የመስከረም ወር ለኢትዮጵያውያን ባለብዙ መልክ ነው፡፡ የክረምቱ ጭለማ አልፎ ብሩህ ወቅት የሚታይበት፤ አበቦች የሚፈኩበት እና ብሩህ ተስፋ የሚለመልምበት፤ በርካታ ብሔረሰቦች አዲስ ዓመታቸውን የሚያከብሩበት ወር ነው፡፡ ለአብነትም ኢሬቻ፣ ያ ሆዴ፣ ዮዮ ጊፋታ፣ ዮ ማስቃላ፣ ማሽቃሮ ከብዙ በጥቂቱ ይገኙበታል፡፡
ጎቤና ሺኖዬም ዓመታዊ የኦሮሞ ወጣት ወንዶችና ልጃገረዶች የዘመን መለወጫ የብሥራት የአደባባይ ጨዋታ (ካርኒቫል) ነው። ይህ የወጣቶችን ባሕላዊ ክዋኔ የሕዝቦችን አንድነትና ፍቅር የሚያጠናክር የዘመን መለወጫ ባሕላዊ ጨዋታ (ካርኒቫል) መሆኑም ተገልጿል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ጀሚላ ሲምቢሩ ትላንት በተጠናቀቀው ስድስተኛ ዙር ”ጎቤና ሺኖዬ” የወጣቶች የባሕላዊ ጭፈራ ፌስቲቫል ላይ ተገኝተው እንደገለጹት፣ ”ጎቤና ሺኖዬ” ወጣት ወንዶችና ሴቶች ክረምቱ አልፎ የብራ ወቅት መምጣቱን ለማመላከት በባሕላዊ አልባሳት አጊጠው የሚጨፍሩት ባሕላዊ ጭፈራ ነው ይላሉ።
የ”ጎቤና ሺኖዬ” አዲስ ዓመትን የባሕላዊ ጭፈራ ፌስቲቫል ከጳጉሜ 1 ቀን 2016 ጀምሮ ሲከናወን መቆየቱን ጠቅሰው፣ በፌስቲቫሉ ወጣት ወንዶችና ልጃገረዶች የተለያዩ ባሕላዊ አልባሳት አጊጠው ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ ሲያከብሩ መቆየታቸውን ይገልጻሉ።
ወጣቶቹ በተለያዩ ጎዳናዎች፣ በታዋቂ ግለሰቦችና በመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች መኖሪያ ቤት የእንኳን አደረሳችሁ መልካም ምኞት ሲገልጹና የተለያዩ ስጦታዎችን ሲቀበሉ መቆየታቸውንም የገለጹት ኃላፊዋ፣ ፌስቲቫሉ ወጣቶች አንድነታቸውን ያጠናከሩበት፣ ደስታቸውን ያጋሩበትና ተስፋቸውን ያንጸባረቁበት እንደነበርም ይናገራሉ።
የኦሮሞ ሕዝብ በመስከረም ወር መጀመሪያ ከሚያከብራቸው ባሕላዊ ጭፈራዎች መካከል ”ጎቤና ሺኖዬ” አንዱ መሆኑን ገልጸው፣ ወጣቶች የአዲሱን ዓመት መምጣት የሚያውጁበትና አንድነታቸውን የሚያሳድጉበት፣ የሚገናኙበት፣ ግንኙነታቸውን የሚያጠናክሩበት መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
የአደባባይ በዓላት ዜጎች ማንነታቸውን፣ ባሕላቸውንና ቋንቋቸውን እንዲያስተዋውቁ ምቹ ሁኔታዎችን እንደፈጠሩ በመግለጽ፣ መንግሥት ባሕላዊ ማንነቶች በአደባባይ እንዲገለጡ በልዩ ትኩረት እየሠራ እንደሚገኝም ይገልጻሉ፡፡
ከሰሜን ሸዋ የመጣው ወጣት ሰይፉ ቱራ ደበሌ እንደተናገረው፣ የ”ጎቤና ሺኖዬ” ወጣቶች ባሕላችንን፣ ቋንቋችንንና ማንነታችንን በአደባባይ ወጥተን የምናሳይበት ነው ሲል ይናገራል፡፡
ቀደም ሲል የ”ጎቤና ሺኖዬ” ጭፈራዎች ወጣቶች በየመንደሩ ሲያከብሩ እንደነበርና አሁን ግን በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ በባሕላዊ አልባሳት ደምቀው በአደባባይ መከበሩ ልዩ ስሜት እንደፈጠረበት ያስረዳል፡፡
ባሕላዊ ጭፈራ ወጣቶችና ልጃገረዶች ተሰባስበው አንድነትን የሚያሳዩበት መሆኑን በመግለጽ፣ አንድነትን መፍጠር ከተቻለ ባሕልን ማስተዋወቅ፣ ሠላምን ማረጋገጥ፣ ልማትን ማምጣት እንደሚቻል ይገልጻል፡፡
የ”ጎቤና ሺኖዬ” በርካታ ወጣቶች የሚሳተፉበት በመሆኑ በዓሉን አጎልብቶ ለሀገር አንድነትና ሠላም ማዋል ተገቢ ነው የሚለው ደግሞ ወጣት ብሩክ ግርማ ነው፡፡
ለሀገር አንድነትና ሠላም ትልቁን ሚና የሚጫወተው ወጣቱ ነው የሚለው ወጣት ብሩክ፣ ወጣቶች የራሳቸውን ባሕልና ማንነት ይዘው በአደባባይ ተገልጠው የሚተዋወቁበት፣ ስለሀገራቸው ዕጣ ፈንታ የሚወስኑበትንና የሚመክሩበትን ዕድል መፍጠር ተገቢ መሆኑን ይናገራል፡፡
በተለያዩ የሀገሪቱ ጫፍና ጫፍ የሚገኙ ወጣቶች የሚገናኙበትን ዓውድ መፍጠር እንደሚያስፈልግ በመግለጽ፣ በክልል ደረጃ የተጀመረው የ”ጎቤና ሺኖዬ” የአደባባይ በዓል በሀገር አቀፍ ደረጃም መፈጠር እንዳለበት ያስረዳል፡፡
አዲሱን ዓመት የሠላም ፍቅር፣ የብልፅግና የሚሆንበትን መንገድ ወጣቶች ተገናኝተው፣ ተግባብተው፣ ስለ ሠላም አንድነት ሲነጋገሩ ተግባራዊ እንደሚሆን ወጣት ብሩክ ይናገራል፡፡
የአደባባይ በዓላት የግጭት ምንጭ መሆን እንደሌለባቸውና ባሕል ፖለቲካ የሌለበት በመሆኑ ሰዎችን የሚያጋጭ አንድም ነገር እንደሌለ በመግለጽ፣ ማኅበረሰብ ውስጥ የነበረን እሴትና ባሕልን በአደባባይ መግለጥ ለሀገራዊ አንድነትና ሠላም አቅም እንደሚሆን ይገልጻል፡፡
ማርቆስ በላይ
አዲስ ዘመን መስከረም 14 ቀን 2017 ዓ.ም