የአምራች ዘርፉን እድገት የሚያፋጥኑት የኢንዱስትሪ ፓርኮች

የኢንዱስትሪ ፓርኮች (Industrial Parks) ልማት የኢትዮጵያን መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግርን እውን ለማድረግ አስተዋፅዖ ይኖራቸዋል ተብለው ትኩረት ከተሰጣቸው ተግባራት መካከል አንዱ ነው። የኢንዱስትሪ ፓርኮች የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የመሳብ፣ የሥራ እድል ፈጠራን የማስፋት እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን እውን የማድረግ ዋና ዋና መሰረታዊ ተልዕኮዎች አሏቸው። ፓርኮቹ በሚገነቡባቸው አካባቢዎች ለሚኖረው የኅብረተሰብ ክፍል ስራ በመፍጠርና ከአካባቢ ጋር ተስማሚ የሆነ የሥራ ከባቢ እውን በማድረግ ለሀገራዊ የምጣኔ ሀብት እድገት ትልቅ አስተዋፅዖ ይኖራቸዋል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ተመራጭ ከሚያደርጓቸው ነገሮች መካከል በርካታ አገልግሎቶችን አንድ ሥፍራ ላይ ሰብሰብ አድርገው የሚያቀርቡ መሆናቸው፣ ተገቢ መሰረተ ልማት የሚገነባላቸው እንዲሁም ከሌሎች አምራቾች ጋርም የሚያገናኙ መሆናቸው ይጠቀሳሉ። ከዚህ አንፃር በኢትዮጵያም ብዙ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በማቋቋም እንዲሁም በአንፃራዊነት ዝቅተኛ ዋጋ የሚከፈልባቸውን የሰውና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን፣ ማሽኖች ከቀረጥ ነፃ ማስገባትን፣ የብድር አቅርቦትን፣ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን እና የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን እንደማበረታቻ በማቅረብ ትልልቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ፋብሪካዎቻቸውን ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲከፍቱ ጥረቶች ተደርገዋል።

በእርግጥም ኢትዮጵያ የአፍሪካ የማምረቻ መናኸሪያ (Manufacturing Hub) እንድትሆን የሚደረገውን ጥረት ለማቀላጠፍ እንዲሁም ሥራ አጥነትን ለመቅረፍ ላቅ ያለ ሚና ይጫወታል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ውጤቶች ተገኝተውበታል። በተለይም ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድሎችን በመፍጠር ቀላል የማይባል አስተዋፅዖ አበርክተዋል።

በአሁኑ ወቅት የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣናን ጨምሮ በመላ ሀገሪቱ 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚገኙ ሲሆን በስራ እድል ፈጠራ፣ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትና በቴክኖሎጂ ሽግግር ለሀገራዊ ምጣኔ ሀብት እድገት አስተዋፅዖ እያበረከቱ ይገኛሉ።

የእነዚህ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ለማሳደግ ከተደረጉት ጥረቶች መካከል የሚጠቀስ ሲሆን፣ በመንግሥት እየተወሰዱ ያሉትን የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብሮችን ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ፓርኮቹም ዘርፉን የማሳደግ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ፍስሃ ይታገሱ፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት መንግሥት የአምራች ዘርፉን በተቀናጀ መልኩ ለመደገፍና ለማልማት ከወሰዳቸው ተግባራዊ እርምጃዎች መካከል አንዱ እንደሆነ ይገልፃሉ። እሳቸው እንደሚሉት፣ የግል እና የተቀናጁ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ሳይጨምር ለሌሎቹ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለመገንባት ብቻ መንግሥት ከአንድ ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጭ አድርጓል። ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ መንግሥት የአንድ መስኮት አገልግሎትን ጨምሮ የተቀናጀ መሰረተ ልማት ያቀረበባቸው የማምረቻ ቦታዎች ናቸው። 85 በመቶ የሚሆኑት የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ሼዶች በባለሃብቶች ተይዘዋል።

ፓርኮቹ ሲሰሩ ታሳቢ ተደርጎ የነበረው ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች እንዲመረቱባቸው ነበር፤ በዚህም አብዛኞቹ ፈቃድ የወሰዱት የውጭ ባለሃብቶች ነበሩ። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለሀገር ውስጥ ባለሃብቶች በተሰጠው ትኩረት አማካኝነት የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል። በአሁኑ ወቅት በፓርኮቹ ውስጥ ከሚገኙት ኢንቨስተሮች መካከል ከ51 በመቶ በላይ የሚሆኑት የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ናቸው።

