ወጣቶችና አዲስ ዓመት

አሮጌው ዘመን በአዲሱ የመቀየሩን ብሥራት አብሣሪው የአዲስ ዓመት (ዕንቁጣጣሽ) በዓል፤ በእኛ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ልዩ ሥፍራ ከሚሰጣቸው በዓላት ውስጥ አንዱና ዋነኛው ነው። የጨለማ ተምሳሌት የሆነው ጭጋጋማው የክረምት ወቅት አልፎ፣ ቀን ከሌሊት ይዘንብ የነበረው ዝናብና አስገምጋሚው መብረቅ ጋብ የሚልበት፣ ምድር በዐደይ አበባ ተጥለቅልቃ በልምላሜ የምትታይበት፣ አሮጌው ዘመን ወደ ኋላ ተትቶ አዲሱ ሊተካ “እዮሃ አበባዬ” የሚባልበት በዓል በመሆኑ በብዙዎቻችን ዘንድ የተለየ ትርጓሜ ይሰጠዋል።

አዲስ ዓመት ሲመጣ በዓሉን በአዲስ መንፈስ እና ስሜት ለመቀበል የሚደረገው የቤት ጽዳትና ዕድሳቱ፣ ልብስ አጠባውና አሮጌውን በአዲስ ለመቀየር የሚከናወነው ግብይት፣ የሳር፣ የአደይ አበባ ጉዝጓዞ፣ የጠላው፣ የጠጁ፣ የዶሮው፣ የዳቦው ዝግጅት እና አጠቃላይ ሽር ጉዱ፤ ዕለቱን በይበልጥ እንድንናፍቀውና ከአሁን አሁን ዐውደ ዓመቱ በደረሰ እያልን በጉጉት እንድንጠባበቀው የሚያደርግ ስሜት ይፈጥርብናል።

ታዲያ አሮጌ ያልነው ዘመን አብቅቶ በአዲስ መተካቱን ከሚያበስሩን ከእነዚህ ማኅበራዊና ትውፊታዊ የዓውድ ዓመት ሥነ ሥርዓቶች በተጨማሪ፣ ተፈጥሮም እራሷን በውበት አሰማምራ የአዲስ ዓመትን መጥባት የምታመለክትባቸው ልዩ ልዩ መገለጫዎች አሏት።

አዲስ ዓመት ሲመጣ ሜዳው፣ ሸንተረሩ፣ ጋራና ሸለቆው በውብ የአበቦች ፍካት ይታጀባል፤ የአዋፋት ዝማሬ በየቦታው ይሰማል፤ ዐደይ አበባም ለረጅም ወራቶች ሳትታይ ቆይታ ወቅቱን ተከትላ በየስፍራው ብቅ ማለቷን ትጀምራለች፡፡ የክረምቱን ማብቃትና የአዲሱን ዘመን መግባት የምታበስረው የመስቀል ወፍም በውብ ላባዋ ደምቃ ከተደበቀችበት በመውጣት የምትታይበት ወቅት ነው።

እኛም የ2017 አዲስ ዓመትን መነሻ በማድረግ በተለይ አዲሱን ዓመት ወጣቶች በምን መልኩ መቀበል አለባቸው እነርሱስ በምን መልኩ ለመቀበል አስበዋል በሚል በተለያየ የሥራ ዘርፍ ከተሰማሩ ወጣቶች ጋር ቆይታ አድርገናል።

ወጣት ጫላ አሰፋ ይበላል። በሙያው ኢንጂነር ነው። በተጨማሪም የኢትዮጵያ ወጣቶች ለሰላም ማህበር መስራችና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ነው። እርሱ እንደሚናገረው፤ አዲስ ዓመት ሲመጣ በአሮጌው ዓመት ለመሥራት አስበን ማሳካት ያልቻልናቸው ሥራዎች በአዲስ ጉልበትና በአዲስ እስትራቴጂ ለመሥራት ዕድል የምናገኝበት ዓመት ነው ይላል።

አዲስ ዓመትና ወጣትነት በባህርዩ ተመሳሳይነት አለው የሚለው ወጣት ጫላ፤ ወጣት የአዲስ ሀሳብ የፈጠራ ባለቤት ትኩስ ኃይል ነው። ይህ የወጣት ጉልበት ሀገራችን በአግባቡ ከተጠቀመች ሕዝብ የሚፈልገውን ነገር ማምጣት ይቻላል፤ ስለዚህ በአዲሱ ዓመት የወጣቱን እውቀትና ጉልበት በመጠቀም ለመለወጥ መዘጋጀት አለብን ይላል።

