለጽ ባይቻልም ለሃገር የሚገባው የውጪ ምንዛሪ እንዲሁም በብርቱ አትሌቶች የተፈጠሩ የሥራ ዕድሎች እጅግ ከፍተኛ ሲሆኑ፤ አትሌቶች በሚገነቧቸው ሕንጻዎችና ሆቴሎችም በከተማ ገጽታ እንዲሁም በቱሪስት ፍሰት ከፍተኛ ድርሻን መጫወት ችለዋል።

ይህ ኢትዮጵያውያን እንደ ብሌናቸው የሚሳሱለት ስፖርት በውጤት እያደገና ከጊዜው ጋር እየዘመነ መሄድ ቢገባውም በአሠራርና በብቁ አመራር ችግር ለዓመታት ተመሳሳይ መንገድ እየተጓዘ ይገኛል። ይባስ ብሎም በታላላቆቹ መድረኮች ይጠበቁ የነበሩ ውጤቶች ቀርተው፣ ‹‹ሃገራችንን እንወክል›› ያሉ አትሌቶቻችንም በብልሹ አሠራር ልባቸው ተሰብሮ አማራጮችን ሲፈልጉ እየተመለከትን ነው።

በእርግጥም የዚህን ሁኔታ አስፈሪነት የስፖርቱ ተቆርቋሪዎች ዓመታትን ቀድመው ቢያሳስቡም ሰሚ ጆሮ ባለማግኘታቸው በቅርቡ በተካሄደው የፓሪስ ኦሊምፒክ እንዳየነው ኢትዮጵያን የማይመጥን ውጤት ልንመለከት በቅተናል። ይህ ሁሉ ሲሆን ግን የአንድ ወቅት ጫጫታ እንጂ ‹‹ለምን?›› የሚል ጠንካራ ጠያቂና የጉዳዩን ተዋናዮች ተጠያቂ የሚያደርግ አካልና አሠራር አልታየም።

ከመንግሥት አንስቶ ጉዳዩ እስከሚመለከታቸው ተቋማት ሁኔታውን መርምረው መፍትሔ በማምጣት ፋንታ ከዳር ሆነው መመልከታቸው ደግሞ ስጋቱን በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ እንዲያይል አድርጎታል። ስፖርቱን የሚመራው ጠቅላላ ጉባኤም ቢሆን በየዓመቱ ተሰብስቦ ሥራ አስፈጻሚ ከመምረጥና የየክልሉን ሪፖርት አዳምጦ ከመበተን ያለፈ ስፖርቱን ለቁልቁለት ጉዞ ያበቃውን አሠራር እንዲሻሻል ምንም ያደረገው ነገር የለም። ይህም ኢትዮጵያን ባደመቃት ስፖርት፣ ድል እንዳይርቃት በእጅጉ ያሳስባል።

በሌላ በኩል ስፖርትን የሚመሩ ማኅበራት ኃላፊነታቸውን ከመሳት አልፈው አልጠየቅም ባይነታቸው ስፖርቱን በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ የኋሊት እንደሚጎትተው አያጠያይቅም። በተለይ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የአሁኑ አካሄድና የሥራ አስፈጻሚዎቹ እብሪተኛነት የስፖርቱን ቤተሰብ ብቻም ሳይሆን ዜጎች የሚመሩበትን ሕገመንግሥትም እስከመናድ የደረሰ ሆኖ እያየን እንገኛለን። ሥራ አስፈጻሚው ላለፉት ዓመታት በሥልጣን ላይ ሲቆይ ለስፖርቱ ያበረከተው የተለየ ነገር ባይኖርም ከፍተኛ ገንዘብ መመዝበሩ በቀረበበት ክስ ላይ ተመላክቷል።

ይሁንና ጉዳዩ በመደበኛ ፍርድ ቤት የተያዘ ቢሆንም ክስ የቀረበበት አመራር በስዊዘርላንዱ የስፖርት ግልግል ፍርድ ቤት ካልሆነ ልጠየቅ አይገባም ማለቱ ብዙዎችን አስገርሟል። የቀድሞዎቹን የፊፋ አመራሮች የእነ ሴፕ ብላተርና ሚሼል ፕላቲኒን እንዲሁም የቀድሞውን የዓለም አትሌቲክስ ፕሬዚዳንት ላሚን ዲያክ ታሪክና ዕጣፋንታ አለማወቅ ይመስላል፡፡

ከስፖርታዊ ሕገወጥ አሠራር ባለፈ በገንዘብ ምዝበራ እና በሙስና የተጠረጠሩት የቀድሞ ዓለም አቀፍ የስፖርት አመራሮች ኤፍቢአይ እና የኢንተርፖልን በመሳሰሉ አካላት ጣልቃ ገብነት በመደበኛ ፍርድ ቤት ወህኒ እንደወረዱ መዘንጋት የለበትም። የእነዚህ ሰዎች መጨረሻም ለሕይወት ዘመን ከስፖርት ከመታገድ ባለፈ ከፍተኛ ሞራላዊ ውድቀት ያደረሰ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ እግር ኳሱም ቢሆን የኋሊት እያዘገመ የሚገኝ ስፖርት ነው። ወጪው እንጂ ገቢው የማይታወቀውና በአመዛኙ አሁንም በመንግሥት ላይ የተንጠለጠለው የኢትዮጵያ እግር ኳስ በብሔራዊ ቡድን ደረጃ እየተመዘገበ ያለው ውጤት አልባ ጉዞ እንደታመመ ይገኛል።

