ኢትዮጵያ በቀንድ ከብት ሀብቷ በአፍሪካ ቀዳሚ በዓለም ደግሞ ከቀዳሚዎቹ ተርታ ብትሆንም፤ በተለይ በአርብቶ አደርና ቆላማ አካባቢዎች ላይ በተደጋጋሚ በሚከሰተው ድርቅ ሳቢያ በርካታ እንስሳቷን ታጣለች፤ ይህን ሀብቱን የሚያጣው አርብቶ አደርም ለተለያዩ ችግሮች የሚዳረግባቸው ሁኔታዎች ሰፊ ናቸው፡፡
እንደ ሀገር የአርብቶ አደሩንም ሆነ የእንስሳቱን ሕይወት ለመታደግ የሚደረግ ጥረት ቢኖርም፣ ብዙዎን ጊዜ ርብርብ የሚደረገው አደጋው ከደረሰ በኋላ በመሆኑ የጠፋውን ሕይወትና ንብረት መታደግ አይቻልም፡፡
የግብርና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተውም፤ በኢትዮጵያ አርብቶ አደር አካባቢ የሚባለው ከ60 እስከ 63 በመቶ የሚሆነውን የቆዳ ስፋት የያዘ ከመሆኑም ባሻገር፣ በሀገሪቱ ካሉት የቀንድ ከብት ብዛት ከ20 በመቶ በላይ የሚሆነው የሚገኘውም በእዚሁ አካባቢ ነው፡፡ በተጨማሪም ከሀገሪቱ በጎች ከ40 በመቶ በላይ፣ ፍየሎች ደግሞ ከ60 በመቶ በላይ እንዲሁም መቶ በመቶ በሚባል ደረጃ ግመሎች ያሉትም በዚሁ አካባቢ ነው፡፡
ከዚህም ባሻገር ኢትዮጵያ ከእንስሳት ሀብት ከምታገኘው የውጭ ምንዛሬም ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው ከዚህ አካባቢ የሚገኝ ነው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ከ12 እስከ 15 ሚሊዮኑ በእዚሁ አካባቢ ይኖራል፡፡ ይሁንና ይህ አካባቢ በአየር ንብረት ለውጥ ችግርም ሆነ በተፈጥሮ ዝናብ አጠር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለተደጋጋሚ ድርቅ ይጋለጣል፡፡
‹‹እ.ኤ.አ በ2021 በተከሰተው ድርቅ ሶስት ሚሊዮን ከኦሮሚያ ክልል፣ 2 ነጥብ 3 ሚሊየን ከሶማሌ ክልል እንዲሁም 300 ሺ ከቀድሞው ደቡብ ክልል በድምሩ 5 ነጥብ 6 ሚሊዮን እንስሳቷን አጥታለች›› የሚሉት በግብርና ሚኒስቴር የአደጋ ስጋት ቅነሳና አካታች የኢኮኖሚ እሴት ማሻሻያ ፕሮጀክት ብሔራዊ ማናጀር አቶ ጀማል አልዬ፣ ይህም የኢኮኖሚዋ መሰረት የሆነውን ዘርፍ በከፍተኛ ደረጃ መጉዳቱን ያስረዳሉ፡፡
ይህንን ያህል ሰፊ የእንስሳት ሀብት ያላትን ሀገር፣ ለሀገር ኢኮኖሚ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ያለውን ማህበረሰብ መታደግ ያስችል ዘንድ በመንግሥትም ሆነ በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሳይቀር የተለያዩ የድጋፍ ሥራዎች ይሰራሉ፡፡
ከእነዚህም ሥራዎች መካከል ቀደም ሲል ሲተገበር የቆው አርብቶ አደሩን ድርቁ ከተከሰተ በኋላ የእንስሳት መድህን አገልግሎት (ኢንሹራንስ) ተጠቃሚ የማድረግ ሥራ አንዱ ነው፡፡ አቶ ጀማል ይህ አገልግሎት በኢትዮጵያ ከተጀመረ 12 ዓመታት ማስቆጠሩን ጠቅሰው፣ አሁንም ድረስ ግን አርብቶ አደሩ የእንስሳት መድህን አገልግሎትን ፋይዳ ተገንዝቦ በሚገባው ልክ ተጠቃሚ አልሆነም ይላሉ፡፡
