-ከሁለት ነጥብ አራት ሚሊዮን በላይ በጎ ፍቃደኞች ተሳትፈዋል
አዲስ አበባ፡- በመዲናዋ በክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከ950 ሺህ በላይ ዜጎች ተጠቃሚ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ኅብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፍቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን አስታወቀ። ከሁለት ነጥብ አራት ሚሊዮን በላይ በጎ ፍቃደኞች መሳተፋቸውም ተጠቁሟል።
በኮሚሽኑ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ግንዛቤ ማስረጽ ቡድን መሪ አቶ ቢኒያም ጊቻ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ኮሚሽኑ በ2016 ግንቦት ወር ተጀምሮ መስከረም 2017 ዓ.ም ላይ በሚጠናቀቀው የክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በተለያዩ ፕሮግራሞች ከ950 ሺህ በላይ ዜጎች ተጠቃሚ ሆነዋል።
እንደ አቶ ቢኒያም ጊቻ ገለጻ ፤ የአዲስ ዓመት የበጎ ፍቃድ አገልግሎትን ሳይጨምር ከግንቦት እስከ ጳጉሜን አራት ባሉ ጊዜያት 2 ነጥብ አራት ሚሊዮን በጎ ፍቃደኞችን በማሳተፍ ከ950 ሺህ በላይ ዜጎች ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።
በበጎ ፈቃድ መርሐ ግብሩም የአቅመ ደካማና አረጋውያን ቤት እድሳት መደረጉን ገልጸው፡፡ በዚህም 2 ሺህ 300 በላይ ቤቶችን በመገንባት ለተጠቃሚዎች ማስተላለፍ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
በልዩ ፍላጎት የድጋፍ መርሐግብር የተለያዩ አካል ጉዳት ላለባቸው 590 ዜጎች ፍላጎታቸውን ያማከለ ድጋፍ እንደተደረገላቸው አቶ ቢኒያም ጠቁመዋል፡፡
ኮሚሽኑ በአረንጓዴ ልማትና አካባቢ ጥበቃ መርሐ ግብርም በድግግሞሽ ሦስት ሚሊዮን የሚሆኑ በጎ ፍቃደኞችን በችግኝ ተከላና ጉድጓድ ዝግጅት ሥራዎች እንዲሳተፉ ማድረግ ችሏል ብለዋል፡፡
በበጎ ፈቃደኞች ከተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት መካከል ማዕድ በማጋራት ሲሆን በዚህም ከ500 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ማዕድ ማጋራት መቻሉን አስረድተዋል፡፡
ሌላኛው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የጤና እንክብካቤ መርሐግብር ሲሆን ባለፉት ሦስት ዓመታት ትልቅ ውጤት የታየበት መሆኑን አውስተው፤ በዘንድሮ ክረምት 95 ሺህ
334 ለሚደርሱ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውና አቅመ ደካማ ዜጎች በመንግሥትና በግል የጤና ተቋማት ነፃ መሠረታዊ የሕክምና ቅድመ ምርመራና ድጋፍ እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል፡፡
በክረምቱ ወራቶች የተለያዩ የበጎ ፍቃድ ተግባራት የተከናወኑ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ የክረምት የማጠናከሪያ ትምህርት፣ ደም ልገሳና የትራፊክ አደጋን መከላከል ከተሰጡ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ውስጥ ተጠቃሽ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የመዲናዋ ነዋሪዎች፣ ወጣቶች፣ ባለሀብቶች፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ የሚያደርጉት ተሳትፎ እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ውስጥ አካታችነትን ለማረጋገጥ ሚናው የላቀ መሆኑን አቶ ቢኒያም ገልጸዋል።
አማን ረሺድ
አዲስ ዘመን መስከረም 5/2017 ዓ.ም