ዶክተር አለምሰገድ ደበሌ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ መምህር
ኢትዮጵያውያኑ አሮጌውን ዓመት ተሻግረው የሚቀበሉት አዲስ ዓመትን ብቻ አይደለም፤ በዓመቱ መጨረሻ ወራት ውስጥ በሚዘንበው ዝናብ ምድር ረስርሳ የምትሰጠውን የመስከረም ወር አዝመራ እንዲሁም በዓመት ዞሮ የሚመጣውን ዓደይ አበባንም ጭምር ነው። በተለይም ሐምሌ እና ነሐሴ ወር ላይ እየደነፋ የሚያልፈው ወንዝ ጠርቶ፣ መስኩም በአበባ አጊጦ ስለሚታይ በየሰው ልብ ውስጥም ብሩህ ተስፋ መፈንጠቅ የሚጀምርበት ጊዜ ነው።
አሮጌውን ዓመት ከነበረው ጭንቀት ጋር ወዲያ በመጣል፤ እንደየአቅም መጠን በአዲስ ዓመት በአዲስ ተስፋ ለመኖር መስከረም ሲጠባ አንድ ተብሎ ኑሮ በአዲስ መልክ ይጀመራል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ በተጠናቀቀው ዓመት ችግር ሆነው የቆዩ ጉዳዮች በአዲሱ ዓመት ደግመው እንዳይከሰቱ መፍትሔው ምንድን ነው? አዲሱን ዓመት በምን አይነት ስነ ልቦና መቀበልስ ያሻል? በተለይ በአሮጌው ዓመት የታጣው ሰላም ዘንድሮ እንዴት መታደስ ይችላል በሚሉና በመሰል ጥያቄዎች ዙሪያ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ መምህር ከሆኑትና ብዙ ጊዜ በሰላም ዙሪያ ከሰሩ አለምሰገድ ደበሌ (ዶ/ር) ጋር አዲስ ዘመን ቃለ ምልልስ አካሂዷል። እንደሚከተለውም ቀርቧል።
አዲስ ዘመን፡- 2016 ዓ.ም እንደ ሀገር እንዴት ይታያል ?
አለምሰገድ (ዶ/ር)፡- በተጠናቀቀው በ2016 ዓ.ም በርካታ መልካም የሆኑ ስራዎች ተሰርተዋል። ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ እንደ አገር ፈታኝ የሆኑ ነገሮችም ነበሩ። ከተከናወኑ የተሻሉ ተግባራት ውስጥ መንግስት በተለይ በኢኮኖሚው ዘርፍ የወሰዳቸው ማሻሻያያዎች የሚጠቀሱ ናቸው። ፋይዳው ምንድን ነው? ተብሎ የሚጠየቅ ከሆነ ደግሞ በሂደት የሚታይ ይሆናል የሚል ምላሽ አለኝ።
ሌላው መንግስት ዲፕሎማሲው ላይ ጥሩ ሰርቷል የሚል አተያይ አለኝ። ከዚህ ከዲፕሎማሲው ጋር ተያይዞ እንደ አገር በመልካም ሁኔታ የተንቀሳቀስን ይመስለኛል። በተለይ ከምዕራባውያን፣ ከአሜሪካ፣ ከአውሮፓ ኅብረት ጋር ያለንን ክፍተት በጥሩ ዲፕሎማሲያዊ አካሔድ የሞላን ይመስለኛል። ከዚህም የተነሳ ወሳኝ የሆኑ ተቋማት እርዳታም ብድርም ለመስጠት መወሰናቸው በተፈጠረው መልካም የሆነ ዲፕሎማሲ አማካይነት ነው የሚል እምነት አለኝ።
በአንጻሩ ደግሞ እንደሚታወቀው ሲፈትነን የቆየው የሰላም መታጣት ሁኔታ ነው። በእርግጥ ሰላም እንዲሰፍን ብዙ ጥረት ተደርጓል። ይህም ጥረት በመንግስት፣ በኃይማኖት አባቶች፣ በአገር ሽማግሌዎችና በተለያዩ አካላት እየተደረገ ነው። እኔ በበኩሌ በሰላም ዙሪያ የተወሰኑ ስራዎችን ስሰራ ቆይቻለሁ። በእንዲህ አይነት መልኩ ጥረቱ ቢኖርም ስኬቱ ላይ ግን ያን ያህል ለውጥ አልታየም።