‹‹የእንስሳት ኢንሹራንስ ከተጀመረ አንስቶ በየዓመቱ ሲሸጥ የነበረው ኢንሹራንስ ከ500 ያልበለጠ ነው፤ በእነዚህ ዓመታት የተሸጠው ኢንሹራንስ በጠቅላላ ብዛት ሲታይም ወደ 20 ሺ አካባቢ ብቻ ናቸው›› ሲሉ ያስረዳሉ፡፡ ለዚህም የተለያዩ ችግሮች እንደ ምክንያት ቢጠቀሱም በዋናነት ግን በአርብቶ አደሩ ዘንድ የሚገባውን ግንዛቤ መፍጠር አለመቻሉ ላይ እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡
በሌላ በኩልም የመድህን አገልግሎቱን አስፈላጊነት አምነው ኢንሹራንስ የገዙት ጥቂት አርሶ አደሮችም ቢሆኑ በድርቁ የተጎዱ እንስሶቻቸውን ከሞት ለመታደግ አልያም በሌላ ለመተካት ጥረት ከማድረግ ይልቅ ለሌላ አገልግሎት የሚያውሉት በመሆኑ አገልገሎቱ በተጨባጭ ለውጥ እንዳያመጣ ያደረገው መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
ይህንን የተገነዘበው ግብርና ሚኒስቴርም ከዓለም ባንክ ጋር በመመካከር፤ ስምምነት በመፍጠር ዘላቂ መፍትሔ ይሆን ዘንድ በጋራ የሚተገበር የአርብቶ አደሩ ኢኮኖሚ እሴት ማሻሻያ ፕሮጀክት የዛሬ ሶስት ዓመት መንደፋቸውን ያስታውሳሉ፡፡
ፕሮጀክቱ ከዓለም ባንክ በተገኘ 120 ሚሊዮን ዶላር ተግባራዊ መደረጉን አቶ ጀማል ገልፀው፤ ከዚህ ውስጥ ደግሞ ትልቁ በጀት ለእንስሳት መድህን አገልግሎት እንዲውል መደረጉን ያመለክታሉ፡፡ በእነዚህ ዓመታትም በ187 ወረዳዎች ላይ ለሚገኙ አርብቶ አደሮች አገልግሎቱ ሲሰጥ መቆየቱን ጠቅሰው፣ በመጀመሪያው ዓመት 52 ሺ 805 አርብቶ አደሮች ኢንሹራንሱን መግዛታቸውንና 365 ሚሊዮን ብር በፕሮጀክቱ የተከፈላቸው መሆኑን አብራርተዋል፡፡
እንደ አቶ ጀማል ገለፃ፤ በዓለም ባንክ የሚደገፈው ይኸው የመድህን አገልግሎት ከዚህ ቀደም ከነበረው አሰራር በተለየ መልኩ በድርቅ ለሚሞቱት እንስሳት ሳይሆን አገልግሎቱን የሚሰጠው፣ አስቀድሞ እንዳይሞቱ ለመከላከል ታልሞ ነው እየተተገበረ ያለው፡፡ ይህም በአርብቶ አደር አካበቢዎች ላይ በሚወሰደው የሳተላይት መረጃ ላይ ተንተርሶ የሚሰራ ሲሆን፣ መረጃው በእነዚህ አካባቢዎች 20 ዓመት ወደኋላ በመሄድ የነበረውን የአየር ሁኔታ፣ የእርጥበትና የሳር መጠንን ጭምር አጠናቅሮ የያዘ ነው፡፡ በተጓዳኝ የአደጋው ስጋት የሚያጠቃቸውን አካባቢዎች መጠንና ወደፊት ሊከሰት የሚችለውን ጭምር ከግምት ውስጥ የያዘ ትንበያንም ያካትታል፡፡
በሳተላይቱ መረጃ መሰረት እነዚህ የአርብቶ አደር አካባቢዎች ወረዳዎች በሶስት የሚከፈሉ መሆናቸውን ያስረዱት የፕሮጀክቱ ማናጀር፤ ‹‹አንደኛው ሁልጊዜም አረንጓዴ መስለው የሚታዩ አካባቢ ሲሆን፣ በዚህ አካባቢ ላይ ኢንሹራንስ አይሸጥበትም›› ይላሉ፡፡ የዚህን ምክንያት ሲያብራሩም ልዩነት እንደማይታይና ኢንሹራንሱን ለመክፈል አስቸጋሪ በመሆኑ ነው›› ሲሉ ይገልፃሉ፡፡
ሁለተኛዎቹ ደግሞ ሁልጊዜም ድርቅ መስለው የሚታዩ ሲሆኑ፣ እነዚያም ቢሆኑ ለመክፈል አዳጋች በመሆናቸው ለኢንሹራንስ አዋጭ አለመሆናቸውን ያመለክታሉ፡፡ በመሆኑም ኢንሹራንሱ በቀጥታ የሚሸጠው ዝናብ በሚመጣበት ጊዜ በጣም አረንጓዴ መስለው ለሚታዩ፣ ዝናብ ሲጠፋ ደግሞ ዝናብ መጥፋቱ በግልፅ የሚታወቅ ልዩነት ላለባቸው አካባቢዎች መሆኑን ነው ያስገነዘቡት፡፡