ቡድኑ በሜዳው መጫወት አለመቻሉ ዋነኛው ችግር ሆኖ ሳለ ጠንካራና ተፎካካሪ የሆነ ቡድን ከመመሥረት አንጻር ግን እንደሃገር የምርጥ ተጫዋቾች እጥረት ስለመኖሩ አሠልጣኞች በተደጋጋሚ የሚያነሱት ጉዳይ ነው። የስፖርቱን የኋሊት ጉዞ ቁልጭ አድርጎ ከሚያሳዩት መካከል አንዱ ከእግር ኳስ ተጫዋችነት እስከ ስኬታማ አሠልጣኝነት ለረጅም ዓመታት የዘለቁ አሠልጣኞች በስፖርቱ መታከታቸውን በግልፅ እየተናገሩ ነው፡፡

በስፖርቱ በክለብ ደረጃም ሆነ በብሔራዊ ቡድን የእግር ኳስ ተጫዋቾች ብቃት፣ ውጤታማነትና አጨዋወት ከክፍያቸው ጋር አለመመጣጠኑ የስፖርት ቤተሰቡ መነጋገሪያ ቢሆንም የባለሙያዎች ምላሽ ግን ለሌላ ሃገር ጋር ማነጻጸር እንጂ ሁኔታውን ያገናዘበ አለመሆኑ አሳዛኝ ነው። ይህም ብቻ ሳይሆን በቅርቡ የተከሰተው የተጫዋቾች ለጨዋታ በሄዱበት ሃገር መጥፋት ታዳጊዎች ላይ ምን ዓይነት ተፅዕኖ ያሳድራል የሚለው አሳሳቢ ነው። ከዚህ ባለፈ የጠፉ ተጫዋቾች ከወቅቱ የክለቦች ክፍያ አንጻር እንደሃገር ከፍተኛ የሚባል ቢሆንም የመኮብለላቸው አንዱ ምክንያት ኢኮኖሚያዊ ሳይሆን የስፖርቱ አለመለወጥና ተስፋ ቢስነት ነው።

ሃገር አቀፍ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችም ለስፖርቱ እድገት ግልጽ ማሳያዎች ሲሆኑ ለዓመታት እየታየ ባለው ሁኔታ የኋልዮሽ ጉዞው በከፍተኛ ደረጃ እየተንደረደረ ያለበት ዘርፍ ሊባል ይችላል። ስፖርት ብዙዎችን የሚያሰባስብ፣ የአንድነት መድረክ ነው ቢባልም በኢትዮጵያ ግን የችግሮች መንስኤ ሆኗል።

በመሆኑም የስፖርት ማኅበራት በግላቸው ከሚመሯቸው ውድድሮች ባለፈ ከዚህ ቀደም በሃገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄዱ እንደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የስፖርት ውድድር፣ የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች፣ ሃገር አቀፍ የፕሮጀክቶች ሻምፒዮናን የመሳሰሉ ውድድሮች ከተቋረጡ ቆይተዋል። ችግሮችን ለመፍታት የተለያዩ መፍትሔዎችን ከመጠቀም ይልቅ ውድድሮችን መሰረዝ በመመረጡም በሃገር አቀፍ ደረጃ ስፖርተኞች እንዳይገናኙ፣ የውድድር ልምድ እንዳያገኙ፣ የስፖርት ቤተሰቡም ውድድሮችን በማየት እንዳያሳልፍ እንዲሁም ሌሎች በርካታ ጥቅሞች አጥተዋል።

ሌላው ዓለም በእያንዳንዱ ደቂቃ አዳዲስ ጉዳዮችን በሚያስተናግድበት ዘመን የኢትዮጵያ ስፖርት ጉዞ ዓላማ ሳይኖረው በማዝገም ላይ ነው። ራሱን ማዘመንና ከወቅቱ ጋር መራመድ ባለመቻሉም ከዜጎች አሳታፊነት አንጻር ከሚፈለገው ደረጃ ላይ ሊደርስ አልቻለም። ታዳጊዎችን በዕድሜያቸው ኮትኩቶ ምርጥ ስፖርተኛ ከማድረግ አንጻርም ሊነሳ የሚችል ተሞክሮም የለም፡፡

በአሕጉርና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይም በቋሚነት መዝለቅ ካልቻለው አትሌቲክስ ባለፈ፤ አልፎ አልፎ ከሚገኙ ውጤቶች ውጪ ተሳታፊነትን እንኳን ማረጋገጥ አልተቻለም። የስፖርት ማዘውተሪያዎቻችንም ቢሆኑ እንዳለፉት ዓመታት ጅምር ላይ ናቸው። በዚህ አካሄድ ስፖርቱ በመንግሥት ከመደገፍ አልፎ በሃገሪቷ ኢኮኖሚ ላይ የድርሻውን የማበርከት አቅም መፍጠር አልቻለም። ይህ የስፖርቱ ወዳጅና ተቆርቋሪ ማጣት በዚሁ የሚቀጥል ከሆነም የምንመኘውን ድልን የምናገኝ ሳይሆን በረከቶቻችንን አሳልፈን የምንሰጥ ይሆናልና ይታሰብበት።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን መስከረም 15 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You