አሁንም ቢሆን እዚህ እና እዚያ የሚታዩ ውጥረቶች አሉ። ባለፉት ጊዜያት ፈታኝ ሆኖ የሰነበተው የሰላም መታጣቱ ጉዳይ እስከ ዓመቱ መጨረሻ አሳሳቢ ሆኖ ዘልቋል። በተለይ ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉ አካባቢዎች እንደልብ ማምረት እንዳይቻልና ኢንቨስት እንዳይደረግ የሚያግድ ሁኔታ ተስተውሎ ከርሟል።
ሌላው በአሮጌው ዓመት ሲያስጨንቀን የነበረው የኑሮ ውድነቱ ነው። በእርግጥ የኑሮ ውድነቱ በኢትዮጵያ ብቻ የተከሰተ ተዓምር ላይሆን ይችላል። ምክንያቱም የኑሮ ውድነቱ ዓለም አቀፋዊ ነው። እኛ ዘንድ ደግሞ ከጊዜ ወደ ጊዜ የኑሮ ሁኔታው ሲያሻቅብ ይታያል። እሱ ደግሞ ሕዝቡን ሲፈትነው ከርሟል። በእኔ እይታ እነዚህ ሁለቱ ጉዳዮች ፈታኝ ነበሩ ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡- መጥፎ ነው ከምንለው ከትናንቱ ታሪካችን መማር የምንችለው እንዴት ነው?
አለምሰገድ (ዶ/ር)፡- ከአጭሩም ሆነ ከረጅሙ ታሪክ የምንማራቸው ብዙ ነገሮች አሉ። ታሪክ ራሱ ትምህርት ቤት ነው። የሚያስተምረው ነገር አለው። ትልቁ ነገር ከጥሩውም ሆነ ከመጥፎው ነገር ትምህርት መውሰድ መቻል ነው። ጥሩነቱ ጥሩውን ነገር ለመቀጠል የሚስችል መሆኑ ነው። ለምሳሌ ዲፕሎማሲ ላይ የተሰራው አይነት በጎ ተግባር መማርና ለቀጣዩም ዓመት የበለጠ ጠንክረን ለመስራት መጣር ነው። የስራ አጥ ቁጥሩን ለመቀነስ የተወሰኑ መልካም ተግባራት ተሳክተዋል። እነዚያን የበለጠ ማጎልበት ወሳኝ ነው።
ነገር ግን እንዳይደገም ማድረግ ያለብን መጥፎውን ታሪክ ነው። ስለዚህ ከመጥፎ ታሪክ መማር ያለብን ደግመን ላለመስራት ስንጥር ነው። በተቻለ መጠን ሁሉ መጥፎውን ታሪክ ለማስቀረት መስራት ነው። ዋናው ጥያቄ የሚሆነው ምን ያህል እንማራለን የሚለው ነው። የምንቀየረውም ለውጥም ማምጣት የምንችለው በተማርነው ልክ ነው። ከመጥፎው ታሪካችን ብዙ መማር ከቻልን በብዙ መንገድ እንቀየራለን። በመቀየራችንም ብዙ ለውጥ በሕይወታችን ላይ እናመጣለን። በግለሰብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን ይህ እንደ ማኅበረሰብም እንደዚያው ብዙ ለውጥ ማስመዝገብ ይቻላል።
ባሉብን ችግሮች ላይ ተወያይተን ችግራችንን የምናልፍበትን መንገድ መፈለግ ነው። ይህ ደግሞ ለአንድ አካል ወይም ማኅበረሰብ የሚተው ሳይሆን አሊያም ደግሞ ለመንግስት ብቻ የሚተው ሳይሆን የሁሉም ድርሻ መሆኑን መረዳቱ ተገቢ ነው። ከታጠቁ ቡድኖች ጋር ውይይት አድርጎ በተለይ በሰላሙ ዙሪያ መምከሩ ወሳኝ ነው። መስማማት የሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መምከርና የተራራቀውን አካል ለማቀራረብ መጣር መልካም ነው የሚል አተያይ አለኝ። በዚህ ውስጥ ሁሉም የየራሱን ፍላጎት ከመለጠጥ ይልቅ ጠበብ ማድረግ የሚጠበቅበት ይመስለኛል። በዚህ ውስጥ መጥፎ ታሪክ የምንለውን ጉዳይ ወደጥሩ መቀየር ይቻላል ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- አዲስ ዓመትና አዲስ ተስፋ የሚያገናኛቸው ምንድን ነው? አንድ ሰው እቅድ ማቀድ ያለበት አዲስ ዓመትን ብቻ ጠብቆ መሆን አለበት?
