አዲስ ዘመን ድሮ

ሁኔታዎችን፣ ኩነቶችን፣ ታሪክንና አጠቃላይ እንቅስቃሴዎችን እለት በእለት፣ እግር በእግር ሲሰንድ የኖረው፤ ጎምቱው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ያላነሳቸውን ነገሮች ከመዳሰስ ይልቅ ″ምን የቀረው ነገር አለና″ የሚለውን በመያዝ አንዳንድ አስተናግዷቸው የነበሩ ጉዳዮችን ማንሳቱ ይበጃል።

የዛሬዎቹ ምርጫዎቻችን ከየዘርፎቹ ናቸው። በየራሳቸው የቆሙ እንጂ በታሪክ አንዱ ከሌላው የተሳሰሩ አይደሉም። በወቅቱ የተከናወኑ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮችን ትኩረት ያደረጉ ናቸው። እንደሚከተለው አቅርበናቸዋል።

የፖርቱጋል ጋዜጣ ለመነን መጽሔት የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች በተለይ ስለ እኛ ሀገር የበለጠ በማስረዳት ሰፊ ሐተታ በመስጠት ላይ ናቸው።

የታወቀ ባለ ሥዕል የመነን መጽሔት በአዲስ አበባ በአማርኛና በእንግሊዝኛ ይታተማል፤ በመጨረሻውም ክፍል እትሙ የግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን ኦፊሴዬላዊ ጉብኝት መሠረት በማድረግ የዛሬይቱ ፖርቱጋል ከደረሰችበት ደረጃ በፊት የነበረችበትን ታሪካዊ ሁኔታ ከፍ ባለ አስተያየት ያለ ፖለቲካ ስሜት መጽሔቱ ሰፊ አርቲክል አውጥቷል።

መጽሔቱ በኢትዮጵያና በፖርቱጋል መካከል ያለውን ብዙ መቶ ዓመታት የቆየውን የወዳጅነት ግንኙነት ከዛሬው የአፍሪካ ምርመራ ጋር የተያያዘውን የነገሥታቶቻችንንና የባሕር መሪዎቻችንን ተግባሮች ከገለፀ በኋላ በፖርቱጋል መንግሥት በሁለቱ የዓለም ጦርነቶች ጊዜ የነበረውን አቋምና የላይቤሪያን አገሮች ጀርመኖች በሁለተኛው የዓለም ጦርነት እንዳይወሩ የተደረገውን የፖለቲካ ትግል ይገልፃል። የፖርቱጋል መንግሥት የኦዞር ደሴቶችን የተባበሩት መንግሥታት የጦር ሰፈር እንዲሆን መፍቀዱ በጣም ጠቃሚ ሆኗል።

ከዚህ በላይ የተዘረዘሩትን ጉዳዮች ካስረዳ በኋላ መነን መጽሔት ፖርቱጋል ምን እንደ ሆነች ለወዳጅዋ ኢትዮጵያ ለማስገንዘብ በእርሻ፣ በኢንዱስትሪና በኢኮኖሚ ረገድ የተደረገውን መሻሻል ገልጿል።

በዚህ ከሚገባ አርቲክል ጋር ጎን ለጎን ሆነው የፖርቱጋል ፕሬዚዳንት የአንዳንዶች ሐውልቶቻችንን የአዲሲቷ ሊስቦን ሕንፃዎችና ያለፉት የሁለት ዓመታት ሕንፃዎችና የኢንዱስትሪ ውጤቶች አስረጂ ፎቶግራፎች ታትመው ወጥተዋል።

(አዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ ዓርብ ነሐሴ 1 ቀን 1951 ዓ·ም)

አፍሪካውያን መምህራን

ዋሽንግተን:- ስድስት አፍሪካውያን መምህራን በዛሬው ዘመን የአፍሪቃን አሕጉር የገጠማቸው የትምህርት አሰጣጥ ችግር የሠለጠኑ መምህራን ማነስ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

እነዚህ መምህራን በዓለም ትምህርት አሰጣጥ ሙያ ድርጅት ዋና ጽሕፈት ቤት ለጋዜጠኞች በተደረገው ጉባኤ ላይ የየራሳቸውን አገር የትምህርት አሰጣጥ ችግር አብራርተው ገልፀዋል። እነዚህም መምህራን በዚህ ሳምንት ውስጥ የትምህርትን ችግር የሚያጠና ቋሚ ኮሚሲዮን ለመመሥረት ጉባኤ በማድረግ ላይ የሚገኘው 24 ሰዎች የሚገኙበት ኮሚቴ አባሎች ናቸው።

ለቀረቡለት ጥያቄ መልስ ሲሰጥ 50,000 አባላት የሚገኙበት የናይጄሪያ የመምህራን ኅብረት ዋና ጸሐፊ የሆነውና የኮሚቴው ሊቀመንበር አዲሱ የአፍሪቃ ኮሚሲዮን በጥር 1960 ዓ/ም የመቋቋሙ ክንውን እንዳለቀ የመምህራን እጥረትን ችግር [የ]ማቃለል [ሥራ] ይጀመራል ሲል ተናግሯል።

ኮሚሲዮኑ እንደ አማካሪ ሆኖ በማገልገል ከመንግሥቱ ጋር መምህራንን በማዘጋጀት በኩል ይረዳል የተባለውን ችግር በፍጥነት የሚያቃልል ይሆናል ሲል ጨምሮ ገልጿል።

