የዘመን አቆጣጠራችን ለምን ተለየ?

ብዙ ነገራችን ከተቀረው ዓለም የተለየ ወይም ወጣ ያለ ነው። አንዳንድ ነገራችን ደግሞ ይብሱን አፈንጋጭ ነው። የአየር ንብረታችን ሳይቀር። ቅኝ ያልተገዛን፣የራሳችን ፊደልና የዘመን አቆጣጠር ያለን። ባህላችንና ወጋች ከአይሁዱም፣ ከአረቡም፣ ከምሥራቅ ኦርቶዶክስ ወይም ቤዛንታይን ያጣቀሰ። ሶስቱን አብርሃማዊ እምነቶችን አጋምዶ የያዘ።የሰው ልጅ ቀደምት መገኛ እያልን ብዙብዙ መዘርዘር እንችላለን።

ከጎርጎሮሳውያን በተለየ አዲስ አመትን እንቀበላለን። እኔም ስለ የዘመን አቆጣጠራችን ከበይነ መረብና ከድረ ገጽ የቀራርምሁትን ላካፍላችሁ ወደድሁ። መጀመሪያ መላ ኢትዮጵያውያን እንኳን ለአዲሱ አመት አደረሳችሁ። አዲሱ አመት የሰላምና የፍቅር አመት ይሁንልን። አሜን።

በመምህር ተመስገን ዘገዬ ድረ ገጽ መ/ር ሸዋንዳኝ አበራ፤ ”የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ከካቶሊክ አውሮጳውያን (ጎርጎርዮሳውያን)፣ ከምሥራቅ ኦርቶዶክስ (የባይዛንታይን)፣ከዕብራውያን እና ከዐረቦች የዘመን ቀመር ጋር ያለው ልዩነት፤ “በሚል ርዕስ ባስነበቡን መጣጥፍ፤የአይሁድ እና የክርስትና ሃይማኖት መነሻ ስፍራ በሆነችው እስራኤል ዕብራውያን የሚጠቀሙት የዘመን አቆጣጠር በሐሳበ ጨረቃ እና በሐሳበ ጸሐይ መሠረት (lunisolar) የተቀመር ሲሆን፤ በአንድ ወር ውስጥ የሚገኙት ቀናት ጨረቃ መሬትን ለመዞር የሚፈጅባትን ቀን መሠረት ያደረገ በመሆኑ የአንድ ወር ርዝመት በ29 ወይም በ30 ቀናት የተወሰነ ነው።

አንድ ዓመትም በመደበኛው ባለ 12 ወራት ውስጥ 353፣ 354 ወይም 355 ቀናት እና በተውሳክ ባለ 13 ወራት ባለ 29 እና 30 ቀናት ይኖሩታል። በተውሳክ በዓመት ውስጥ 383፣ 384 ወይም 385 ቀናት ሲኖሩት በ19 ዓመት አንድ ጊዜ ከሐሳበ ፀሐይ ጋር እንዲስተካከል ያደርጉታል። ይህ የዕብራውያን የዘመን አቆጠጠር የአመቱ የመጀመሪያ ወር ሃይማኖታዊው መጋቢት- ኒሳን ( נִיסָן -Nisan)፤ እንዲሁም የአዲስ ዓመት መጀመሪያ በሰባተኛው ወር መስከረም (תִּשְׁרִי Tishrí) (First month of civil year.) በመሆኑ እንደ ልደት፣ ጥምቀትና ሌሎች የክርስቲያን በዓላትን ወቅቱን ጠብቀው ለማክበር ሲቸገሩ የትንሣኤን በዓል ግን የአይሁድን ፋሲካ ተከትለው ( נִיסָן Nisan) 14 ያከብሩ ነበር። (ይህ ዕለት በእኛ፣ በጁሊያንና በግሪጎሪያን አቆጣጠር መጋቢትና ሚያዝያ ላይ ይመላለሳል።)

በሌላም በኩል ሌሎቹም የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች በሐሳበ ጨረቃ (lunar) የሚመራ የዘመን አቆጣጠር ይጠቀማሉ፤ በአንድ ወር ውስጥ የሚገኙት ቀናትም እንደ ዕብራውያን ጨረቃ መሬትን ለመዞር የሚፈጅባትን ቀን መሠረት ያደረገ በመሆኑ የአንድ ወር ርዝመት በተመሳሳይ በ29 ወይም በ30 ቀናት የተወሰነ ነው። በአንድ ዓመት በ12 ወራት ውስጥ የተመደቡ 354 ቀናት ያላቸው በመሆኑ ከጸሐይ ዓመት በ11 ቀናት በማነሱ ዓመቱን ጠብቆ እንደ ልደት፣ ጥምቀትና ሌሎችንም ዓመታዊ የክርስትና በዓላት ለማክበር ስለሚቸገሩ እንደሚኖሩበት ይፋ የዘመን አቆጣጠር በተለያዩ ቀናት ለማክበር ይገደዱ ነበር።