አለምሰገድ (ዶ/ር)፡- አዲስ ዓመትና ተስፋ ሁለቱም አዲስ ናቸው። የሰውን ልጅ የሚያኖረው በተስፋ ነው። የሰው ልጅ ተስፋ የቆረጠ ዕለት የሚሞተው በቁሙ ነው። ስለሆነም ተስፋ ሁልጊዜ መኖር አለበት። ነገር ግን ጊዜያት የሚለኩት በወራት፣ በዓመታት ስለሆነ ምናልባት ከአምናው የተሳካልን ነገር ሲኖር እቅዱም የግድ ያስፈልጋል።
በእርግጥ እቅድ የሚታቀደው በአዲስ ዓመት ብቻ አይደለም። እቅዱ በሚያስፈልግበት ሰዓትና እንደተቋምም ካሰብነው የሶስት፣ የስድስት፣ የዘጠኝ ወርና የዓመት እቅዶች አሉና የሚታቀደው በዚያ ውስጥ ነው። የአጭርና የረጅም ጊዜ እቅዶች አሉ። ግን መሆን ያለበት እቅድ እንኳ ባይኖረን በአዕምሮ መዘጋጀት ያስፈልገናል። ወዴት እና እንዴት ነው የምንሔደው የሚለውን ለማሰላሰል ይጠቅመናል፤ በአዕምሮአችን የምናወጣውና የምናወርደው ሐሳብ እንደ ዝግጅት የመሚቆጠር ነውና ወደ እቅድ ለመቀቀየር ይረዳናል።
እቅዳችንን በተቻለ መጠን ሳይንሱ እንደሚለው የተሻለ ማድረግ ነው። በጣም አጭር የሆነ፣ ሊተገበር የሚችል፣ የሚመዘን፣ የሚታይ አድርገን ማቀዱ አዋጭ ነው። እቅድን በጣም ለጥጦ ማቀድ ተግባራዊ እንዳይሆን ሊያደርገው ይችላል። አዲስ ዓመት ሲመጣ የሰው ልጅ ያስባል፤ ከአምናው ዘንድሮ የተሻለ ነገር አገኛለሁ ብሎ ተስፋ ስለሚያደርግ ይዞለት የሚመጣው ተስፋን ነው።
በተለይ በእኛ አገር ደግሞ ወቅቶቹ ራሳቸው ያንን የሚያመለክቱ ናቸው። ደረቅ ከሆነው በጋ፤ እርጥብ ወደሆነው ክረምት ገብተን ልክ መስከረምና ጥቅምት ላይ ደግሞ አረንጓዴ ነገሮችን የምናይበት ነውና በተስፋ እንሞላለን። እቅዶችን የምናቀድው በዚህ ተስፋ ውስጥ ሆነን ነው። በዓመቱ መጀመሪያ ሰዎች የሚያቅዱትም ለዚያ ነው። እቅድ በተከታታይ በአጭር ጊዜና በረጅም ጊዜ ተብሎ መታቀድ ያለበት ሲሆን፣ እቅዱ ውስጥም ተስፋ መኖሩን አመላካች ነው። የሰው ልጅ ደግሞ የሚኖረውም ተስፋውን ነው። የሰው ልጅ ወደ ስኬት የሚቀይረውም ያንኑ ተስፋውን ነው። አዲስ ዓመትና ተስፋ የሚያያዙት ለዚያም ነው።
አዲስ ዘመን፡- ብዙ ሰዎች በአዲስ ዓመት እቅድ ያቅዳሉ፤ ከሚታቀዱ እቅዶች መካከል ብዙዎቹ ራሳቸውን ከሱስ ወጥመድ ለማላቀቅ ነው፤ ከዚህ ባለፈ ግን ለተሻለ ነገ የሚያስፈልገን የስነ ልቦና ዝግጅት ምን መሆን አለበት ይላሉ?