ፕሮጀክቱ የመድህን አገልግሎት የሚሰጠው አርብቶ አደሮቹ ኢንሹራንሱን በገዙላቸው የእንስሳት መጠን ልክ የሚወሰን መሆኑን አቶ ጀማል ያመለክታሉ። ‹‹ለአምስት ትሮፒካል ዩኒት የሚከፈለው 140 ዶላር አካባቢ ሲሆን፣ ይህም ማለት በቀንድ ከብት ለአንድ በሬ ወይም ላም፤ በበግና ፍየል ሲታሰብ ደግሞ ለ10 በጎች፤ 10 ፍየሎች ይሆናል›› ሲሉ ያስረዳሉ፡፡
እሳቸው እንዳብራሩት፤ ፕሮጀክቱ በተጀመረበት ዓመት አርብቶ አደሩ በእንስሳት መድህን አገልግሎት ላይ ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግና አሰራሩን እንዲለማመድ በማለም 10 በመቶውን ብቻ እንዲከፍል በማድረግ ቀሪው ማለትም 90 በመቶው በፕሮጀክቱ እንዲሸፈን ተደርጓል፡፡ በዚህ መሰረትም 52 ሺ 805 አባወራዎች ኢንሹራንሱን ገዝተዋል፤ 365 ሚሊዮን ብርም ተከፍሏቸዋል፡፡
በፕሮጀክቱ የሚሸፈነው የገንዘብ መጠን በሁለተኛው ዓመት ወደ 80 በመቶ መውረዱን ጠቅሰው፣ ዘንድሮ ደግሞ 70 በመቶ እንዲሆን ተደርጓል ይላሉ፡፡ ቀሪውን 30 በመቶ በመክፈል የአደጋ ስጋት ተጋላጭ የሆኑ አርብቶ አደሮች እንደሚከፍሉ ተናግረዋል፡፡
በሁለቱ የዝናብ ወቅቶች ላይ መሠረት አድርጎ ለሁለት ጊዜ ሽያጭ የሚከናወንበት ይኸው የመድህን አገልግሎት የሚከፈለው ገንዘብ የሚውለው በሳተላይት መረጃ መሠረት እርጥበት አጠርና የሳር ክምችታቸው ተመናምኖ የድርቅ ስጋት ለተጋለጠባቸው አርብቶ አደሮች ነው፡፡ ገንዘቡ የሚውለውም ለውሃ፣ ለሳርና ለመድኃኒት ብቻ ሲሆን፣ ይህም አደጋው ሳይከፋ በፊት የእንስሳቱን ሕይወት ለመታደግ ያለመ ነው፡፡
አደጋው ሲከሰት አርብቶ አደሮቹ ገንዘቡን በራሳቸው ከተከፈተው ዝግ አካውንት ወዲያውኑ አውጥተው መጠቀም የሚችሉበት አሰራር መዘርጋቱን ጠቅሰው፤ ‹‹አንድ አርብቶ አደር ኢንሹራንስ ሲገዛ የራሱ አካውንትና ስልክ ሊኖረው ይገባል፤ ምክንያቱም ዲጂታላይዝድ ስለሚደረግ ነው፡፡ ልክ ድርቁ እንደሚከሰት መረጃው ሲገኝ በዝግ አካውንት የገባላቸውን የኢንሹራንስ ገንዘብ አውጥተው ሳርና ሌሎች ግብዓቶችን የሚገዙበት ሁኔታ ተመቻችቶላቸዋል›› በማለት ያብራራሉ፡፡ በተጓዳኝም ሳር፤ ውሃና መድኃኒት በአቅራቢያቸው እንዲያገኙ የሚደረግ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡
የዚህ ኢንሹራንስ ዋና አላማ እንስሳቱን ከሞት መታደግ ወይም በሕይወት ማቆየት መቻል መሆኑን ያመለከቱት አቶ ጀማል፣ ከዚህ ጎን ለጎን አርብቶ አደሩ የቁጠባ ባሕል እንዲያዳብር ማድረግ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ በዚህም የተጎዱት እንስሳት እንዲያገግሙ በማድረግና በመሸጥ የሚያገኘውን ገንዘብ መልሶ በአካውንቱ በማስቀመጥ ተጠቃሚ እንዲሆን የሚበረታታ መሆኑን ያስገነዝባሉ፡፡ ‹‹ይህ ሲሆንም አርብቶ አደሩ ባስቀመጠው ገንዘብ ልክ ፕሮጀክቱ አስር በመቶ ጉርሻ ይከፍላል›› ይላሉ፡፡
