ከፖሊሲ ማሻሻያ እስከ ኢንቨስትመንት አማራጭ

በ2016 ዓ.ም በጤናው ዘርፍ በርካታ አበይት ተግባራት ተከናውነዋል። ከፖሊሲ ማሻሻያ ጀምሮ የጤናውን ዘርፍ ሊያዘምኑ የሚችሉ በርካታ አዳዲስ የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ውጤቶች ተዋውቀዋል። በተለይ እያደገ ከመጣው የሕብረተሰቡ የጤና አገልግሎት ፍላጎትና ቀደም ሲል ያሉና አሁን ላይ ያሉ የበሽታዎችን ስርጭት ከግምት ውስት በማስገባት የፀደቀው አራተኛው የኢትዮጵያ ጤና ፖሊስ ባለፈው ዓመት በጤናው ዘርፍ ከተከናወኑ ተግባራት ውስጥ በግምባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ነው።

አራተኛው የኢትዮጵያ የጤና ፖሊሲ እስካሁን የተመዘገበውን ውጤት ይበልጥ ለማጠናከር፣ ለወቅታዊና ወደፊት ለሚከሰቱ ተላላፊና ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች አገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጤናና ጤና ነክ ፍላጎቶች ይበልጥ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ስለመሆኑ ተነግሮለታል። እያደገ የመጣውን የሕዝብ ፍላጎት ምላሽ ለመስጠትና ከወቅቱ ጋር የተናበበ የጤና ስርዓት ለመፍጠር ዓላማ ባደረገ መልኩ ፖሊሲው እንደተዘጋጀም ታውቋል።

ከጤና ፖሊሲ ማሻሻያው በዘለለ ባሳለፍነው ዓመት ሌሎችም በርከት ያሉ የጤናው ዘርፍ ስራዎች የተከናወኑ ሲሆን፣ የሀገር ውስጥ አምራቾችን ለማበረታት ‹‹ጤናችን በምርታችን›› በሚል መሪ ቃል የተካሄደው የመጀመሪያው የሀገር ውስጥ የሕክምና ግብዓት ምርትና ኢኖቬሽን የሀገር ውስጥ የማምረት አቅምን በማሳደግ ረገድ ተስፋ ሰጥቶ አልፏል።

በሌላ በኩል ክትባት ያልጀመሩና ጀምረው ያቋረጡ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሕፃናትን ተደራሽ የሚያደርግ የክትባት ዘመቻም በዚሁ ዓመት የተከናወነ ሲሆን ዘመቻው በተለይ በግጭትና በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት ከክትባት ውጪ የሆኑ ሕፃናትን ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል። በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር) ይፋ ተደርጎ የተጀመረው የፅዱ ኢትዮጵያ ፕሮጀክት አካል የሆነው የፅዱ ጤና ተቋም ንቅናቄም አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ክልሎች ሲሰራ የቆየው ባሳለፍነው ዓመት ነበር።

እነዚህ ስራዎች እንዳሉ ታዲያ የክረምት ወቅትን ተከትሎ የተከሰቱ የኮሌራና ወባና ወረርሽኞች ለኢትዮጵያ ስጋት ደቅነው የነበረ ቢሆንም በተከናወኑ ጠንካራ የመከላከልና የመቆጠር ስራዎች ወረርሽኞቹ የከፋ ጉዳት ሳይስከትሉ ለመቆጣጠር ተችሏል። በተመሳሳይ የዝንጀሮ ፈንጣጣ (Mpox) በሽታ የመከላከልና የመቆጣጠር ስራ በትኩረት በመሠራቱ እስካሁን ድረስ በሽታው በኢትዮጵያ እንዳልተከሰተ ተነግሯል። የዓለም ጤና ድርጅት ይህን በሽታ የዓለም አሳሳቢ የድንገተኛ የጤና አደጋ መሆኑን ካስታወቀ ጊዜ ጀምሮ የጤና ሚኒስቴር ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን አስቀድሞ ለመከላከልና ለመቆጣጠር በርካታ ስራዎችን በትኩረት እየሠራ መሆኑም ተገልጿል።

ከነዚህ የጤናው ዘርፍ አበይት ክንውኖች ባሻገር ግን ሌሎች በጤናው ዘርፍ ላይ አንድ እርምጃ የሚጨምሩ ስራዎችም በጤና ሚኒስቴርና በሌሎች አጋር አላት ተከናውዋል። ዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ ጉባኤዎች ተካሂደዋል። የልምድ ተሞክሮ ጉብኝቶች ተደርገዋል። አዳዲስ የጤና ፕሮጀክቶች ይፋ ሆነዋል። የጤና ተቋማትን ለመገንባት የሚያስችሉ ድጋፎችና ስምምነቶች ተደርገዋል። አዲስ የሆስፒታሎች ግንባታ ተከናውኗል። የክረምት የጤና በጎ ፍቃድ አገልግሎት በሀገር አቀፍ ደረጃ ተካሂዷል።

በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት መጨረሻ 27ኛው የዓለም የቲቢ ቀን እና 18ኛው ዓመታዊ የቲቢ ምርምር ጉባኤ ተካሂዷል። በዚህ ጉባኤ በኢትዮጵያ የቲቢን በሽታ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተሰሩ ስራዎች ውጤት ያስመዘገቡ ቢሆንም በቲቢ የተያዙ ሰዎች አሁንም ድረስ መገለል እንደሚደርስባቸውና ይህን ችግር ለማስወገድ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተጠቁሟል። ከዚሁ ጎን ለጎን አዲስ ሀገራዊ የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ስትራቴጂክ እቅድ የማስተዋወቂያ መድረክ ተከናውኗል። ሀገር አቀፍ የጤና ተቋማት የጥራት ደረጃ መረጃ የማሰባሰብ ስራም በዚሁ በጀት ዓመት ተጀም ሯል።

በስዊዘርላንድ ጀኔቫ በተካሄደው 77ኛው የዓለም ጤና ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ ተሳትፋ በተለያዩ የጤና ጉዳዮች ላይ መግለጫ አቅርባለች። የጤና ሚኒስቴር ዶክተር መቅደስ ዳባ ለጉባኤተኞቹ ባደረጉት ንግግር የጤና አገልግሎት የዜጎች ሰብአዊ መብት መሆኑን ኢትዮጵያ በፅኑ ታምናለች ብለዋል። ዓለም አቀፍ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ስናረጋገጥ ማንንም ወደ ጎን መተው የለብንም፤ ምንም አይነት ልዩነትና ድምበር ሳይኖር ለዜጎቻችን ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት መስጠት ይገባል ብለዋል።

በተያያዘም የጤና ሚኒስቴር ዶክተር መቅደስ ዳባ ከዓለም ጤና ድርጅት ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ጋር ተወያይተዋል። በውይይታቸውም የዓለም ጤና ድርጅት በኢትዮጵያ የጤና ዘርፍ የሰው ኃይል ልማት፣ የጤና ፋይናንሲንግ፣ መደበኛ የክትባት ፕሮግራምን ለማጠናከር እንዲሁም ወባና ኮሌራ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር የሚወሰዱ እርምጃዎችን እንደሚደግፍ አስታውቋል።

የ2 ሺ የጤና ማእከላት ግንባታ የአራትዮሽ የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት ባሳለፍነው በጀት ዓመት የተፈረመ ሲሆን የአራትዮሽ ስምምነቱ በጤና ሚኒስቴር፣ በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ቦንጋ ዩኒቨርስቲና የሩሲያ ፓን አፍሪካ ዴቨሎፕመንት ሴንተር መካከል ተፈርሟል። ፕሮጀክቱ በ250 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የ2 ሺ ጤና ማእከላት ግንባታ ከተሟላ የሕክምና ቁሳቁስ ጋር በቀጣይ አምስት ዓመት እንደሚካሄድ ተጠቁሟል። በተመሳሳይ ለሰባተኛው ዙር የግሎባል ፈንድ መተግበሪያ 440 ሚሊዮን ዶላር ግራንት በጤና ሚኒስቴር፣ ግሎባል ፈንድና ሲ ሲ ኤም ኢትዮጵያ በኩል ተፈርሟል።

28 ሚሊዮን ዶላር በጀት የተያዘለት ወረዳን መሰረት ያደረገ የተቀናጀ ጤና ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮጀክትም ይፋ የተደረገው ባሳለፍነው ዓመት ሲሆን ፕሮጀክቱ የሚከናወነው ከጤና ሚኒስቴር፣ አምሬፍ ኸልዝ አፍሪካ እና ቢል ኤንድ ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር በአምስት ክልሎች በተመረጡ በ50 ወረዳዎች መሆኑ ተነግሯል።

በሌላ በኩል ጤና ሚኒሰቴር ባለፈው በጀት ዓመት ከኢትዮጵያ ጤና ትምህርትና ፕሮሞሽን ባለሙያዎች ማህበር እንዲሁም ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ሶስተኛውን ሃገር አቀፍ የማህበራዊ እና ባህሪ ለውጥ ጉባዔ “የማህበራዊ እና ባህሪ ለውጥ ተግባራት ለዘላቂ የጤና ልማት” በሚል መሪ ቃል ከ13 ዓለም አቀፍ አገራት ከመጡ የዘርፉ ባለሙያዎችን ጨምሮ 400 በላይ ተሳታፊዎች በተገኙበት በአዲስ አባባ አካሂዷል።