አለምሰገድ (ዶ/ር)፡- ሰዎች የሚያቅዱት እንደየፍላጎታቸው ነው። ከሱስ መላቀቅ አለብኝ ብሎ የሚያቅደውም ሰው ዋናው ችግሩ ሱስ ነው ማለት ነው። የሌሎችም ሰዎች ችግር እንደዚያው የተለያየ ነው። ገንዘብ የሚያባክን ሰው ከሆነ ደግሞ ገንዘቡን እንዴት በቁጠባ መጠቀም እንዳለበት እቅድ ያወጣል። እኛ እንደ አገር ያለብን ችግር ምንድን ነው? ማቀድ ያለብን እዛ ላይ ነው። እና በአጠቃላይ ችግሮቻችንን አይተን ነው እቅዶቻችንን የምናቅደው።
ሌላው ደግሞ ችግሮቻችን ላይ ብቻ ሳይሆን ጥሩ ነገሮቻችንም ላይ እቅድ ማቀድ ያስፈልጋል። አምና የተሳካልንን ስኬት ዘንድሮ በአዲሱ ዓመትም ለመድገም እቅድ አስፈላጊ ነው። ከዚህ የተነሳ እቅዶቻችንን ስኬታማ ለማድረግ የስነ ልቦና ዝግጅት ያስፈልጋል። ለምሳሌ ያቀድኩት እቅድ ባይፈጸም አማራጭ ብለን የምንይዘው ነገር ይኖራል። ስለዚህ እቅዶቻችንን ስናቅድ አጋጣሚ ሆኖ ባይሳካ ተለዋጭ እቅድ ሊኖረን ይገባል። በስነ ልቦናም ዝግጁ መሆን ይጠበቅብናል። ያቀድነው ባይሳካ በተለዋጭ በያዝኩት እቅድ እዴት ማሳካት እችላለሁ የሚለው መጤን ይኖርበታለል። ያልተጠበቁ ነገሮች ቢከሰቱብን ያንን ነገር እንዴት መመለስ እንችላለን በሚል በስነ ልቦና ረገድ መዘጋጀት ይኖርብናል። ስለዚህ እዛ ላይ መስራትና መወያየት ያስፈልጋል። ከዚህ የተነሳ የአዕምሮ ዝግጅት ወሳኝ ነው።
ይህ ብቻ ሳይሆን ስትራቴጂም ያስፈልጋል። እቅዱን ለማሳካት መከተል ያለብኝ ስትራቴጂ ምንድን ነው? የሚለውን መገንዘብ ወሳኝ ነው። ለምሳሌ የአጭር ጊዜ እቅዴ እንዲሳካልኝ መከተል ያለብኝ ስትራቴጂ ምን አይነት ነው? የምከተላቸው ስትራቴጂዎችስ በትክክል እቅዴን ማስፈጸም የሚችሉ ናቸው? የሚለውን መረዳት ተገቢ ነው። ‘መጥፎ ነገር ቢከሰት በዚህ በዚህ ስትራቴጂ ልወጣው እችላለሁ’ የሚል የስነ ልቦና ዝግጅት መኖር አስፈላጊ ነው። የስነ ልቦና ዝግጅት ካለ ለሚመጣው ችግር ሁሉ ቅድመ ዝግጅት ስለሚኖር በማማከር አሊያም በራስ በመተማመን ችግሩን መሻገርና ለአዲስ ተስፋ መዘጋጀት የሚያስችል ይሆናል። ከራስ የተሻለ አካል ካለ ደግሞ ካለፉበት መንገድ ትምህርት ለመውሰድም በቂ ማንነት ስለሚኖረን የሚገዳደር ነገር አይኖርም።
እንደ አገር ከሆነ ደግሞ የምናስበው፤ እንደ አገር የምናሳካቸውን ነገሮች ለማሳካት ማቀድ ነው። ተሳክቶልን ከሆነ ደግሞ እሰየው ነው። ካልተሳካልን በአዲስ መንፈስ ለቀጣዩ መዘጋጀት ነው። አገር ማለት የመሪዎች ስብስብና ሕዝብ አንድ ላይ የሚኖርበት ስፍራ ነው። ስለዚህ ልምድ የምንቀስመው ከዚያ ነው። ወደ ማኅበረሰባችንም ተመልሰን ልምድ መውሰድ ያስፈልጋል። የተሻሉ አገራትም እቅዶቻቸውን እንዴት እንዳሳኩም ልምድ መውሰድ ብልህነት ነው። በተለይ ደግሞ ከእኛ አገር ጋር ተቀራራቢ የሆነ ነገር ካላቸው አገራት ልምድ መውሰዱ ተገቢ ነው ባይ ነኝ።
