የሚያፀና ትውልድ

በዓለማችን በየጊዜው የሚከሰተው የአየር ንብረት ለውጥ ስጋት መሆን ከጀመረ በርካታ ጊዜያትን አስቆጥሯል። ለውጡ በዓለም ላይ እየደረሱ ላሉ ተግዳሮቶችና ለኦዞን መሳሳት መንስኤ ሆኖም ይታያል። ለእነዚህ ሁሉ ችግሮች በዋና ምክንያትነት የሚጠቀሱት ደግሞ ወደከባቢ አየር የሚለቀቁ የበካይ ጋዞች ልቀት መጨመርና የደን ሀብት እየተመናመነ መምጣት ነው ።

በአየር ንብረት ሚዛን መዛባት ምክንያት የበረዶ ግግር እየቀለጠ፣ አካባቢን ለውሃ መጥለቅለቅ አደጋ እያጋለጠ፣ በአውሎ ንፋስና በእሳት አደጋ የሰው ሕይወትና ንብረት እየጠፋ መሬት እየተደረመሰና ሕንፃዎች እየፈራረሱ፣ የፀሐይ ንዳዱም ሕይወት ያለውን ፍጡር እስትንፋስ እያሳጠረ ስለመሆኑ ዓለማችን ያስተናገደቻቸው ክስተቶች ይመሰክራሉ።

የዓለም መሪዎች ከዓመታት በፊት በኳታር በተካሄደው የዶሃ ጉባኤ ስምምነት ላይ ምንም እንኳን የካርቦንዳይ ኦክሳይድ ልቀት መጠንን ለመቆጣጠር ስምምነት ላይ ቢደርሱም፤ የምድር ሙቀት ከእለት ወደ እለት እየጨመረ መምጣቱን ቀጥሏል። በዚህ የተነሳ ምድራችን በቅርቡ መቋቋም የማትችለው ሙቀት እንደምታስተናግድ፤ የምድር የውሃ አካላትም ከፍታቸው እንደሚጨምር ጥናቶች ያሳያሉ::

የሰውን ልጅ በከፍተኛ ሁኔታ እያሳሰቡ ያሉት የአየር ንብረት ለውጥና ሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎች አጠቃላይ የምድርን ተፈጥሯዊ ሂደት እየጎዱት ነው:: ይህ ማለት ደግሞ ከምድራችን ጋር ያለንን ግንኙነት ካስተካከልን የወደፊቱን ዕጣ ፈንታችንን ማሳመር እንችላለን፤ ካልሆነ ደግሞ ለከፋ ችግር ይዳርገናል።

120 ሚሊዮን ገደማ ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ በድርቅ ከሚጎዱ ሃገራት አንዷ መሆኗን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ ያመለክታል። ኢትዮጵያ ቀደም ሲል በየ10 ዓመቱ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ በየዓመቱ ድርቅ እየተፈራረቀባት ለበርካታ ቀውስ ስትዳረግ ቆይታለች::

እየተፈራረቀ በሚያጠቃት ድርቅ እና ርሃብም በርካታ ዜጎች ከቀያቸው ለመሰደድ ከመገደዳቸውም ባሻገር ስፍር ቁጥር የሌላቸው የቤት እንስሳት ለሞት ተዳርገዋል:: አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩም አምርቶ ለሀገር መትረፍ ሲገባው በምትኩ ርዳታ ጠባቂ ለመሆን ተገዷል:: ይህም ክስተት ኢትዮጵያን የረሃብ ተምሳሌት አድርጓት ቆይቷል:: ከቅርብ ግዜያት ወዲህ ግን ነገሮች ተለውጠዋል::

በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አፍላቂነት ‘አረንጓዴ ዐሻራ’ በሚል ሀገር አቀፍ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በተከታታይ መካሄድ ከጀመረ በኋላ ኢትዮጵያ አዲስ ተስፋ ሰንቃለች:: የተራቆቱ መሬቶቿና የተመናመኑ ደኖቿ ዛሬ ማገገም ጀምረዋል:: ኢትዮጵያ በየዓመቱ አረንጓዴ መልበስ ጀምራለች::

ሀገሪቱ ካሏት እምቅ የተፈጥሮ ሀብቶችና የመልሚያ ዕድሎች አንዱ የደን ሀብት ሲሆን የደን ሀብቶችን መጠበቅ፣ ማልማት እና በዕቅድ ጥቅም ላይ ማዋል ኢኮኖሚያዊ፣ ሥርዓተ-ምኅዳራዊና ማኅበራዊ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን በዘርፉ የተሠሩ ጥናቶች ያመላክታሉ::

የማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ እንደሚያመለክተው በኢትዮጵያ 83 በመቶ ሕዝብ ነዋሪነቱ በገጠር ነው። ይህ ማለት በርካታው የሀገራችን ሕዝብ አኗኗር በአንድም ሆነ በሌላ ከግብርና ጋር የተሳሰረ እንደሆነ መገመት አያዳግትም። በመሆኑም በዚህ መሠረተ ሰፊ በሆነው ዘርፍ ላይ የሚደረግ ርብርብ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ ለውጥ ለማምጣት የማገዝ ዕድሉ ከፍተኛ ነው::