የግብጽ ቤተ ክርስቲያንና የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር በሐሳበ ፀሐይ መሠረት (solar) የተቀመረና የዓመቱ እና የወራቶቹ እርዝማኔ እኩል ሲሆን፤ በሁለቱ መሃል ያለው ልዩነት የወራትና ቀናት የቋንቋ ስያሜ እና የዓመቱ አቆጣጠር በስተቀር በዘመን መለወጫ ቀን፣ በወራትና ቀናት አቆጣጠር ተመሳሳይ ናቸው። ለምሳሌም፦ የዓመቱ የመጀመሪያ ቀን በኢትዮጵያ መስከረም አንድ ሲሆን በግብጽም ይህንኑ ዕለት ቶውት አንድ (Tout 1) በማለት የዓመቱ የመጀመሪያ ቀን ነው።

በአጠቃላይ በሁለቱም የዘመን አቆጣጠር በመጀመሪያዎቹ ሦስት ዓመታት 12 ባለ 30 እና 1 ባለ 5 ቀናት በድምሩ 365 ቀናት ሲኖሩ፤ አራተኛው ዓመት (በተውሳክ) 12 ባለ 30 ቀናትና 1ባለ 6 ቀናት በድምሩ 366 ቀናት ያሏቸው ስለሆነ ምንም እንኳን በአውሮጳ እና በመካከለኛው ምሥራቅ ከሚገኙ ክርስቲያኖች ጋር ቢለያይም በሁለቱ ሀገሮች የሚኖሩ ክርስቲያኖች ሃይማኖታዊ በዓላትን ላንድ ቀን ያከብራሉ።

የግብጽ፣ የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አብያተ ክርስቲያናት የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር አንድ ሲሆን፤ የቀኖችና ወሮች ስያሜና የዘመን ቁጥር በተመለከተ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ አንድ ሲሆን የሁሉም አቅጣጠር ከጌታ ልደት ጀምሮ አንድ ብሎ በመጀመር ዘመኑንም ዓመተ ምሕረት ይሉት የነበረውን ግብጻውያኑ በሮም ቅኝ ግዛት ሥር የነበሩ በመሆኑ በ284 (፪፻፸፮ ዓ.ም.) ጀምረው በጨካኙ የሮም ንጉሥ ስም ዓመተ ዲዮቅልጥያኖስ (Anno Diocletian) ብለው እንዲቀይሩ በመገደዳቸው ዘመኑን በስሙ ሲጠራ ነበር።

በእርሱም ዘመን አያሌ ክርስቲያኖች ሰማዕትነትን በመቀበላቸው ምክንያት ዘመኑ ለሰማእታት መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ከስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ስያሜውን ዓመተ ሰማዕታት (Era of the Martyrs ወይም በላቲን Anno Martyrum) በማለት አሻሽለው ሲሰይሙት አቆጣጠሩን ግን ከ284 (፪፻፸፮ ዓ.ም.) ጀምሮ እንደ ነበረው በመቀጠላቸው የኢየሱስ ክርስቶስን ልደት የሚያመለክት አይደለም።

እኛ በእግዚአብሔር እርዳታና በአባቶቻችን ጀግንነትና መስዋዕትነት ከቅኝ ግዛት ነጻ ሆነን ስለኖርን ምንም የባእድ ተጽእኖ ሳይጨመርብን ዘመኑን ዓመተ ምሕረት እያልን ቀጥለናል። በዚሁ መሠረት ለምሳሌ የዘንድሮውን የዘመን መለወጫ ወይም አዲስ ዓመት በአኃዝ በእኛ 01/01/2017 ዓመተ ምሕረት ሲሆን፤ ግብጾች ግን 01/01/1740 ዓመተ ሰማዕታት ይሉታል። ኤርትራ ከኢትዮጵያ ከተለየች በኋላ መንግሥት የግሪጎርያውያንን የዘመን አቆጣጠር ሲከተል የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንም ከኢትዮጵያ ሲኖዶስ ከተለየች በኋላ የኢትዮጵያን የዘመን አቆጣጠርን መጠቀሙን የቀጠለች ቢሆንም ስያሜውን ግን የግእዝ አቆጣጠር ብላ ሰይማዋለች።