በስነ ልቦና ደረጃ ጠንካራ መሆን ብቻ ሳይሆን በፋይናንስ ደረጃ ጠንካራ መሆንም የግድ ይላል። አንዳንድ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን በአገር ደረጃ ለማከናወን ሲታቀዱ በገንዘብ በኩል መዘጋጀትም የግድ ነው። ምክንያቱም አንድም ትልልቅ ፕሮጀክቶች ታቅደው ስኬታማ መሆን የማይችሉትና የሚከሽፉት ከፋይናንስ እጥረት የተነሳ ነው። ስለሆነም ፋይናንሱን እንዴት ማስተዳደር ይቻላል? የሚለው ከግምት ውስጥ መግባት ይኖርበታል። ለታቀደው እቅድ እንዴት መዋል ይችላል የሚለው በአግባቡ መጤን ይኖርበታል። በዚህ ደረጃም አጥብቆ መስራት ያስፈልጋል ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያን በተጠናቀቀው በ2016 ዓ.ም ያጋጠማት ብዙ ስብራት መኖሩ ይታወቃል፤ እነዚያ ስብራቶች በ2017 ዓ.ም እንዳይደገሙ ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
አለምሰገድ (ዶ/ር)፡- ያለፈው ዓመት ችግሮቻችን መንስዔ እኛ ከሆንን ዘንድሮ እንዳይደገም የመፍትሔውም አካል መሆን ያለብን እኛው ነን፡ ስለዚህ በቀጣይ ችግሩ የበለጠ እንዳይፈትነን ለመፍትሔው መጣር ነው። እኔ መምህር ነኝ። በመመምህርነቴ ማድረግ የምችለው ማስተማር ነው። ለችግሩ መፍትሔ ለማበጀት ስምምነት ላይ መድረስ የግድ ነው። አንዳንድ ጊዜ ሁሉም በአንድ አይነት ሀሳብ ሊስማማ አይችልም። ስለዚህም በማያስማሙን ነገሮች ላለመስማማት መስማማትም ያስፈልጋል።
በአሁኑ ወቅት እንኳን በአንድ አገር ውስጥ ያለን ዜጎች ቀርተን በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ማኅበረሰብ እንኳ በብዙ ጉዳዮች ወደስምምነት እየመጡ ያለበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው። ስለዚህም ማሰብ የሚኖርብን እንደዛ ነው። በተቻለን መጠን ያሉንን ልዩነቶች ከልብ ተወያይተን ስምምነት ላይ መድረስ ወሳኝ ነው። ውይይት ሲባል እንዲሁ ለይስሙላ የሚደረግ መሆን የለበትም። አምነንበትና ይበጀኛል ብለን የምናደርገው መሆን አለበት። ዋናው ነገር የችግሩን ጭብጥ ማወቅ ነው። ችግሩን በትክክል ከተረዳነው ለዚያ ችግር መፍትሔ መፈለግ ነው። የችግራችን ጊዜ የቱንም ያህል የረዘመ ቢሆንም መፍትሔ አይታጣለትም።
