ዜና ትንታኔ
የገጠሩንና የከተሜውን ማኅበረሰብ ከእሩቁም ሆነ ከቅርብ የሚያሰባስበውና የሚያስተሳስረው ማኅበራዊ ሕይወት ብቻ ሳይሆን የግብይት ሥርዓትም ነው፡፡ ግብይት ከዕቃ ልውውጥ ባለፈ ለማኅበራዊ ትስስርና ለኢኮኖሚያዊ እድገት ትልቅ ሚና አለው፡፡ የግብይት ሥርዓትን የተሳለጠ መሆን የምርት አቅርቦት እጥረት ያቃልላል፤ የዋጋ ንረትን ችግርን ያስወግዳል፡፡ የግብይት ትስስርን ለማጠናከር፤ አምራችና ሽማችን በቀጥታ ለማገናኘት የመንገድ መሠረተ ልማት ግንባታ፤ ጥገናና የመሻገሪያ ድልድይ ዝርጋታ ለነገ የማይባል የቤት ሥራ ነው፡፡
በ2012 ዓ.ም 56 በመቶ የሚሆነው ማኅበረሰብ ክረምት ከበጋ የሚያስኬድ መንገድ ለማግኘት አምስት ኪሎ ሜትር ይጓዝ ነበር፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት በተከናወኑ የመንገድ መሠረተ ልማት ሥራዎች አሁን ላይ ክረምት ከበጋ የሚያስኬድ መንገድ ለማግኘት አምስት ኪሎ ሜትር የሚጓዘው ሕዝብ ብዛት 32 ነጥብ 7 በመቶ መሆኑን በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር መረጃ ያመለክታል፡፡
አሁንም ቢሆን ኢትዮጵያ ከሕዝብ ብዛቷ ጋር በተሰናሰለ መልኩ ተደራሽነት እና ፍላጎትን ታሳቢ ያደረገ የመንገድ መሠረተ ልማት ግንባታ፣ ጥገና እና እንክብካቤ ሥራ ማካሄድ ጊዜ የሚሰጥ አይደለም፡፡ በአሁኑ ጊዜም ከአሁን በፊት ተገንብተው ጉዳት የደረሰባቸውን በመጠገን፤ መሻገሪያ ድልድይ የሌለባቸውን አካባቢዎች መሸጋገሪያ በመሥራት የገበያ ትስስርን ለማጠናከር የተለያዩ ፕሮግራሞች ተነድፈው በዓለም ባንክ ድጋፍና በሀገር ውስጥ መደበኛ በጀት እየተሠሩ ነው፡፡
በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የክልል መንገድና አቅም ግንባታ ቡድን መሪ ኢንጂነር ነብዩ ካሣሁን ለኢፕድ እንደገለጹት፤ የገጠሩን ማኅበረሰብን የመሠረተ ልማት ቁልፍ ጥያቄን የሚመልስ፤ ምርቱን ወደ ፈለገበት የገበያ ማዕከል እንዲያቀርብ፤ በቀጥታ የገበያ ትስስር ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያደርግ የወረዳ መንገድ ግንባታ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡
የገጠሩን ማኅበረሰብ በመንገድ ግንባታ መሠረተ ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ በመንግሥት በጀት ከሚገነቡ መንገዶች በተጨማሪ በተወሰነ የዓመታት ገደብ ውስጥ የሚጠናቀቁ ፕሮግራሞችን በመቅረፅ የማልማት ሥራ እየተሠራ ነው ይላሉ፡፡
አርሶ አደሩን በመንገድ ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ በቀጣይ አስር ዓመታት 52 ሺህ ኪሎ ሜትር የገጠር መንገድ ለመገንባት እቅድ ተይዞ እየተሠራ ነው ሲሉ ይገልጻሉ፡፡
የገጠሩን ማኅበረሰብ በጋ ከክረምት አገልግሎት ከሚሰጡ ዋና መንገዶች ጋር የሚያገናኙ፤ መንደሮችን ከመንደር፤ መንደሮችን ከገበያ ማዕከል የሚገናኙ መንገዶችን እንዲሁም መሸጋገሪያ ድልድዮችን ለመገንባት ከተቀረፁ ፕሮግራሞች መካከል ‹‹ የገጠር ትስስርና ተደራሽነት ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ›› አንዱ ነው ሲሉ ይናገራሉ፡፡
‹‹የገጠር ትስስርና ተደራሽነት ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ›› የገጠር መንገድ ግንባታ ፕሮግራም የገጠር ቀበሌ ማዕከላትን አቅራቢያቸው ከሚገኙ ዋና መንገዶች የሚያገናኝና በቆላማ አካባቢዎች ያሉ የመሻገሪያ ችግሮችን የሚፈታ ነው ሲሉ ያብራራሉ፡፡
ፕሮግራሙ በሀገሪቱ በ120 ወረዳዎች ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን ሰባት ሺህ 554 ኪሎ ሜትር የገጠር መንገድ ግንባታ፤ ከ10 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ ጥገና፤ 373 ተንጠልጣይ የእግረኛና 717 ቆላማ አካባቢ መሻገሪያ ድልድዮችን የያዘ ነው፡፡ ከ10 ሺህ ኪ.ሜ በላይ የጥራትና የአገልግሎት ችግር ያለባቸውን የመንገዶች በመጠገን የትራንስፖርት አገልግሎት የተቀላጠፈ የሚያደርግም ጭምር ነው ይላሉ፡፡