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚገኙ አምራቾች እስካሁን ለውጭ ገበያ ካቀረቧቸው ምርቶች ከአንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል። ከወጪ ንግድ በተጨማሪ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ትኩረት በተሰጠው የተኪ ምርት ዘርፍም ተስፋ ሰጭ ውጤቶች እየተመዘገቡበት ይገኛል። በዚህም እስካሁን ከ750 ሚሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ያላቸው ተኪ ምርቶች ተመርተዋል። በስራ እድል ፈጠራ ረገድ ከ70ሺ በላይ ሰራተኞች በኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ውስጥ ተቀጥረው እየሰሩ ይገኛሉ።

የወጪ ንግድ (Export Trade) አፈፃፀም ዝቅተኛ እንዲሁም በአምራቾችና በግብዓት አቅራቢዎች መካከል ያለው ትስስር (Link­age) ደካማ መሆኑ፣ ውስጣዊና ዓለም አቀፍ አለመረጋጋቶች፣ ጥሬ እቃን በሀገር ውስጥ ምርት ያለመተካት ድክመት፣ የስራ እድል ፈጠራው በቂ አለመሆን፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ የቢሮክራሲ ውስብስብነት እንዲሁም የመሰረተ ልማት ጥገና ክፍተቶች በመንግሥትና በባለሃብቶች በኩል ያሉ የዘርፉ ልማት ተግዳሮቶች እንደሆኑም ዋና ስራ አስፈፃሚው ይገልፃሉ።

ሀገራት የኢንቨስትመንት ዘርፋቸውን በማሳደግ ጥቅል አገራዊ እድገታቸውን ዘላቂ ለማድረግ ከሚተገብሯቸው አሰራሮች መካከል አንዱ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎችን (Special Eco­nomic Zones) ማቋቋም ነው። ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎች የሚፈጥሩትን የስራ እድል፤ ለአገር በቀል የሎጂስቲክስ ኢንዱስትሪው መስፋፋት የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ፤ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰትን፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርንና የባለሙያዎችንና የሠራተኞችን ክህሎት ለማሳደግ እና የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስ የሚኖራቸውን ወሳኝ ሚና እንዲሁም የወጪና ገቢ ንግድን ለማቀላጠፍ ያላቸውን አበርክቶ በአጠቃላይ ለሀገራዊ የምጣኔ ሀብት እድገት መሻሻል የሚኖራቸውን ጉልህ ፋይዳ ከግምት ውስጥ በማስገባት አገራት ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎችን ያቋቁማሉ፣ ያስፋፋሉ።

በኢትዮጵያ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎችን በማቋቋም የሀገሪቱን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ። ግንባታቸው እየተከናወኑ ከሚገኙት ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎች በተጨማሪ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎች የማሸጋገር ጥረት ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎችን የማስፋፋት እንቅስቃሴ አካል እንደሚሆን ሲገለፅ ቆይቷል። ከሁለት ዓመታት በፊት ከኢንዱስትሪ ፓርክነት ወደ ነፃ የንግድ ቀጣናነት ተሸጋግሮ ስራ የጀመረው ድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣናም የዚሁ ማሳያ ነው።

በዚህም መሰረት በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ኢንዱስትሪ ፓርኮቹን ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎች ለማሸጋገር እንደታቀደ ዶክተር ፍስሃ ይናገራሉ። በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና የተጀመረውን ስራና ልምድ ወደሌሎች ኢንዱስትሪ ፓርኮች በማስፋት፣ ኢንዱስትሪ ፓርኮቹን ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎች ለማሸጋገር ታቅዷል። በነፃ የኢኮኖሚ ቀጣናዎቹ ከምርት ስራዎች በተጨማሪ የንግድና የሎጂስቲክስ ተግባራትም ይከናወናሉ።

ከዚህ በተጨማሪም ፓርኮቹ በብዙ ዘርፎች የሚሰማሩ ባለሃብቶችን እንዲቀበሉ ማድረግ እንደሚስፈልግ ጠቁመው፣ በአንድ የምርት ዘርፍ ላይ ብቻ ያተኮሩ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በሌሎች ዘርፎች ላይ የሚሰማሩ ባለሃብቶችን እንዲያስተናግዱ እንደሚደረግና ለተኪ ምርት የተሰጠው ትኩረትም ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ዋና ስራ አስፈፃሚው ያብራራሉ።

መንግሥት ባለፉት ጥቂት ዓመታት የወሰዳቸው የምጣኔ ሃብት ማሻሻያ እርምጃዎች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የተሰማሩ ባለሃብቶችን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ የሚያስረዱት ዶክተር ፍስሃ፣ ማሻሻያዎቹን በብቃት በመተግበር ተጨማሪ ኢንቨስትመንትን መሳብ እንደሚገባ ይገልፃሉ።