እርግጥ ነው ጊዜ ሊወስድ ይችል ይሆናል፤ ምናልባትም በአንድ ወር አሊያም በአንድ ዓመትም ላይፈታ ይችል ይሆናል። በረጅም ጊዜ ሂደት ውስጥም ቢሆን ችግሮችን ለመፍታት የመፍትሔ አካል ለመሆን መዘጋጀት ትልቁ ጉዳይ ይሆናል። ወደ መፍትሔው ለመምጣት መረጋጋት በራሱ አንድ ጉዳይ ነው።
በሁሉም አቅጣጫ ብዙ ልናጣቸው የምንችላቸው ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ። እንደዚያ እንኳ ቢሆን ለአገር ሰላም ሲባል ልብን ማስፋት ተገቢነቱ አጠያያቂ አይሆንም እላለሁ። በውይይት ደግሞ የማይፈታ ነገር አይኖርም፤ በመነጋገር ውስጥ መፍትሔ አይጠፋም። ስንወያይ ግን እውነትነት ባለው አካሔድ መሆን አለበት።
ከዚህ ውጭ ዝም ብለን ዓመቱን ሙሉ ተሰብስበን ፋይዳ የሌለው ውይይት አድርገን መመለስ አይነት ከሆነ ትርጉም አይኖረውም። እሱ በጊዜ፣ በገንዘብና በጉልበት መቀለድ ነው። እንደዚያ ከሆነ የምንፈልገውን ለውጥ ማምጣት፤ አንዳች ስምምነት ላይም መድረስ አንችልም። የምንናፍቀው ሰላምም በተግባር መሬት ላይ ወርዶ ማየት አንችልም።
እኔ ሁሌ የሰላም ጉዳይ ያሳስበኛል፤ በአሁኑ ወቅት የምንሰማውና የምናስተውለው ነገር እየከበደ መጥቷል። ከዚህ በኋላ ባሳለፍነው አይነት መንገድ ማለፍ አንፈልግም፤ ሰላም መሰረታዊ የሆነ ነገር ነው፤ ሰላም ካለ ቋጠሮው ሁሉ ይፈታል። ከባዱ ነገር ሁሉ ቀላል ይሆናል። ለሁሉ ነገር መሰረቱ ሰላም ነው። ሰላም ሲኖር ልማት አይስተጓጎልም፤ ምርታማነት ይጨምራል። ምርታማነት ጨመረ ማለት ደግሞ በኑሮ ውድነት የጎበጡ ወገቦች ቀና ይላሉ።
ትልቁ ነገር ሰው የመንቀሳቀስ፣ የማልማትና የማምረት ነጻነት እንዲኖረው በሰላሙ ዙሪያ አበክሮ መስራት ነው። አንዱ እዚህ አገር ላይ ችግር የሚፈጥርብን እና የሚያጋጨን የኢኮኖሚ ችግር ነው። ሁሉም ሰው የተሻለ ነገር ቢኖረው ከዚያም የተነሳ የተሻለ ኑሮ ቢመራና ገቢውም እያደር የተሻለ ቢሆን አሁን እየፈተነን ያለው ችግር በጣም ይቀንሳል። እያስቸገረን ያለው የሰላም እጦት በዚህ ልክ አይገዳደረንም። ስለሆነም እዚህ ላይ እንደምንም በማለት በጣም በጥልቀት መስራት ያስፈልገናል፤ እኔ ማለት የምችለው ይህንን ነው።
አዲስ ዘመን፡- በአዲሱ ዓመት በተለይ ኢትዮጵያ ምርታማ የሆነች እና ሰላም የሰፈነባት አገር እንድትሆን ከሕዝብና መንግስት ይጠበቃል? ቁርጠኛ መሆን የሚጠበቅባቸውስ በየትኞቹ ጉዳዮች ላይ ነው? ቁርጠኝነታቸውስ የት ድረስ መሆን አለበት ይላሉ?