ፕሮግራሙ 11 ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ዜጎችን በኢኮኖሚ እድገት፤ በገበያ ትስስር፤ በመሠረተ ልማት ተደራሽነት፤ በምግብ ዋስትና መረጋገጥ ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው፡፡ ለ200 ሺህ ሰዎች ቀጥተኛ የሥራ ዕድል የሚፈጥርም ሲሆን ለ300 ሺህ ሥራአጥ ወጣቶች ተዘዋዋሪ ሥራ የሚፈጥር መሆኑን ነው ያብራሩት፡፡
ፕሮግራሙን ለማጠናቀቅ ከዓለም ባንኩ ድጋፍ 400 ሚሊዮን ዶላርና ከክልሎች 7 ሚሊዮን ዶላር በአጠቃላይ አራት መቶ ሰባት ሚሊዮን ዶላር መበጀቱን ተናግረዋል፡፡
የገጠር መንገዶችን በመገንባት በግብርና መልማት የሚገባቸው መንደሮችን ለማልማት፤ የግብርና ግብዓትን በፍጥነት ተደራሽ ለማድረግ፤ የተመረተውንም ምርት ለገበያ እንዲቀርብ የሚያደርጉ መንገዶች በመደበኛ በጀት እየተሠሩ ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡
በአማራ ክልል የመንገድ ቢሮ ኃላፊ ጋሻው አወቀ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ መንግስት የማኅበረሰብ ገበያ ትስስር ለማስፋት፤ የተሟላ የንግድ ሥርዓት እንዲዘረጋ በመደበኛ በጀትም ሆነ በተለያዩ ፕሮግራሞች የገጠር መንገድ ልማትን የመገንባት ሥራ እየሠራ ነው ይላሉ፡፡
የገጠር ማኅበረሰብ ጥያቄን ለመመለስና መሠረተ ልማትን ለማሳለጥ ለተወሰነ ዓመታት ተቀርፀው ከሚሠሩ ፕሮግራሞች ውስጥና ሰፊ ድርሻ የያዘው ‹‹የገጠር ትስስርና ተደራሽነት ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ ፕሮግራም›› አንዱ ነው ይላሉ፡፡
‹‹የገጠር ትስስርና ተደራሽነት ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ›› የመንገድ ግንባታ ፕሮግራም የአርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነትን የሚጨምር፤ የተሟላ የንግድ ሥርዓትን የሚያስፋፋ፤ የግብርና ግብዓት በወቅቱ ለአርሶ አደሩ ተደራሽና የተመረተውን ምርት ለገበያ ለማቅረብ የሚረዳ፤ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እድገቶችን የሚደግፍ ነው ሲሉ ይናገራሉ፡፡
መንግሥት የገጠሩን ማኅበረሰብ በመንገድ መሠረተ ልማት ተጠቃሚ በማድረግ የሀገርን ኢኮኖሚ ይበልጥ ለማሳደግ እንደ ሀገር ጠንካራ ሥራ እየሠራ ነው ሲሉ ይጠቁማሉ፡፡
መንገድ የመሠረተ ልማቶች ሁሉ ቁንጮ ነው፤ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ መስተጋብሮችን ለማጠናከር ትልቅ አቅም አለው ሲሉ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ መስፍን ስለሽ ያስረዳሉ፡፡
መንገድ ለሁሉም መሠረት ነው፤ ለኢኮኖሚው እድገት፤ ለማኅበራዊው መስተጋብር ብቻ በአጠቃላይ ለእድገት ቁልፍ ሚና አለው፤ ይህን ለሁሉም መሠረት የሆነውን መንገድ በማልማት ትራንስፖርቱን የማሳደግ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ነው ያብራሩት፡፡
የመንገድ ልማትን ለማሳደግና ለማስፋፋት እየተቀረፁ ተግባራዊ የሚደረጉ ፕሮግራሞች ጥሩ ውጤት እያስገኙ ነው ‹‹የገጠር ትስስርና ተደራሽነት ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ›› የተሰኘውም አርሶ አደሩ ያመረተውን ምርት ወደ ማዕከላት ገበያ በቀላሉ ተደራሽ ለማድረግ የሚረዳ፤ ለማኅበራዊ እንቅስቃሴ እንቅፋት የሆኑ ችግሮችን የሚፈታና ለኢኮኖሚ እድገት ትልቅ ፋይዳ ያለው ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡
በገጠር ያለው የመንገድ መሠረተ ልማት ተደራሽነት ዝቅተኛ ነው፤ ዝቅተኛ በመሆኑም የማኅበረሰቡ የልማት ጥያቄ ሆኗል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የ10 ዓመቱ እቅድ ሲዘጋጅ የኢትዮጵያ የመንገድ ሽፋን 144 ሺህ ኪሎ ሜትር ያህል የነበረ ሲሆን፣ ይህን አኀዝ በአስር ዓመቱ ወደ 245 ሺህ ኪሎ ሜትር ለማድረስ እንደ ሀገር ግብ መቀመጡን ይታወቃል። ይህ የመንገድ ፕሮግራምም ሽፋኑን ለማሳደግ ከፍተኛ ድርሻ ይኖረዋል፡፡
ታደሠ ብናልፈው
አዲስ ዘመን መስከረም 5/2017 ዓ.ም