በመሆኑም ሀገሪቱ የአየር ንብረት ለውጥ በግብርና ምርታማነት ላይ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተፅዕኖ ቀድማ በመገንዘብ የአረንጓዴ ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂን እየተከተለች ትገኛለች። የአካባቢ ጥበቃ መሠረት ያላደረገ ፕሮግራም በየትኛውም መስፈርት ውጤታማ ሊሆን አይችልምና ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ላይ ወገቧን ጠበቅ ማድረግ ጀምራለች::

የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ንጹሕና ጤናማ አካባቢ እንዲኖረው ጥረት ማድረግ እና ማንኛውም ኢኮኖሚያዊ ልማት አካባቢ ደኅንነትን የሚያናጋ መሆን እንደሌለበት እንዲሁም ማንኛውም ሰው ጤናማና ንጹሕ አካባቢ የመኖር መብት እንዳለው ይደነግጋል።

በዚህ መሠረት ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገቷን በማረጋገጥ ድህነትን ለመቀነስና ዘላቂ ብልፅግናዋን ለማረጋገጥ የምታደርገው ጥረት በአብዛኛው የተፈጥሮ ሀብቶቿን በተገቢው መንገድ ከመያዝ፣ ከማስተዳደር እና ጥቅም ላይ ከማዋል ጋር የተያያዘ ነው:: ከነዚህም ተፈጥሯዊ እምቅ ሀብቶች ውስጥ የግብርና፤ ታዳሽ የኃይል አማራጮች ግንባታና አቅርቦትን ማሳደግ፤ ተደራሽ የማኅበራዊ አገልግሎት አቅርቦትና የሠው ሀብት ልማትን ታሳቢ ያደረገ ዘላቂ ልማትን መሠረት ያደረገ ነው::

ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ የጋዝ ልቀትን የመቀነስ፣ ከፀሐይ ኃይል ኤሌክትሪክ የሚያመነጭ ቴክኖሎጂዎችን በአማራጭነት የመጠቀም፣ የተፈጥሮ ሀብቷን በተገቢው የመገልገል፣ የተፋሰስ ልማትን የማስፋፋትና፣ የደን ልማትን በስፋት የማካሄድ ስትራቴጂዎችን በዋናነት በመቀበሏና ለተግባራዊነቱም ቁርጠኛ አቋም ያላት መሆኑን በአረንጓዴ ልማት ዙሪያ በነደፈችውና በመተግበር ላይ ባለችው ስትራቴጂ አሳይታለች።

የኢትዮጵያ የደን ሃብት ከግብርና፣ ከማገዶ፣ ከከሰል ማክሰል፣ ከልቅ ግጦሽ፣ ከግንባታና ከእንጨት ሥራ ጋር በተያያዘ በማይታመን ፍጥነት መጠኑ ሲቀነስ እያስተዋልን ዛሬ ላይ ደርሰናል::

ኢትዮጵያ በደን ሃብቷ ከአፍሪካ ሀገራት ግንባር ቀደም የነበረችባቸው ዘመናት የማይረሱ ቢሆንም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የሕዝብ ብዛት፣ የእርሻና የግጦሽ መሬት እጥረት እንዲፈጠር በማድረጉ ሰዎች የደን ሃብቱን ያለመሰሰት በመጨፍጨፍ መሰረታዊ ፍላጎታቸውን እንዲያሟሉ አስገድዷቸዋል::

ሀገሪቷን በተለያዩ ዘመናት ያስተዳደሯት መንግሥታት የደን ሃብቱን ለመንከባከብ የተለያዩ ጥረቶችን ቢያደርጉም ሙከራቸው ያዝ ለቀቅ ስለነበር የታሰበውን ውጤት ማሳካት አልቻለም:: የደን ሀብት ከሰብዓዊ ሕይወት ጋር ያለውን ቁርኝት ሁሉም ባይዘነጉትም የሰጡት ትኩረት አነስተኛ በመሆኑ ሀገሪቱ አሁን ላይ እየገጠማት ላለው የተፈጥሮ አደጋና ድርቅ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ተጠያቂ ናቸው::

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመራር ወደ ሥልጣን ከመጣበት እለት አንስቶ ችግሩን ለመቅረፍ በቁርጠኝነት እየተገበረው ያለው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር ከፍተኛ ለውጥ እያስገኘ ይገኛል:: መርሐ ግብሩ ቀደም ብለው ከተጀመሩ ጥረቶች በተለየ በጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል በመተግበሩ አሁን ላይ ዓለም አቀፍ ምስጋና የተቸረው ውጤት ማሳየት ችሏል:: መርሐ ግብሩ ሀገሪቱን በድጋሚ አረንጓዴ ገጽታ በማላበስ፣ የገጠሩን ማኅበረሰብ ሕይወት በማሻሻል የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም መልክዓ ምድር በመገንባት በኩል የተሳካ የሚባል ውጤት አስገኝቷል::

ነሐሴ 17 ቀን 2016 ዓ.ም በነበረው በአንድ ጀንበር 615.7 ሚሊዮን ችግኝ ሚሊዮን ችግኝ የመትከል መርሐ ግብር ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዐሻራውን በማሳረፍ ሀገር የማጽናት ተልዕኮውን ተወጥቷል:: ይህም ጥረት ከዓድዋ ድል እና ከህዳሴ ግድብ ቀጥሎ ኢትዮጵያውያን በጋራ በመሆን ለሀገራቸው ታሪክ የጻፉበት ትልቅ ገድል ነው ማለት ይቻላል::

ክብረአብ

አዲስ ዘመን መስከረም 6 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You