አዲስ ዘመን ድሮ

ከዛሬው የድሮው ይሻላል እንዳንል የማያስችሉ ታሪኮች በቀድሞዎቹ የአዲስ ዘመን ገጾች ላይ ሰፍረው እናገኛቸዋለን። በተለይ በአንዳንድ ዘርፎች የነበሩን እመርታዎች እጅን አፍ ላይ አስጭነው በአርምሞ እናነባቸው ዘንድ ግድ የሚሉ ናቸው። ከመምህርነት ሙያ፣ ከኪ(ሥ)ነጥበብ አኳያ ወዘተ የነበሩትን ወደ ኋላ መለስ ብለን ስናነባቸው አነሳሳቸው የት የሚያደርስ ሆኖ ሳለ፣ ዛሬ ያለንበት ግን መሠረቱ እነሱ እስከማይመስሉን ድረስ የሚያስገርም ሁኔታ ላይ ነው ያሉት።

ስለሥነጥበብ የተደረገ ስብሰባ

ባለፈው ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ ሰባ ያህል የሚሆኑ አርቲስቶችና የሥነጥበብ ተግባር ልምድ ያላቸው የድንጋይ ቅርፅ ሠዓሊዎች በብርሃንህ ዛሬ ነው ኢንስቲትዩት በተደረገው ጉባዔ ተገኝተዋል።

ይህ ስብሰባ እንዲደረግ በማስተባበር የትምህርትና የሥነጥበብ ሚኒስቴር ብሔራዊ የአርቲስቶች ማህበር እንዲቋቋም ምኞት አለው።

ምንም እንኳን ይህንን የመሰለ ስብሰባ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገ ቢሆንም አሁን የተመሠረተበት ሁኔታ ለወደፊት ለሚያደርገው ርምጃ በጣም ጠቃሚ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።

በዚሁ ስብሰባ ላይ የሥነጥበብ እድገት የተፋጠነ መደብ እንዲይዝ የሚወዱ ወጣቶችና በእድሜ የበሰሉ አርቲስቶች ተገኝተዋል። አብዛኞቹ የሥነጥበብ ተግባር አዋቂዎች በየቤተክርስቲያኖችና እንዲሁም በየጠቅላይ ግዛቶቹ የሠሩት ሥዕል የተደነቀላቸው ሠዓሊዎች ነበሩ።

የቀድሞዎቹ አርቲስቶች ወደ ፊት ኢትዮጵያ በሥነጥነበብ ረገድ ለምታደርገው የርምጃ ድልድይ ጠቃሚ መሠረት በመጣል ያለፈውንና የዛሬውን ትውልድ ያገናኛሉ።

ከዛሬዎቹ አርቲስቶች መካከል የማስታወቂያ ቀራጮች፣ እውነትን ተከታታይ አርቲስቶች፣ የድንጋይ ቀራጮች፤ እንዲሁም እጅግ ከታወቁት አርቲስቶች መካከል ቦታ ለማግኘት የሚጥሩ የሥነጥበብ አፍቃሪ አርቲስቶች ተገኝተዋል።

አቶ አበበ ከበደ የትምህርት ሚኒስቴር የሥነጥበብ ዲሬክተር ብሔራዊ የአርቲስቶች ማህበር የኢትዮጵያን የሥነጥበብ ተግባር እንደሚያስፋፋ በንግግራቸው ላይ ገልፀዋል። ንግግራቸውንም በመፈፀም የትምህርትና ሥነጥበብ ሚኒስቴር እንዲህ ያለ ማህበር እንዲቋቋም ፈላጊ ነው ሲሉ አስታውቀዋል።

አርቲስቶቹ ሁለት ሰአት ያህል በሚሆን ጊዜ ውስጥ እርስ በርሳቸው ንግግር አድርገዋል። በመጨረሻም የማስታወቂያና የዝግጅት ኮሚቴ እንዲቋቋም ውሳኔ በማድረግ በዚህ ተግባር ሃላፊነት የሚኖራቸው ሰዎች ስድስት እንዲሆኑ ተስማምተዋል።

ምንም እንኳን ይህ የአርቲስቶች ህብረት የመጀመሪያው ተግባር ቢሆንም፤ ለወደፊት የሚታወስ ነገር የሚፈጥር ስለሆነ፣ የማህበሩ ባልደረቦች እንዲሆኑ ፈላጊዎችን ለማቅረብ በታወሱ ወቅቶች የሚመጡ የሥዕል መጽሔቶችን ያዘጋጃል። ተገቢ የሥዕል ማሳያ ቦታ እስኪዘጋጅ ድረስ ስድሳ ያህል የሚሆኑ የአርቲስቶች የሥራ ፍሬ በአዲስ አበባ እንዲታይ ተወስኗል።