ወጣት አዲስ አሰራር ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ ፍላጐት ያለው የሕብረተሰብ ክፍል ስለመሆኑ የሚናገረው ጫላ፤ በአዲሱ ዓመት በተለያየ መስክ የተሰማሩ ወጣቶች ያላቸውን ሀሳብ በመሸጥ መለወጥ እንዲችሉ አቅሙ ያላቸው አካለት ከጎናቸው በመሆን ሊያግዟቸው ይገባል ይላል።

በሀገራችን ባለማወቅ ያሳለፍናቸው ጎዶሎዎች አሉ የሚለው ወጣት ጫላ፤ ይህንን ገደል በድልድይ ማገናኘት ከወጣቶች ይጠበቃል፤ በተጨማሪም በማወቅም ሆኖ ባለማወቅ የተገነቡ የጥላቻና የፍራቻ ግንቦች አሉ፡፡ ይህንን ግንብ በመናድ የሀገራችን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትና ፍቅር እንዲያድግ ማድረግ ከወጣቶች የሚጠበቅ በመሆኑ በአዲሱ ዓመት በኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል የእርስ በእርስ መተሳሰብ እንዲያድግ መሥራት አለባቸው ይላል።

ሀገሪቱ ወደፊት ሆና ማየት የምንፈልጋትን እንድትሆን በርካታ ሥራ ከወጣቶች ይጠበቃል፤ ይህንን ከባድ ኃላፊነት ለመወጣት በአዲስ መንፈስ፣ በአዲስ እውቀት፣ በአዲስ ጉልበት ተነስቶ መሥራት ያስፈልጋል የሚለው ወጣት ጫላ፤ ብዙ ግዜ ወጣቶች የነገ ሀገር ተረካቢ ይባላሉ ነገር ግን ወጣቶች የነገ ሀገር ተረካቢ ብቻ ሳይሆኑ የዛሬውን ሀገር ተረክበው ማስተዳደርና መኖር ይችላሉ ይላል።

ወጣቶች መገፋፋትን ትተን መቀራረብን፣ ጥላቻን ትታን ፍቅርን፣ መስበክ አለብን የሚለው ጫላ፤ ከነጠላ ትርክት ወጥተን ወደ ወል ትርክት መጓዝ መቻል አለብን የሚለው እምነት አለው፡፡ ይህ ሲሆን ሀገራችን ተለውጣ የምናይበት ግዜ እሩቅ አይሆንም ለዚህ ሁላችንም የሚጠበቅብንን ሚና መወጣት አለብን ይላል።

በኢትዮጵያ የሕዝብን ኑሮ መቀየር የሚችሉ የልማት ሥራዎች እየተሰሩ ስለመሆኑ የሚናገረው ወጣት ጫላ፤ ይህንን ልማት ለማስቀጠል ወጣቱ በባለቤትነት መሥራት አለበት፤ መንግሥትም ወጣቱ መሥራት እንደሚችል አምኖ ዕድል በመስጠት ወጣቱን አሳታፊ መሆን እንዳለበት ያስረዳል።

በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ የፀጥታ ችግሮችን ለመቅረፍ ከመንግሥት ባሻገር ወጣቱ ኃላፊነት እንዳለበት የሚናገረው ጫላ፤ በሰላም ግንባታ ሂደት የራሳቸውን ድርሻ በመውሰድ የተረጋጋች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ያለሰለሰ ጥረት ማድረግ እንደሚገባቸው ይናገራል።

በኢትዮጵያ በእስከአሁኑ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የማህበራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ወጣቶች ተጎጂ ሆነው ቆይታዋል የሚለው ጫላ፤ ጉዳቱ የሚደርሰው ወጣቶች ባልፈጠሩትና ባላደረጉት ነገር ነው፤ ስለዚህ ይህንን ችግር ለመፍታት ወጣቶች መነጋገርና መወያየት አለባቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ ሀገራዊ ምክክር መልካም ዕድል ሆኖ መጥቷል በዚህ ሂደት በንቃት በመሳተፍ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ መሥራት አለባቸው ይላል።