የጁሊያን የባይዛንታይን (Byzantine calendar) እና የግሪጎሪያን አቆጣጠር ዓመት በቀናት ርዝማኔ ማለትም በመደበኞቹ ሦስት ዓመታት 365 ቀናት አራትኛው ዓመት (በተውሳክ) 366 ቀናት ያሉት በመሆኑ ከእኛና ከግብፅ ጋር እኩል ሲሆን፤ አንድ ዓመት 7 ባለ 31 ቀናት፣ 4 ባለ 30 ቀናትና 1 ባለ 28 ቀናት፣ በተውሳክ ባለ 29 ቀናት 12 ወራት አሉት። የባይዛንታይን ዘመን አቆጣጠር (Byzantine calendar) የጁሊያን ዘመን አቆጣጠርን መሠረት ያደረገ ሲሆን፤ ልዩነቱ የጁሊያን ኦገስት 31 የዓመቱ መጨረሻ ሲሆን በማግስቱ ሴፕቴምበር 1 የዓመቱ የመጀመሪያ ቀን ነው።

በሌላም በኩል የጁሊያን ከ525 ጀምሮ የጌታ ዓመት (AD) ሲሉ ባይዛንታይን ደግሞ ዓመተ ዓለም Anno Mundi (in the year of the world) በማለት ይጠሩታል ለምሳሌ በጁሊያን ኦገስት 31 ቀን 2023 AD በባይዛንታይን ኦገስት 31ቀን 7531 AM ሲሆን፤ በማግስቱ በጁሊያን ሴፕቴምበር 1 ቀን 2024 AD ሲባል በባይዛንታይን ደግሞ ሴፕቴምበር 1 ቀን 7532 AM (በኢትዮጵያ ፳፻፲፭ (2015) ዓ.ም ወይም ፸፭፻፲? (7513) ዓመተ ዓለም) በማለት ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ከስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ በመጠቀም ላይ ሲሆኑ፤ ከመንግሥታዊ አገልግሎት ከራሺያ (የቀድሞው ሶቪየት ህብረት) በ1917፣ ከግሪክ በ1926 ቦታውን ለግሪጎርያን አቆጣጠር ለቋል።

ከላይ ያየናቸው የዕብራውያን እና የመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት ከሚጠቀሙበት የዘመን ስሌት አንጻር በአንድ ዓመት ውስጥ ያሉት ቀኖች ቁጥር በሐሳበ ፀሐይ መሠረት የዘመን አቆጣጠር ዘዴ በሚከተሉ ሀገራት ከአለው የቀኖች ቁጥር ጋር ሲነጻጸር የዕብራውያን በመደበኛው ዓመት ከ10-12 ቀኖች የሚያጥር እና በተውሳክ ከ28-30 ቀኖች የሚረዝም በመሆኑ በግብጽ፣ በኢትዮጵያ፣ በጁሊያን፣ በባይዛንታይን (Byzantine calendar) እና በግሪጎሪያውያን ዘመን ከሚጠቀሙ ክርስቲያኖች ጋር በአንድ ቀን አጽዋማትን መጀመርና በዓላትን ለማክበር አስቸጋሪ ስለሆነ የተለየ የአቆጣጠር ዘዴ መፈለጉ ተገቢ ሆኖ ተገኝቷል።

በአውሮፓ፣ በመካከለኛው ምሥራቅና በሰሜንና በምሥራቅ አፍሪቃ የሚኖሩ ክርስቲያኖች ከአባቶቻቸው በተላለፈላቸው ትውፊት መሠረት የጌታችንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል እንደ አካባቢው ሁኔታ በግልና በማኅበር ሆነው የተወሰኑት በየዓመቱ በጁሊያን አቆጣጠር ዲሴምበር 24፣ በእኛ አቆጣጠር ታኅሣሥ ፳፰ ቀን ይኸውም በግብጽ አቆጣጠር ኪያህክ 28፣ ከፊሎቹ ደግሞ በጁሊያን አቆጣጠር ዲሴምበር 25 በእኛ አቆጣጠር ታኅሣሥ ፳፱ ቀን ይኸውም በግብጽ አቆጣጠር ኪያህክ 29፣ ቀን ሲያከብሩ ጥቂቶችም ደግሞ ሌሎቹ ካከበሩ ከአሥር ቀናት በኋላ ማለትም በእኛ ጥር ፲፩ ቀን፣ በግብጽ አቆጣጠር ቶባ 11 ቀን ይኸውም በጁሊያን ጃኑዋሪ 6 ቀን ከጥምቀት በዓል ጋር በመደረብ አንድ ላይ የሚያከብሩም ነበሩ።