አለምሰገድ (ዶ/ር)፡- ሰላምን የማስፈን ስራ ለመንግስት ብቻ የሚተው ጉዳይ አይደለም። አሊያም ደግሞ በአንድ አካል ጫንቃ ላይ ብቻ የሚጣል አይሆንም። ሕዝቡም ቢሆን ሰላም ፈላጊነቱን በተግባር ማንጸባረቅ መቻል ይኖርበታል። ጠብመንጃ ያነሱትንና ችግር የሚፈጥሩትን አካላትን በሚቻለው መንገድ ሁሉ ወደ ሰላም መድረክ እንዲመጡ እና እንዲወያዩ መጋበዝ ነው።
በአሁኑ ወቅት ነፍጥ አንግተው ከኅብረተሰቡ መካከል ያፈነገጡ አካላት የወጡት ወይም የመጡት ከሌላ አገር አይደለም። የወጡት ከእኛው ማኅበረሰብ ውስጥ ነው። ስለሆነም ከአብራኩ የወጡትን አካላት ራሱ ማኅብረሰቡ ጣልቃ ገብቶ “ሃይ” ሊል እንዲሁም ለሰላም እጃቸውን ዘርግተው የወጡበትን ማኅበረሰቡን እንዲቀላቀሉ ማድረግ ይጠበቃል።
በእርግጥ ለእንደዚህ አይነት ችግር ፖለቲካዊ መፍትሔም የግድ የሚል እንደሆነ አምናለሁ። ስለሆነም በመንግስትም በኩል ፖለቲካዊ የሆነ መፍትሔ ለመስጠትና ለሰላም ቁርጠኛ መሆን የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ለዚህ ደግሞ ዝግጅት አስፈላጊ ነው። በእርግጥ በአሁኑ ወቅት ጥሪዎች በመደረግ ላይ ናቸው። እነዚያን ጥሪዎች እንዳስተዋልነው በአገር ውስጥም ሆነ በውጪውም ማወያየት ተጀምሯል። ማወያየት በራሱ አንድ ትልቅ ጅማሮ ነው። ያንን ደግሞ እንደምንም በማለት ወደፍጻሜው ማምጣት ወሳኝ ነው። ከአሁን በፊት የፕሪቶሪያው ስምምነት እንደተደረገው አይነት በዛ መልኩ ተንቀሳቅሶ ሰላምን ለማምጣት መሞከር በጣም አስፈላጊ ነው።
ሰላም እንደሚታወቅ ከግለሰብ የሚጀምር ነው። በአንድ ሰው አዕምሮ ውስጥ ሊፈጠር የሚችል ነው። ሰላማዊ የሆነ አዕምሮ ያለው ሰው የአገር ሰላምን ማምጣት ይችላል። ደግሞም ትክክለኛ የፖለቲካ መፍትሔ ለሚሹት ጉዳዮች ትክክለኛውን ፖለቲካዊ መፍትሔ መስጠት ወሳኝ ነው፤ እሱ ሲደረግ ከልብ የሆነ ምላሽ በመስጠት ጭምር መሆን አለበት። እንዲህ ሲሆን ብዙ ሊታጣ የሚችል ነገር ሊኖር እንደሚችል ማጤኑ ተገቢ ነው። እነዚህ ሁሉ ተግባራት በአንድ ጊዜ የሚከናወኑ ነገሮች አይደሉም፤ ረጅም ሒደትን የሚከተል ሊሆን ይችላልና ማኅበረሰቡም በዚያ መልክ መዘጋጀት ይኖርበታል። ከንግግር ያለፈ ዝግጅት ከሕዝቡ የሚጠበቅ ይሆናል። ሰላም የሚመጣ ከሆነ ሁሉም ነገር ሰላሙን ተከትሎ የሚመጣ ይሆናል የሚል አመለካከት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- በእርስዎ አተያይ ኢትዮጵያን የፈተናት ልጓም ሊበጅለት ይገባዋል የሚሉት ጉዳይ ምንድን ነው? ምን አይነትስ መፍትሔ ይሰጠው ይላሉ?