እኛው ተመካክረን ለራሳችን ችግር መፍትሔ ማበጀት ከልቻልን ማንም መጥቶ ችግራችንን ሊፈታልን አይችልም የሚለው ወጣት ጫላ፤ ወጣቶችን የገፋ ወይም በተገቢው መልኩ ያላሳተፈ ሀገራዊ ምክክር ደግሞ ውጤታማ መሆን አይችልም ይላል፡፡ የተለያዩ ሀገራት ስኬታማ ሀገራዊ ምክክር አድርገው ችግሮቻቸውን መፍታት የቻሉት ወጣቶችን በማሳተፍ ነው፤ ከዚህ አኳያ በሂደቱ የምክክር ኮሚሽኑ የወጣቶች ተገቢ ውክልና መኖሩን ማረጋገጥ እንዳለበት ይናገራል።

ሌላው አዲስ ዓመትንና ወጣትነት በተመለከተ ከአዲስ ዘመን ጋር ቆይታ ያደረገው ወጣት ሄኖክ ፍቃዱ ነው። የባዩሽ ኮልፌ በጎ አድራጎት ማህበር መሥራች አባል የሆነው ወጣት ሔኖክ እንደሚናገረው፤ አዲስ ዓመት ሲመጣ ምን ያህል የበጎ አድራጎት ሥራዎች ሠርተናል የሚለው ነው የሚያሳስበኝ ይላል።

በአዲሱ ዓመት በተቻለ መጠን ያሉብንን ጉድለቶች በማሻሸል በአዲስ መንፈስ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን ለመሥራት ተዘጋጅተናል የሚለው ሔኖክ፤ <<ለበጎ ሥራ ረፍዶ አያውቅም>> የሚለውን መርህ ቃላችንን መሠረት በማድረግ የበጎነት አድማሳችንን በማስፋት የተለያዩ ሥራዎችን ለመሥራት እቅድ እንዳለቸው ይናገራል።

በ2016 ዓ.ም በባዩሽ ኮልፌ አማካኝነት በተሰሩ የበጎነት ሥራዎች ጎዳናን ቤታቸው ያደረጉ ከጎዳና የራሳቸውን ቤት የሰሩ ከዚህ ባለፈ ሥራ ፈጥረው ከእርሳቸውን በተጨማሪ ሰራተኛ ቀጥረው ለሌሎች የሥራ ዕድል የፈጠሩ፣ ለራሳቸው ጥሩ ኑሮ ከመምራት በዘለለ ለሌሎች መትረፍ የቻሉ እንዳሉ የሚናገረው ሔኖክ፤ በዚህም ትልቅ ደስታና እርካታ እንደሚሰማው ይገልጻል።

ወጣት ሆኖ በበጎ አድራጎት ለይ መሳተፍ ምን አይነት ስሜት እንዳለው ሔኖክ ሲናገር፤ በጎነት በቃላት የማይገለጽ ትልቅ ደስታና ዋጋ ያለው ነገር ነው። የተከፉ ፊቶች በደስታ ሲሞሉ ማየት፣ ጠያቂና አጋዥ ለሌላቸው ሰዎች ጊዜ በመስጠትና አብሮ በማሳለፍ የሚገኘው ውስጣዊ እርካታ ትልቅ እንደሆነ ይናገራል።

በዚህ የበጎ አድራጎት ሥራ ውስጥ ብዙ ደስ የሚያሰኙ በዛው ልክ የሚያስከፉ አጋጣሚዎች ይኖራሉ የሚለው ወጣት ሔኖክ፤ ከፍተኛ ሕክምና የሚያስፈልጋቸው በገንዘብ እጥረት ምክንያት ግን ሕክምና መገኘት ተስኗቸው ሞታቸውን የሚጠባበቁ ሰዎች ለበጎነት በተዘረጉ እጆች እርብርብ ተግዘው ለሕክምናቸው የሚያስፈልጋቸው ገንዘብ ተሟልቶ ታክመውና ድነው ደስተኛ ሲሆኑ ማየት ያለው ስሜት በቃላት የማይገለጽ እንደሆነ ይናገራል።

በበጎ አድራጎት ሥራ ላይ እንደተሰማራ ወጣት በ2017 አዲሱ ዓመት ወጣቶች በበጎ አድራጎት ሥራ ላይ በንቃት ተሳታፊ እንዲሆኑ መበረታታት እፈልጋለሁ የሚለው ሔኖክ፤ በአጠገባችን ያሉትን ሰዎች ማየት፣ መንገድ ላይ የምናገኛቸውን አቅመ ደካማ ሰዎች መንገድ ማሻገር በራሱ በጎነት ስለሆነ ትንሽ ወይም ትልቅ ሰንል በጎነትን በአካባቢያችን ላሉ ሰዎች በማድረግ መጀመር አለብን ይላል።

