ባሳለፍነው ሳምንት 12ኛው የአሜሪካና የአፍሪካ አገራት የቢዝነስ ስብሰባ ተካሂዶ ነበር። በሞዛምቢክ ማፑቶ በተካሄደው ስብሰባ የአስራ አንድ አገራት መሪዎች እና አንድ ሺ የሚሆኑ የቢዝነስ መሪዎች ተሳትፈውበታል። ሶስት ቀናት በፈጀው ስብሰባ ቀደም ብሎ የአሜሪካ ባስልጣናት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የአፍሪካ አገራት ውስጥ የ60 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስመንት ለማካሄድ ፍላጎት ላይ ውይይት ተደርጎ ነበር ።
አሜሪካ ፍላጎቷን ካሳወቀች ከስድስት ወራት በፊት የአገሪቱ ብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ጆን ቦልተን ለትራምፕ አስተዳደር ‹‹አዲሱን የአፍሪካ ስትራቴጂ›› አቅርበዋል። ስትራቴጂው ዋነኛ ተቀናቃኝ የሆኑትን ቻይናና ሩስያን በአፍሪካ ውስጥ በከፍተኛ መጠን በፋይናስና በፖለቲካ ተፅዕኖ እያሳደሩ እንደሚገኙ ያትታል። ሁለቱ አገራት በአፍሪካ ውስጥ በኢንቨስትመንት ዘርፍ የአሜሪካንን ተፅዕኖ ለመቀነስ እየሰሩ መሆኑንም ይገልፃል።
በስትራቴጂው ቻይናና ሩስያ በተደጋጋሚ በመጥቀስ ባለፉት ወራት አሜሪካ ሁለቱ አገራት በአፍሪካ ያላቸው ተሰሚነት እንዲቀንስ በርካታ ስራ አከናውናለች። ይህ ሁኔታ ደግሞ በቀጣይ አፍሪካ ቀዝቃዛ የሆነ ጦርነት እንድታስተናግድ የሚያደርጋት ሲሆን በቻይናና በአሜሪካ መካከል የንግድ ጦርነቱ እየተባባሰ እንዲመጣም አድርጎታል። በአህጉሩ የውጭ አገራት ወታደሮች እየገቡ ሲሆን የዲፕሎማሲ ግንኙነቶች እየጨመሩ መጥተዋል። አፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ የቀዝቃዛው ጦርነት ጅማሮ ምልክቶች እያየች ትገኛለች። ይህ እንቅስቃሴ እንደቀድሞው አህጉሪቱን እየናጣት ሲሆን የአፍሪካ አገራት መሪዎች በግዳጅ ያለፍላጎታቸው የኢኮኖሚ አቅጣጫቸውን እንዲለውጡ ተደርጓል። ይህ ደግሞ የአፍሪካን እድገትና ሰላም እያናጋ ይገኛል።
የኢኮኖሚ ጦርነት
ቻይና የአፍሪካ አገራትን ስትቀርብ ለኢኮኖሚ ጥቅሟ ብቻ ነው የሚሉ ወገኖች በርካታ ናቸው። አብዛኛው የአፍሪካ አገር የቻይና ኢንቨስትመት ተጠቃሚ መሆን የጀመረው እአአ 1999 ቻይና ባወጣችው ‹‹በሌሎች አገራት ኢንቨስት ማድረግ›› ፖሊሲ ተከትሎ ነው። ይህ ፖሊሲ የቻይና ባለሀብት የተለያዩ አገራት በመሄድ ኢንቨስት እንዲያደርጉ የሚያበረታታ ነው። በዚህ ምክንያት በአፍሪካ የቻይና የንግድ እንቅስቃሴ ባለፉት 20 ዓመታት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። እአአ 2017 የንግድ እንቅስቃሴው 140 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል። እአአ 2003 እስከ 2017 የቻይና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በየዓመቱ አራት ቢሊዮን ዶላር እያስመዘገበ መጥቷል። የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ድርሻ በአጠቃላይ 43 ቢሊዮን ዶላር የደረሰ ሲሆን ይህ ደግሞ በብዛት በመሰረተ ልማትና በሀይል ማመንጫ ዘርፍ የተገኘ ነው።
ቻይና በአፍሪካ የመሰረተ ልማትና የባቡር መስመር ዝርጋታዎችን በስፋት ያከናወነች ሲሆን ኬንያ፣ ኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ፣ አንጎላ እና ናይጄሪያ ግንባታ ካከናወነችባቸው አገራት መካከል ተጠቃሽ ናቸው። በአሁን ወቅት ደግሞ በአንጎላ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድብ እና ኢትዮጵያንና ጅቡቲን የሚያገናኝ በአፍሪካ ረጅሙ የባቡር መስመር እየሰራች ትገኛለች። በተጨማሪም በአዲስ አበባ የሚገኘውን የአፍሪካ ህብረት ዋና መስሪያ ቤትና በአቡጃ የኢኮዋስ ህንፃ መገንባቷም ይታወሳል።
ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት
በአሜሪካና በቻይና መካከል ያለው ውጥረት እየተባባሰ በመምጣቱ በአህጉሪቱ የፀጥታ ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ እየደረሰ ይገኛል። ለዚህም ሁለቱም አገራት ወታደሮቻቸውን በአፍሪካ አሰማርተዋል። ባለፉት 15 ዓመታት የቻይና ህዝቦች ላይብሬሽን ፍሮንት ወታደሮች በአፍሪካ የተለያዩ ሰላም ማስከበር ስራዎች ላይ ተሳትፈዋል። በተለይ ደግሞ በሱዳን፣ በደቡብ ሱዳን፣ በላይቤሪያ፣ በማሊና በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ውጤታማ ሰላም ማስከበር ስራ አከናውነዋል። በሌላ በኩል ደግሞ በአፍሪካ ህብረት ሰላም ማስከበር ተልዕኮ ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው መሳሪያዎችን ለግሳለች። በሶማሊያና በደቡብ ሱዳን ውስጥ ለተደረጉ የሰላም ማስከበር የድርድር ስራዎች ከፍተኛ የሆነ ድጋፍ አድርጋለች።
እአአ 2017 የመጀመሪያው የቻይና ወታደራዊ ካምፕ በጅቢቲ ተከፈተ። ካምፑ አስፈላጊ ነገሮች የተሟሉለት ሲሆን በአሁኑ ወቅት 400 ወታደሮችን ይዟል። ነገር ግን ካምፑ እስከ አስር ሺ ወታሮች የመያዝ አቅም አለው። በጅቡቲ የሚገኙት ወታደሮች የቻይና ባህር ሀይል ወታሮችን የሚጠብቁ ሲሆን በተጨማሪም በአካባቢው የሚኖሩ ስጋቶችን ለመቀነስ አላማ አድርገው ይንቀሳቀሳሉ። ቻይና በአፍሪካ ያላትን የንግድ እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ከፍተኛ የሆነ በጀት መድባ እየሰራች ትገኛለች።
በአህጉሪቱ ውጥረት መብዛት
ጅቡቲ በአሁኑ ወቅት እራሷን በቻይናና በአሜሪካ መካከል የሚደረገው የዲፕሎማቲክ ክርክር መናኸሪያ ሆና አግኝታዋለች። ጅቡቲ ለሁለቱ አገራት ወታደራዊ መቀመጫ በመሆንዋ ወደየትኛው እንደምታዘነብል የከበዳት ይመስላል። እአአ 2018 ላይ ጅቡቲ በአረብ ኢምሬት ተይዞ የነበረውን ዶራላህ የኮንቲነር ዴፖ ለነፃነቴ አመቺ አይደለም በሚል ተቀብላች። ነገር ግን የጅቡቲ ባለስልጣናት አረብ ኢምሬት በሶማሌ ላንድ የሚገኘውን የበርበራ ወደብን በማልማት የጅቡቲ ወደብን ይቀናቀናል የሚል ስጋት ገብቷቸዋል። በዚህ ደግሞ በወደቡ ከፍተኛ ተጠቃሚ የሆነችው ኢትዮጵያን ልናጣ እንችላለን የሚል ፍራቻቸው አይሏል። በጅቡቲ ባለስልጣናት ውሳኔ የአረብ ኢምሬት ድርጅት ሲሰናበት አሜሪካ ተቃውሟዋን ያሰማች ሲሆን የትራምፕ አስተዳደር ጅቡቲ ከአረብ ኢምሬት የቀማችውን ዴፖ ለቻይና ልትሰጥ ትችላለች የሚል ስጋት ገብቷት ነበር።
የአሜሪካው የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ጆን ቦልተን ጅቡቲ ለቻይና ዴፖዎቹን አሳልፋ ከሰጠች በምስራቅ አፍሪካ አካባቢ በባህር ላይ ከአውሮፓ፣ ከመካከለኛው ምስራቅና ከደቡብ እስያ ጋር የሚደረገው ንግድ በቻይና እጅ እንደሚወድቅ ተናግረዋል። ለዚህ ደግሞ የአሜሪካን ወታደሮች ህዝቦቻቸውን ለመጠበቅ ሲሉ ማንኛውንም እንቅስቃሴ እንደሚያደርጉ ጠቅሰዋል። ጅቡቲ የኮንቴነር ማከማቻ ዴፖዎቹን ለቻይና እንዳትሰጥ ግፊት የተደረገባት ሲሆን ግፊቱ ከአሜሪካ ፍራቻ ጋር የተያያዘ አልነበረም። አሜሪካ እስካሁን ድረስ በአፍሪካ ወታደራዊ ካምፕ ለመመስረት የሚያስችላትን አማራጭ ቦታ እየፈለገች ሲሆን በቅርቡ ኤርትራን መዳረሻዋ አድርጋለች።