በተያያዘም ከዩ ኤስ ኤ አይ ዲ (USAID) ጋር በመተባበር ከስርዓተ-ምግብ እና ጤና ጋር የተያያዙ አዳዲስ ፕሮጀክቶች ባሳለፍነው ዓመት ተግባራዊ ሊደረጉ እንደሆነ ተገልጿል። ዩ ኤስ ኤ አይ ዲ አዳዲስ ከስርዓተ- ምግብ ጋር የተያያዙ ፕሮጀክቶችን ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር መተግበር እንደሚፈልግ ከጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ጋር ባደረጉት ውይይት ለማወቅ ተችሏል። ድርጅቱ ለሚተገብራቸው ፕሮጀክቶች ጤና ሚኒስቴር አስፈላጊውን ትብበር እንደሚያደርግም ተጠቁሟል። ፊድ ዘ ፊዩቸር በUSAID የሚተገበር የስርዓተ-ምግብ ፕሮግራም ሲሆን፤ ሴቶች፣ ታዳጊ እና ጨቅላ ሕጻናት የተሻለ ስርዓተ-ምግብ ተጠቃሚ ያደርጋል።

ባለፈው ዓመት ከተከናወኑ አዲስ ክስተቶች ውስጥ ሌላኛው ጤና ሚኒስቴር ከኮሪያው ሪፐብሊክ ዓለም አቀፍ የጤና እንክብካቤ ፋውንዴሽን (ኮፊ) ጋር በመተባበር የሕክምና አገልግሎት መስጫ መሳርያዎች ማደሻና ማሻሻያ ማዕከል ግንባታ መጀመር የሚያስችል የመሰረት ድንጋይ ማስቀመጡ ሲሆን ግንባታው ሲጠናቀቅ በኢትዮጵያ ታድሰው ዳግም አገልግሎት መስጠት እየቻሉ በርካታ የሕክምና መሣሪያዎች ለብክነት እንዳይዳረጉ ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተጠቁሟል።

ሰላሳ ሁለት ሀገራት የተሳተፉበት የአፍሪካ መደበኛ ስፔሻላይዝድ የጤና፣ ስነ-ምግብ፣ ሕዝብ እና መድሀኒት ቁጥጥር ውይይት የተካሄደውም ባሳለፍነው የ2016 በጀት ዓመት ነበር። በአፍሪካ ሕብረት የስብሰባ አዳራሽ በተካሄደው በዚህ ውይይት “ጤናን ማዳበር በአፍሪካ፡ ሁለንተናዊ የጤና፣ የተመጣጠነ ምግብ፣ የሕዝብ ቁጥር፣ የመድኃኒት ቁጥጥር፣ ወንጀል መከላከል እና ትምህርት የተነሱ አንኳር ጉዳዮች ነበሩ።

ከአፍሪካ የልማት አጀንዳ ጋር በማጣጣም ከጤና፣ ከሥነ-ምግብ፣ ከሕዝብ እና ከመድኃኒት ቁጥጥር ጋር የተያያዙ በርካታ የሥራ ሰነዶች ፀድቀዋል። በኮንፈረንሱ ከ32 አባላት የተውጣጡ ሚኒስትሮች እና ልዑካን ቡድኖች የተገኙ ሲሆን ከተለያዩ የአፍሪካ ሕብረት አካላት እና አጋር ድርጅቶች ተወካዮች የተውጣጡ ኃላፊዎችና ባለሙያዎችም ተሳትፈውበታል።

የመጀመሪያው ዙር ዓለም አቀፍ የክረምት ነጻ የጤና አገልግሎት ሰጪዎች ቡድን ወደ ሃገር ውስጥ መግባቱም የባለፈው ዓመት አብይ ክስተት ነበር። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የክረምት በጎ አድራጎት አካል የሆነው ነጻ የጤና ምርመራና ሕክምና አገልግሎት በሃገር አቀፍ ደረጃ በሁሉም የጤና ተቋማት ተከናውኗል። ይህንኑ መልካም ተግባር ለማጠናከር ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የተለያዩ ሃገር ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው የክረምት ነጻ የጤና አገልግሎት ሰጥተዋል።