‹‹በቅርቡ መተግበር የጀመረው በገበያ ላይ የተመሰረተ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ስርዓት በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ለተሰማሩ/ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ዘርፍ ብዙ ጥቅሞችን ያስገኛል። የውጭ ባለሃብቶች በጅምላና ችርቻሮ ንግድ እንዲሰማሩ መፈቀዱም የውጭ ባለሃብቶችን ወደ ሀገር ውስጥ ለመሳብ ተጨማሪ እድል ይፈጥራል። የካፒታል ገበያ እንዲጀመር የሚደረጉ ዝግቶች ከዚህ ቀደም በባንኮች ላይ ተንጠልጥሎ የነበረውን ካፒታል ለማግኘት ያስችላል›› ይላሉ።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በርካታ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን በማድረግ የአምራች ዘርፉን ብሎም ሀገራዊ ኢኮኖሚውን ለማሳደግ ጥረት ስለመደረጉ ይገልፃሉ።

እሳቸው እንደሚናገሩት፣ ባለፉት ስድስት ዓመታት የአምራች ዘርፉን አፈፃፀም በማሻሻል በሀገር ውስጥና በውጭ ተወዳዳሪ ለመሆን በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል። የፖሊሲ ማሻሻያዎች ተደርገዋል፤ ቅንጅታዊ አሰራሮችና የባለድርሻ አካላት ትብብሮች እንዲጠናከሩ፣ የኃይል አቅርቦት እንዲሻሻል፣ የሎጂስቲክስ ስርዓቱ እንዲዘምን እና ለአምራች ዘርፍ የሚቀርበው የፋይናንስ መጠን እንዲጨምር ተደርጓል። የዘርፉን ውጤታማነት ለማሳደግ የተከናወኑት ተግባራት ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ የሆኑ የአምራች ዘርፍ ተግዳሮቶችን ለማቃለል አስተዋፅዖ ነበራቸው፤ የዘርፉ ዓመታዊ እድገት 10 ነጥብ አንድ በመቶ እንዲሆን አስችለዋል።

አቶ መላኩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ምርቶች እሴት ተጨምሮባቸው ለገበያ እንዲቀርቡ ትልቅ ሚና እንዳላቸው ያስረዳሉ። ‹‹በ2016 የበጀት ዓመት ወደ ውጭ ከተላከው ምርት ውስጥ 78 በመቶ የሚሆነው በጥሬ የተላከ ነው። በምርቶች ላይ እሴት ጨምሮ ለውጭ ገበያ ማቅረብ ይገባል። ይህን ለማድረግ ደግሞ በአምራች ዘርፍ የሚሰማሩ ባለሃብቶች ወደ ኢንዱሰትሪ ፓርኮች መግባት እና ኢንዱስትሪ ፓርኮችም በሙሉ አቅማቸው ማምረት ይጠበቅባቸዋል። የምጣኔ ሃብት ማሻሻያዎችን የሚጠቀም ባለሀብት ያስፈልጋል። ባለሀብት ገብቶ ካልሰራበት ፖሊሲውም ሆነ መሰረተ ልማቱ ብቻውን ለውጥ አያመጣም›› ይላሉ።

የአገሪቱን የምጣኔ ሀብት መዋቅር ከእርሻ መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለማሸጋገር የሚያግዙ በርካታ መልካም አጋጣሚዎችና እድሎች አሉ። ይሁን እንጂ እነዚህን መልካም አጋጣሚዎች በመጠቀም የኢኮኖሚውን መዋቅራዊ ሽግግር ለማሳካት የተከናወኑ ተግባራት ሀገሪቱ ካላት አቅምና ፍላጎት ጋር ተመጣጣኝ አይደሉም። ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ያላትን አቅም በመጠቀምና ከዚሁ ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ በማሳደግ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ የምታደርገውን መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግር ለማሳካት አምራች ዘርፉ አሁን ካለው አፈፃፀም በብዙ እጥፍ እንዲጨምርና እንዲሻሻል ማድረግ ያስፈልጋል።

የአምራች ዘርፉ እድገት ሊሻሻል የሚችለው ከኢንቨስትመንት መስፋፋት ጋር ተያይዞ ነው። የኢንዱስትሪ ፓርኮች ደግሞ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ተግባራዊ በማድረግ ለኢንቨስትመንት መስፋፋት ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥሩ ናቸው። ስለሆነም መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግሩን ለማሳካት የኢንዱስትሪ ፓርኮችን አፈፃፀም ማሻሻል ይገባል። ይህም ባለሀብቶች ወደ ፓርኮቹ ገብተው ለማምረት የሚያስችሏቸውን የመሰረተ ልማት ግብዓቶች፣ የሰለጠነ የሰው ኃይልና የፋይናንስ አቅርቦት ማሟላትን እንደሚያካትት ሊታወቅ ይገባል።

አንተነህ ቸሬ

አዲስ ዘመን ሐሙስ መስከረም 2 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You