ታላቁን የጌታ ጾምም እንዲሁ በቅዱስ ወንጌል በሦስቱ ወንጌላውያን እንደ ተጻፈው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠምቆ ከውሃው ውስጥ እንደወጣ በመንፈስ ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ በመሄድ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት መጾሙን መነሻ በማድረግ (ማቴ.፬፥፩-፪፤ ማር.፩፥፱-፲፫፤ ሉቃስ ፬፥፩-፪) የጥምቀት በዓልን ባከበሩበት ቀን በማግስቱ ማለትም ጥር ፲፪ ቀን በግብጽ አቆጣጠር ቶባ 12 ቀን ይኸውም በጁሊያን ጃኑዋሪ 7 ቀን ዐቢይ ጾምን በመጀመር ከጥንተ ስቅለቱ እና ከአይሁድ ፋሲካ በዕብራውያን አቆጣጠር ኒሳን ( נִיסָן -Nisan)14 ቀን፣ በጁሊያን አቆጣጠር March 23 ቀን፣ በግብፅ (ኮፕት) አቆጣጠር ባራምሃት (Baramhat) 27 ቀን፣ በእኛ አቆጣጠር መጋቢት ፳፯ ቀን ቀደም በማለት በዓለ ትንሣኤን መጋቢት መጀመሪያ አካባቢ ያከብሩ ነበር።

የሮማውያን ዘመን አቆጣጠር በተለያዩ ጊዜያት በተደጋጋሚ እየተስተካከለ መጥቶ ከጌታ ልደት 46 ዓመት በፊት (708 AUC) በጁሊየስ ቄሳር ከሐሳበ ጨረቃ ወደ ሐሳበ ፀሐይ ሲቀየር እንደገና ከጌታ ልደት 8 ዓመት በፊት (746 AUC) አንዲት ቀንን ከሁለተኛው ወራቸው ቀንሰው ስምንተኛው ወራቸው ላይ ጨምረው ዘመኑንም AUC (Anno Urbis Conditae) በማለት የሮም ከተማን ከመሠረቱበት ከጌታ ልደት በፊት 753 ጀምሮ ከጌታ ልደት በኋላ እስከ 284 (፪፻፸፮ ዓ.ም.) ድረስ በዚህ ስያሜ ሲጠሩበት ኖረዋል። ከ284 (፪፻፸፮ ዓ.ም.) ጀምረው ዘመኑን AUC ማለትን በመተው ዓመቱንም እንደ አዲስ ከታች ጀምረው አንድ ብለው በመቁጠርና ዘመኑንም ዓመተ ዲዮቅልጥያኖስ (Anno Diocletian) በማለት ተኩት።

በመቀጠልም በ525 በአሁኑ ጊዜ አውሮፓውያን የሚጠቀሙበትን AD (Anno Domini) የጌታ ዓመት የተሰኘውን አቆጣጠር ዲዮኒሲዩስ ኤክሲጉስ የተሰኘ የሮማን ቤተ ክርስቲያን መነኩሴ (Dionysius Exiguus) ሐሳብ አመጣ፤ በዚሁም ሐሳብ መሠረት ከ247 Anno Diocletian ቀጥሎ ያለውን ዘመን 532 (Anno Domini) የጌታ ዓመት በማለት በነበረው ዘመን ላይ ሰባት ዓመት በመጨመራቸው በእኛና በአውሮፓውያን ዘመን መሃከል በኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ላይ የሰባት ዓመት ልዩነት አመጣ።

