የነገዋ ኢትዮጵያ ተስፋ ታዳጊዎች

የነገዋ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ያደገች ፣ በቴክኖሎጂ የላቀች ፣ ሰላሟ የተረጋገጠ እንድትሆን የተለያዩ ተግባራት እየተከናወነ ነው። ከእነዚህ ተግባራት አንዱ ታዳጊዎች በቴክኖሎጂው ዘርፍ ያላቸውን እምቅ አቅም ወደ ተግባር እንዲለውጡ ምቹ ዕድል መፍጠር ነው።

ከእነዚህ ምቹ ሁኔታዎች አንዱ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት 200 የኤ አይ ሰመር ካምፕ መርሃ ግብር በቴክኖሎጂው ተሠጥኦ ያላቸውን ታዳጊዎች እያሠለጠ ይገኛል።

ታዳጊ መልካም አስራት ፤ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን በመጠቀም የኮሌራ በሽታ ከመከሰቱ በፊት ውሃ ውስጥ የኮሌራ ቫይረስ መኖርና አለመኖሩን የሚያሳውቅ መሣሪያ መሥራቷን ትናገራለች።

የ10ኛ ክፍል ተማሪና ከዲላ ከተማ እንደመጣች የምትናገረው መልካም ሥልጠና እድሉን ያገኘሁት ክረምትን ቤት ከማሳልፍ በሚል ኢንስቲትዩቱ ባወጣው ማስታወቂያ መሠረት በኦንላይን ተመዝግቤ ነው ትላለች። ከዚህ በፊት በዲላ ከተማ የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችን እንደሠራችም ትገልጻለች።

በአገኘችው የኤ አይ የክረምት ሥልጠና የኮሌራ መመርመሪያ መሣሪያውን እንድሠራ ያነሳሳት በምትኖርበት የዲላ ከተማ ሁሌም ክረምት ሲሆን በሸታው መቀስቀሱና ለህብረተሰቡ ስጋት መሆኑ ነው የምትለው ታዳጊዋ፤ በሰራሁት መሣሪያም ከዚህ በኋላ የበሸታው ስም እንዳይነሳ እንደማደርግ ተስፋ አለኝ ብላለች።

መሣሪያው በሽታው ከመከሰቱ በፊት ውሃ ውስጥ ያለውን የሚመረምር ሲሆን ከተከሰተም በኋላም የበሽታው መጠን ምን ያህል እንደሆነ በመመርመር ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ ነው ስትል ገልጻ፤ ታማኒነቱም 95 በመቶ ነው፤ ይህም አንድ የቤተ ሙከራ (ላብራቶሪ) ባለሙያ ከሚሰጠው ምላሽ እኩል ነው ስትል ታብራራለች።

ታዳጊዋ፤ ወደፊት መሣሪያው ላይ ተጨማሪ ፈጠራዎችን በማከልና ሥራ ላይ በማዋል ከኢትዮጵያ አልፎ የአፍሪካን የኮሌራ በሽታ ችግር የመቅረፍ እሠራለሁ ትላለች።

የክረምት ቆይታዬ የተለያዩ እውቀቶችን እንዳገኝ እንዲሁም ይህን ማሽን በኤ አይ አማካኝነት እንደሠራ እድሉን አግኝቻለው የምትለው ታዳጊ መልካም፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ ሠልጣኞች በሚፈልጉት ዘርፍ በተግባር መሠልጠናቸው የሚያስደስትና ውጤታማ ቆይታ እንዲኖር አድርጓል ብላለች።

የግብርናው ዘርፍ ላይ የሚሠራ ሮቦት የሠራው ደግሞ ታዳጊ አብዱራህማን ሙህዲን ነው። ታዳጊው የፈጠራ ሥራውን የሠሩት በቡድን መሆኑን ተናግሮ፤ ሮቦቱ አንድ ሰብል ተዘርቶ ጎተራ እስከሚገባ ድረስ የተለያዩ እቃዎች እየተቀየሩለት የሚሠራ ነው ይላል።

በኢትዮጵያ 80 በመቶ በላይ የሚሆነው ዜጋ በግብርናው ዘርፍ ላይ ያለ ነው። እንዲህም ሆኖ ሀገራችን በምግብ እራሷን አልቻለችም። ይህም የሆነበት ምክንያት አብዛኛው የግብርናው ዘርፍ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የአስተራረስ ዘዴ ባለመከተላችን ነው ሲል ይገልጻል።

የፈጠራ ሥራውን ልንሠራ የቻልነው ብቸኛው ኢትዮጵያ በምግብ እራሷን እድትችል ማድረግ የሚቻለው የግብርና ዘርፉን በሮቦቶች በመደገፍ መሆኑን በመረዳት ነው።

የሠራነው የፈጠራ ሥራ አሁን ኢትዮጵያ ላይ ተግባራዊ የሚደረገውን የእርሻ ስልት ማለትም የተለያዩ ማሽነሪዎች በመጠቀም ማረስ፣ ማለሰለስ፣ መዝራት፣ ፀረ ተባይና አረም መርጨት እንዲሁም ማጨድ በአጠቃላይ ከ10 በላይ ማሽነሪዎች የሚሠሩትን ሥራ ከስር ያለውን ጥርስ ብቻ በመቀየር በአንድ ሮቦት እንዲከወን የሚያደርግ ነው ሲል ያብራራል።

ይህም ለተለያዩ ማሽነሪዎች የሚወጡ ወጪዎችንና ጊዜን የሚቆጥብ ነው ። በተጨማሪም ሮቦቱ አየር ሁኔታንና አፈር አሲዳማነትን የሚቆጣጠር ቴክኖሎጂ የተገጠመለት በመሆኑ ጥሩ ምርት ለማምረት የሚያስችል ነው ሲል ይገልጻል።

የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የመጡ ሶስት ሺህ 500 ተማሪዎች ተመዝግበው መስፈርቱን ያሟሉ 200 ተማሪዎች በዘንድሮው ክረምት እንዲሰለጥኑ መደረጉን ገልጸዋል።

ሥልጠናው በአምስት ዘርፎች እንደተከናወነ ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ በዘርፉ ብቁና ተወዳዳሪ የእውቀት ባለቤት የሆኑ ወጣቶችን ማፍራት ተችሏል ብለዋል።

ሥልጠናው በዘርፉ እውቀት ባላቸው አሠልጣኞች ከተሟላ ግብዓት ጋር የቀረበ ሲሆን የክረምት ሥልጠናው የኢትዮጵያ ወጣቶች በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ችግር ፈቺና በዓለም ተወዳዳሪ የሆኑ ፕሮጀክቶችን እንዲሠሩ ያደረገ ነው ያሉት።

ከሰሞኑ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ለሁለት ወራት በአምስት ዘርፎች ሲያሠለጥናቸው ቆየውን 200 የኤ አይ ሰመር ካምፕ ሠልጣኞች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት አስመርቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ተመራቂዎቹ በሰመር ካምፕ መርሐ ግብር የተሰጣቸው ሥልጠና በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው “የ5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ ኢኒሼቲቭ” ሥልጠና ቁልፍ መሠረት መሆኑን ገልጸው አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ለዛሬ ሳይሆን ለነገ መልካም ፍሬ የሚሰጥ ምርጥ ዘር መሆኑን ነው የገለጹት።

ዳግማዊት አበበ

አዲስ ዘመን መስከረም 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You