ጤና ሚኒስቴርና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እንዲሁም ልዩ ልዩ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የአስገዳጅ የብሔራዊ የምግብ ማበልጸግ ፕሮግራምና የ5 ዓመት ስትራቴጂ እቅድ ማስተዋወቅ መርሃ ግብርም ባለፈው ዓመት ይፋ ተደርጓል። በኢትዮጵያ ከአምስት ዓመት በታች ከሆኑ ሕጻናት መካከል በተመጣጠነ ምግብ እጥረት 39 በመቶው የሚሆኑት የመቀንጨር ችግር እንደሚያጋጥማቸው በወቅቱ ተገልጿል። 11 በመቶው የሚሆኑት ሕፃናት የመቀጨጭ እንዲሁም 22 በመቶው የሚሆኑት ደግሞ የክብደት መቀነስ ችግር እንደሚያጋጥማቸው የተነገረ ሲሆን የአስገዳጅ የብሔራዊ የምግብ ማበልጸግ ፕሮግራም እና ስትራቴጂ ይህን ችግር ለመቅረፍ በእጅጉ እንደሚረዳ ተጠቁሟል።

ባለፈው ዓመት በኮንጎ ብራዛቪል የተካሄደው 74ኛው የአፍሪካ አህጉር የዓለም ጤና መድረክ የአፍሪካ አባል አገራት በተለይም ወረርሽኞችንና ድንገተኛ የጤና አደጋዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የአፍሪካ ተጨባጭ ሁኔታን ባገናዘበ መልኩ ዝግጁነትና የቅድመ መከላከል ስራዎችን እንዲሁም ፈጣን ምላሽ ለመስጠት በትብብርና በቅንጅት ለመስራት፣ የአመራር ክህሎትና የጤና ባለሙያውን አቅም ለማሳደግ፣ የጤናውን ዘርፍ የፋይናንስ አቅምና ኢንቨስትመንት ለመደገፍ ከምንግዜውም በላይ በጋራ ለመስራት ቁርጠኝነት ታይቶበታል።

አምስተኛው የአፍላ ወጣቶች እና ወጣቶች ጤና ፎረም “ተደራሽነትና ጥራት፡ ምላሽ ሰጪ ስርዓት ለሁሉም የአፍላ ወጣቶች እና ወጣቶች!” በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ ዓድዋ መታሰቢያ ሙዚየም የተካሄደው በዚህ ዓመት መጨረሻ ነበር፡ በፎረሙ ጤና ሚኒስቴር የአፍላ ወጣቶችንና ወጣቶችን ሁለንተናዊ ጤና ለመጠበቅ በፖሊሲ የተደገፉ አቅጣጫዎችን ከባለድርሻ እና አጋር አካላት ጋር እየሰራ እንደሆነ ገልጿል።

በፎረሙ ከጤና ሚኒስቴር በተጨማሪ ሌሎች የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ሚኒስትሮችና ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች መገኘታቸው የአፍላ ወጣቶችና ወጣቶች ጤና የጤናው ዘርፍ ብቻ ሳይሆን ሁሉንም የሚመለከት መሆኑን ማሳያ መሆኑም ተጠቁሟል። ፎረሙ ጥራት ያለው የወጣቶች እና አፍላ ወጣቶች ጤናን ታሳቢ ያደረገ ስራ ለመስራት ከባለድርሻ አካላት ምን እንደሚጠበቅ ለመወያያት የተዘጋጀ መሆኑንም ተነግሯል።

በበጀት ዓመቱ መቋጫ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በቻይና ቤጂንግ እየተካሄደ በሚገኘው የኢትዮ-ቻይና ከፍተኛ የቢዝነስ ፎረም ላይ ተሳትፏል። ከዚሁ ጎን ለጎን በፎረሙ ላይ በመገኘት በጤናው ዘርፍ ያለውን ሁኔታ አስመልክቶ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በማብራሪያቸውም በኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጭ መኖሩን ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ የፋርማስቲካል ዘርፍ ብቻ በዓመት ከ1 ጥብ 5 ቢልዮን ዶላር በላይ ገበያ መኖሩን ሚኒስትሯ አንስተው መንግስት በጤናው ዘርፍ ስድስት ዋና ዋና ዘርፎችን በመለየት አስፈላጊውን መሰረተ ልማት በማሟላት እየሰራበት መሆኑን ተናግረዋል። እነዚህም ሜዲካል ቱሪዝምን ማእከል ያደረገ የቴሪሸሪ ጤና አገልግሎት፣ በቴክኖሎጂ የታገዘ የዲያግኖስቲክ አገልግሎት፣ የሕክምና ግብአቶች ማምረቻ፣ የጤናው ዘርፍ የሰው ኃይል ልማት፣ የቅድመ ድንገተኛ ሕክምና አገልግሎት፣ የጤና ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን መሆኑን አብራርተዋል።

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ረቡዕ መስከረም 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You