ሳውዲ አረቢያ እና የተባሩት አረብ ኢምሬት በአካባቢው የሚገኙ አገራትን በመደገፍ እንዲነቃቁ አድርገዋል። ከዚህ ውስጥም ለረጅም ጊዜ ከዓለም ተገላ የነበረችውን ኤርትራ ወደ መስመር እንድትገባ አድርገዋል። የረዥም ጊዜ ጠላቶች የነበሩት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ለ20 ዓመት ያክል ያደረጉትን ሞት አልባ ጦርነት በማስቆም የሰላም ስምምነት ሲያደርጉ የተባበሩት መንግስታት በኤርትራ ላይ ጥሎት የነበረውን ማዕቀብ አንስቷል። በዚህ ምክንያት ኤርትራ የጅቡቲ ተቀናቃኝ ልትሆን እንደምትችል ግምቶች እየተሰጡ ነው። በኤርትራ የውጭ አገራት ወታደሮች የማስፈርና ኢኮኖሚያዊ መሰረተ ልማቶች እየገነቡ ይገኛሉ። ለምሳሌ የተባበሩት አረብ ኢምሬት በአሰብ ወደብ አቅራቢያ ወታደራዊ ካምፕ ሰርታለች።
ሰሜን ሱዳን ስልጣን ለመያዝ በሚደረግ ብጥብጥ ከፍተኛ የሆነ ሽኩቻ ውስጥ ናት። ቻይና የረጅም ጊዜ የኦማር አልበሽር ደጋፊ ናት። በአልበሽር የስልጣን ዘመን ቻይና የነዳጅ ኢንዱስትሪውን በመቆጣጠርና 80 በመቶ ነዳጅ በመግዛት ለአልበሽር ከፍተኛ የገንዘብ ምንጭ ነበረች። አልበሽር በሚያገኘው ገንዘብ የጦር መሳሪያ በመግዛት ከአማፅያን ጋር ሲዋጋበት ቆይቷል። የተወሰኑ አገራት ማለትም ሩስያን ጨምሮ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ህግ ጥሰው ለአልበሽር የጦር መሳሪያ ይሸጡም ነበር።
እአአ 2011 ደቡብ ሱዳን ነፃነቷን ካገኘች በኋላ ቻይና ለሁለቱም ሱዳኖች አጋር ሆና ቀጥላለች። ቻይና በሁለቱም ሱዳኖች ውስጥ ንግዷን እያጧጧፈች ትገኛለች። እአአ 2018 ላይ ቻይና በአፍሪካ አገራት የ60 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት የጀመረች ሲሆን ከኢንቨስትመንቱ ሱዳን አንደኛዋ ተጠቃሚ ነች። በተጨማሪም 10 ቢሊዮን ዶላር እዳ ቻይና ለሱዳን ሰርዛለች። የቻይና መንግስት በሱዳን ባህር ዳርቻ የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን ለመገንባት እቅድ አላት። በባህር ዳርቻ ልማት ስራዎች ኳታርና ቱርክ ከአልበሽር ጋር መፈራረማቸው የሚታወስ ነው።
ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት ታህሳስ ወር ላይ የህዝብ ተቃውሞ ሲነሳ ቻይና ከአልበሽር ጎን ቆማ ነበር። የአልበሽር መንግስት በአገሪቱ መረጋጋት እንዲመጣና ቻይና እየሰራችው ያለው መንገድ እንዳይቆም ጥረት አድርጓል። በሌላ በኩል የትራምፕ አስተዳደር በተደጋጋሚ አልበሽር ለሌላ ዘመን ለፕሬዚዳንትነት እንዳይወዳደር ውትወታ አድርጎም ነበር። በህዝባዊ ተቃውሞዎች አልበሽር ከስልጣን መነሳት አሜሪካ የተቀበለችው ሲሆን በውሳኔው ሳውዲ አረቢያና አረብ ኢምሬት የተደሰቱ አይመስሉም።
ሁለቱ የባህረሰላጤ አገራት በሱዳን ሌላ ጠንካራ መሪ መጥቶ የአካባቢውን ፖለቲካ እንዲቆጣጠር ፍላጎት ነበራቸው። ሱዳን በየመን፣ በቱርክና በኳታር በሚደረጉ ጦርነቶች ላይ ተሳታፊ እንድትሆን ምኞት ነበራቸው። ቻይና በአረብ ኢምሬትና በሳውዲ አረቢያ ጣልቃ ገብነት በአሁኑ ወቅት አገሪቱን እያስተዳደረ ካለው ወታደራዊ ካውንስል ተቀባይነቷ እየቀነሰ መጥቷል። ከጅቡቲና ከቻይና ውጭ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት በቻይናና በአሜሪካ ፍጥጫ እየተጎዱ ይገኛሉ። የሁለቱ አገራት ፖለቲካዊ ሽኩቻ በሌሎች በአካባቢው ጣልቃ በገቡ በተለይ ግብፅ፣ የባህረሰላጤ አገራት፣ ኢራንና ቱርክ ላይ ውጥረት ፈጥሯል። የትራምፕ አስተዳደር በተለይ ከግብፅ፣ ከሳውዲ አረቢያና ከአረብ ኢምሬት ጋር በመስማማት በምስራቅ አፍሪካ አካባቢ ያለውን የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለመለወጥ እየሰራ ይገኛል።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 1/2011
መርድ ክፍሉ