በሌላ በኩልም የእንስሳቱን ሕይወት ከመታደግ ጎን ለጎን አርብቶ አደሩ በቀጥታ ከገበያው ተጠቃሚ እንዲሆን በማለም 187ቱም ወረዳዎች ውስጥ ያሉ ማህበራት በሙሉ ስልጠና እንደሚሰጣቸው ያስረዳሉ፡፡ በመቀጠልም ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጋር በመነጋገርም 20 ሚሊዮን ዶላር በፕሮጀክቱ አማካኝነት እንዲቀመጥ መደረጉን ያመለክታሉ። በመሆኑም በተጨባጭ ገበያ ውስጥ ገብተው ሊነግዱ፣ ሳር አምርተው ሊሸጡ፣ በማጓጓዝ ሥራ ላይ ሊሰማሩ፣ በህክምና ዘርፍ አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉ ማህበራት ካሉ ብድር እንደሚመቻችላቸው ጠቁመዋል፡፡
‹‹ኢንሹራንሱ የሚሸጠው በማህበራት በኩል ነው፤ እነዚህ አባላት ከሞት የታደጓቸውን እንስሳት ወደ ማህበራቱ የሚያመጡበት ሁኔታ እንዲተሳሰር ተደርጓል›› ሲሉ ይናገራሉ፡፡ እሳቸው እንዳሉት፤ ለዚህም ይረዳ ዘንድ የአርብቶ አደር አካባቢዎች በዘጠኝ ክላስተር የተከፈሉ ሲሆን፣ በሁሉም ጠንካራና ጥሩ የእንስሳት ሀብት ያለበት ቦታ ላይ የእንስሳት መሰብሰቢያ ማዕከላት ለመሥራት ታቅዷል። በእያንዳንዱ ክላስተር ሁለት ሁለት በጥቅሉ 18 የእንስሳት ማቆያ ማዕከላት ይገነባሉ፡፡ ዘንድሮ አስሩን ማዕከላት ለመገንባት ጨረታ ወጥቶ ወደ ግንባታ ለመግባት ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡
የዘንድሮ የእንስሳት መድህን አገልግሎት ሽያጭ ነሐሴ 26 ቀን 2016 ዓ.ም መጀመሩን ጠቅሰው፣ መስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም ይጠናቀቃል ብለዋል። በተመሳሳይ ጊዜ ድርቅ በሚያጠቃቸው የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ማለትም በኬንያ፤ ሶማሊያና ጅቡቲ ኢንሹራንሱ እየተሸጠ መሆኑን ገልጸው፣ የሚጠናቀቀውም በተመሳሳይ ጊዜ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ በመሆኑም አርብቶ አደሩ የዚህ የመድህን ዋስትና ተጠቃሚ ለመሆን በተቀመጠው ጊዜ ውስጥ የዋስትና ክፍያውን ማለትም 30 በመቶውን ማከናወን እንደሚገባው አሳስበዋል። ይህ ክፍያ የሚያገለግለው ለአንድ ዓመት ብቻ መሆኑን አስታውሰው፤ ቀሪው 70 በመቶ በፕሮጀክቱ እንደሚሸፈን አስታውቀዋል፡፡
በዓመት ሁለት ጊዜ በሚከናወነው የእንስሳት መድህን ዋስትና ሽያጭ በዚህ ዓመት ለ80 ሺ አርብቶ አደሮች ተደራሽ ለማድረግ የታቀደ መሆኑን አቶ ጀማል ጠቁመው፤ ‹‹ አርብቶ አደሩ ይህንን ምቹ እድል በመጠቀም የእንስሳት መድህን ዋስትና በመግዛት እንስሳቱንም ሆነ ራሱን ከአደጋ አስቀድሞ ሊከላከል ይገባል›› በማለትም ያሳስባሉ፡፡ በዚህም ረገድ የሚዲያ ተቋማትን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የእንስሳት መድህን ዋስትና ያለውን ሀገራዊ ፋይዳ ለአርብቶ አደሩ ግንዛቤ በመፍጠር ብሎም ተደራሽነቱ እንዲሰፋ ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 13 ቀን 2017 ዓ.ም