የኢትዮጵያ መምህራን ኅብረት ሊቀመንበር የሆኑት አቶ እሸቴ ባዩ ስለ ኢትዮጵያ ሲናገሩ መንግሥታቸው የመምህራንን ቁጥር ለመጨመር በትጋት በመሥራት ላይ መገኘቱን ገልፀው ንግግራቸውንም በመቀጠል ምንም እንኳን ችግሩ ሊወገድ የሚችል ባይሆን ቅሉ በመምህርነት የሠለጠኑ ወጣቶች ብዛት በየዓመቱ እየጨመረ መሄዱን አላቋረጠም ሲሉ አስረድተዋል። ከዚህም በማያያዝ ይህንንም ተግባር በትጋት እንዲከናወን ያደረገው መምህራንን ከፍ ባለ ዋጋ ከውጭ አገር እየቀጠሩ ሟምጣት ያሳየው ጉዳት ነው ሲሉ ጨምረው ገልፀዋል።

(አዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ ቅዳሜ ሐምሌ 30 ቀን 1951 ዓ·ም)

በወ.ወ.ክ.ማ የሚደረግ ንግግር

ነሐሴ 9 ቀን 1951 ዓ/ም ከምሽቱ 1 ሰዓት አቶ ዮሐንስ ወልደ ገሪማ በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የጤና ጥበቃና የሕዝብ አገልግሎት ዲሬክተር ″የሕዝብ አገልግሎት″ በሚል አርዕስት በወጣቶች ወንዶች ክርስቲያናዊ ማኅበር አዳራሽ ንግግር ስለሚያደርጉ ማንኛውም ሰው ንግግሩን ሊያዳምጥ ይችላል።

(አዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ ነሐሴ 8 ቀን 1951 ዓ·ም)

በትምህርት ረገድ ልዩነት

ማድረግ ያራርቃል

ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ሚስተር ሲ ኤስ ጃ የሕንድ ዋና መልዕክተኛ በአንዳንድ የእንግሊዝ ግዛቶችና በሌሎች ጥገኞች ግዛቶች በትምህርት ረገድ የሚደረገውን የዘር ልዩነት ተቃውመዋል። ሚስተር ጃ በትምህርት የሚደረግ የዘር ልዩነት ″የዘር ክፍያን ምግባር የሚደግፍ ስለሆነ እንዲህ ያለውን አለመግባባት የሚያባብስ ነው″ ብለዋል።

ራሳቸውን ከማይገዙ ግዛቶች የደረሳቸውን ዜና ለኮሚቴው በመግለፅ ማንኛውም ዘር ከሌላው ይበልጥ ወደ እግዚአብሔር የቀረበ አለመሆኑንና ማንኛውም ዘር ከሌላው የበታችነት የሌለበት መሆኑን ታሪክ ይነግረናል።

″ነገር ግን በኮንጎ፣ በመካከል አፍሪካ፣ በኬንያ፣ በዩጋንዳና በሌሎች በብዙ ግዛቶች ትምህርት የዘር ልዩነት እየተደረገ ይሰጣል″ ብለዋል።

የሠለጠነና የተሻለ ትምህርት ለፖለቲካ ርምጃና ለራስ አገዛዝ ይጠቅማል በማለት በትምህርትና በፖለቲካ ኃላፊነት መካከል የጋራ ግንኙነት እንዲኖር ያሻል ብለዋል።

ስለተገዥዎቹ አገሮች ርምጃ በጠቅላላ አስተያየት በመስጠት በኦስትራሊያ ስር የምትተዳደረዋ ፖፑአ ያደረገችው መሻሻል ከፍ ያለ መሆኑንና፣ ኒው ዚላንድ በኩክ፣ በኒኡና ቶኮሎ ደሴቶች ትምህርትን ለማስፋፋት ባደረገችው ጥረት ሕንድ የተደሰተች መሆኑን አስገንዝበዋል።

ሕንድ ቤልጂክ ወደ ኮሚቴው መልዕክተኛ አለመላክዋን በማሳሰብ ፖርቱጋል በርስዋ ስር የሚተዳደሩት አንጎላ፣ ሞዛምቢክ እንዲሁም አነስተኛ የሆኑ የፖርቱጋል ግዛቶችን ከቁምነገር አለመቁጠርዋ በዘመናችን ከሚያሳዝኑት ጉዳዮች አንዱ ነው ብለዋል።

ንግግራቸውን በመቀጠልም፣ እነዚህ ግዛቶች የገዥው ሀገር ክፍል ናቸው ተብሎ ቢወራም፣ በእርግጥ የቅኝ አገር መሆናቸው ጥርጥር እንደ የሌለው በመግለፅ፤ እነዚህ በሃያኛው መቶ ክፍለ ዘመን ማለቂያ ክፍል የኮሎኒያሊዝምን (የቅኝ አገዛዝን) ቀንበር የተሸከሙት ሕዝቦች ኃዘን ተካፋይ መሆናችንን እንገልፃለን ብለዋል።

(አዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ ሚያዝያ 28 ቀን 1951 ዓ/ም)

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን መስከረም 14/2017 ዓ.ም

Recommended For You