በመቀጠልም ከ13/05/1572 እስከ 10/04/1585 ድረስ የሮማን ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሁለት መቶ ሃያ ስድስተኛው ሊቀ ጳጳስ የነበረው ጎርጎርዮስ አሥራ ሦስተኛ (Pope Gregory XIII) ጥቅምት ፯ ቀን ፲፭፻፸፭ዓ.ም (1582 AD) በነበረው አቈጣጠር ላይ የአሥራ አንድ ቀናት ልዩነቶች አሉ በሚል ሐሳብ ከሐሙስ ኦክቶበር አራት (4 October 1582) (በእኛ ጥቅምት ፯ ቀን ፲፭፻፸፭ ዓ.ም) ማግስት ያለው ቀን ዐርብ ኦክቶበር አስራ አምስት (15 October 1582) ተብሎ እንዲቆጠር (በእኛ ጥቅምት ፰ ቀን ፲፭፻፸፭ ዓ.ም ) በማድረጉ እንደ ዓመታቱም የቀናት ልዩነት ተጨመረ።

በዲዮኒሲዩስ ስሌት መሠረት የጌታ ዓመት AD -Anno Domini (in the year of the Lord) ተሰኝቶ የቀጠለው የአውሮፓውያኑ ዘመን ሰባት ዓመት በስህተት ጭማሪ እንዳለው የታሪክና የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃዎች ማረጋገጫ ሲሆኑ፤ እ.ግ.አ. ከ2005- 2013 የሮማን ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሁለት መቶ ስድሳ ስድስተኛ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክት አሥራ ስድስተኛ (Pop Benedict XVI) የናዝሬቱ ኢየሱስ (Jesus of Nazareth) በሚል ርዕስ እ.ግ.አ. 15/05/2007 ባሳትሙት ጥናታዊ የነገረ ክርስቶስ መጽሐፍ ውስጥ በጌታችን ልደት ላይ የሰባት ዓመት በመጨመር ስህተት መፈጸሙን በጥናታቸው አረጋግጠዋል። ይህ ማለት የያዝነው የአውሮፓውያን ዘመን 2023 ላይ ሰባት ዓመት ሲቀነስ ውጤቱ 2016 ስለሆነ የኢትዮጵያ የዘመን ስሌት ትክክል ሆኖ እናገኘዋለን።

ሐዋርያውና ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ ምዕራፍ ፪ ከቁጥር ፩ እስከ ፳፪ እንደጻፈው «ኢየሱስ በሄሮድስ ዘመን እንደተወለደ፣ .. . በቤተ ልሔምና በአውራጃዋ የነበሩትን፣ ሁለት ዓመት የሆናቸውንና ከዚያም የሚያነሱትን ሕፃናት ሁሉ ሄሮድስ እንደ አስገደለ። . . . ሄሮድስ እንደ ሞተና በምትኩ ልጁ አርኬላዎስ እንደ ነገሠ፤» የተጻፈውን ስንመረምረው ሄሮድስ የሞተውና አርኬላዎስ የነገሠው ኢየሱስ የሦስትና የአራት ዓመት ልጅ በነበረበት ወቅት እንደሆነ እንረዳለን፤ በሌላም በኩል የታሪክ ተመራማሪዎችም የሮማው መነኩሴ ዲዮኒሲዩስ (Dionysius Exiguus) ካሰላው ሰባት ዓመት በፊት (7BC) ኢየሱስ መወለዱንና ሄሮድስ የሞተውና አርኬላዎስ የነገሠው ከዚሁ ስሌት አራት ዓመት በፊት (4BC) መሆኑን አረጋግጠዋል። (World History- A chronological Dictionary of Dates; by Rodney Castleden London 1994 PARRAGON Book Service Ltd) ከዚህና ከመሳሰሉት የታሪክና የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃዎች አንጻር የአውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ሰባት ዓመት ከድርጊት የቀደመ መሆኑን ራሳቸው አውሮፓውያን አምነዋል።

