በባለሥልጣኑ የተጀመረው ወረቀት አልባ የሶፍትዌር ልማት ፕሮጀክት 58 በመቶ ተከናውኗል

አዲስ አበባ፡- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን በ150 ሚሊዮን ብር የሚያከናውነው ወረቀት አልባ የሶፍትዌር ልማት ፕሮጀክት 58 በመቶ መድረሱን አስታወቀ፡፡

ባለሥልጣኑ በዓመቱ ውስጥ የተሠሩ ሥራዎችን ነሐሴ 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ከባለድርሻ አካላት ጋር በኔክሰስ ሆቴል በገመገመበት ወቅት የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሙሉ እመቤት ታደሰ እንደገለጹት፤ የባለሥልጣኑን ማንኛውም ሥራ ወረቀት አልባ ለማድረግ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ጋር በመተባበር 150 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የሶፍትዌር ፕሮጀክት እየተከናወነ ነው፡፡

ፕሮጀክቱ 58 በመቶ መከናወኑን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሯ፤ ሶፍትዌሩ አስራ ሁለት ተግባራትን ዲጂታላይዝ የሚያደርግ መሆኑንና በ2017 ዓ.ም. ተጠናቆ ወደ ሥራ ለማስገባት ከፍተኛ ርብርብ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

እንደዋና ዳይሬክተሯ ማብራሪያ ይህ ፕሮጀክት ለዚህ ደረጃ መብቃቱ ከቢሮውና ከባለሥልጣኑ በላይ የከተማው አስተዳደር የሚያደርገው ክትትልና እገዛ ከፍተኛ ነው፡፡

በባለሥልጣኑ በኩል የተሰጡ የብቃት ማረጋገጥ ሰርተፍኬት፣ የጤና ባለሙያዎች የብቃት ማረጋገጥ ብቻ ሲታይ በዓመቱ ውስጥ በጥቂት ሠራተኞች ከ 14 ሺህ በላይ ሰርተፍኬት የተሰጠ መሆኑን ያነሱት ወይዘሮ ሙሉእመቤት፤ ይህ ከእቅድ በላይ የተሠራ ተግባር በሠራተኞቹ ከፍተኛ የሥራ ትጋት የተገኘ ውጤት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አያይዘውም ፋይሎቹ የድሮ ፋይሎች በመሆናቸው አቧራ ማራገፍ፣ ፈልጎ ማግኘት እና በቁርጠኝነት ሳይሰለቹ ዕለት በዕለት ተግቶ መሥራትን የሚጠይቅ መሆኑን ጠቅሰው፤ አሁን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ጋር በመተባበር እየለማ ያለው ወረቀት አልባ የሶፍትዌር ፕሮጀክት ተግባራዊ ሲሆን አሠራሩ እጅግ ስለሚዘምን ይህን መሰል ችግሮች ይወገዳሉ ብለዋል፡፡

በዕለቱ በበጀት ዓመቱ የተከናወኑ የቁልፍ ተግባራት ግቦች አፈጻጸም ሪፖርት ሲቀርብ እንደተጠቀሰው ክትትል እና ቁጥጥር ከተደረገባቸው የጤና ተቋማት ውስጥ 109 ተቋማት ጉድለት የተገኘባቸው ሲሆን 87 ተቋማት የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ፣ 21 ጊዜያዊ እሸጋ እና 1 ተቋም ፍቃድ የመሰረዝ ርምጃ ተወስዶባቸዋል፡፡

ከመድኃኒት ተቋማት ውስጥ ደግሞ 116 ተቋማት ላይ ችግር የተገኘባቸው ሲሆን 77 ተቋማት የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ፣ 38 ተቋማት ላይ ጊዜያዊ እሸጋ እና 1 ተቋም ፍቃድ የመሰረዝ ርምጃ የተወሰደ ሲሆን 90 ሺህ 584 ኪ.ግ. የሚመዝንና አርባ ሰባት ሚሊዮን አምስት መቶ አርባ ሰባት ሺ አራት መቶ ዘጠና ስድስት ብር ከ84 ሳ.ም. ዋጋ ያላቸው መድኃኒቶች ተወግደዋል፡፡

የምግብ እና ጤና ነክ ተቋማት ውስጥ 941 ተቋማት ላይ ችግር የተገኘባቸው ሲሆን 855 ተቋማት የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ፣ 83 ተቋማት ላይ ጊዜያዊ እሸጋ እና 3 ተቋም ፍቃድ የመሰረዝ ርምጃ ተወስዷል፡፡

በአጠቃላይ በዓመቱ የተወገዱ ጊዜ ያለፈባቸውና የተበላሹ ምግቦች 132 ሺ 250 ኪ.ግ. በቁጥጥርና የኦፕሬሽን ሥራ በመሥራት 13 ሚሊዮን 345 ሺ 270 ብር ዋጋ ያለው ጊዜ ያለፈባቸውን ምርቶች እንዲወገዱ ተደርጓል ሲሉ ዳይሬክተሯ ጠቅሰዋል፡፡

ከዚህ ውስጥ ስድስት ሚሊዮን ብር የሚገመት 109 ማዳበሪያ ቅቤ የናሙና ምርመራ በማድረግ በውጤቱም መሠረት ከባዕድ ጋር የተቀላቀለና ለጤና አስጊ መሆኑ በመረጋገጡ እንዲወገድ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

ስሜነህ ደስታ

አዲስ ዘመን መስከረም 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You