የአማራ ሕዝብ ጽንፈኛ ኃይሎችን በእውነተኛ ማኅበረሰባዊ ማንነቱና እሴቶቹ በጽናት ታግሎ ያሸንፋቸዋል!

የአማራ ሕዝብ ከኢትዮጵውያን ወንድሞቹ የተለየ ፍላጎት የለውም ። ፍላጎቱ ሰላም እና ፍትሃዊ ልማት የሰፈነባት የበለጸገች ሀገር መፍጠር ነው። ይህን እውን ለማድረግም እንደ አንድ ትልቅ ሕዝብ በየዘመኑ ሰፊ ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል ። እንደ ሀገር ባለን የጋራ ታሪክ ውስጥም ይህ ጥረቱ ሰፊ ሥፍራ እንዳለው የታሪክ መዛግብት ያመላክታሉ።

በሀገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ የጎላ ድርሻ ያለው የአማራ ሕዝብ ፤ ከሌሎች የሀገሪቱ ብሄር ፣ ብሄረሰቦች እና ሕዝቦች ጋር በፍቅር አብሮ መኖር የሚያስችል የዳበረ መንፈሳዊ ፣ ማኅበራዊ እና ባህላዊ እሴቶች ባለቤት ነው ፤ ይህም በዘመናት የሀገረ መንግሥት ታሪክ ውስጥ ጎልቶ የታየ፣ ዛሬም የሚታይ እውነታ ነው።

የአማራ ሕዝብ ፈርሀ አምላክ ያለው ፤ ለፍትህ እና ለነጻነት ቀናኢ የሆነ ፤ ሰው ሰው በሚሸቱ ማኅበራዊ እሴቶች የደመቀ ነው ። ይህ ማኅበረሰባዊ ማንነቱ ለዘመናት ከሌሎች የሀገሪቱ ሕዝቦች ጋር ተስማምቶ፣ ተፋቅሮ ፣ ተጋብቶ እና ተዋልዶ እንዲኖር ያስቻለው እና የአብሮ መኖር ተምሳሌት ያደረገው ነው ።

እንደ ሀገር ለሉዓላዊነት ፣ለፍትህ እና ለነጻነት በተደረጉ ብሔራዊ ትግሎች ውስጥ ግንባር ቀደም በመሆን በሀገር ባለውለታነት የሚጠቀሱ ብሔራዊ ጀግኖችን በየዘመኑ የሚያፈራ ፣ እንደ ሕዝብ የወደፊት እጣ ፈንታው ከመላው ኢትዮጵያውያን ወንድም ፤ እህቶቹ ጋር የተቆራኘ መሆኑን ተረድቶ ለዚሁ የሚተጋ ነው።

በየዘመኑ በተፈጠሩ የለውጥ ንቅናቄዎች ውስጥ በስፋት ከመንቀሳቀስ ባለፈ ፤ ለለውጥ እሳቤዎች መስዋዕትነትን በመክፈል ፤ ለሀገር እና ለሕዝብ ባለውለታ የሆኑ በብሔራዊ ታሪካችን ውስጥ በደማቸው ደማቅ ምዕራፍ የጻፉ ባለውለታዎችን መፍጠር የቻለ ፤ መቼም ቢሆን ለዚህ የሚሆን ሁለንተናዊ ዝግጁነት ያለው ነው ።

የአማራ ሕዝብ ረጅም ዘመን ባስቆጠረው ሀገረ መንግሥት ውስጥ ከሌሎች ወንድም የሀገሪቱ ብሔር ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ጋር ክፉና ደጉን የተጋራ ፤እንደ ሕዝብ የሚያነሳቸው ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጥያቄዎችም እንደሀገር ከሚነሱ ጥያቄዎች የሚመዘዙ ፤ ከመላው ሕዝባችን ጥያቄዎች ያልተለዩ ናቸው።

ከሁሉም በላይ ጥያቄዎቹ ሰላም እና ከሰላም የሚመነጭ ፍትሃዊ ልማት ፤ ጠንካራ የሀገረ መንግሥት ግንባታ እና ከዚህ የሚመነጭ ብሄራዊ ማንነት ፤ ሀገራዊ ብልጽግና እና ከዚህ የሚመነጭ ብሄራዊ ክብር ነው። ለዚህ ደግሞ በየዘመኑ ብዙ መስዋዕትነት ሲከፍል ቆቷል ፤ ዛሬም እየከፈለ ነው።

ይህ የአማራ ሕዝብ ጥያቄ የመላው ሕዝባችን ጥያቄ ነው። ምላሽ ሊያገኝ የሚችለውም እንደ ሕዝብ ባለን አንድነት እና አንድነቱ በሚፈጥረው አቅም ነው። ይህንን በአግባቡ በመረዳቱ ነው ፤ በለውጡ ማግስት የአማራ ሕዝብ የለውጡ ትልቁ አቅም ሆኖ የተገለጠው ። ዛሬም ዋነኛ የለውጥ አቅም ሆኖ የቀጠለው።

ከዚህ ውጪ በአማራ ሕዝብ ስም የሚነሱ ጥያቄዎችም ሆኑ ፤ ጥያቄዎቹን መሠረት አድርገው በየመንደሩ የሚካሄዱ ከሕዝቡ መንፈሳዊ፣ ማህበራዊ እና ባህላዊ እሴቶች ያፈነገጡ በደመነፍስ የሚዘወሩ ተግባራት የአማራን ሕዝብ የሚወክሉ አይደሉም ፣ ይወክላሉ ብሎ ማሰብም ይህንን ትልቅ ሕዝብ አሳንሶ ከማየት የሚተናነስ አይሆንም።

የአማራ ሕዝብ ፤ለፍትህ እና ለነጻነት ቀናኢ የሆነ፤ ለሀገሩ ሉዓላዊነት በየዘመኑ መስዋዕትነት ሲከፍል የቆየ እንጂ ፤ ፍትህን የሚያጠለሽ ፤ በነጻነት የሚያፌዝ ፤ በሀገር ጉዳይ በባንዳነት የሚሰለፍ፤ ባንዳነትን ክብር አድርጎ በአደባባይ የሚያዜም አይደለም።

ጀብደኝነት እና ነፍሰ ገዳይነት እንዲሁም ጽንፈኝነት እና አክራሪነት የአማራ ሕዝብ ማኅበራዊ እሴቶች አይደሉም። በዚህ መልኩ አደባባይ የሞሉ ግለሰቦች ሆኑ ቡድኖች ፤ ከዚህም አልፈው እራሳቸውን የአማራ ነጻ አውጪ አድርገው የሚያዩ ኃይሎች በዚህ ማንነታቸው መቼም ቢሆን የአማራን ሕዝብ ሊወክሉ እንደማይችሉ ሊገነዘቡ ይገባል። እነዚህን የጥፋት ኃይሎችም የአማራ ሕዝብ በእውነተኛ ማኅበረሰባዊ ማንነቱ በጽናት ታግሎ ያሸንፋቸዋል!

አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 13 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You