አዲስ አበባ፦ በአዲሱ ዓመት የቦንጋ ከተማን ለዜጎች ምቹ የመኖሪያና የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የከተማው ከንቲባ አስማማው አደመ ገለጹ።
ከንቲባ አስማማው ለኢፕድ እንደገለጹት፤ በአዲሱ ዓመት የቦንጋ ከተማን ለዜጎች ምቹ የመኖሪያና የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ የመሠረተ ልማት ማስፋፋት ስራ በመስራት የህዝብን ጥያቄ መመለስ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው።
እንደ ከንቲባው ገለጻ፤ ከተማው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የአስተዳደርና ፖለቲካ መቀመጫ እንደመሆኑ መጠን ይህንን የሚመጥን መሰረተ ልማት ለማሟላት የመሀል ከተማውን 44 ሄክታር መሬት በመለየት መልሶ የማልማት ተግባር እየተከናወነ ነው።
የህብረተሰቡን ተሳትፎ በማጠናከርና የፋይናንስ ምንጭ እንዲሆን በማድረግ ከ136 ሚሊዮን በላይ ብር ማሰባሰብ መቻሉን የገለጹት አቶ አስማማው፤ በዚህም የልማቱ ተነሽ ዜጎችን እንዲቋቋሙ ድጋፍ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
በተጨማሪም የከተማውን የመንገድ ደረጃን ለማሳደግና ከተማው ልዩ ውበት እንዲኖረው ለማስቻል ከ23 ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍን የኮሪደር ልማት እየተከናወነ ነው። ይህም በቅርቡ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ከንቲባው አመላክተዋል።
በአዲሱ ዓመት በተለይም በመልሶ ማልማት ስራው ህብረተሰቡን በማስተባበርና በጀት በመመደብ የመንገዶችን ደረጃ ማሳደግና ባለፈው ዓመት ተጀምሮ ያልተጠናቀቁ የመንገድ ጥገና ስራዎችን እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
በከተማው የሚገኘውን ብሄራዊ የቡና ሙዚየም የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ በኃላፊነት በመቀበል ሙዚየሙንና ዙሪያውን እያለማ መሆኑን የጠቆሙት ከንቲባው፤ በዚህም የመኪና ማቆሚያን ጨምሮ የተለያዩ ልማቶችን ያካተተ ዲዛይን ተዘጋጅቶ ተግባራዊ በመሆን ላይ ይገኛል ነው ያሉት።
እንዲሁም ለወጣቶች ቋሚ የስራ ዕድል ለመፍጠር እየተከናወነ ባለው ስራ ለዶሮ ማርቢያ የሚያገለግሉ 10 ሼዶች ተዘጋጅተዋል። በዚህም ወጣቶቹ ከጥቂት ቀናት በኋላ ወደ ስራ የሚገቡ ሲሆን፤ ይህ ተግባር የስራ ዕድል ፈጠራን ከማጠናከር በተጨማሪ ገበያን እንደሚያረጋጋ አቶ አስማማው ገልጸዋል።
በከተማው የእግዜር ድልድይ፣ አንድራቻ መድኃኒዓለም፣ ቶንጎላ መስኪድ፣ የባርታ ፏፏቴ፣ የቦንጌ ሻንቤቶ ወይም የጥንት የከፋ ነገስታት መናገሻና ሌሎችም ለቱሪስት መዳረሻ የሆኑ ስፍራዎች እንደሚገኙ ያስታወሱት ከንቲባው፤ ለዚህም የሚሆን የሆቴልና ቱሪዝም ኢንቨስትመንት አስፈላጊ በመሆኑ ለአልሚዎች መሬት የማስተላለፍ ተግባር ተከናውኗል ብለዋል።
አቶ አስማማው፤ እስካሁን በተሰራው ስራ ለአብነትም የሌዊ ሪዞርት ከ60 በላይ ለቪአይፒ የሚሆኑ ማረፊያዎችን ያዘጋጀ ሲሆን፤ ይህም ለካፍቾ ብሄር ዘመን መለወጫ ማሽቃሬ ባሮ ስራ የሚጀምር ይሆናል። እንዲሁም በቅርቡ በቦንጋ ዩኒቨርሲቲ አማካኝነት የተሰሩ 20ሎጆች አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ። በዚህም ከተማውን የማልማት ስራው በጥሩ ሁኔታ ላይ መሆኑን አውስተዋል።
በከተማው በጤና፣ ትምህርት፣ ኢንቨስትመንት፣ ስራ ዕድል ፈጠራ በሌሎችም ዘርፎች እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ተግባራት ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆናቸውን ያመላከቱት ከንቲባው፤ አካባቢው ለኢንቨስትመንት ምቹ በመሆኑ ወደ ከተማው ለሚመጡ አልሚዎች ቢሮክራሲዎችን በማሳጠር በፍጥነት ወደ ልማት እንዲገቡ ምቹ ሁኔታዎች መፍጠራቸውን ተናግረዋል።
ቃልኪዳን አሳዬ
አዲስ ዘመን መስከረም 4 ቀን 2017 ዓ.ም