የዜጎችን የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ የተጀመረው ሥራ ውጤት እያስገኘ ነው

አዲስ አበባ፦ በግብርናው ዘርፍ የዜጎችን የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተጀመረው ሥራ ውጤት እያስገኘ መሆኑን ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ኢፋ ሙለታ (ዶ/ር) ለኢፕድ እንደገለጹት፤ በግብርናው ዘርፍ የዜጎችን የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በአረንጓዴ ዐሻራ፣ በስንዴ ልማት እና በሌማት ትሩፋት እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች ውጤት እያስገኙ ናቸው።

ኢትዮጵያ ግብርናን በማዘመን የዜጎችን የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ የጀመረችው የስንዴ ልማት ፍሬ አፍርቶ ከውጭ የሚገባውን ከማስቀረት ባለፈ የውጭ ምንዛሪ አስገኝቷል ያሉት ኢፋ ሙለታ (ዶ/ር)፤ ከለውጡ ማግስት በሦስት ሺህ ሔክታር መሬት ላይ የተጀመረው የበጋ ስንዴ መስኖ ልማት በየዓመቱ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።

በስንዴ ልማት የተጀመረውን ሥራ ጨምሮ የሩዝ፣ የቅባት እህሎች፣ አትክልትና ፍራፍሬ እና የቡና ምርት መጠንን የሚጨምሩ ሥራዎች እየተሠራ መሆኑን የገለጹት ኢፋ ሙለታ (ዶ/ር)፤ በስንዴ፣ በበቆሎ እና በጤፍ ምርት ተጨባጭ ለውጥ መታየቱን ተናግረዋል።

በእንስሳት ዘርፉ ያለውን እምቅ አቅም ወደ ምርታማነት ለመቀየር ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ያሉት ኢፋ ሙለታ (ዶ/ር)፤ በተለይም በወተት ምርት፣ በዶሮና እንቁላል፣ በሥጋ፣ በዓሣና በማር ምርት ላይ እየተደረገ ያለው ምርታማነትን የማሳደግ ሥራ ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል ብለዋል።

የዘርፉን ምርታማነት ለማሳደግ አሠራርን ማዘመንና ልዩ ትኩረት መስጠት ላይ ሰፊ ርብርብ እየተደረገ ነው። ለዚህ ማሳያ ደግሞ የዘርፉን ምርታማነት በማሳደግ ድርሻውን እየተወጣ የሚገኘው የሌማት ትሩፋት ፕሮግራም አንዱ እንደሆነ ገልጸዋል።

የሌማት ትሩፋት የእንስሳትና ዓሣ ሃብት ልማት ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ላይ መሠረታዊ ለውጥ ማምጣትን ዓላማ አድርጎ የተጀመረ ሲሆን በአጭር ጊዜ ተጨባጭ ለውጥን እያመጣ ይገኛል። ለዚህ ደግሞ የፕሮግራሙን ዓላማ፣ ግብና ዝርዝር የማስፈጸሚያ ስልቶችን በማዘጋጀት ከፍ ባለ ሀገራዊ ንቅናቄ እንዲሠራ አስችሎታል ነው ያሉት።

ከፕሮግራሙ መጀመር ማግስት ክልሎች ያላቸውን ተፈጥሯዊ ፀጋና እምቅ የእንስሳት ሃብት አቅም በመጠቀም በወተት፣ በማር፣ በሥጋና በእንቁላል ላይ በልዩ ትኩረት እየሠሩ ሲሆን በእንስሳት ዘርፉ ምርታማነት ላይ ተጨባጭ ለውጦችን እያስመዘገቡ ይገኛሉ ብለዋል።

ፕሮግራሙ የታለመለትን ግብ እንዲያሳካ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ቴክኒካዊ፣ ቁሳዊና የአመራር ድጋፎችን በተከታታይ እየሰጠ እንደሚገኘ ገልጸው፤ ፈጣን ለውጥ እንዲመጣ ደግሞ በተዋረድ የሚገኘው የዘርፉ ተዋንያንና ባለድርሻ አካላት ለፕሮግራሙ ስኬት ያላሰለሰ ጥረት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል ባለፈ የምግብ ዋስትና መሠረት መሆኑን አንስተው፤ ለሥራ ዕድል ፈጠራና ሌሎችም ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች አስተዋፅዖ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም በአትክልትና ፍራፍሬ ተክሎች ወይም የጥምር ደን ልማት ሥራዎች ዜጎች የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ ከማስቻል ባለፈ ምርታቸውን ወደ ገበያ በማውጣት ተጨማሪ ገቢ እንዲያመነጭ ያስችላል ነው ያሉት።

በሌላ በኩል በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የለማው የመኖ ልማት አርሶ እና አርብቶ አደሩ ማኅበረሰብ ለእንስሳቱ በቂ መኖ እንዲያገኝ በማስቻል የእንስሳት ተዋፅዖ ምርታማነት ማሳደጉን ተናግረዋል። የእንስሳት ተዋፅዖ ምርታማነት መጨመር ደግሞ በተመጣጠነ ምግብ ዕጦት ሳቢያ በሕጻናት ዕድገት ላይ ሲስተዋል የነበረውን ችግር እያቃለለ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ሳሙኤል ወንደሰን

 አዲስ ዘመን መስከረም 5/2017 ዓ.ም

Recommended For You