በጎነት የሚታይ ፍሬና የሕይወትን ጎተራ የሚሞላ ለግለሰብና ለሀገር የሚተርፍ ተግባር ነው የሚለው ወጣት ሔኖክ፤ በጎነት ከማሰብ በዘለለ፤ አብዝቶ ከመልካም ስራዎች ጎን መሰለፍን፣ ሌሎችን ማገዝ ላይ ማትኮርን ከሰው ምላሽ ሳይጠብቁ ከራስ በላይ ለሌሎች ማድረግን የሚጠይቅ የንፁህ ልብ ክዋኔ እንደመሆኑ ወጣቶች በ2017 ዓ.ም ቀኝ እጃቸውን ለመዘርጋት መዘጋጀት እንዳለባቸው ይናገራል።

ከዚህ በፊት በበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ የተሰማሩ ወጣቶችም በአዲሱ ዓመት የበጎነት አድማሳቸውን በማስፋት በተሻለ ኃይልና ትጋት ዓመቱን በበጎነት ለማሳለፍ መዘጋጀት አለባቸው የሚለው ሔኖክ፤ እንደ ወጣት ትንሽ ትልቅ ሳንል ግዜና ጉልበታችንን ለበጎነት መስጠት አለብን ይላል።

ጎዳና ለወደቁ ዜጎች ማሕበረሰቡ የሚያደርገው አስተዋፅኦ ማደግ ያለበት ነው የሚለው ወጣት ሔኖክ፤ በኢትዮጵያ ካለውና እርዳታ ከሚያስፈልገው የሰው ቁጥር አንፃር በሀገር ደረጃ ድጋፍ የሚያደርጉ ተቋማት ጥቂት ናቸው፡፡ ይህ ማለት ተቋማቱ የያዙት የሰው ቁጥር ትንሽ ነው። በየጎዳናው የወደቀው ሰው ደግሞ ብዙ ነውና እንደ ተቋም እንደ ግለሰብ፣ እንደሃይማኖት ተቋም፣ እንደመንግሥት በዚህ አይነት ሥራዎች ላይ በስፋት በመሳተፍ መስራት የግድ እንደሚል ይናገራል።

የተረጂው ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ ከማህበረሰቡም ሆነ ከመንግሥት ብሎም ከሕዝቡ ብዙ የሚጠበቅ ሥራ እንዳለ የሚናገረው ሔኖክ፤ ለበጎ ሥራዎች በእኔነት ስሜት መተጋገዝ እና መረዳዳት ከሁሉም የሰው ልጆች የሚጠበቅ የውዴታ ግዴታ እንደሆነም ያስረዳል።

በሌላ በኩል ወጣት ጠብ አጫሪ ከሆኑ ነገሮች እራሱን በማራቅ በተለይ የማህበራዊ ሚዲያን በአግባቡና መልካም ለሆነ ነገር ብቻ በመጠቀም ብሎም በማይመለከተው ነገር ተሳታፊና ሀሳብ ሰጪ ከመሆን እርሱን በመጠበቅ ለሀገሪቱ ሰላም የራሱን ድርሻ መወጣት እንዳለበት ይናገራል።

ወጣት ሔኖክ እንደሚናገረው፤ በአዲሱ ዓመት ወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከመስጠታቸው በተጨማሪ አሁን በአገራችን ላይ ያለው የሰላም እጦት መፍትሔ እንዲያገኝ ወጣቱ ግንባር ቀደም ተዋናይ በመሆን ሚናውን መጫወት ይኖርበታል፡፡ ከነዚህ ሚናዎች መካከል በዋናነት ከበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ በተጓዳኝ በማህበራዊ ሚዲያ ድህረ ገፆች አማካኝነት ሰላም ጠፍቶ ግጭት፣ ልማት ጠፍቶ ጥፋት፣ እድገት ሳይሆን ውድቀት እንዲነግስ ለማድረግ ብሔርን ከብሔር፣ ሐይማኖትን ከሐይማኖት በማጋጨት የሀገርን ሰላም የዜጎችን ወጥቶ መግባት አደጋ ለይ ለመጣል የሚጥሩ ኃይሎችን ሀይ ልንላቸው ይገባል ይላል።

በመጨረሻም ወጣቶቹ ባስተላለፉት መልዕክት አዲሱ ዓመት ኢትዮጵያ ሰላም የሰፈነበት የሕዝቦቿ መተባበርና ፍቅር የጎላበት እንዲሆን ተመኝተው ለመላው የኢትዮጵያ ወጣቶች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ክብረአብ በላቸው

አዲስ ዘመን መስከረም 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You