(አዲስ ዘመን፣ ሀሙስ፣ ሀምሌ 2 ቀን 1951 ዓ.ም)

የመምህራን ስብሰባ በዋሽንግተን

የዓለም መምህራን የኮንፌዴራሲዮን ዝግጅት እኤአ ከ1959 እስከ 1960 ዓ•ም የሚደረገውን የዓለም ሕዝቦች ማግባቢያ ፕሮግራም በሙሉ ድምፅ ተቀብሎታል።

አንድ ሺህ ያህል የሚሆኑ የአራት ሚሊዮን አባሎች ኮንፌዴራሲዮን መልእክተኞች ተካፋይ ሆነው ድምፅ ሠጥተዋል። ከድምፅ ሰጪዎቹ መካከል የ74ቱ ሀገሮች መምህራን ይገኙባቸው ነበር።

ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና ከዩኔስኮ ጋር ሕብረትና ግንኙነት ለማድረግ የቀረበውን ሃሳብ በሙሉ ድምፅ ተቀብለውታል። በተለይም የአፍሪካና የእሲያ ሕዝቦች ርምጃቸው የተቃና የትምህርት ውጤት እንዲሰጥ ንግግር ተደርጎ ነበር። የኦስትራሊያና የኒውዚላንድ አባሎች እኤአ በ1960 ዓ•ም በሚደረገው የእሲያ ክፍለ ዓለም ጉባኤ ተካፋይ እንዲሆኑ ስምምነት ተደርጓል። ከዚህም በስተቀር አንድ ልዩ ኮሚቴ የእሲያን የትምህርት ሁኔታ በተመለከተ ሪፖርት እንዲሰጥ ተጠይቋል።

ከእሲያ ጓድ መካከል የተገኙት የሴሎን፣ የህንድ፣ የፓኪስታንና የኢራን መልእክተኞች ናቸው። እንዲሁም የአፍሪካ የትምህርት ሁኔታ የበለጠ ፍሬ እንዲያስገኝ ሰፊ ሀተታ ተደርጎ ጉዳዩ ስምምነትን አግኝቷል።

የሱዳን፣ የጋና፣ የናይጄሪያ፣ የኬንያ፣ የኢትዮጵያ፣ የቤልጅግ ኮንጎ፣ የግብፅ፣ የጋምቢያ፣ የዩጋንዳ፣ የታንጋኒካ፣ የሰሜን ሮዴሺያ፣ የናያሳላንድ፣ የጊኒ፣ የደቡብ አፍሪካ፣ የሴራሊዎን፣ የእንግሊዝና የአሜሪካ የመምህራን ሕብረት አባላት ስለ አፍሪካ ትምህርት መልካም ርምጃ ለመመካከር ተገናኝተዋል።

(አዲስ ዘመን፣ ነሀሴ 1 ቀን 1951 ዓ•ም)

ከእንግሊዝ ንግሥት ለዶክተር ንክሩማህ የተሰጠ የክብር ሥም

የጋና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ክዋሜ ንክሩማህ የንግሥቲቱ ምክር ቤት አባል እንዲሆኑ የእንግሊዝ ንግሥት ግርማዊት ዳግማዊት ኤልሳቤጥ እንደሾሟቸው ከለንደን ተነገረ። የዚህም የክብር ሥም አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓት የተከናወነው የሎርዶች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሎርድ አይቻን በተገኙበት በባልሞራል ቤተመንግሥት ነው።

በዚህም ጊዜ ሎርድ አይቻን ባደረጉት ንግግር ውስጥ ጋና ብዙ ሀብት ያላት ሀገር መሆኗን፤ እንዲሁም ዶክተር ንክሩማህ ከሌሎች የእንግሊዝ አንድነት ሀገሮች መሪዎች መካከል ከፍ ያለ ግምት ያላቸውና እንዲሁም በተደረገላቸው አቀባበል ከሌሎቹ ሁሉ የተለየ መሆኑን ተናግረዋል። እንዲሁም ዶክተር ንክሩማህ በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር ውስጥ ግርማዊት የእንግሊዝ ንግሥት ጋናን እስቲጎበኙ ድረስ ባለቤታቸው ልዑል ፊሊፕ ጋናን እንዲጎበኙ ሲሉ አሳስበዋል። ቀጥለውም ግርማዊት ዳግማዊት ኤልፃቤጥ እኤአ በ1961 ዓ•ም የጋናን ሀገር እንዲጎበኙ ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል። ዶክተር ንክሩማህ ነገ ጠዋት ከለንደን እንደሚነሱ ታውቋል።

(አዲስ ዘመን፣ ነሀሴ 8 ቀን 1951 ዓ.ም)

ግርማ መንግሥቴ

 አዲስ ዘመን መስከረም 7/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You