በሁሉም የዓለማችን ማዕዘናት የተበተኑት ክርስቲያኖች በየሀገራቸው በሚጠቀሙበት የተለያዩ የዘመን አቆጣጠሮች ምክንያት በዓላትንና አጽዋማትን በተለያዩ ወራትና ቀናት ያከብሩ ስለነበር ይህን ልዩነት ለማስቀረትና ሁሉም ክርስቲያን በአንድ ቀን ጾሙን እንዲጀምርና እንዲጨርስ እንዲሁም የጌታን በዓላት አንድ ቀን ማክበር እንዲቻል በማሰብ ጌታችን የተወለደበትን፣ የተጠመቀበትን፣ በቀራንዮ ቤዛ የሆነበትን፣ ሞትን ድል አድርጎ የተነሳበትን፣ ያረገበትን፣ ዘመን፣ ወርና ቀን ለይቶ ለማወቅ እንዲረዳ በሉቃስ ወንጌል የተጠቀሰውንና ሌሎችን ትውፊቶችንና የታሪክ ድርሳናትን በመርመር እና ጌታ ባረገ በሃያ ሁለት ዓመት (በ፶፭ ዓ.ም ንና አካባቢ) አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት፣ ሰባ ሁለቱ አርድዕት፣ ቅዱስ ጳውሎስ እና የኢየሩሳሌሙ ኤጲስ ቆጶስ ቅዱስ ያዕቆብ በኢየሩሳሌም ተሰብስበው የወሰኑት ሕግ የቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያው የቀኖና መጽሐፍ በሆነው በዲድስቅሊያ ላይ የወሰኑትን መነሻ በማድረግና ዘመኑንም በማስላት ቀናቱን ለይቶ ለማወቅና ይህንን ለማከናወንም ይችል ዘንድ እግዚአብሔር እንዲረዳው ሱባኤ በመያዝ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተወለደበት ዓመት አንድ ብሎ የሚጀምር ዓመተ ምሕረት እና የአጽዋማትንና በዓላትን ቀን ማውጣት የሚያስችል ባሕረ ሐሳብ ከ፻፹፪ዓ.ም (189) እስከ ጥቅምት ፪፻፳፭ዓ.ም. (22/10/232) ድረስ በመንበረ ማርቆስ ፲፪ኛው የአሌክሳንድያ ሊቀ ጳጳስ የነበረው ቀዳማዊ ዲምጥሮስ መንበሩን በያዘ ፳፯ ዓመቱ በ፪፻፱ዓ.ም አዘጋጀ።

ይህን የቅዱስ ዲምጥሮስን ባሕረ ሐሳብ በተወሰነ አካባቢ የሚኖሩ ክርስቲያኖች ብቻ ሲጠቀሙበት ቆይቶ በ325 በአርዮስ የስህተት ትምህርት ምክንያት በኒቅያ የተሰበሰቡት ፫፻፲፰ቱ አባቶች ሙሉ በሙሉ ተቀብለውት ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት በዚህ ባህረ ሐሳብ መሠረት በዓላቶችንና አጽዋማትን በተመሳሳይ ዕለት እንዲያከብሩ በቀኖ በወሰኑት መሠረት በዚሁ ቀመር ዛሬ ሁሉም ክርስቲያኖች በዓላትን በአንድ ጊዜ ለማክበር የሚያስችል ስሌት ቢኖርም አሁንም ምእራባውያን በ525 የተከለሰውን የአባ ዲዮናሲዮስ የተሳሳተ ቀመርን በመከተል ከአንድነት ይልቅ ልዩነተን በመምረጣቸው አንድ ዓይነት ሥርዓት መከተል አልተቻለም።

በአጠቃላይ ከላይ በስፋት ለመግለጽ እንደተሞከረው፤ ሮማውያኑ ከጌታ ልደት በፊት በነበራቸው የዘመን አቆጣጠር (AUC) የጀመሩት አዲስ ዓመት በተሻሻሉት በጁሊያንና የግሪጎሪያን አቆጣጠርም ቀጥሎ በሁሉም አዲስ ዓመት የሚጀመረው ጃኑዋሪ (January) ጥር ላይ ሲሆን፤ በግብጻውያኑ ቶውት አንድ (Tout) እና በኢትዮጵያ መስከረም አንድ ላይ በአንድ ቀን የመጀመሪያ አዲስ ዓመታቸውን ሲጀምሩ፤ በጁሊያን ሴፕቴምበር አንድ ቀን የባይዛንታይን (Byzantine calendar – ኋላ የምሥራቅ ኦርቶዶክስ አቆጣጠር)፣ ሴፕቴምበር (September) አንድ ላይ አዲስ ዓመት የመጀመሪያ ቀን በመሆኑና በወር ውስጥ ያሉት ቀናት ማጠርና መርዘም የወራትና የቀናት ልዩነት፣ በ525 በዲዮኒሲዩስ (Dionysius Exiguus) በተጨመረው ሰባት ዓመት ልዩነት፣ በ1582 በሮማን ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ጎርጎርዮስ ፲፫ኛ (Pope Gregory XIII) በተደረገው የአሥር ቀን ጭማሪ ምክንያት በእኛና በምእራባውያን መካከል የቀናት፣ የወራትና የዓመታት ልዩነት ይታያል።
ሻሎም ! አሜን።

አዲስ ዘመን  መስከረም 6 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You