አለምሰገድ (ዶ/ር)፡– አስቀድሜ ለመግለጽ እንደሞከርኩት ትልቁ ነገር የሰላሙ ጉዳይ ነው። ሁለተኛው የኑሮ ውድነቱ ነው። በእርግጥ መንግስትም የሚችለውን እያደረገ ድጎማ የሚያስፈልጋቸውን እንደ ነዳጅ አይነቱን እየደጎመ ይገኛል።
ከሰላሙ አንጻር እንደሚታወቀው ሁሉም ሕዝብ ሰላም ፈላጊ ነው። በተመሳሳይ መንግስትም ሰላም ፈላጊ ነው። እንዲህ ከሆነ ደግሞ የኢትዮጵያ ተግዳሮት ሆኖ የሰነበተውን የሰላም እጦትን መላ ለማለት ወደ ውይይቱ መምጣት መልካም ነው እላለሁ። ለዚህ ደግሞ በአሁን ወቅት በመንቀሳቀስ ላይ በሚገኘው ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ መድረክ መጠቀምና መወያየቱ አንዱ መፍትሔ ነው ብዬ አስባለሁ። በምንችለው አቅም ሁሉ ሰላምን ማምጣት የሚችሉ ጉዳዮች ላይ መስራት ነው። በሶስተኛ ወገንም ቢሆን በአገር ደረጃ ሽማግሌዎችንና የኃይማኖት አባቶችን በመጋበዝም ጭምር መስራት ወሳኝ ነው። ሰላምን ለማምጣት መሰልቸት አያስፈልግም፤ ብዙ መድከም የሚጠይቅ ቢሆንም ከብዙ ድካም በኋላ ለውጥ ይገኛል የሚል ተስፋ ሰንቆ ለስኬታማነቱ መትጋት ወሳኝ ነው። በጉዳዩ ላይ ተከታታይ ስራ መስራት እንጂ አንዴ ሞክሬዋለሁና ሊሳካልኝ አልቻለም በሚል ተስፋ መቁረጥ አይገባም። ስኬት እስከሚመጣ መውደቅና መነሳት እንደሚኖር በማመን ለለውጡ መትጋት የሁሉም ኃላፊነት ጭምር ነው ብዬ አስባለሁ። መውደቅ እንዳለ ሁሉ መነሳት መኖሩን ተስፋ በማድረግ ወደፊት መሔድ ያስፈልጋል።
የኑሮ ወድነቱን ለማረጋጋትም ደግሞ እሱም ልክ እንደ ሰላም ማስፈን ሁሉ ትልቅ ስራ የሚጠይቅ ነው። በእርግጥ ችግሮቻችን ተደማምረው የበዙ ሆነዋል። አንዱን መፍትሔ ሊገኝለት ነው ሲባል ሌላው ችግራችን ይቀጥላልና መፍትሔው እርስ በእርስ መተሳሰብ ነው። በተቻለ መጠን የወጡ ሕጎችን ማክበር እና በእነሱ መገዛት ወሳኝ ነው። ጎን ለጎን ደግሞ መንግስትም ሕዝብም መወጣት የሚጠበቅበትን ሚና መወጣት ይኖርበታል። እንደ አጠቃላይ ሰላም መስፈን ቢችልና የኑሮ ውድነቱ ቢረጋጋ አገራችን በተሻለ ጎዳና ላይ መሆን ትችላለች እችላለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ለቃለ ምልልሱ ፈቃደኛ ስለሆኑ ከልብ አመሰግናለሁ።
አለምሰገድ (ዶ/ር)፡– እኔም አመሰግናለሁ።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ሐሙስ መስከረም 2 ቀን 2017 ዓ.ም